Advertisement Image

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች

ምዕራፍ አራት : የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ዝርዝር ጥናት

4.1 የህግ መጽሐፍት (ብሔረ ኦሪት)
ኦሪት፡- የሚለው ቃል የሱርስት ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ብርሃን ማለት ነው:: መዝ 118-105 ዕብራዊያን ቶራ ብለው ይጠሩታል:: ትርጉሙም ህግ ማለት ነው:: የህግ መጽሐፍት የሚባሉት አምስት(5) መጽሐፍት ሲሆኑ የተጻፉትም በነቢየ እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት ነው:: ሙሴ ከሌዋዊያን ወገን የተወለደ ታላቅ አባት ነው:: የእስራኤልን ህዝብ ከግብጽ ባርነት ያወጣ ዘንድ እግዚአብሔር የመረጠው ታላቅ መሪ ነው:: አስተዳደጉ በፈርኦን ቤት ቢሆንም ልቡ የወገኖቹን ጉዳት ይመለከት ስለነበር በእግዚአብሔር ፈቃድ አስቸጋሪውን የእስራኤል ህዝብ ይመራ ዘንድ ተመረጠ:: ነብዩ ሙሴ እግዚአብሔርን ከ570 ጊዜ በላይ ቃል በቃል ያነጋገረ፣ በእግዚአብሔር አንደበት እንድ ሙሴ ያለ ትሁት ሰው የለም ተብሎ የተመሰከረለት ታላቅ አባት ነው፡፡

በአጠቃላይ አምስቱ የሙሴ መጽሐፍት ጠቅለል ባለመልኩ የሰው ልጅና የሌሎችን ፍጥረታት አፈጣጠር፣ የእስራኤላዊያንን ስደት እንዲሁም ከስደት መመለስን፣ የተስፋይቱን ምድር መወረስና ሌሎችንም አቤት ታሪኮች ይዘዋል:: ከ5ቱ የኦሪት መጽሐፍት በመጀመሪያ የምንመለከተው ኦሪት ዘፍጥረትን ነው::

4.1.1 ኦሪት ዘፍጥረት
ይህ መጽሐፍ የስነ ፍጥረት ልደት ወይም አጀማመር እንዴት አንደመጣ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው:: የፍጥረታትን ልደት የሚዘክር በመሆኑ ኦሪት ዘልደት ተብሎም ይጠራል:: የመጽሐፍ ቅዱስን የታሪከ ቅደም ተከተል ከመጠበቅ አንጻር በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ይገኛል:: ዘፍ 1-1 ነገር ግን በመጀመሪያ የተጻፈው መጽሐፈ ሔኖክ ነው፡፡ ነብዩ ሙሴ ስለ ስነ-ፍጥረት የጻፈው በወቅቱ ኖሮ ሳይሆን እንደ ቤተ-ክርስቲያን አስተምህሮ 40 ቀን 40 ሌሊት በጾምና በጸሎት ቆይቶ ህግጋትን ሲቀበል ፍጥረታት ከመፈጠራቸው ጀምሮ እርሱ እስካለበት ዘመን ድረስ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ምስጢር ገለጦለት(አስተምሮት) ጽፎታል:: አንድም ከአባቶቹ በትውፊት የሰማውን ጽፎታል፡፡ የመጽሐፉ ዓላማ ከስነ ፍጥረት አንስቶ እስራኤላዊያን ወደ ግብጽ ምድር እስከወረዱበትጊዜ ደረስ ያለውን የመለኮት መገለጥ ታሪክ በአጭሩ የሚያስረዳ ነው::

የመጽሐፉ አከፋፈል-ኦሪት ዘፍጥረት 50 ምዕራፎች በወስጡ የያዘ ሲሆን ለጥናት ይረዳን ዘንድ አቤት የታሪኮቹ አከፋፈል እንደሚከተለው ይቀረባል:-

ምዕራፍ 1-2 ስለ ስነ-ፍጥረትና ስለ ሰው ነጻ ፍቃድ ይናገራል::
ምዕራፍ 3-4 ስለ ሰው ልጅ ፈተናና ውድቀት፣ ከገነትም ስለመባረሩ ይናገራል::
ምዕራፍ 5-10 የቅዱሳን አበውን ታሪክ ይናገራል::
ምዕራፍ 6-11 ስለ ጥፋት ውሃ፣ ስለ ኖኀ ቤተሰቦች ድህነት፣ ስለ ስናኦር (ባቢሎን)ሰዎች ግንብ መሰረት(በእግዚአብሔር ላይ መነሳት)፣ ስለ ቋንቋ መደበላለቅ ይተርካል::
ምዕራፍ 12-23 ስለ አብርሐም ታሪክ
ምዕራፍ 24-26 ስለ ይስሐቅ ታሪክ
ምዕራፍ 27-36 ስለያዕቆብታሪክ
ምዕራፍ 37-50 ስለ ዮሴፍ ታሪክ ይናገራል፡፡

በአጠቃላይ ኦሪት ዘፍጥረት ብዙ ጠቃሚ ነገሮች ያስተምረናል፡፡ የዓለም ፈጣሪ እና መጋቢ እግዝአብሔር ከፍጥረታት ሁሉ አስበልጦ ለፈጠረው ለሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ መሰጠቱ፡፡ ይህ ነጻነት የሰው ልጁ ኃጢአትን ለመስራት እንደተጠቀመበት ያስረዳል፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአትን እንደሚጠላ፣ ኃጢአተኞችን ደግሞ እንደሚቀጣ፣ ቅዱሳንን በህይወት ሁሉ እንደሚጠበቅ የሚያስተምሩ የብዙ ትምህርቶች እና ቁም ነገሮችን በውስጡ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡

4.1.2 ኦሪት ዘጸአት
ጸአት፡- ማለት የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም መውጣት ማለት ነው፡፡ ይህንን ስያሜ ያገኘው የእስራኤል ህዝቦች ለ430 ዘመናት የግፍና የመከራ ኑሮ በኋላ በሙሴ መሪነት ከግብጽ ምድር መውጣታቸው እና የተስፋይቱ ምድርን ለመውረስ የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያሳይ በመሆኑ ነው፡፡ 70 ሆነው ወደ ግብጽ ምድር የገቡት የያዕቆብ ልጅ ሲወጡ ከ60000 በላይ ሆነው ወጡ፡፡

መጽሐፉ 40 ምዕራፎች በወሰጡ የያዘ ሲሆን አከፋፈሉ እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

