Advertisement Image

ልሳነ ግእዝ

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የልሳነ ግእዝ ምዕራፎች

ምዕራፍ ፪ : ሥርዓተ ንባብ ዘልሣነ ግእዝ

የግእዝ ቋንቋ የራሱ የሆነ የተወሰነ ሥርዓተ ንባብ አለው፡፡ይህ የንባብ ሥርዓቱ ከተፋለሰ ቋንቋው ለዛ ያጣል፡፡አንባቢውም ሆነ አድማጩ ምሥጢሩን ስለማይረዳው ቃሉ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ የግእዝ መጻሕፍትን ሁሉ ለማንበብ የግእዝ ቋንቋን ሥርዓተ ንባብ መማር ይጠበቅብናል፡፡በግእዝ ቋንቋ ትምህርት ውስጥ አንዱ እና ትልቁ ክፍል የንባብ ህግጋቱነው፡፡በግእዝ ቋንቋ ሶስት ዓይነት የንባብ ዓይነቶች አሉ፡፡ ይህም አከፋፈል በንባብ ጊዜ ከድምፅ አወጣጥ አንጻር ነው፡፡

፩ ግእዝ ንባብ ፦ ይህ የንባብ ዓይነት ቃልን ከቃል እየለዩ የሚነበብበትየንባብ ዓይነት ሲሆን በአብነት ትምህርት ቤቶች የንባብ ትምህርት የመጀመሪያው የንባብ ደረጃ ነው፡፡ ፊደል የለየ ተማሪ የሚያነበው የመጀመሪያው የንባብ ዓይነት ነው፡፡ ሲነበብም ፊደልን ከፊደል እየለዩ በዝግታ ሳብ ሳብ እያለ የሚነበብ የንባብ ዓይነት ነው፡

፪ ውርድ ንባብ ፦ ይህ ሁለተኛው የንባብ ደረጃ ግእዝ ንባብን አንብቦ የጨረሰ ተማሪ የሚያነበው ቀጣይ ደረጃ ሲሆን የኅዘን ዜማ መልክ ያለው የንባብ ዓይነት ነው፡፡ሲነበብም ቃላትን ከቃላት እየለዩ ነው፡፡የግእዝ ንባብ ጐተት ዝግ ይል የነበረውን ሳብ ሳብ በማድረግ ይነበባል፡፡ሳቢ እና ተሳቢው ተነሽ እና ወዳቂው አንቀጹ እና አንቀጽ አጐላማሹ በየአመሉ እየተለየ የሚነበብበት የንባብ ዓይነት ነው፡፡

፫ ቁም ንባብ ፦ ከውርድ ቀጥሎ ሶስተኛው የንባብ ደረጃ ሲሆን ያለአንዳች ችግር ሕግጋተ ንባባትን ተነሽ ተጣዩን ወዳቂና ሰያፉን ጠንቅቆ በመለየት ጠበቅ ያዝ ለቀቅዘለግ ፈጠን እየተደረገ የሚነበብበት የንባብ ደረጃ ነው፡፡ ይህ የንባብ ዓይነት ዘወትር በቤተክርስቲያን በሊቃውንት ፊት ቅዱሳት መጻሕፍት የሚነበቡበት የንባብ ዓይነት ነው፡፡

፪.፩ የንባብ ዓይነቶች
በግእዝ ቋንቋ ትምህርት ውስጥ የታወቁት የንባብ ዓይነቶች አራት ናቸው፡፡ እነርሱም፦

፩, ተነሽ
፫, ወዳቂ
፪, ሰያፍ
፬, ተጣይ

አንድን ቃል የአነባበብ ሥርዓቱን ለማወቅ የሚከተሉትን መለያዎች እንጠቀማለን

- መድረሻ ቀለም
- የሆሄያት ተጽዕኖ
- ተነባቢ ቀለም
- የቃሉ ባህርይ(ስም ወይም ግስ መሆኑ) በዚህ ክፍል ለአካሄድ እንዲያመቸን ከግስ ውጭ የሆኑትን ሁሉ ስም እንላቸዋለን

