Advertisement Image

ልሳነ ግእዝ

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የልሳነ ግእዝ ምዕራፎች

ምዕራፍ ፩ : መሠረተ ግእዝ

፩,፩ ግእዝ የሚለው ቃል ትርጓሜ
1, የፊደል ስም ሲሆን፡- ግእዝ የሚለው ቃል የፊደል ስም ሲሆን የመጀመሪያ፣ ፈርጅና ቅጥያ የሌለው፣ከዘመነ አብርሃ ወአጽብሐ በፊት የነበረው የመጀመሪያ ፊደል ማለት ነው።
‘ሀ’- ግእዝ፣ ‘ሁ’- ካዕብ፣ ‘ሂ’- ሣልስ፣ ወዘተ… ስንል ‘ሀ’- አንደኛ፣ ‘ሁ’- ሁለተኛ፣ ‘ሂ’- ሦስተኛ ወዘተ… ማለታችን ነው።

2, የንባብ ስም ሲሆን፡- ግእዝ የሚለው ቃል የንባብ ስም ሲሆን የመጀመሪያ ንባብ፣ ውርድ ንባብና ቁም ንባብ ከሚባሉት ውስጥ የመጀመሪያው ማለት ነው። በአብነት ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያ የሚነበበው ግእዝ ንባብ ነው። ከዚያ ውርድ ንባብ ከዚያም ቁም ንባብ ይከተላል።

3, የዜማ ስም ሲሆን፡- የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልቶች ሦስት ሲሆኑ አነርሱም ግእዝ፣ ዕዝልና አራራይ ናቸው። ስለዚህ ግእዝ የዜማ ስልት ይሆናል ማለት ነው።

4, የቋንቋ ስም ሲሆን፡- የመጀመሪያ ቋንቋ፣ አዳማዊ ቋንቋ፣ ሴማዊ ቋንቋ፣ ጥንታዊ ቋንቋ ማለት ነው።

፩.፪ ፊደላተ ግእዝ
የግእዝ ቋንቋ ፊደላት ጠቅላላ ብዛት ሠላሳ ሲሆን ሃያ ስድስቱ መደበኛና አራቱ ዲቃላ ፊደላት ናቸው። በአማርኛ ቋንቋ ከሚታወቁት ሠላሳ ሦስት መደበኛ ፊደላት ውስጥ ሰባቱ በግእዝ ያልነበሩ እና በአማርኛ የተጨመሩ ናቸው። እነዚህም በፊት ከነበሩት የግእዝ ፊደላት ትንሽ ለውጥ በማድረግ የተገኙ ናቸው። እነርሱም ከታች የተጠቀሱት ናቸው።

ሸ-- ‘ሰ’ ን
ኘ-- ‘ነ’ ን
ጀ-- ‘ደ’ ን
ቸ-- ‘ተ’ ን
ጨ-- ‘ጠ’ ን
ዠ-- ‘ዘ’ ን
ኸ-- ‘ከ’ ን በተወሰነ ቅርጽ በመቀየር የተገኙ ናቸው።
ከነዚህ የተረፉት ሃያ ስድስቱ መደበኛ ፊደላት የግእዝ ፊደላት ናቸው።

በግእዝ ቋንቋ ዲቃላ ፊደላት የሚባሉት ከመደበኛ ፊደላት የተገኙ ሲሆኑ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው።





















ሞክሸ ፊደላት

ሞክሸ ፊደላት የሚባሉት አንድ ዓይነት ድምፀት ያላቸው ሆነው የተለያየ ቅርፀ ፊደል ያላቸው ናቸው። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው።