ከምዕራፍ 1-4
- ግብጻዊያን በእስራኤላዊያን ላይ ስለፈጸሙት ግፍ
- ስለ ሙሴ ልደትና ስለወንድሞቹ እርዳታ
- ሙሴ ከፈርኦን ሸሽቶ ወደ ምድያም ስለመሄዱ
- በሚነደው ቁጥቋጦ ውስጥ የሙሴ መጠራት
ከምዕራፍ 5-11
- ሙሴ እና አሮን ከፈርኦን ጋር መከራከራቸውን ይተርካል
- በእስራኤለዊያን ላይ የባርነት ቀንበር ስለመጠበቁ
- በፈርኦን እንቢተኝነት በግብጽ ስለመጡት አስራ አንድ መቅሰፍቶች
ከምዕራፍ 12-15
- እስራኤላዊያን ከግብጽ ምድር ስለመውጣት
- ግብጻዊያን እስራኤላዊያንን ከለቀቁ በኋላ እንደገና በመከተላቸው በእግዚአብሔር ድንቅ ስራ እስራኤላዊያን ባህረ
ኤርትራ ተሻግረው ሲሄዱ ግብጻዊያን ግን በባህር ውስጥ ሰጥመው መቅረታቸውን ይተርካል፡፡
- እስራኤላዊያን በመዝሙር እግዚአብሔርን ማመስገናቸው፡፡
ከምዕራፍ 16-40
- በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት 10ቱ ትዕዛዛት የተጻፈበትን ጽላት መስጠቱ
- ለእስራኤል መተዳደሪያ ደንቦች መሰጠታቸው
- ስለ ደብተራ ኦሪት አሰራር የተሰጠ መመሪያ
- ስለ አሮን ስልጣነ ክህነት፣ስለ ልብሰ ተክህኖ እና ስለ ስርአተ አምልኮ
- እስራኤላዊያን የወርቅ ጥጃ ሰርተው ስለማምለካቸውና ሙሴም ለአምላክ ቀንቶ ጽላቱን በጣኦቱ ላይ መሰበሩ እና የቃልኪዳኑ ህግ ድጋሚ መሰጠቱ ይተርካል፡፡
- የእስራኤል ልጆች ወደ ከነአን በሚያደርጉት ጉዞ ከሰማይ መና እየወረደላቸው እየተመገቡ ስለመጓዛቸው
- እግዚአብሔር አሮንን እና ልጆቹን መርጦ መቅደስ እንዲሰሩለት ማዘዝ
- በሲና ተራራ እንደተገለጠው የእግዚአብሔር ማደሪያ መስራታቸው

ኦሪት ዘጸአትን ጠቅለል ባለመልኩ መልኩ ስንመለከት የሰው ልጅ ከህገ ልቦና ዘመን ወደ ህገ ኦሪት ዘመን(ከልቦናዊ ህግ ወደ የጽሑፍ ህግ) የተሸጋገረበት ሂደትን የሚያሳውቅ መጽሐፍ ሲሆን የበደል ውጤት ምን እንደሆነ እና እግዚአብሔር ህዝቡ በመከራ ጊዜ እንደማይረሳ ያስተምረናል፡፡ በተጨማሪም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ታሪክ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ምሳሌ ነው፡፡ ግብጽ የሲኦል ፈርኦን እና ሰራዊቱ የዲያቢሎስና የጭፍሮቹ፣ሙሴ የክርስቶስ፣የሙሴ በትረ የመስቀል፣እስራኤል የክርስቲያኖች፣ከነአን የመንግስተ ሰማያት፣ባህረ ኤርትራ የጥምቀት፣በረሐውና ሙቀቱ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ፈተና፣የበጉ ስጋ እና ደም የክርስቶስ ስጋ እና ደም(ቅዱስ ቁርባን) ምሳሌ ናቸው፡፡

4.1.3 ኦሪት ዘሌዋውያን
በብሉይ ኪዳን ህዝበ እስራኤል ኃጢአት ሲሰሩ የሚያስታርቋቸውና ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቧቸው የሌዋዊያን ካህናት ነበሩ፡፡ ይህ መጽሐፉ ዘሌዋውያን የሚለው ስያሜ ያገኘው ከአስራ ሁለቱ ነገደ አንዱ በሆነው በሌዊ ነገድ ስም ነው፡፡ መጽሐፉ ለእግዚአብሔር ስለሚቀርቡ የመስዋዕት አይነቶች ይገለጻል፡፡በተጨማሪም ስለበዓላት አከባበር፣ ለእስራኤላዊያን ስለተሰጡ ማኀበራዊ እና ግለሰባዊ ህጎች ይተርካል፡፡ ኦሪት ዘሌዋውያን የቅድስና ህይወት የሚገኝበት መጽሐፍ ነው፡፡ስለቅድስና ብዙ ጊዜ ስለሚነገር የቅድስና መጽሐፍ ተብሎ ይጠራል፡፡ይህ መጽሐፍ 27 ምዕራፎች በውስጡ ይዟል፡፡በዘሌዋውያን ውስጥ ከሚገኙት አቤት ትምህርቶች መካከል የመስዋዕት አይነቶች እና የበዓላት አከባበር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

4.1.3.1 የመስዋዕት አይነቶች
ሀ.የሚቃጠል መስዋዕት ፡-በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም የመስዋዕት አይነት ነው፡፡ (ዘሌ.6፣8-13)
ለ.የደኀነት መስዋዕት ፡-ህዝቡ ከእግዝኣብሔር ጋር የቅድስና ህብረት እንድኖርው የሚቀርብ መስዋዕት ነው፡፡(ዘሌ.3፣1-17)
ሐ.የበደል መስዋዕት ፡-ይህ መስዋዕት የሚቀርበው አንድ እስራኤላዊ እግዝኣብሔርን መበደሉን ሳያውቅ ቆይርቶ መበደሉን ባወቀ ጊዜ የሚቀርብ መስዋዕት ነው፡፡(ዘሌ.5፣4-7)
መ.የኃጢአት መስዋዕት ፡- 10ቱን ትዕዛዛት በተላለፈ ጊዜ የሚቀርብ መስዋዕት ነው፡፡(ዘሌ.4፣5-25)
ሠ.የስዕለት መስዋዕት ፡-የተሳለው ስዕለት ሲሰምርለት የሚቀርበው መስዋዕት ነው፡፡(ዘሌ.6፣7-15)
ረ.የፈቃድ መስዋዕት ፡-ይህ መስዋዕት ከሌሎች የሚለየው የግዳጅ መስዋዕት ሳይሆን አንድ እስራኤላዊ ህይወቱ(ቤቱ) የተስተካከለ ሲሆን በፈቃዱ የሚያቀርበው መስዋዕት ነው፡፡

4.1.3.2 የበዓላት አከባበር
እስራኤላዊ እግዝኣብሔር ያደረገላቸው ነገር የሚዘክሩባቸው የተለያዩ በዓላት ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ የሚከተሉት እንመለከታለን፡-

1.የሰንበት በዓል፡- ሰንበት ማለት እረፍት ማለት ሲሆን እግዝአብሔር በ6ቱ ቀናት ፍጥረታት ፈጥሮ በሰባተኛ ቀን ማረፉን በማሰብ የሚከበር በዓል ነው፡፡የሰንበት በዓል አከባበር እንደ ህግ የተሰጠው በዚህ መጽሐፍ ላይ ነው፡፡ እንደ ሊቃውንተ ቤ/ክ አስተምህሮ ሶስት አይነት ሰንበታት ሲኖር ይህ መጽሐፍ የሚዘከር ስለ ሰንበት አይሁድ ነው፡፡በሐድስ ኪዳን በሰንበት አይሁድ በሰንበተ ክርስቲያን (በዕለተ እሑድ)ተተክታለች፡፡

- ሰንበት እግዝአብሔር(ሰንበተ አይሁድ) ወይም 7ተኛ ቀን
- ሰንበተ ከንዓን (ከግብጽ ምድር የወጡበት ቀን)
- ሰንበተ መንግስተ ሰማያት

2.በዓለ ፋሲካ (የነጻነት በዓል)፡- ከግብጽ ምድር (ከባርነት የወጡበት) የነጻነታቸው ቀን በማሰብ የሚከብሩት ነው ፡፡አይሁዳዊያን ፋሲካ ማክበር የጀመሩት ከግብጽ ምድር ሳይወጡ ነው፡፡ዘዳ 12 በዓለ ፋሲካ የአይሁድ አዲስ ዓመት በገባ በመጀመሪያው ወር(ሚያዝያ) 14 ቀን የሚከበር በዓላቸው ነው፡፡በሐዲስ ኪዳን በበዓለ ፋሲካ በዓለ ትንሣኤ ተተክቷል፡፡/p>

