Advertisement Image

ዐውደ ወራዙት

ለአዋቂዎች የተዘጋጁ ስፔሻል የሃይማኖት ትምህርት ፕሮግራሞች

የዝምታ ጩኸት

እስራኤል ጭንቅ ላይ ናቸው:: ከባርነት ተላቅቀው ከግብፅ ከወጡና ጉዞ ከጀመሩ በኁዋላ ፈርኦን የለቀቀው ሕዝብ ጉልበት ቆጭቶት በቁጣ ነድዶ ሠራዊቱን አስከትቶ በፈጣን ሠረገላ እየጋለበ መጣባቸው:: ከፊታቸው ደግሞ የሚያስፈራ ባሕር ተደቅኖአል:: ሕዝቡ የፈረደበት ሙሴ ላይ ጮኹበት:: መጽሐፈ መቃብያን "ያንን ሁሉ ሕዝብ ሲጠብቅ ያልተበሳጨ ሙሴን አስበው" እንደሚል እንደ ሙሴ ትሑትና ታጋሽ መሪ ታይቶ አይታወቅም:: ልክ በዚያች ዛፍ ላይ እሳት ሲነድባት እንዳልተቃጠለች እስራኤላውያንም ሙሴ ላይ ለዓመታት ቢነዱም አላቃጠሉትም::

"በግብፅ መቃብር ጠፍቶ ልታስፈጀን ነው?" "ከሞት ባርነት በስንት ጣዕሙ?" እስራኤል በኤርትራ ባሕር ዳርቻ ሙሴን በቁጣ እየጮኹ አስጨነቁት::

መሪነት ከባድ ነው:: ያንን ሁሉ ድንቅ ነገር አድርጎ እግዚአብሔር ነፃ ሲያወጣቸው ሙሴ ለእነርሱ ቤዛ ሆኖ ተሹሞ ብዙ ዋጋ ከፍሎአል:: ውለታውን ረስተው አፋጠጡት::

"ሙሴም ለሕዝቡ፦ አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ፡ አላቸው"
ሙሴ ሕዝቡን ከጩኸታቸው ሲያረጋጋ ሳለ የእግዚአብሔር ድምፅ ወደ ሙሴ መጣ
"ሙሴ ሆይ ለምን ትጮኽብኛለህ?" አለው::ልብ አድርጉ የጮኸው ሕዝቡ ነው ሙሴ አረጋጋ እንጂ ቃል አልተናገረም::

ሆኖም ሙሴ አፉ ዝም ቢል ልቡ ይጮኽ ነበር:: ከእስራኤል ጩኸት ይልቅ የሙሴ ዝምታ እግዚአብሔር ጆሮ ደረሰ:: እግዚአብሔር ኤልያስ እንዳላገጠባቸው የአሕዛብ አማልክት በጩኸት ብዛት የሚሰማ አምላክ አይደለም:: በትዕቢትና አመፅ ከሞላበት ጩኸት ይልቅ በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ዝምታ እግዚአብሔር ጋር ይጮኻል:: የእስራኤል ጩኸት ፍርሃት ይነዛል:: ልናልቅ ነው የሚል ሽብር ይፈጥራል:: የሙሴ ዝምታ ግን ባሕር ይከፍላል::

ጌታ ሆይ ጩኸታችን አልሆነልንም:: ዝምታችንን ሰምተህ ሀገራችንን ከከበባት ጥፋት ታደግልን:: የእኛ መጨቃጨቅና ጠብ ባሕር አይከፍልም:: የእኛ ጩኸት ከመነካከስ በቀር አያሻግርም::
በአርምሞ የሚለምኑህን በእኛ ፊት ዝም አሉ የምንላቸው በአንተ ፊት ግን የሚጮኹትን ሰምተህ ታደገን::

የኤርትራ ባሕር በዝምታ ተከፈለ:: እስከ ራማ የተሰማው ራሔል ስለ ልጆችዋ ያለቀሰችው ዕንባ ባሕር ከፈለ:: እመቤታችን ሆይ ስለ እኛ ስለልጆችሽ እባክሽን አልቅሺ:: የራሔል ዕንባ ራማ ከደረሰ የአንቺ ዕንባ የት ሊደርስ ነው? በየበረሃ እየወደቀ ስላለው ልጅሽ ስለሞተለት ወንድም እባክሽን ለምኚ::