፩ ተነሽ ንባብ

ተነሽ ንባብ የሚባለው እንደ ቁጣ ቃል የሚነገር ተፈላጊውን ቀለም አንስቶ አንዝሮ የሚነበብ ንባብ ነው፡፡ተነስተው የሚነበቡ ቃላትን ለመለየት የሚከተለውን ዘዴ እንጠቀማለን፡፡

ሀ, መድረሻ ቀለም ፦ ተነስተው ሊነበቡ የሚችሉ ቃላት በአምስቱ የሆሄ ስልት የጨረሱ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡እነዚህም፦ ግእዝ፣ካዕብ፣ሳልስ፣ራብዕ እና ሳብዕ ናቸው፡፡በእነዚህ ያልደረሰ ቃል ፈጽሞ ሊነሳ አይችልም፡፡

ምሳሌ፦
በግእዝ፡ ቆመ፣ገብረ፣ሐቀለ፣አንፈርዐፀ፣ሰበከ
በካዕብ፡ ቆሙ፣ገብሩ፣ሐቀሉ፣አንፈርዐፁ፣ሰበኩ
በሣልስ፡ ቁሚ፣ግበሪ፣ ሕቅሊ፣ስብኪ፣ቀድሲ
በራብዕ፡ ቆማ፣ ቀደሳ፣ አእመራ፣ ያእምራ
በሳብዕ፡ አሥመረቶ፣ንሴብሖ፣ይግብሮ

በግእዝ ወይም በሌሎቹ የጨረሰ ሁሉ ግን ተነስቶ ይነበባል ማለት አይደለም፡፡
ለምሳሌ የሚከተሉትን ህገወጦች መመልከት እንችላለን፡፡
ህየ፣እወ፣ሠለስተ፣ክልዔተ፣አርባዕተ በግእዝ ቢጨርሱም ተነስተው አይነበቡም፡፡
አሐዱ፣ክልዔቱ፣ሠለስቱ፣አርባዕቱ በካዕብ ቢጨርሱም አይነሱም፡፡

ለ, ተነባቢ ቀለም ፦ የተነሽ ቃላት ተነባቢ ቀለማቸው ቅድመ መድረሻቸው ነው፡፡ ቅድመ መድረሻቸው ቆጣ ነዘር ብሎ ይነበባሉ፡፡
ምሳሌ፡ አእመረ፣ወረደ፣ቀተለ፣ሐወጸ

ሐ, የቃል ክፍል ፦ በአብዛኛው ተነስተው የሚነበቡ ቃላት ግሶች ናቸው፡፡
ማስታወሻ፦ ሶስት ቀለም ያላቸው በግእዝ ጀምረው ቅድመ መድረሻቸው ሳድስ በሆኑ ግሶች ሳድስ ቀለሙ ተውጦ ይነበባል፡፡

ምሳሌ፦ ገብረ፣ፈርሐ፣መርሐ፣መጽዐ
ኅረየ ዐሥርተ ወክልዔተ አርድእተ
አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ ደይ እዴከ ኅበ ዘፈቀድከ
ንሴብሐከ እግዚኦ

፪ ተጣይ ንባብ

ተጣይ ቀለማት ሲነበቡ እንደ ወዳቂ ቀለም ያዝ ለቀቅ በማድረግ ነው፡፡

ሀ, መድረሻ ቀለም ፦ ተጣይ ቀላት የሚጨርሱት በሳድስ ቀለም ብቻ ነው፡፡
ምሳሌ፦ ቅዱስ፣ ኅሩይ፣ መንሱት፣ መንበር፣ ሰዋስው፣ ልብ፣ ዮም፣ ጾም