3.የቂጣ በዓል፡-የፋሲካን በዓል ካከበሩ ከ15 ቀን በኋላ ለ7 ቀናት የሚያከብሩት በዓልነው፡፡በወንጌል የቂጣ በዓል በደረሰ ጊዜ ተብሎም ተተቅሷል፡፡

4.በዓለ ሰዊት /የእሸት በዓል/፡- በዓለ ሰዊት ከ7 ሰንበታት /49 ቀናት/ ነዶ ሰብስበው በ50ኛ ቀን ያከበሩት የነበረ በዓል ነው፡፡በዓለ ሰዊት በበዓል ጰራቅሊጦስ ተተክቷል፡፡

5.ሠርቀ ወር፡- በሰባተኛ ወር በመጀመሪያ ቀን (ጥቅምት 1) መለከት በመንፋት የሚክብሩት በዓል ነው፡፡በሠርቀ ወር መጠቅ እና አበቅቲ ተተክቷል፡፡

6.ዕለተ አስተሰርዮ፡-ይህ በዓል የሚከበረው በሰባተኛ ወር በ10ኛ ቀን (ጥቅምት 10) ሲሆን ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት የህዝቡ ኃጢኣት የሚያስተሰርይበት ቀን ነው፡፡ይህ በዓል የሚከበረው የዮሴፍ መሸጥን ምክንያት በማድረግ አባቶቻችን ኃጢአት በእኛ ላይ አይሁን በማለት ያቀርቡ ነበር፡፡በዕለተ አስተሰርዮ የጥምቀት በዓል ተተክቷል፡፡

7.በዓለ መጸለት፡- ይህ በዓል ከጥቅምት 15 ጀምሮ ለ7 ቀናት ያህል የሚከበር ሲሆን ህዝቡ ከቤት ወጥቶ የቅጠል ዳስ በመስራት ያከብረዋል፡፡በበዓለ መጸለት የልደት በዓል ተተክቷል፡፡

የኦሪት ዘሌዋውያን መጽሐፉ አከፋፈል፡- ከላይ እንደ ተጠቀሰው መጽሐፉ 27 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን አከፋፈሉም እንደሚከተለው ይቀረባል

ከምዕራፍ 1-7 ስለ መስዋዕት አይነቶች፣ ከእግዝአብሔር ድህነት ስለመለመንና ለምስጋና
ከምዕራፍ 8-10 ለክህነት አገልግሎት አሮን እና ልጆቹ እንደተሾሙ
ከምዕራፍ 11-14 ስለሚበሉ እና ስለማይበሉ እንሰሳት፣ የእስራኤላዊያን ሴቶች ልጅ ሲወለዱ ስላለው ስርዓተ
ከምዕራፍ 15-16 ከወንድ እና ከሴት ስለሚወጡ ፈሳሾች መንጻት ስነ-ሥርዓት
ከምዕራፍ 17-22 ስለተከለከሉ ጋብቻዎች፣ ከጥንቆላ ስራ ስለመከልከል
ከምዕራፍ 23- 27 ስለ በዓላት አከባበር፣ ስለ ትዕዛዛት መጠበቅ የሚሰገኑ በረከቶች ይተረካል፡፡

ማጠቃለያ:- ኦሪት ዘሌዋውያን ህዝበ እስራኤል ከእግዝኣብሔር ጋር በቅድስና ለመኖር እንደችሉ የተሰጡ ህጎች እና የተለያዩ መመሪያዎች ይዟል፡፡የተሰጡት መጠበቅ ወደ ቅድስና ህይወት እንደሚድርስ መሆኑን ሲያሳይ በተቃራኒ መተላለፍ ደግሞ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት እንደሚያሰከትል ያስተምረናል፡፡ኦሪት ዘሌዋዊያን የኦሪት ዘጸአት ትርጓሜ ነው፡፡ ምክንያት በዘጸአት ውስጥ የተሰጡት መመሪያዎች እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረጉ ሰለሚያስተምር ነው፡፡ (ዕብ 7፣11)

4.1.4 ኦሪት ዘኁልቅ
ኁልቅ ማለት የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ቆጠረ ማለት ነው፡፡ እስራኤላዊያን ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ መቆጠራቸው ስለሚተርክ ዘኁልቅ ተባለ፡፡ ኦሪት ዘኁልቅ 36 ምዕራፎች ሲኖሩት በውስጡ የሚከተሉትን ፍሬ ሀሳቦች ይዟል፡

ሀ.ምድረ ከነዓንን እንዲሰልሉ የተላኩ ከ12ቱ ሰላዮች ከኢያሱ እና ከካሌብ በቀር የምድሪቱን ለምነት ፍሬዎች በማሳየት ከገለጹ በኋላ በምድሪቱ ላይ ሚኖሩህዝቦች ከእነርሱ እንደሚበረቱ በመናገራቸው እስራኤልዊን ሁከት በማስነሳታቸው ምክንያት 40 ቀን ይፈጅ የነበረውን ጉዞ እግዚአብሔር ተቆጥቶ 40 ዓመት በበረሀ እንዲንከራተቱ አድርጓቸዋል፡፡20 አመት ሞልቷቸው ከግብጽ ምድር ከወጡት መካከል ምድረ ርስትን የወረሱት ኢያሱና ካሌብ ብቻ ነበሩ፡፡

ለ.ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን በማግባቱ አሮንና ማርያም በሙሴ ላይ ማመጻቸው በዚህም ምክንያት ማርያም በለምጽ መመታቷን፣ እና በለአም እስራኤልን ለመርገም ጉዞ እንደጀመረ ያትታል፡፡

የመጽሐፉ አከፋፈል

ከምዕራፍ 1-12
- እስራኤላዊያን በየነገዳቸው መቆጠራቸው
- ከሲና ተራራ እስከ ቃዴስ በረሀ ድረስ ያደረጉት ጉዞ
- የሙሴ ኢትዮጲያዊቷን ማግባት አሮንና ማርያምን እንዳስቆጣ በዚህም ማርያም እንደተቀጣች
ከምዕራፍ 13-25
- ከነአንን ይሰልሉ ዘንድ ስለተላኩ ሰላዮች
- ስለ 10ሩ ሰላዮች መቀሰፍ
- ሙሴ ስለህዝቡ ማማለዱ
- እስራኤላዊያን ለሙሴ ባለመታዘዛቸው ለ40 ዓመት በምድረ በዳ መንከራተታቸው
- በለአም እራኤልን ለመርገም ያደረገው ጉዞ
ከምዕራፍ 26-36
- ህዝበ እስራኤል ወደ ምድረ ርስት(ከነአን) ለመግባት መዘጋጀታቸውን ይተርካል

መጽሐፉን ጠቅለል ባለመልኩ ስንመለከተው ታላቅ ተአምራትን በማደረግ ከግብጽ ምድር ያወጣቸው የእግዚአብሔር ኃይልን በመርሳት የከነአን ሰዎችን ኃይልን በመስጋት በሙሴ ላይ ህዝቡ በማመጹ ምክንያት የ40 ቀን መንገድ 40 አመት መሆኑና የሙሴ (የቅዱሳን) የማማለድ ስልጣንን እንዳላቸው ያስተምራል፡፡