በሙሴ በትር ባሕሩ ተከፈለ:: የኤርትራ ባሕር (ቀይ ባሕር [በግሪኩ erythos ማለት ቀይ ነው]) እጅግ ባለ ታሪክ ባሕር ነው:: ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደረቅ ሆኖ ፀሐይ ያየውና ግማሽ ሚልየን የሚሆን ሕዝብ በመካከሉ ተራምዶ ያለፈበት ይህ ባሕር እንንደ ግድግዳ የቆመ ብቸኛው የዓለማችን ባሕር ነው::

በዚህ ባሕር እስራኤል ሲሻገሩ ፈርኦን ከነሠራዊቱ ሰጠመ:: በእግር የሔዱት የተሻገሩትን ባሕር በሠረገላ የሔዱት አቃታቸው:: የኤርትራ ባሕር ለእስራኤል ትንሣኤ ሲሆን ለፈርኦን ግን መቃብር ሆነ:: ፈርኦን ደንግጦ መመለስ የነበረበት ባሕሩ ሲከፈል ሲያይ ነበር:: ፈርኦንን ያደቆነ ሰይጣን ግን ባሕር መካከል ሳያቀስስ አልለቀቀውም::

እግዚአብሔር ማን ነው? ብሎ ነበር በዚያ ባሕር ተዋወቀው:: እሱ ሲሰጥም እስራኤል በኩራት "እግዚአብሔር ማን ነው? " ለሚለው የፈርኦን ጥያቄ ከባሕር ማዶ ሆነው መልስ ሠጡ "እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው" አሉ:: እስራኤል በኤርትራ ባሕር መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ "በባሕርና ደመና ተጠመቁ" ተብሎላቸዋል:: ፈርኦን ግን እስራኤል በተጠመቁበት ጠበል ውስጥ ሰጠመ::

የኤርትራን ባሕር ሲሻገሩ ከሙሴ ሌላ እስራኤልን ሲመራ የነበረ ጠባቂ ነበረ:: እርሱም የእስራኤል ጠባቂ (advocate of Israel) በመባል የሚታወቀው ቅዱስ ሚካኤል ነበር:: "በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ" ዘጸ 14:19 እንዲል ቅዱስ ሚካኤል እስራኤልን ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን ዐምድ እየተመሰለ በመንገድ መራቸው::

ኢትዮጵያውያን ያለነው ከባሕሩ ዳርቻ ላይ ነው:: ሁሉም መሻገር ይፈልጋል:: ከእኛ መካከል እንደ ፈርኦን ሰጥሞ የሚቀር ይኖራል:: እንደ እስራኤል የሚሻገር ይኖራል: : ቅዱስ ሚካኤል ሆይ ለእኛም ድረስልን:: ይህንን ክፉ ዘመን በክንፎችህ አሻግረን::

በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

Event Image

ምፅዋት

ገንዘባችሁን በድኾች ቀኝ እጅ የምታስቀምጡ ከኾነ ሐሜተኛ አያገኘውም፤ ቀናተኛ አያየውም፤ ሌባ አይሰርቀውም፤ ቀማኛ አይነጥቀውም፤ የቤት ውስጥ ሠራተኛ ደብቆ አይወስደውም፤ ማንም ይኹን ማን ሊያገኘው በማይችል ቦታ የተቀመጠ ነውና፡ በሌላ መልኩ ከቤት ውስጥ ብታስቀምጡት ግን ሌባም፣ ቀማኛም፣ ቀናተኛም፣ ሐሜተኛም፣ የቤት ውስጥ ሠራተኛም፣ ሌላም ሰው አግኝቶ ሊወስድባችሁ ይችላል፡፡ በጽኑ በርና ቁልፍና ስለ ዘጋነው ከውጭ ቀማኞች ሊተርፍ ይችል ይኾናል፤ ከቤት ውስጥ ቀማኞች ግን ላይተርፍ ይችላል፡፡ ይህ እንዲህ እንደሚኾን በብዙ ሰዎች ዘንድ ስለምናየው የታወቀ የተረዳ ነውና፡ እንግዲህ ገንዘባችንን በድኾች እጅ ስናስቀምጥ የገንዘባችን ጌቶች መኾናችንን ታያላችሁን? በድኾች እጅ ማስቀመጣችን ግን በአስተማማኝ ቦታ እንዲቀመጥልን ብቻ አይደለም፤ የብዙ ብዙ ትርፍና ወለድም ስላለው እንጂ፡፡ ምን ማለት ነው? ገንዘባችንን ለሰዎች ብናበድራቸው ምናልባት አንድ ፐርሰንት ትርፍ እናገኝ ይኾናል፡፡ በድኾች አማካኝነት ለእግዚአብሔር ብናበድረው ግን የምናገኘው ትርፍ መቶ ጊዜ መቶ እንጂ አንድ ፐርሰንት ብቻ አይደለም፡፡