ለ, ተነባቢ ቀለም ፦ የተጣይ ቀለም ተነባቢ ቀለሙ ቅድመ መድረሻው ስለሆነ ይህን ቀለም ያዝ ቆየት በማድረግ ይነበባሉ፡፡

ሐ, የቃል ክፍል ፦ ተጣይ ቃላት በአብዛኛው ስሞች ናቸው፡፡ ከግስ የወጡ ዘሮች በአብዛኛው ተጥለው ይነበባሉ፡፡

ምሳሌ፦ ኀሩያን፣ ቡሩክ፣ ሲሳይ፣ መላእክት
ፃድቃን ወሰማዕት ጽኑዓን በሃይማኖት
ንጉሥ ወካህናት ክቡራን በኅበ እግዚአብሔር

ማስታወሻ፦ የተጣይ ቃላት ሳድስ ቀለማት ተከታትለው ሲመጡ ቅድመ መድረሻቸው ተውጦ ይነበባሉ፡፡
ምሳሌ፦ወርቅ፣ ፍቅር፣ ምድር፣ ምግብ፣ ዘርዕ፣ ቅድስት፣ ትስብእት

፫ ወዳቂ ንባብ

ይህ የንባብ ዓይነት ተፈላጊውን ቀለም ያዝ ቆየት በማድረግ ይነበባል፡፡ ወዳቂ ንባብ ወዳቂ ዜማ ባለው ድምጸ ማኀዘኒ ይነበባል፡፡

ሀ, መድረሻ ቀለም ፦ የወዳቂ ቀለማት መድረሻ ቀለማት ሰባቱም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ምሳሌ፦
በግእዝ፦ ህየ፣ አሐደ፣ ክልዔተ
በካዕብ፦ ኵሉ፣ ብሔሩ፣ ዝንቱ፣ እሙንቱ፣ እማንቱ
በሳልስ፦ ቀታሊ፣ ገባሪ፣ ዛቲ፣ ኖላዊ፣ ነጋሢ፣ ዜናዊ
በራብዕ፦ ዜና፣ መና፣ ሠረገላ፣ ተድላ፣ መክራ፣ ሀገራ
በኅምስ፦ አይቴ፣ ምናኔ፣ ሥላሴ፣ ልምላሜ፣ ትካዜ
በሳድስ፦ ዝ ብቻ ነው(በሳድስ ወዳቂ ዝ ብቻ ነው)
በሳብዕ፦ ከበሮ፣ አእምሮ፣ እፎ፣ ተዋህዶ

ለ, ተነባቢ ቀለም ፦ በወዳቂ ንባብ ጊዜ ተነባቢ ቀለሙ መድረሻ ቀለሙ ነው፡፡ተነባቢ ቀለሙን ያዝ ቆየት በማድረግ ይነበባል፡፡

ሐ, የቃል ክፍል ፦ ወድቀው የሚነበቡ በአብዛኛው ስሞች ናቸው፡፡ በዚህ ትምህርት ከግስ ውጭ ያሉትን ሁሉ በስም ስር መድበናቸዋል

፬ ሰያፍ ንባብ

ይህ የንባብ ዓይነት ተፈላጊውን ቀለም እንደ ተነሽ ንባብ አስቆጥቶ አንዝሮ ይነበባል፡

ሀ, መድረሻ ቀለም ፦ ሰያፍ ንባብ በሳድስ ብቻ ይጨርሳል፡፡
ለ, ተነባቢ ቀለም ፦ ተነባቢ ቀለሙ ቅድመ መድረሻው ነው፡፡
ሐ, የቃል ክፍል ፦ ተሰይፈው የሚነበቡ ስሞችም ግሶችም ናቸው፡፡

ምሳሌ፦ አእመረት፣ ቀተለት፣ ይወርድ፣ ይገብር፣ እቀትል፣ ቅትል፣ግበር፣ንላዕ
ኢሳያስ፣ ቶማስ፣ ገብርኤል፣ ጴጥሮስ፣ ዳንኤል፣ ቴዎፍሎስ
ገብርኤል ሰብሐ ኪያሃ
ንፁም ፆመ ወናፍቅር ቢጸነ

ማስታወሻ፦ ሰያፍ እና ተነሽ በአነባበብ አንድ ናቸው የሚለያዩት በመድረሻ ቀለማቸው ነው፡፡
ወዳቂ እና ተጣይ ሥርዓተ ንባባቸው አንድ ነው ቢባልም በተነባቢ ቀለም እና በመድረሻ ቀለም ይለያያሉ፡፡