ሀ፣ ሐ፣ ኀ፤ አ፣ ዐ፤ ጸ፣ ፀ፤ ሰ፣ሠ

እነዚህም ፊደላት አንደኛው ከአንደኛው ተለይቶ የሚታወቅበት ስም ተሰጥቶታል።

ሀ-- ሃሌታው ‘ሀ’ ይባላል። ሃሌ ሉያ ለአብ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ፊደል ስለሆነ ነው።
ሐ-- ሐመሩ ‘ሐ’ ይባላል። ሐመር ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ፊደል ስለሆነ ነው።
ኀ-- ብዙኀኑ ‘ኀ’ ይባላል። ብዙኅ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ስለሆነ ነው።
አ-- አልፋው ‘አ’ ይባላል። አልፋ ወዖሜጋ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ስለሆነ ነው።
ዐ-- ዓይኑ ‘ዐ’ ይባላል። ዓይን ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ስለሆነ ነው።
ጸ-- ጸሎቱ ‘ጸ’ ይባላል። ጸሎት ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ስለሆነ ነው።
ፀ-- ፀሐዩ ‘ፀ’ ይባላል። ፀሐይ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ስለሆነ ነው።
ሠ-- ንጉሡ ‘ሠ’ ይባላል። ንጉሥ ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ስለሆነ ነው።
ሰ-- እሳቱ ‘ሰ’ ይባላል። እሳት ብለን ስንጽፍ የምንጠቀመው ይህን ስለሆነ ነው።

ስለዚህ ‘ሠ’ ን ‘ንጉሡ’ የሚል ሰው ‘ንጉሥ’ ብሎ ሲጽፍ ‘ንጉስ’ ብሎ ከጻፈ ታላቅ ስህተት ይሆንበታል። እነዚህ ሞክሸ ፊደላት አንዱ በአንዱ ቦታ አይገቡም። ከገቡ ግን የትርጉም ለውጥ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ምሳሌ፡- ሠረቀ-- ወጣ አመት-- አገልጋይ
ሰረቀ-- ሰረቀ ዓመት-- ዘመን

ሰዐለ-- ስዕል ሳለ አ/አ-- አዲስ አበባ
ሰአለ-- ለመነ ዓ/ዓ-- ዓመተ ዓለም

፩,፫ አኀዝ
የግእዝ ቋንቋን በሥነ-ጽሑፍ ምሉዕ ካደረጉት ነገሮች አንዱ የራሱ የሆነ አኀዝ ያለው መሆኑ ነው። አኀዝ የሚለው ቃል አኀዘ-- ያዘ፣ ቆጠረ፣ ጀመረ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ቁጥር፣ መጀመሪያ፣ መያዣ ማለት ነው። አኀዝ ተብሎ በግእዙ ‘ኀ’ ሲጻፍ ነጠላ ቁጥርን ያመለክታል፤ አኃዝ ተብሎ በራብዑ ‘ኃ’ ሲጻፍ ብዙ ቁጥርን ያመለክታል። ይህም አኀዝ-- ቁጥር፤ አኃዝ-- ቁጥሮች ማለት ነው። የግእዝ አኀዝ መሥራች ቁጥሮች ብዛታቸው ሃያ ነው። በእነዚህ በሃያዎቹ ማንኛውንም ቁጥር መጻፍ ይቻላል። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው።

መዋቅር የግእዝ አኀዝ / በፊደል/ የዐረበኛ ቁጥር

፩/ አሐዱ/1 ፰/ስምንቱ/8 ፷/ስድሳ/ስሳ/60
፪/ ክልዔቱ/2 ፱/ተስዐቱ/9 ፸/ሰብዐ/70
፫/ ሠለስቱ /3 ፲/ዐሠርቱ/10 ፹/ሰማንያ/80
፬/ አርባዕቱ /4 ፳/እሥራ/20 ፺/ተስዐ/90
፭/ ኃምስቱ/5 ፴/ሠላሳ/30 ፻/ምዕት/100
፮/ ስድስቱ /6 ፵/አርብዓ/40 ፼/እልፍ/10000
፯/ ሰብዐቱ/7 ፶/ሃምሳ/50 ፻፼/አእላፋት/1000000

በግእዝ ቋንቋ ዜሮን የሚወክል አኀዝ የለም። ይህም የሆነው በግእዝ አሥርን ለመጻፍ ራሱን የቻለ አሥር ቁጥር ስላለ ነው። ከአንድ ጀምሮ እስከ ተፈለገው ቁጥር ድረስ ከላይ ያየናቸውን መሥራች ቁጥሮች በመጠቀም መጻፍ ይቻላል።