4.1.5 ኦሪት ዘዳግም
ዘዳግም፡- ማለት በግዕዝ የተደገመ ማለት ሲሆን ሙሴ ከ40 ዓመት በፊት በተጻፉት በሶስቱ መጽሐፍት(በኦሪት ዘጸአት፣ዘሌዋዊያንና ዘኁልቅ) ላይ የነበሩት የእስራኤላዊያን ታሪክና ህግ በድጋሚ ለአዲሱ ትውልድ የሚያስታመርበትን ትምህርት የያዘ በመሆኑ ይህን ስያሜ አግኝቷል፡፡ይህ የሆነበት ምክንያት 20 ዓመት ሞልቷቸው ከግብጽ ምድር ከወጡት መካከል በህይወት የተገኙት (ህግና ታሪክ የሚያውቁት) ሙሴ፣ ኢያሱና ካሌብ ሲሆኑ አብዛኞቹ በምድረ በዳ በአመጽ ምክንያት አልቀዋል፡፡ ስለሆነም ህጉ ሲሰጥ ያልነበረው አዲስ ትውልድ የእግዚአብሔር ድንቅ ስራ እንዲያውቁና የተሰጡ ህግጋት በመጠበቅ የትውልድ ኃላፊነት እንዲወጣ በማሰብ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሙሴ በሞአብ አገር ኦሪት አስተምሯቸዋል፡፡

የመጽሐፉ አከፋፈል

ኦሪት ዘዳግም በውስጡ 34 ምዕራፎች የያዘ ሲሆን ለማጥናት ይመችን ዝንድ እንደሚከተለው ይከፈላል፡-

ከምዕራፍ 1-4 በሙሴ መሪነት የተከናወነ የእስራኤል ህዝብ ታሪክ መደገም
ከምዕራፍ 5-26 ከእግዚአብሔር የተሰጡ ህግጋት እንደተደገሙና ህዝቡ ህግጋቱንእንዲጠብቅ የተሰጡ ምክሮችን
ከምዕራፍ 27-30 ለሰዎች የተሰጡ ምርጫዎች በመታዘዝ በረከት ባለመታዘዝ መርገም እንዳለ ያስተምራል
ከምዕራፍ 31ወደፊት ስለሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች መግለጽ
ሀ. የሙሴ መሞት
ለ. የእያሱ በእግዚአብሔር ፈቃድ መሾም
ሐ. የሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት መቀዝቀዝ
መ. የሰዎች በጥፋት ምክንያት መቀጣት
ከምዕራፍ 32-33 የመጨረሻዎቹ የሙሴ መዝሙርና በረከት እና ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነበየው ገለጸ ትንቢት፣
ምዕራፍ 34 ሙሴ በናባው ተራራ የተስፋ ምድርን መመልከቱና ማረፉንይገልጻል፡፡

4.2 የታሪክ መጽሐፍት ክፍል
በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ አከፋፈል ተረታ መሰረት በሁለተኛ ደረጃ የምናገኘው የታሪክ መጽሐፍት ክፍል ነው፡፡ ከአርባ ስድስቱ መጽሐፍት መካከል አስራ ሰባቱ የታሪክ ይዘት ያላቸው መጽሐፍት ናቸው፡፡ እነዚህ አስራ ስባቱ መጽሐፍትን በዚህ ክፈለ ትምህርት የምንመለከታቸው ይሆናል፡፡

የታሪክ መጽሐፍት ተብለው የሚጠሩት መጽሐፍት ከእያሱ ወልደ ነዌ እስከ ዮሴፍ ወደ ኮሪዮን ያሉት ሲሆኑ ቁጥራቸው 17 ናቸው፡፡ በታሪክ መጽሐፍት ውስጥ የሚናገኘው ጠቅላላ ሀሳብ በእግዝአብሔር እና በእስራኤል መካከል ስለነበረው ግንኙነት ነው፡፡ ከእነዚህ መጽሐፍት አንዳንዶቹ በአይሁድ ቀኖና መጽሐፍት ከነቢያት መጽሐፍ ቢመደቡም ከመጽሐፍቶቹ ይዘት አንጻር 72ቱ ሊቃውንት በታሪክ መጽሐፍት እንዲመደቡ ወስነዋል፡፡እስራኤላዊያን በሙሴና በኢያሱ መሪነት ምድር ርዕስትን ከወረሱ ጀምሮ እስከ ባቢሎን መርኮ እና ከመርኮ በኋላ ስላሉት አመታት የእስራኤላዊያን ታሪኮች ይተርካል፡፡ከ17ቱ የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ በሴቶች የተሰየሙት ሁለት ሲሆኑ እነርሱም መጽሐፈ ሩት (ሙኣባዊት) እና መጽሐፈ አስቴር (እስራኤላዊት) ናቸው፡፡ ከዚህ በመቀጠል 17ቱ የታሪክ መጽሐፍት በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

4.2.1 መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ
የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ኢያሱ ሲሆን (8 ፣2 24፣26) ሙሴን እየረዳ ከልጅነቱ ጀምሮ የተከተለው ኢያሱ ከሙሴ ሞት በኋላ ህዝብ እስራኤልን እንዲመራ በእግዚአብሔር የተመረጠ ታላቅ አባት ነው፡፡

እያሱ፡-ማለት አዳኝ፣መሪ፣መድኃኒት ማለት ነው፡፡ኢያሱ የእስራኤል ህዝብ ከስጋ ጠላቶቻቸው ስላዳናቸው መድኃኒት ተብሏል፡፡

<ኢየሱስ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ሁሉ ከነፋስ ጠላት ከሞትና ከዲያብሎስ ያደነን በመሆኑ እውነተኛ መድኃኒት ማለት ነው፡፡ (ማቴ.2፣21፣ ሉቃ.2፣10)

የመጽሐፉ ዋና ይዘት ኢያሱ ህዝቡን ለማስተዳደር ያደረገው ትግል እና የተስፋይቱ ምድር መውረሳቸውን ያትታል፡፡በእግዚአብሔርኃይልበኢያሱ መሪነት ህዝብ እስራኤል የዮርዳኖስ ወንዝን ተሻግረው በተስፋይቱ ምድር ላይ ይኖሩ የነበሩ ነገስታት ድል በማድረግ በየነገዳቸው መስፈራቸው ይተርካል፡፡

የመጽሐፉ አከፋፈል፡- መጽሐፈ ኢያሱ 24 ምዕራፎች በውስጡ ይዟል፡፡ እንደሚከለተው ይቀርባል፡-
ከምዕራፍ 1-5 የእስራኤል ህዝብየዮርዳኖስን ወንዝ መሻገርና ወደ ከነዓን መግባት
ከምዕራፍ 6-12 የከነዓንን ሰዎች ማሸነፋቸው /የአሞራዊንን እና የአሦርን ነገስታት ድል ማድረጋቸው/
ከምዕራፍ 13-22 ህዝብ እስራኤል ምድር ከነዓንን በየነገዳቸው መከፋፈላቸው
ከምዕራፍ 23-24 የመጨረሻው የኢያሱ ምክር እና ሞት

መጽሐፈ ኢያሱ ጠቅለል ባለመልኩን ስንመለከተው በውስጡ፡- የቅዱሳን መላዕክት ተራዳይነትና ክብር(ኢያ.5፣13)፣ የዕምነት ኃያልነት (6፣15-21)፣ የዓላማ ጽናትን እና ለታቦት የሚሰጥ ክብርን ያስተምረናል፡፡

