Advertisement Image

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች

ምዕራፍ ሁለት : የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና

ቀኖና፡- ማለት ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙ መቃ፣መለኪያ፣ቀጥተኛ፣ትክክለኛ ማለት ነው:: የቤተ-ክርስቲያን ቀኖና ሲባል የቤተ ክርስቲያን ህግ ቀጥተኛ እምነት(ዶክትሪን) ማለት ነው:: የቅዱሳት መጽሐፍት ቀኖና የሚባሉት ቤተ-ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖትን ለመግለጥና ለማስተማር እንደሚችሉ በጉባኤ የታመነባቸው መጽሐፍት ማለት ነው:: ይህ ስያሜ ለመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠው በአራተኛ ምዕተ አመት ገደማ በቅዱስ አትናቴዎስ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስረዳሉ:: የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ቀኖናዊያት መጽሐፍት ይይዛል:: ይህም ውሳኔ የተሰጠው የተቀደስ መጽሐፍት ለመሰብሰብ ተብሎ በሎዶቂያ ጉባኤ በተወሰነው መሰረት ነው:: (Canonical Bible)

ሁለት አይነት ቀኖና መጽሐፍት አሉ እነርሱም፤
- 1ኛ (የመጀመሪያ) ቀኖና መጽሐፍት(protocanonical)
- 2ኛ (ሁለተኛ)ቀኖና መጽሐፍት(deuterocanonical) ይባላሉ፡፡

2.1 1ኛ ቀኖና መጽሐፍት (protocanonical)
1ኛ ቀኖና መጽሐፍት የሚባሉት በክርስትናውዓለም ያለ ልዩነት ተቀባይነት ያላቸውን መጽሐፍት ነው:: ይህ ማለት በኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ ፣በካቶሊኮች፣በፕሮቴስታንትና አይሁድ ዘንድ እኩል ተቀባይነት ያላቸው መጽሐፍት ናቸው:: እነዚህም 39(በእኛ አቆጣጠር 46) የሚሆኑት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ናቸው::

2.1.2 2ኛ ቀኖና መጽሐፍት (deuterocanonical)
2ኛ ቀኖና መጽሐፍት የሚባሉት አምላካዊያን መጽሐፍትነታቸው በጥናታውያን አብያተ ክርስቲያን ቦታ ያገኙና ተቀባይነት ያላቸው ሲሆኑ በሌሎች ወገኖች ደግሞ አንዳንዶቹ እንደ አዋልድ መጽሐፍት ተቀባይነት ሲያገኙ አንዳንዶች ጋር ተቀባይነት ያላገኙና መጽሐፍት ናቸው::

2.2 የመጽሐፍ ቅዱስ አቆጣጠር
2.2.1 የአይሁድ አቆጣጠር
፡-በአይሁድ መጽሐፍ አቆጣጠር ውስጥ የተካተቱ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ክፍል ብቻ ናቸው፡፡ በሐዲስ ኪዳን የተገለጠው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመቀበላቸው ምክንያት የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት በአይሁድ ቀኖና መጽሐፍት ውስጥ አይካተቱም፡፡ የአይሁድ ቀኖና መጽሐፍት የሚባሉት 24 የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ሲሆኑ አከፋፈላቸው እና ዝርዝራቸው እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

- አምስቱ የሙሴ መጽሐፍት - የመዝሙር እና የጥበብ መጽሐፍት
- የነቢያት መጽሐፍት - የታሪክ መጽሐፍት
ኢያሱ፣መሳፍንት 1ኛ እና 2ኛ ሳሙኤል፣1ኛ እና 2ኛ ነገስት

- ኢሳያስ፣ኤርሚያስ፣ሕዝቅኤል እና 12ቱ ደቂቀ ነቢያት ናቸው::
- መዝሙረዳዊት፣ምሳሌ፣ኢዮብ፣መኃልየ መኃልየ፣ሩት፣ሰቆቃው ኤርሚያስ፣መክብብ፣አስቴር፣ዳንኤል፣ዕዝራ ነህሚያ(ወይም 2ኛ ዕዘራ) እና 1ኛ እና 2ኛ ዜና መዋዕል

2.2.2 የፕሮቴስታንት አቆጣጠር
ከላይ ያሉት አይሁድ የሚቀበሏቸውን በሙሉ ይቀበላሉ:: በአቆጣጠር ለያይተው አይሁድ 12ቱን ደቂቀ ነብያት መጽሐፍት እንድ አንድ ይቆጥሩ የነበረውን ፕሮቴስታንቶች ለየ ብቻ በመቁጠር 39 አድርሰዋል:: ከሐዲስ ኪዳን 27 በአጠቃላይ 66 መጽሐፍት ይቀበላሉ::

2.2.3 የካቶሊኮች አቆጣጠር
39ኙን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ሁሉንም ይቀበላሉ፡፡ መጽሐፈ ምሳሌ ከምዕራፍ 25 እስከ 31 ያለው መጽሐፈ ተግሳጽ ተብሎ እንደ አንድ መጽሐፍ ይቆጠራል:: በተጨማሪም 7 የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ማለትም፡-
- መጽሐፈ ጦቢት
- መጽሐፈ ዮዲት
- መጽሐፈ ጥበብ
- መጽሐፈ ሲራክ
- መጽሐፈ ባሮክ
- 1ኛና 2ኛ መቃቢያን ይቀበላሉ፡፡
ከሐዲስ ኪዳን 27 መጽሐፍ ይቀበላሉ:: በአጠቃላይ 73 መጽሐፍት ይቀበላሉ:: የኢትዮጲያ ኦ/ተ/ቤ/ክ የምትቀበላቸው 81 ቅዱሳት መጽሐፍት ነው:: ከብሉይ ኪዳን 46 ከሐዲስ ኪዳን ደግሞ 35 መጽሐፍትን ትቀበላለች፡፡