በግእዝ ቋንቋ አምስት የአኀዝ ዓይነቶች አሉ።እነርሱንም እንደሚከተለው እናያቸዋል።

፩, ሕጋዊ አኀዝ፡- ይህ የአኀዝ ዓይነት ከታወቀ ቁጥር ውስጥ ስንተኛነትን የሚነግረን ነው።

ምሳሌ፡- ኣሐድ/ቀዳማይ አንደኛ
ካልእ/ካልዐይ ሁለተኛ
ሣልስ/ሣልሳይ ሦስተኛ ወዘተ

፪, ክፍላዊ አኀዝ፡- ይህ ደግሞ ከሙሉ ነገር ምን ያክል የሚለውን የሚያሳውቅ ነው።

ምሳሌ፡- ካልዒት አንድ ሁለተኛ/ግማሽ
ሣልሲት አንድ ሦስተኛ/ሲሶ
ራብዒት አንድ አራተኛ/ሩብ ወዘተ

፫, ዕፅፋዊ አኀዝ፡- እጥፍነትን ያሳውቀናል።

ምሳሌ፡- ካዕብተ ክልዔቱ ሁለት እጥፍ
ካዕብተ ሰለስቱ ሦስት እጥፍ
ካእብተ አርባዕቱ አራት እጥፍ ወዘተ

፬, መድበላዊ አኀዝ፡- መድበላዊ የሚባለው በውል የማይታወቁ ቁጥሮችን የሚነግረን ነው። ይህም ማለት ጥቂትና ብዙ መሆኑን እንጅ ቁጥሩን በውል ለይተን አናውቀውም።

ብዙኅ ብዙ
ንስቲት ትንሽ
ኅዳጥ ጥቂት

፭, መደባዊ አኀዝ፡- የቁጥሮችን ወይም ነገሮችን ብዛት ስንትነት በውል የሚያሳውቀን ሲሆን ከአንድ ይጀምራል።

፩ ፪ ፫ ፬ ፭ ፮ ፯ ፰ ፱ ፲ ፲፩ - - - - - - - - - -

ቁጥሮችን መቀየር

ከላይ ባየናቸው መደባዊ አኃዝ መሠረት ማንኛውንም የዐረበኛ ቁጥር ወደ ግእዝ መለወጥ እንችላልን። የግእዝ ቁጥርንም ወደ ዐረበኛ መለወጥ እንችላለን። የአረብኛ ቁጥሮችን ወደ ግእዝ ቁጥር ስንለውጥ ከቀኝ ወደ ግራ ሁለት ሁለት አድርገን ከከፋፈልን በኋላ ነወ።

ምሳሌ፡-«235637»ን ለመቀየር 23 56 37 ይህም 23 እልፍ 56 ምዕት እና 37 ይሆናል። በግእዝ ሲነበብም እሥራ ወሰለስቱ እልፍ ሃምሳ ወስድስቱ ምዕት ሰላሳ ወሰብዐቱ ተብሎ ነው። ሲጻፍም ፳፫፼፶፮፻፴፯ ተብሎ ነው።

1. 2452 ሲቀየር ፳፬፻፶፪ ሲነበብም እሥራ ወአርባዕቱ ምዕት ሃምሳ ወክልዔቱ
2. 906 ሲቀየር ፱፻፮ ሲነበብም ተሰአቱ ምዕት ወስድስቱ
3. 1235272 ሲቀየር ፻፼፳፫፼፶፪፻፸፪ ሲነበብም አእላፋት እሥራ ወሰለስቱ እልፍ ሃምሳ ወክልዔቱ ምዕት ሰብዐ ወክልዔቱ
4. 74839200 ሲቀየር ፸፬፼፻፹፫፼፺፪፻ ሲነበብም ሰብዐ ወአርባዕቱ አእላፋት ሰማንያ ወሠለስቱ እልፍ ተስዐ ወክልዔቱ ምዕት

የግእዝን ቁጥር ወደ አረብኛ ለመለወጥ መጀመርያ የግእዙን ቁጥር መበተን ነው።

ምሳሌ፡-«፪፼፸፮፻»ን ለመቀየር 2x10000 ሲደመር 76x100 ማድረግ ነው።ይህም 20000+7600=27600 ይሆናል።

፩.፬ መራሕያን
መራሕያን “መርሐ- መራ” ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መሪዎች ማለት ነው፡፡ መራሕያን የሚባሉት በሰው ስም ፋንታ ተተክተው የሚነገሩ የእርባታ መደቦች ናቸው፡፡ መራሕያን የተጸውዖ (የመጠሪያ) ስሞች፣ የተቀብዖ ስሞች፣ የነገር፣ የአካልና የግብር ስሞች ሁሉ አጻፋ እየሆኑ የሚነገሩ የደቂቅ ሰዋስው ክፍሎች ናቸው፡፡ በአማርኛ ሰዋስው ተውላጠ ስሞች ይባላሉ፡፡ ብዛታቸው አሥር ሲሆን የሚከተከሉት ናቸው፡፡