፪.፪ ተናባቢ ንባብ
ሁለት የተለያዩ ቃላት በዘርፍ እና በባለቤትነት በአንድ ትንፋሽ እንደ እንድ ቃል ሲነበቡ ተናባቢ ንባብ ይባላል። ተናባቢ ሊሆኑ የሚችሉ ቃላት መድረሻቸው ሳድስ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ኃምስ፣ እና ሳብዕ የሆኑ ቃላት ብቻ ናቸው።ይህንንም በምሳሌ እንመለከተዋለን፡-

ሀ. በሳድስ የደረሰ ቃል ተናባቢ ሲሆን፡- በዚህ ጊዜ ሳድስ የነበረው መድረሻ ቀለሙ ወደ ግእዝ ይለወጣል።

ምሳሌ፡-
መሰረት- መሰረተ ሕይወት፣ መሰረተ ዓለም
መንግሥት- መንግሥተ ሰማይ፣ መንግሥተ እግዚአብሔር ፣ መንግሥተ ዳዊት
ቤት - ቤተ መጽሐፍት፣ ቤተ እዚአብሔር፣ ቤተ አማኑኤል
ሊቅ - ሊቀ ካህናት፣ ሊቀ መላእክት፣ ሊቀ ጠበብት
ገብር -ገብረ አምላክ፣ ገብረ ኢየሱስ

ለ. በሣልስ የደረሰ ቃል ተናባቢ ሲሆን፡- በዚህ ጊዜ ሣልስ የነበረው መድረሻ ቀለሙ ወደ ኃምስ ይለወጣል።

ምሳሌ፡-
ቀናዒ - ቀናዔ ቢጹ(በጓደኛው የሚቀና)
ብእሲ - ብእሴ እግዚአብሔር(የእግዚአብሔር ሰው)
ወሃቢ -ወሃቤ ሰላም(ሰላምን የሚሰጥ፣የሰላም ሰጭ)
ገባሪ - ገባሬ መንክራት(ድንቅ የሚሰራ)

ሐ. በራብዕ የደረሰ ቃል ተናባቢ ሲሆን፡- በዚህ ጊዜ ራብዕ የነበረው መድረሻ ቀለሙ ሳይለወጥ ራብዕ ይሆናል።

ምሳሌ፡-
ዜና - ዜና አበው ፣ (የአባቶች ነገር)
ደመና -ደመና ሰማይ፣ (የሰማይ ደመና)
ሰረገላ -ሰረገላ እሳት፣ (የእሳት ሰረገላ)

መ. በኃምስ የደረሰ ቃል ተናባቢ ሲሆን፡- በዚህ ጊዜ ኃምስ የነበረው መድረሻ ቀለሙ ሳይለወጥ ኃምስ ይሆናል።

ምሳሌ፡-
ዝማሬ - ዝማሬ ዳዊት፣ ዝማሬ መላእክት
ምናኔ - ምናኔ ዓለም
ውዳሴ -ውዳሴ ማርያም፣ ውዳሴ አምላክ

ሠ. በሳብዕ የደረሰ ቃል ተናባቢ ሲሆን፡- በዚህ ጊዜ ሳብዕ የነበረው መድረሻ ቀለሙ ሳይለወጥ ራሱ ሳብዕ ይሆናል።

ምሳሌ፡-
መሰንቆ - መሰንቆ ዳዊት (የዳዊት መሰንቆ)
አእምሮ - አእምሮ መጻሕፍት(የመጻሕፍት እውቀት)
ተዋርዶ -ተዋርዶ ክብር

ማስታወሻ፡-፩ ከላይ ካየናቸው ተናባቢዎች የሚለይ ተናባቢ አለ። ይህ የተናባቢ ዓይነት ሲተረጎም ከላይ እንዳየነው «የ» በመጨመር ሳይሆን «እንደዚህ የሚባል» እየተባለ ነው።ይህ ተናባቢ የስያሜ ተናባቢ ይባላል።