እኽል በለም መሬት ብንዘራውና መልካም ምርት ሰጠ ቢባል ቢበዛ የዘራነውን ዐሥር ወይም ኹለት ዕጥፍ ነው፡፡ በድኾች እጅ አማካኝነት በመንግሥተ ሰማያት ብንዘራው ግን መቶ ዕጥፍ ትርፍ ከማግኘታችንም በላይ ማርጀት መፍጀት የሌለውን የዘለዓለምን ሕይወት እናገኛለን፡፡ ገበሬዎች በዚህ ምድር ላይ ዘርተው ምርት ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረድ አለው፡፡ በድኾች አማካኝነት በመንግሥተ ሰማያት ለመዝራት ግን ማረሻ አያስፈልግም፤ በሬ አያስፈልግም፤ ወይም ሌላ ይህን የመሰለ ድካም አይጠይቅም፡፡ ከዚህም በላይ የዘራነው እኽል ዋግ አያገኘውም፤ የዝናብ እጥረት አያገኘውም፤ በረዶ አያገኘውም፤ ድርቅ አያገኘውም፤ አንበጣ አያገኘውም፤ ጎርፍ አያገኘውም፤ ገበሬውን (እኛን) ሥጋት ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ ምንም ነገሮች የሉም፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚዘራ ሰብል ከእነዚህ አደጋዎች ኹሉ ነጻ ነውና፡፡ ስለዚህ ይህን ምርት ለማግኘት ድካም የለውም፤ ሥጋት የለውም፤ መጥፎ አጋጣሚ የለውም፡፡ ከዚህ ይልቅ ምርቱ ከዘራነው በላይ ብዙ የብዙም ብዙ ከመኾኑ የተነሣ እስከ ዛሬ ድረስ የሰው ዓይን ያላየው፣ የሰው ጆሮ ያልሰማው፣ የሰው ልብም ያላሰበው ነው፡፡

ወዮ! ይህን ምርት ለማግኘት እንደ መፍጨርጨር ከመታየቱ የሚጠፋ ጥቂት ምርትን ለማግኘት መድከም እንደ ምን ያለ ስንፍና ነው? ሌቦችስ ይቅርና የሌቦች አለቃ ዲያብሎስ በማያገኘው ሥፍራ ገንዘብን እንደማስቀመጥ ሌቦች ሰርቀው በሚያገኙት ቦታ ማስቀመጥ እንደምን ያለ ዐላዋቂነት ነው? እንግዲህ ይህን በማድረጋችን ሊደረግልን የሚችል ቸርነት እንደ ምን ያለ ቸርነት ነው? ይህን ላለማድረጋችን ዘወትር የምናቀርበው ምክንያት ድኽነታችንን ነው፡፡ እስኪ ንገሩኝ! የቱንም ያህል ድኾች ብንኾን ከዚያች ታዋቂዋና የነበራትን ኹለት ሳንቲም ከሰጠችው ድኻ በላይ ድኾች እንኾናለንን? እንኪያስ ይህቺን ድኻ እንምሰላት፤ ይህቺን ድኻ አብነት አድርገን ገንዘባችንን የት ማስቀመጥ እንዳለብን እንወቅ እንረዳም፡፡ ይህቺ ድኻ ያገኘችውን በጎ ነገር እናገኝ ዘንድ ፈቃዷንም አሁን ገንዘብ እናድርግ፡፡ እኛ ሥራ ሠርተን አንበቃምና በአባቶቻችን ካህናት ጸሎት፣ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነትና ሰውን መውደድ ርስቱንና መንግሥቱን እንድናገኝ ይርዳን፡፡ ለእርሱም ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ጌትነት ኃይልና ክብር ይኹን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

(በእንጦጦ መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ውሉደ ብርሃን ሰንበት ት/ቤት አምደ ብርሃን የሰሌዳ መጽሔት ታኃሣሥ 2015ዓ.ም)

Event Image