መራሒ አማርኛ
ውእቱ እሱ
ውእቶሙ እነርሱ(ተ)
ይእቲ እሷ
ውእቶን እነርሱ(አ)
አንተ አንተ
አንትሙ እናንተ(ተ)
አንቲ አንቺ
አንትን እነርሱ(አ)
አነ እኔ
ንሕነ እኛ
እነዚህም አሥሩ መራሕያን በቁጥር በፆታ እና በመደብ አንደሚክተለው ይክፋፈላሉ::

ሀ, በአንድና በብዙ ቁጥር ሲከፈሉ

ነጠላ ቁጥር: ውእቱ፣ ይእቲ፣ አንተ፣ አንቲ፣ አነ
ብዙ ቁጥር: ውእቶሙ (እሙንቱ)፣ ውእቶን (እማንቱ) ፣አንትሙ፣ አንትን፣ ንሕነ

ለ, በተባዕታይና በአንስታይ ፆታ ሲከፈሉ

ተባዕታይ ፆታ፦ ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ አንተ፣ አንትሙ አንስታይ ፆታ፦ ይእቲ፣ ውእቶን፣ አንቲ፣ አንትን

+ ከመራሕያን መካከል ፆታ የማይለዩት አነ እና ንሕነ ናቸው።

ሐ, በሩቅና ቅርብ መደብ ሲከፈሉ በንግግር ጊዜ ፡-

- ተናጋሪው አንደኛ መደብ ይባላል። - አድማጩ ሁለተኛ መደብ ይባላል። - ተናጋሪ ያልሆኑ በማድመጥም በዋናነት የማይሳተፉ ስለእነርሱ ነገሩ የሚነገርላቸው ሦስተኛ መደቦች ይባላሉ።

አንደኛ መደብ፦ አነ፣ ንሕነ
ሁለተኛ መደብ፦ አንተ፣ አንትሙ፣ አንቲ፣ አንትን
ሦስተኛ መደብ፦ ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ ይእቲ፣ ውእቶን

የመራሕያን አገልግሎት
፩ የስም ምትክ ሆነው ያገለግላሉ፦

መራሕያን በዐ/ነገር ውስጥ ስምን ተክተው በባለቤትነት ይነገራሉ፡፡በዚህም አገልግሎታቸው ተውላጠ ስም ይባላሉ፡፡የሚነገራቸው ትርጉምም እንደሚከተለው ነው፡፡

ማስታወሻ፦ መራሕያን የስም ምትክ ሆነው እንዲያገለግሉ ከግስ በፊት መምጣት አለባቸው፡፡

ምሳሌ፦ ንሕነ አንበብነ መዝሙረ ዳዊት
ይእቲ ተዐቢ እምኪሩቤል ወትፈደፍድ እምሱራፌል
አኮ አንትሙ ዘኀረይክሙኒ ወሤምክሙኒ አላ አነ ኀረይኩክሙ
ውእቱ ጸለየ በቤተ ክርስቲያን

፪ ነባር አንቀጽ ሆነው ያገለግላሉ፦

መራሕያን በአረፍተ ነገር ውስጥ ዐ/ነገሩን በማሰር እንደ ማሰሪያ አንቀጽ ያገለግላሉ፡፡እንደ ዚህ ባለው አገልግሎታቸውም ነባር አንቀጽ ይባላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የሚኖራቸውም ትርጉም እንደሚከተለው ነው፡፡