ምሳሌ፡-
መልአከ ገብርኤል -ገብርኤል የሚባል መልአክ
ሰማዕተ ጊዮርጊስ - ጊዮርጊስ የሚባል ሰማዕት

፪ ከላይ ካየናቸው ሥርዐተ ንባብ ሌላ በመጥበቅ እና በመላላት የቃላት ሥርዓተ ንባብ ይለያያል።

ሀ. ላልቶ መነበብ

በአብዛኛው የእነዚህ ቃላት መሰረታቸው ቀተለ ነው።እነዚህን ቃላት(ላልተው የሚነበቡትን) ያዝ ጠበቅ አድርጎ ማንበብ አይቻልም።
ምሳሌ፡- ተከለ፣ ወለደ፣ ሰከበ፣ መሐለ፣ መሰለ፣ ገብረ ፣ፈትሐ

ለ. ጠብቆ መነበብ

በአብዛኛው የእነዚህ ቃላት መሰረታቸው ቀደሰ ነው። ሶስት ዓይነት አጥብቆ የማንበብ ዘዴ አለ።

1) የተሰጠው ግስ የቀደሰ ቤት ሲሆን
ምሳሌ፡- ጸውዐ፣ ሰብሐ፣ ጸለየ፣ ሐወጸ

2) ሁለት ደጊመ ቃላት ተደጋግመው ከመጡ አንዱ ተጎርዶ ሌላው ጠብቆ ይነበባል።
ምሳሌ፡- ሐመመ=ሐመ፣ጠበበ=ጠበ፣ ነደደ=ነደ

3) በገዳፍያነ ዘመድ ቀለማት(ቀ፣ገ፣ከ፣ነ) የተነሳ የሚተብቁ አሉ።
ምሳሌ፡-ሰጠቀ፣ ሰበከ፣አመነ፣ኀደግሙ

፪.፫ መጠይቃን ቃላት
የአንድን ሰው ማንነት፤ የነገርን ምንነት ፤ የጊዜን መቼነት፤ የቦታን የትነት፤ የቁጥርን ስንትነት ወዘተ ለመጠየቅ የምንጠቀምባቸው ቃላት መጠይቃን ቃላት ይባላሉ። የጥያቄ ጥያቄነት የሚታወቀው በመጠይቃን ቃላቱ ነው እንጅ በጥያቄ ምልክት አይደለም። እነዚህም መጠይቃን ቃላት የሚከተሉት ናቸው።

፩, የሰውን ማንነት ለመጠየቅ የምንጠቀማቸው «መኑ» እና«አይ» ናቸው።

በዐ.ነገር ውስጥ«ማን» ተብለው ይተረጎማሉ። ፊደላትን እየደረቡ ትርጉማቸውን ይለውጣሉ። ምሳሌ፡- ለመኑ---ለማን፣ በመኑ---በማን፣ ከመመኑ----እንደማን ወዘተ ።«መኑ»እና «አይ» ከአስሩ መራሕያን ጋር ሲያገለግሉ በብዙ ቁጥሮች «እለ» ን ከፊት እያስገቡ ነው። እለመኑ የሚለው «እነማን» ተብሎ ይፈታል።

ምሳሌ፡-
መኑ/አይ ዘተሰቅለ በቀራንዮ
መኑ/አይ ዘሣረራ ለምድር
መኑ/አይ ዘነበበ ሐሰተ

፪, የነገርን ምንነት ለመጠየቅ የምንጠቀማቸው «ምንት» እና«አይ» ናቸው።

በዐ.ነገር ውስጥ«ምን» «ምንድን» ተብለው ይተረጎማሉ። ፊደላትን እየደረቡ ትርጉማቸውን ይለውጣሉ።ምሳሌ፡- ለምንት---ለምን፣ ምንተ---ምንን(ተሳቢ) ፣ ምንታት---ምኖች(በብዙ) ወዘተ ። ምንት በአስሩ መራሕያን ይዘረዘራል። አዘራዘሩም እንደሚከተለው ይሆናል።