4.2.2 መጽሐፈ መሳፍንት
መሳፍንት፡- ማለት መስፍን የሚለው ቃል ብዥ ሲሆን ትርጉሙም ገዢ፣አስተደዳሪ፣መሪ፣ፈራጅ(ዳኛ) ማለት ነው፡፡ዋና ሐሳቡ እስራኤላዊያንዋና ንጉስ እንዳልነበራቸው እና በእግዚአብሔር ተመርጠው ጠላቶቻቸው ድል በሚያደርጉ መሳፍንት መገዛታቸውን በሰፊው ይተርካል፡፡እስራኤላዊያን ለ300 አመታት (አንዳንድ መጽሐፍት 450 ዓመታት ይላሉ) 13 በሚደርሱ መሳፍንት ተመረተዋል፡፡ ከእነርሱም አንዷ ሴት ስትሆን ስሟም ዲቦራ ይባላል፡፡መጽሐፉ በተለይ የጌዴዎንን፣የባርቅና ዲቦራን፣ዮፍታሔንና የሳምሶያን ታሪክ አጉልቶ ያሳያል፡፡(ዕብ.11፣32-35) ከእነዚህ መካከል አቤሜሌክ የተባለው ህግ እግዚአብሔርን በመቃወሙ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡መጽሐፉ 21 ምዕራፎች ሲኖሩት ጻፊው ነብዩ ሳሙኤል እንደሆነ ሊቃውንተ ቤ/ክ ያስተምራሉ፡፡ሳሙኤል የኖረው በ1200 እና በ1020 ዓ.ዓ መካከል በመሆኑ ይህ ዘመን ዘመነ መሳፍንት የሚባልበት ዘመን በመሆኑ የመጽሐፉ ጸሐፊ ነብዩ ሳሙኤል እንደሆነ ያሳያል፡፡(አንዳንድ ሊቃውንት ሳሙኤል የነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር ገልጦለት ጽፎታል ይላሉ፡፡) በቤተ-እስራኤል ተሹመው እስራኤልን ሲስተዳድሩ የነበሩት መሳፍንት የሚከተሉት ናቸው፡-

1. ኀቶሊያል(3፣1-11) የመሶፕታሚያ ጠላቶቻቸው ድል ያደረገው መስፍን
2. ናኦድ (3፣12-31) ሞአባዊያን፣አሞናዊያንንና አማሌቃዊያን ጠላጦቻቸው የነበሩ ሲሆን አዳኛቸው ናአድ ነበር፡፡
3. ሰሜጋር (3፣31)
4. ዲቦራ (4እና5 )
5. ጌድዎን (6፣8-11)
6. አቤሜሌክ ( 9፣1-57)
7. ቶላ ( 10፣1-2)
8. ኢያሱ (10፣3-5)
9. ዮፍታሔ( 11፣1 )አሞናዊያን ጠላቶቻቸው ሲሆኑ አዳኛቸው ዮፍታሔ ነበር
10. አብዳን ( 12፣8-10)
11. ኤሎም ( 12፣11-12)
12. ዓብዩን (12፣13-15)
13. ሶምሶን ( 13፣16-31) ከፍልስጤማዊያን ጠላቶቻቸው ያዳናቸው መስፍን ነው፡፡

4.2.3 መጽሐፈ ሩት
መጽሐፈ ሩት በአንስት ከተሰየሙት ጥቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል አንዱ ነው፡፡

የመጽሐፈ ሩት ጸሐፊ ነቢዩ ሳሙኤል ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በዘመነ መሳፍንት መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ ዋና ታሪኩ ሩት ስለምትባል ሙዓባዊት ሴት ይተርካል፡፡ በዚህ ምክንያት መጽሐፉ በስሟ ሊሰየም ችሏል፡፡ አቤሜሌክ የሚባል እስራኤላዊ ከኑአሚንና ከሁለት ወንድ ልጆቿ ጋር በመሆን በሀገረ እስራኤል ረሀብ በነገሰ ጊዜ ወደ ሞአብ ምድር እንደ እንደ ተሰደደ እና ከልጆቿ አንዱ ሩትን አግብቶ በሞአብ ምድር እንደ ተቀመጡ በዚህም ህይውቱ እንዳለፈ ይተረካል፡፡ ኑአሚን በሰው ሀገር በብቸኝነት መኖር አቅቷት ወደ ሀገሯ ስትመለስ ሩትም ‹ህዝብሽ ህዝቤ አምላክሽ አምላኬ› ብላ ከኑአሚን ጋር ወደ እስራኤል መጥታ ቦኤዝ የሚባል ሰው አግብታ የዳዊት አያት የሆነው ዒዮቤድን መውለዷ ይተርካል፡፡ በዚህ እምነቷ ከክርስቶስ የዘር ሀረግ ውስጥ ለመቆጠር ብቅታላች፡፡ ማቴ 1-15

የመጽሐፉ አከፋፈል

መጽሐፈ ሩት 4 ምዕራፎች በውስጡ የያዘ ሲሆን እንደሚከተለው ይከፈላል፡

ምዕራፍ 1 የአቤሜሌክ ቤተሰብ በሞአብ ሀገር
ምዕራፍ 2 ሩት በቦኤዝ ማሳ ውስጥ ቃርሚያ እንደቃረመች
ምዕራፍ 3 ሩት እንዲያገባት ቦኤዝን እንዳነጋገረችው
ምዕራፍ 4 ሩት የቦኤዝ ሚስት እንደሆነችና የዳዊትን አያት የእሴይን አባት አብድዩን እንደወለደች ይተርካል፡፡

4.2.4 መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማይ እና ካልዕ
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ እና ካልዕ እንደ ኢትዮጲያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቀኖና መጽሐፍት አቆጣጠር መሰረት እንደ አንድ መጽሐፍት ይቆጠራል፡፡ በቀደሙት ጊዜያት ሁለቱ መጽሐፍት እንደ ሁለት ይቆጠሩ ነበር፡፡ 72ቱ ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱስ ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ በተረጎሙ ጊዜ ከመጽሐፍቱ ይዘት አንጻር እንደ አንድ እንዲቆጠሩ ወስነዋል፡፡ መጽሐፉ የተጻፈው ከ1100ዓ.ዓ-1000ዓ.ዓ ገደማ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊው ነቢዩ ሳሙኤል ነው፡፡ 1ኛ ሳሙኤል በሁለት ይከፈላል፡-

ከምዕራፍ 1-24 ነቢዩ ሳሙኤል ጽፎታል ከምዕራፍ 25-31 ናታንና ጋድ ጽፈውታል

ሳሙኤል፡- ማለት እግዚአብሔር ሰማኝ ማለት ነው፡፡ የሳሙኤል አባት ህልቃና እናቱ ደግሞ ሐና ይባላሉ፡፡ እናቱ ሐና ልጅ በማጣቷ ታዝን እንደነበረ መጽሐፋይናገራል፡፡እግዚአብሔር ወንድ ልጅ ስለሰጣት ስሙን ‹‹እግዚአብሔር ሰማኝ›› ስትል አወጣችለት፡፡ በሊቀ ካህኑ በኤሊ ፊት ያገለግል ነበር፡፡እሱ ሲሞት ነቢዩ ሳሙኤል ሊቀ ካህነ ሆኖበእስራኤል ላይ ተሾመ፡፡ሳኦልና ዳዊትን ቀብቶ ያነገሰ እርሱ ነው፡፡በአጠቃላይ የመጽሐፉን ይዘት ስለመለከት የዘመነ መሳፍንት መፈጸሙንና ዘመነ ነገስት መጀመሩን ያትታል፡፡

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ አከፋፈል

ምዕራፍ1-7 ስለ ኤሊና ሳሙኤል
ምዕራፍ 8-15 ስለ ሳሙኤልና ሳኦል
ምዕራፍ 16-31 ስለ ሳኦልና ዳዊት በስፋት ይተርካል፡፡

መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ አከፋፈል

መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ዋና ይዘት አድርጎ የተነሳው የዳዊት አገዛዝን መተረክ ሲሆን ከ1000ዓ.ዓ ገደማ በናታንና ጋድ እንደተጻፈ ይታመናል፡፡ይህ ታሪክ በድጋሚ በ1ኛ ዜና መዋዕል ከምዕራፍ11-19 ድረስ ላይ ይገኛል፡፡