መራሒ አማርኛ
ውእቱ ነው፣ ነበር፣ አለ
ውእቶሙ ናቸው፣ ነበሩ፣ አሉ
ይእቲ ናት፣ ነበረች፣ አለች
ውእቶን ናቸው፣ ነበሩ፣ አሉ
አንተ ነህ፣ ነበርህ፣ አለህ
አንትሙ ናችሁ፣ ነበራችሁ፣ አላችሁ
አንቲ ነሽ፣ ነበርሽ፣ አለሽ
አንትን ና ችሁ፣ ነበራችሁ፣ አላችሁ
አነ ነኝ፣ ነበሁ፣ አለሁ
ንሕነ ነን፣ ነበ ርሁ፣ አለሁ
መራሕያን ነባር አንቀጽ ሆነው እንዲያገለግሉ ከስም በኋላ ወይም ካሉት ክፍላተ ነገሮች በኋላ መምጣት አለባቸው። በዐ/ነገሩ ውስጥ ሌላ ማሰሪያ አንቀጽ ከሌለ ማሰሪያ አንቀጽ የሚሆኑት ነባር አንቀጾች ናቸው፡፡

ምሳሌ፦መኑ አነ
ቀዳሚሁ ቃል ውእቱ
ማርያም ይእቲ ሙዳየ መና
ዛቲ ይእቲ ትእዛዘ እንቲአየ ከመ ትትፋቀሩ በበይናቲክሙ
አነ ውእቱ ሐረገ ወይን ዘፅድቅ ወአቡየ ተካሊሁ ውእቱ

፫ አመልካች ቅጽል ሆነው ያገለግላሉ፦

መራሕያን በዐረፍተ ነገር ውስጥ አንድን ነገር ከጓደኞቹ ለይተን «ይህ» ወይም «ያ» ብለን ጠቁመን ለማመልከት ያገለግላሉ፡፡እንደዚህ ባለው አገልግሎታቸውም አመልካች ቅጽል ይባላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የሚኖራቸውም ትርጉም እንደሚከተለው ነው፡፡

መራሒ አማርኛ
ውእቱ ያ
ውእቶሙ እነርሱ(ተ)
ይእቲ ያች
ውእቶን እነርሱ(አ)
አንተ አንተ
አንትሙ እናንተ(ተ)
አንቲ አንቺ
አንትን እነርሱ(አ)
አነ እኔ
ንሕነ እኛ
መራሕያን ነባር አንቀጽ ሆነው እንዲያገለግሉ ከስም በፊት መምጣት አለባቸው፡፡

ምሳሌ፦ውእቱ ወልድ ሖረ ኀበ ሀገረ እንግልጣር
ይእቲ ይእቲ ዘቀተለቶ ለከይሲ
ውእቱ ቃል ሥጋ ኮነ
አንትሙ አርድእት አንትሙ

+ በንግግር ጊዜ በተሳቢነት የሚያገለግሉ የመራሕያን ክፍሎች ገቢር መራሕያን (ተሳቢ መራሕያን) ይባላሉ፡፡ እነዚህም፦
ኪያሁ= እሱን ኪያከ= አንተን ኪያየ= እኔን
ኪያሆሙ= እነርሱን ኪያክሙ= እናንተን ኪያነ= እኛን
ኪያሃ= እርሷን ኪያኪ= አንችን ኪያሆን= እነርሱን ኪያክን= እናንተን

ምሳሌ፦ ኪያሁ አፈቅር
ኪያክሙ ኢያርእየኒ
ኪያከ እግዚኦ ንሴብሐከ

+ በንግግር ጊዜ በባለቤትነት የሚያገለግሉ የመራሕያን ክፍሎች ድርብ መራሕያን ይባላሉ፡፡ እነዚህም፦
ለሊሁ= ራሱ ለሊከ= ራስህ ለልየ= ራሴ
ለሊሆሙ = ራሳቸው ለሊክሙ= ራሳችሁ ለሊነ= ራሳችን
ለሊሃ= ራሷ ለሊኪ= ራስሽ
ለሊሆን= ራሳቸው ለሊክን= ራሳችሁ

ምሳሌ፦ለልየ ውእቱ ዘገበርኩ ዘንተ ግብረ
ለሊነ ነአምር ኵሎ ዘኮነ
ወለልየ ርኢኩ ወአነ ሰማዕቱ ከመ ዝንቱ ውእቱ ወልዱ ለእግዚአብሔር

፩.፭ የግስ ዝርዝር በመራሕያን(የባለቤት ዝርዝር)