ምሳሌ፡-
እግዚአብሔር ምንትነ ውእቱ ለነ
ክርስቶስ ምንታ ውእቱ ለማርያም

ማስታወሻ፡ «መ» በትራስነት እየገባ ተነስቶ እንዲነበብ ያደርገዋል።
ምሳሌ፡- መኑመ ሰብእ ኢየአምሮ ለዝንቱ ወልድ። መኑመ ኢየአምር ምጽአቶ ለክርስቶስ።

፫, የጊዜን መቼነት ለመጠየቅ የምንጠቀማቸው «ማእዜ» እና«አይ» ናቸው።

አንድ ድርጊት የተከናወነበትን ጊዜና ሰዐት ለመጠየቅ የምንጠቀምባቸው ቃላት ናቸው።

ምሳሌ፡-
ማእዜ ተሠገወ ወልደ እግዚአብሔር።
ማእዜ ውእቱ ዘተወለድከ እኁየ።

፬, የቦታን የትነት ለመጠየቅ የምንጠቀማቸው «አይቴ» እና«አይ» ናቸው።

«የት»የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ቦታን ለመጠየቅ ይጠቅማል።

ምሳሌ፡-
አይቴ ሖረ ወልድየ ወአይቴ ኀደረ።
አይቴ ብሔራ ለጥበብወአይቴ ማኅደራ።
አይቴ አሐውር እምቅድመ ገጽከ።
እምኀበ አይቴ ውእቱ መካኑ ዘተቀብረ ክርስቶስ።

፭, ሁኔታን ለመጠየቅ የምንጠቀመው «እፎ»ን ነው።

ትርጉሙም እንዴት፣ ሞንኛ፣ ምነው የሚል ፍቺ ያለው የንዑስ አገባብ ክፍል ነው። ለሰላምታ እና ለደህንነት መጠየቂያ ይሆናል። ከሌሎች ቀለማት ጋርም ሲጫፈር ሌላ ትርጉም ይኖረዋል።

ምሳሌ፡-
በእፎ---ለምን፣ለምንድን ፤ እፎ እፎ---እንዴት እንዴት
እፎ ወጠንክሙ ትምህርተ ግእዝ።
እፎ የዐቢ ዕቡይ ርእሶ።

ማስታወሻ፡-«ኑ፣መ፣ኪ፣እንጋ፣ኢ» በቃሉ መድረሻ እየገቡ ግሡን ያጋንኑታል።
ከመዝኑ እንጋ አምኃ ይትአምኁ።/p>

፮, የቁጥርን ስንትነት ለመጠየቅ የምንጠቀማቸው «እስፍንቱ» እና«ስፍን» ናቸው።

ስፍን ለነጠላ ሲሆን እስፍንቱ ደግሞ ለብዙ ቁጥር ያገለግላሉ። በገቢርነት ለመናገር መድረሻውን ወደ ግእዝ ቀለም መለወጥ ነው።

ምሳሌ፡-
ስፍነ ዘመነ ሀለውከ በዝንቱ መካን።
ስፍን ውእቱ መዋዕሊከ።

፯, በግስ መድረሻ እየገቡ ለመጠየቅ የምንጠቀማቸው «ኑ» እና«ሁ» ።

በግሥ መድረሻ ላይ ገብተው ግሡን መጠይቃዊ ያደርጉታል። በዐ.ነገር ውስጥ «ን» ተብለው ይፈታሉ።

ምሳሌ፡-
ሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል አዶናይ።
አኮኑ ለእግዚአብሄር ትገኒ ነፍስየ።
በይነምንት ይዜኀር ባዕል ላዕለ ነዻይ። ኢይነዲሁ ዘብዕለ ወኢይብዕልሁ ዘነድየ።

፰, ቦኑ በዐ.ነገር ውስጥ «በውኑ» ተብሎ ይተረጎማል።

በአብዛኛው «እፎ» ፣«በእፎ»፣«ለምንት» የሚባሉትን ቃላት አስቀድሞ ይነገራል።

ምሳሌ፡-
በእፎ ያፈቅር ስብእ ዓለመ ቦኑ ይመስሎ ኢየኀልፍ።
ቦኑ በከነቱ ፈጠርኮ ለእጓለእመሕያው።