ከምዕራፍ 1-4 ዳዊት በይሁዳ ግዛት በኬብሮም ከተማ ለ7 አመታት እንደነገሰ
ከምዕራፍ 5-10 ቅዱስ ዳዊት ጠላቶቹን አሸንፎ ድል ማግኘቱን፣ መናገሻ ከተማውን ኢየሩሳሌም ማድረጉን እና የታቦተ ጽዮን ወደ ኢየሩሳሌም መመለሱን ይተርካል
ከምዕራፍ 11-19 የንጉስ ዳዊት ችግሮች
ሀ.የንጉሱ ኃጢአትና የደረሰበት ቅጣት (11-12)
ለ. በልጆቹ ከአምኖንና ከአቤሴሎም ጠብ የተነሳ የደረሰበት ችግር (13-14)
ሐ.በዳዊት የመጨረሻ ዘመኖች የሆኑ ልዩ ልዩ አመጻ፣ችግሮችናመከራዎች(20-24)

4.2.5 መጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊና ካልዕ
መጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊና ካልዕ ልክ እንደ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊና ካልዕ ሁሉ ከ70 ሊቃውንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በፊት እንደ ሁለት ይቆጠሩ ነበር፡፡ ከመጽሐፍቶች በውስጣቸው በያዙት ሐሳብ፣ ምስጢርና በታሪክ የሚመሳሰሉ ሰለሆኑ በአንድ እንዲቆጠሩ 72ቱ ሊቃናት ወስነዋል፡፡

1ኛና 2ኛ ነገስት ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን አንስቶ እስከ ይሁዳ መንግስት ማለቂያ ድረስ ያለውን 400 ዓመታት (ከ1000-590 ዓ.ዓ) የእስራኤልና የይሁዳ ንግስታት ታሪክ ይተርካል፡፡ መጽሐፈ ነገስትን ማን እንደ ጻፈ በግልጽ ባይታወቅም አንዳንዶች ኤርምያስ ነው ይላሉ፡፡

የመጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ አከፋፈል

መጽሐፋ 22 ምዕራፎች ያሉት ሲሆነ እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
ከምዕራፍ 1-10
- ሰሎሞን የአባቱን ዙፋን መወረሱን፣ በአባቱ ጠላቶች ላይ የወሰደው እረምጃ፣ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱ ለመስራት የነበረው ትጋትና የሠራው ቤተ መቅደስ ፍጻሜ
- የሰሎሞን ጥበብ ለማየት ንግስተ ሳባ ጉብኝትና በዘመኑ ሰለነበሩት ነብያት ናታን፣ አኪያና ኢዶ ይተረካል፡፡
ከምዕራፍ 11-22
- ሰሎሞን በፍቅረ አንስት ወድቆ ለጣኦት በመስግዱ እግዚአብሔርን ማሳዘኑ፣ ከነገደ ኤፍሬም የነበረው ኢዮርባዓምን በሰሎሞን መነሳቱ
- በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ዘመን የእስራኤል መንግስት ለሁለት መከፈሉንና ሰለ አራቱ የይሁዳን ነግስታት እና ሰለ 8ቱ የእስራኤል ነግስታት ታሪክ ይተርካል፡፡

የመጽሐፈ ነገስት ካልዕ አከፋፈል

መጽሐፋ 25 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
ከምዕራፍ 1-17 በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኘው ታሪክ እስራኤላዊያን በአሶራዊያን እስከተማረኩበት ጊዜ ድረስ የነበረው የይሁዳና የእስራኤል መንግስት ታሪክ ይተርካል፡፡
ከምዕራፍ 18-25 ስለ 16 የይሁዳ ነግስታትና ስለ 11 የእስራኤል ነግስታት በስፋት ይተርካል፡፡

4.2.6 መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ
ዜና መዋዕል ማለት የዕለት ዜና ማለት ነው፡፡ ይህም ከአዳም ጀምሮ ያለውን የአይሁድ ታሪክ እስከ ባቢሎን ምርኮ መመለስ ድርስ ያለው ሰለ ሚተርክ ይህንን ስያሜ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ቀድሞ በአይሁድ ቀኖና መሰረት እንደ አንድ ይቆጠረ ነበር ከሁለት የተከፈለው በሰባ ሁለቱ ሊቃውንት ነው፡፡ መጽሐፍ ዜና መዋዕል ሰለሃይማኖት እና ሰለመንፈሳዊ ነገሮች አብዝቶ ያወሳል፡፡ መጽሐፍ ነገስት ሰለመንግስት አስተዳደር በይበልጥ ያስረዳል፡፡ የዚህ መጽሐፍ ጻሐፊ እንዳንድ መጽሐፍት ዕዝራ ነው ሲሉ ሌሎች መጽሐፍት ደግሞ ሳሙኤል ነው ይላሉ፡፡

መጽሐፉ ሰለመሲሁ መምጣት ተስፋ ሰለነበረው ይሁዳ ተብሎ ሰለሚጠራው ደቡባዊ መንግስት በሰፊው ይተርካል፡፡ በተጨማሪም ሰለእግዚአብሔር ሁሉንቻይነት፣ ባለጠግነት ይገልጣል፡፡ (2ኛ ዜና 2፤6 1ኛ ዜና 29፤12)

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ አከፋፈል

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ በውስጡ 29 ምራፎችን የያዘ ሲሆን አከፋፈሉ እንደሚከትለው ይቀርባል፡

ከምዕራፍ 1-9 ስለ አይሁድ ጥንታዊ መንግስት
ከምዕራፍ 10-12 የሳኦል መሞት እና የዳዊት ታሪክ
ከምዕራፍ 13-16 የታቦተ ጽዮን ወደ እየሩሳሌም መመለስ
ከምዕራፍ 17- 22 ፍልስጤማዊን እና ሶርያውን በእስራኤላዊያንመሸነፋቸውን
ከምዕራፍ 23-26 ንጉስ ዳዊት ሌዋዊያንን መቆጠሩ እና አገለግሎት መመደቡን
ከምዕራፍ 27-29 ጠቢቡ ሰሎሞን ቤተ-መቅደስ እንደሰራ እና ዳዊት ለሰሎሞን አደራ እንደሰጠው ይተረካል፡፡

4.2.7መጽሐፍ ዜና መዋዕል ካዕል እና ጸሎተ ምናሴ
በቀኖና መጽሐፍት አቆጣጠረ መሰረት መጽሐፍ ዜና መዋዕል ካልይ እና ጸሎት ምናሴ እንደ አንድ መጽሐፍ ይቆጠራሉ፡፡በ2ኛ ዜና 33፣18 ላይ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ የጸለየው ጸሎት ተመዝግቦ ሲለሚገኝ መጸሐፉ (ጸሎተ ምናሴ) ከዜና መዋዕል ካልዕ ጋር አብሮ ኢንዲቆጠር ተወስኗል፡፡

ምናሴ፡- ማለት ማሰረሻ ማለት ሲሆን በ12 ዓመቱ የይሁዳን ክፍል ለማሰተዳደር የነገሠ ሰው ነው፡፡ ምናሴ በደግነቱ ከዳዊት ቀጥሎ የሚነሳው የንጉሱ ሕዝቅያስ ልጅ ነው፡፡ (1ነገ 20፣1) ምናሴ ግን አባቱ በሄደበት መንግድ መጓዘን ትቶ በጣኦት አምልኮት እና በተለያዩ በደሎች እግዚአብሔር አሳዘን፡፡ ልዑል እግዚአብሔርም በነብዩ በኢሳይያስ አድሮ በ10ሩ ነገድ ላይ ያመጣሁትን መከራ አመጣለው በማለት ተናግሮት ነበር፡፡ (2ኛ ነገ 21፣11) የነብዩ ተግሳጽ ከመሰማት ይልቅ በመጋዝ አሰተርትሮ እንዲገደል አድርጎታል፡፡ ከዚህ በኃላ የአሶር ንጉስ በብረት ቀፎ አድርጎ ወደ ባቢሎን ወስዶታል፡፡ በባቢሎን ሳለ በደሉ በማሰታወስ ንሰሐ ቢገባ እግዚአብሔር ንሰሐውን ተቀብሎት ምሕረት አድርጎለታል፡፡ (2ኛ ዜና 33፣14-26)