በመራሕያን ባለቤትነት ግሶች መጠነኛ ለውጦችን እያደረጉ የሚዘረዘሩት መዘርዘር የባለቤት ዝርዝር ይባላል። ለባለቤት ዝርዝር የሚረዱ ቀለማት መዘርዝራን ተውላጠ ስም ይባላሉ። እነርሱም ከግሱ መጨረሻ የሚገቡ ባዕዳን ቀለማት ናቸው። የግሶችም አዘራዘር የሚከተለውን ይመስላል።

ሀ , በውእቱ ጊዜ የሚጨመርም ሆነ የሚቀየር የለም ግስ የሚገኘው በውእቱ ባለቤትነት ስለሆነ ለ , በውእቶሙ ጊዜ የግሱን መድረሻ ቀለም ወደ ካዕብ መቀየር ብቻ ነው፡፡ ሐ , በይእቲ ጊዜ የግሱ መድረሻ ፊደል ሳይቀየር “ት” ፊደልን መጨመር ነው፡፡ መ , በውእቶን ጊዜ የግሱን መድረሻ ፊደል ወደ ራብዕ መቀየር ነው፡፡ ሠ , በአንተ ጊዜ የግሱን መድረሻ ፊደል ወደ ሳድስ ከቀየርን በኋላ “ከ” ፊደልን መጨመር ነው፡፡ ረ , በአንቲ ጊዜ የግሱን መድረሻ ፊደል ወደ ሳድስ ከቀየርን በኋላ “ኪ” ፊደልን መጨመር ነው፡፡ ሰ , በአንትሙ ጊዜየግሱን መድረሻ ፊደል ወደ ሳድስ ከቀየርን በኋላ “ክሙ” ፊደልን መጨመር ነው፡፡ ሸ , በአንትን ጊዜ የግሱን መድረሻ ፊደል ወደ ሳድስ ከቀየርን በኋላ “ክን” ፊደልን መጨመር ነው፡፡ ቀ , በአነ ጊዜ የግሱን መድረሻ ፊደል ወደ ሳድስ ከቀየርን በኋላ “ኩ” ፊደልን መጨመር ነው፡፡ በ , በንሕነ ጊዜ የግሱን መድረሻ ፊደል ወደ ሳድስ ከቀየርን በኋላ “ነ” ፊደልን መጨመር ነው፡፡

+ የተለየ ህግ የሌላቸው ግሶች ሁሉ ከላይ ባየነው አረባብ መሰረት ይዘረዘራሉ፡፡

ምሳሌ ፦
ውእቱ : ቀተለ ዘገበ ሐወጸ ዐቀበ መጽወተ ሰከበ
ውእቶሙ፡ ቀተሉ ዘገቡ ሐወጹ ዐቀቡ መጽወቱ ሰከቡ
ውእቶን ፡ ቀተላ ዘገባ ሐወጻ ዐቀባ መጽወታ ሰከባ
ይእቲ ፡ ቀተለት ዘገበት ሐወጸት ዐቀበት መጽወተት ሰከበት
አንተ ፡ ቀተልከ ዘገብከ ሐወጽከ ዐቀብከ መጽወትከ ሰከብከ
አንትሙ ፡ ቀተልክሙ ዘገብክሙ ሐወጽክሙ ዐቀብክሙ መጽወትክሙ ሰከብክሙ
አንቲ ፡ ቀተልኪ ዘገብኪ ሐወጽኪ ዐቀብኪ መጽወትኪ ሰከብኪ
አንትን ፡ ቀተልክን ዘገብክን ሐወጽክን ዐቀብክን መጽወትክን ሰከብክን
አነ ፡ ቀተልኩ ዘገብኩ ሐወጽኩ ዐቀብኩ መጽወትኩ ሰከብኩ
ንሕነ ፡ ቀተልነ ዘገብነ ሐወጽነ ዐቀብነ መጽወትነ ሰከብነ

ማስታወሻ ፦፩ በባለቤት ዝርዝር(በግስ ዝርዝር) ጊዜ ወድቆ የሚነበበው ይአንትን ዝርዝር ብቻ ነው፡፡
ቀተልክን ዘገብክን ሰከብክን ዐቀብክን መጽወትክን ሰበክን (ሁሉም ወድቀው ይነበባሉ፡፡)
፪ በገብረ ቤቶች ዝርዝር በሁለተኛ እና በአንደኛ መደብ ሳድስ ቀለሙ ወደ ግእዝ ቀለም ተለውጦ ይዘረዘራል፡፡