ጸሎት ምናሴ ተብሎ የሚጠራው መጽሐፍ አንድ ምዕራፍ እና 13 ቁጥሮች የያዘ ነው፡፡ በምናሴ ጽሎት ውስጥ የእግዚእብሔር ፈጣሪነት፣ ኃያልነት፣ ፈራጅነት፣ ይቅር ባይነት እንዲሁ ንሰሐ የተሰጠው ለኃጢአተኞች መሆኑን የሚገለፅ የምስጋና እና የጸሎት መጽሐፍ ነው፡፡

4.2.8 መጽሐፈ ዕዝራ ነህምያ
4.2.8.1 መጽሐፈ ዕዝራ
እንደ ሊቃወንተ ቤተ-ክርስቲያን አስተምህሮ በቅዱስት መጽሐፍት አቆጣጠር መጽሐፈ ዕዝራና መጽሐፈ ነህምያ እንደ አንድ ይቆጠራሉ፡፡ ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቀሱ ነጥቦች፡-

ሀ. ሁለቱ መጽሐፍት በይዘታቸው ተመሳሳይ በመሆናቸው፣ በመጽሐፈ ዕዝራ ከመጀመሪያዎቹ ከስደት ተመላሾች መካከል የነህምያ ስም መጠቀሱ እና በመጽሐፈ ነህምያ የካህኑ የዕዝራ ስም መጠቀሱ፡፡

ለ. ሁለቱም መጽሐፍት የሚተርኩት እስራኤል ከባቢሎን ምርኮ በኃላ ስለነበረ ሰለይሁዳ መንግስ ነው፡፡ መጽሐፋ የተጻፈው በ455 ዓ.ዓ ገዳማ ሲሆን በፋርስ ንጉስ በቄሮስ ፍቃድ አይሁዳ ከምርኮ ተመለስው ቤተ መቅድስ ስለመስራታቸው ይተርካል፡፡

የመጽሐፋ አከፋፈል

መጽሐፈ ዕዝራ 10 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን እንደሚከተለው ይከፈላል፡-

ከምዕራፍ 1-6 በፍርስ ንግሱ በቄሮስ እስራኤላዊያን ወደ ሀገራቸው እንደመለሱ የተነገረው አዋጅ
ከምዕራፍ 7-10 የተቀሩት እስራኤል ነገዶች በዕዝራ መሪነት ወደ ኢየሩሳሌም መመለሰቸው፡፡
በዕዝራ ልመና እና ለቅሶ ከስደት የተመለሱ ወገኖቹ ከአረማዊያን ሚስቶች እንደሚለዩ ቃል መግባታቸው ተዘርዝሯል፡፡

4.2.8.2 መጽሐፈ ነህምያ
ነህምያ ማለት እግዚአብሔር አድነኝ/አዳኝ/ ማለት ነው፡፡ ከምርኮ በኃል ከሚጠቀሱ ነብያት መካከል ነው፡፡ ነህምያ የፋርስ ንጉስ ለነበረው አርጤክስ በቤተ-መንግስት ጠጅ አሳላፊ የነበረ አይሁዳዊ ነው፡፡ ነህ 1፣1-6 መጽሐፉን የጻፈው ራሱ ነህምያ ነው፡፡ ነህ 1፣1 በሃሳ ሁለት/52/ ቀናት ውስጥ በንጉሱ ፍቃድ በእርሱ እምነት ጽናት የእየሩሳሌም ቅጥር ተገነብቷል፡፡ መጽሐፈ ነህምያ ይዘቱን ስንመለከት ስለ እየሩሳሌም ቅጽር መገንባት ይተርካል፡፡

የመጽሐፉ አከፋፈል፡-

መጽሐፈ ነህምያ በውስጡ 13 ምዕራፎችን የያዘ ሲሆን ለአጠናን ይመች ዘንድ እንደ ሚከተለው ይከፈላል፡-

ከምዕራፍ 1-2 -የእየሩሳሌም ቅጽሮች መፍረስና እንደገና መታነጽ
ከምዕራፍ 3-6 - ነህምያ በተቃውሞ ውስጥ አልፎ ቅጽረ እየሩሳሌምን መስራቱ
ከምዕራፍ 7-13 - እስራኤላዊያን በአምልኮተ እግዚብሔር መጽናታችን ይተርካል፡፡

4.2.9 መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤልና መጽሐፈ ዕዝራ ካልዕ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ቀኖና መጽሐፍት አቆጣጠር መስረት መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤልና መጽሐፈ ዕዝራ ካልዕ እንደ አንድ ይቆጠራሉ፡፡

4.2.9.1 መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል
ሱቱኤል (ስላትያል) የጻፈውን የካህኑ ዕዝራ ድርብ ስም ነው፡፡ ሱቱኤል ማለት በግእዝ ዘስየት /ናጠጣ/ ማለት ነው፡፡ ይዘቱ፡- ካህኑ ዕዝራ በተማረከበት ሀገር ስላያቸው ራዕይ፣ ለጠየቀው ጥያቄ ያገኘው ምላሽ፣ 40 ቀን ጾም ቅዱሳት መጽሐፍትን እንደጻፈ እና በጸሎት ጸጋና በረከትን ከእግዚአብሔር እንዳገኘ ይተርካል፡፡

አከፋፈል፡- መጽሐፍ ዕዝራ ሴቱኤል 13 ምዕራፎች ሲኖሩት በ3 ዓበይ ክፍሎች ይከፈላል፡-

ከምዕራፍ 1-3 ዕዝራ ከእግዚአብሔር እና ከመላዕከ እግዚአብሔር ከቅዱስ ዑራኤል ጋር መነጋገሩ
ከምዕራፍ 4-7 ስለ አዕማደ ምስጢራት፣ ጻድቃን እና ስለ ኃጥአን ያየው ራዕይ
ከምዕራፍ 8-13 ዕዝራ መጾሙና ስለተገለጸለት ምስጢር ይገልጻል፡፡

4.2.9.2 መጽሐፈ ዕዝራ ካልዕ
ይዘቱ፡- ይህ መጽሐፍ በመጽሐፍ ዕዝራ ቀዳማዊ ከምዕራፍ 7-9 እና በዜና መዋዕል ካልዕ ከምዕራፍ 35 እስከ 36 የተገለጸውን ታሪኮች አብራርቶ ይተነትናል፡፡

አከፋፈል፡-መጽሐፉ 9 ምዕራፎች ሲኖሩት በካህኑና በጻፊው ዕዝራ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡

ከምዕራፍ 1-2 ከምርኮ መልስ ቤተ-መቅድስ ማነጻቸውን
ከምዕራፍ 5-7 በዳርዮስ ፈቃድ ቤተ-መቅድስ መስራቱ
ከምዕራፍ 8-9 የፋርስ ንጉስ እየሩሳሌምን መውረሩ ያትታል፡፡

4.2.10 መጽሐፈ ጦቢት
ጦቢት/ጦቢና/ ማለት ስናይ፣ ኄር ማለት ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ስለ ጦቢት እና ጦቢያ በንጉስ ስልምናሶር ዘመን የደረሰባቸው መከራና እግዚብሔር በመልአኩ ሩፋኤል አማካኝነት አንዴት እንደረዳቸው የሚያሳይ መጽሐፍ ነው፡፡

ይዘቱ፡- መጽሐፈ ጦቢት በንጉስ ስልምናሶር ጊዜ በስደት የነበሩት አይሁድ ሲሞቱ ጦቢት የተባለው ስው ይቀብራቸው እንደነበር፣ ይመክራቸውም እንደነበር ያትታል፡፡ ዓይኑ ጠፍቶበት በእግዚብሔር መልአክ አማካኝነት እንዴት እንደዳነ ይገልጻል፡፡

የመጽሐፉ አከፋፈል፡- መጽሐፈ ጦቢት 14 ምዕራፎች ሲኖሩት በ3 ይክፈላል፡-

ከምዕራፍ 1-3 ጦቢት በበጎ ስራው ያገኘው መከራና የሣራ ጸሎት
ከምዕራፍ 4-12 ጦቢት በመከራው ጊዜ ልጁ ጦቢያን ወደ ወገኖች ቢልከው ቅዱስ ሩፋኤል በስው ተመስሎ እንዴት እንዳዳነው
ከምዕራፍ 13-14 የጦቢት ምስጋና እና ምክር እናገኛለን፡፡

4.2.11 መጽሐፈ ዮዲት
ይህ መጽሐፍ ከታሪክ መጽሐፍት መካከል አንዱ ሲሆን ንጉስ ናቡከደነጾር እስራኤላውያንን ለመወጋት የላከው ሆሎፎርኒስ የተባለ የጦር መሪ ዮዲት በተባለች እስራኤላዊት ሴት እጅ እንዴት ተላለፎ እንደተሰጠና እንደተገደለ የሚያትት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፋ አስራ ስድስት(16) ምዕራፎች ያሉት መጽሐፍ ነው፡፡

4.2.12 መጽሐፈ አስቴር
የቀድሞ ሰሟ ሀዴሳ ይባል የነበረው አስቴር የንጉስ አርጤከስ ሚስት ሆና በወገኖቿል ላይ የተቃጣውን የሞት አደጋ በእግዚብሔር ፍቃድ ማስቀረቷን የሚተርክ መጽሐፈ ነው፡፡ አስቴር ማለት ‹‹ኮከብ›› ማለት ነው፡፡

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የእግዚብሔር ስም በየትኛው ቦታ ያለተጠቀሰ ሲሆን ለዚህ ምክንያቱ በምርኮ የሚኖሩት እስራኤላዊያን በሚኖሩበት ባዕድ ሀገር የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ታላቅ አደጋ ስለሚያስከተል ነበር፡፡

የመጽሐፋ አከፋፈል

የዚህ መጽሐፍ ጻፊ መርዶክዮስ ሲሆን መጽሐፋ 10 ምዕራፎችን በውስጡ ይዟል፡፡

ከምዕራፍ 1-2የፋርሱ ንጉስ አርጤክስ ሚሰቱን አስጢንን ፈቶ አይሁዳዊቱን አስቴርን ያገባ መሆኑን፣ እናትና አባት የሌላት አስቴር አጎቷመርዶክዮስ እንደ አባት እንዳሳደጋት፣ መርዶክዮስ በንጉሱ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሴራ ማጋለጡ ይዘርዝሯል፡፡
ከምዕራፍ 3-5ሐማ የተባለ ሰው ወደ ስለጣን መምጣቱ፣ መርዶክዮስ ለሐማ አልስግድም በማለቱ ሐማ የአይሁድ ዘርን ሁሉ በአንድ ቀንለማጥፋት ከንጉስ ፍቃድ መቀበሉ ተገልጿል፡፡
ከምዕራፍ 6-10 መርዶክዮስ የአስቴርን እርዳት መጠየቁ፣ አይሁድ በጾምና ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት መቆማቸው፣ አስቴር ንጉሱና ሐማንግብዣ መጥረቷ፣ የመርዶክዮስ መሾምና የሐማ መሰቀል እንዲሁም አይሁድ ፋሪም በዓል ማክበራቸው ይተርካል፡፡

4.2.13 መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ
መቃቢስ /መቃባ/ ማለት ጸረ-ጠላት፣ ቀስት፣ ጀግኖች ማለት ነው፡፡ መጽሐፈ መቃብያን የተለያዩ ታሪካዊና መንፈሳዊ ይዘቶች ያሏቸው ስምንት መጽሐፎች አሏቸው፡፡ ነገር ግን ማን እንደጻፋቸው በውል አይታወቁም፡፡ ከእነዚህ መጽሐፍቶች ውስጥ ሦስቱ በግዕዝና በአማርኛ ተተርጉመው ይገኛሉ፡፡ በፍትሐ ነገስት ውስጥ ስማቸው የተጠቀሱ ግን ወደ አራት የሚሆኑ ስዎች አሉ እነሱም፡-

1. መቃብያን ዘመቃቢስ አልዓዛር
2. መቃብያን ዘመቃቢስ ሞዓብ
3. መቃብያን ዘመቃቢስ ዘብንያም
4. መጽሐፈ መቃብያን ራብዕ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ዜና አይሁድ /ዜና ሥርወ/ ናቸው፡፡

መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ፡-ይህ መጽሐፍ 36 ምዕራፎች አሉት፡፡ በዚህ መጽሐፍ ዉስጥ የብንያም ወንድሞች የአይሁድን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመጠበቅ ሲባል ከሌሎቹ ነገስታት ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ እንመለከታለን ፡፡

ይዘቱ ፡- አርበኛ የሆኑ 3 ልጆች ለጣኦት አንሰግድም በማለታቸዉ ንጉስ እንዳሰቃያቸዉ፣ ከብሉይ ኪዳን ታሪኮችን ምሳሌዎችን እየጠቀሰ ስለ በረከትና መርገም ይገልፃል ፡፡

መጽሐፉ አከፋፈሉ፡- 36 ምዕራፎች ያሉትን መጽሐፈ መቃቢያን ቀዳማዊ በ 3 ክፍሎች ከፍሎ መመልከት ይቻላል ፡፡

ከምዕራፍ 1-5 ስለ ጺሩጻይዳ ግፍ እና የመቃቢስ ሰማዕትነት
ከምዕራፍ 6-11 ስለ ዳግም ምጽአት
ከምዕራፍ 12-36 በብሉይ ኪዳን ስለ ነበሩ አበዉና እስራኤላዉያን ይናገራል ፡፡

4.2.14 መጽሐፈ መቃብያን ካልዕና ሣልስ
4.2.14.1 መጽሐፈ መቃብያን ካልዕ
ይህ መጽሐፍ 21 ምዕራፎች አሉት ፡፡ በግሪክ ቋንቋ እንደተጻፈ ይታመናል፡፡

ይዘቱ፡- እስራኤላዊያን በድለዉ ሞአባዊ መቃቢስ እንዲነሳባቸዉ እስራኤልን በሰይፍ ገድሎ ሲታበይ እግዚያብሔር በመቃቢስ ስራ ተቆጥቶ ነብይ ልኮ በንስሐ እንዲመለስ ሲነግረዉ በእግዚያብሔር ፊት ራሱን አዋርዶ ምህረት መግኘቱን ፡፡

መጽሐፉ አከፋፈሉ፡- በ 3 ዓበይት ክፍሎች ይከፈላል ፡፡

ከምዕራፍ 1-4 የመቃቢስ ዘሞዓብ የተባለዉን ንጉስ ያደረሰዉን ጥፋት በንስሐ ተመልሶ የሰራዉን በጎ ስራና ዕረፍቱ
ከምዕራፍ 5-12 የመቃቢስ ዘሞዓብ ልጆች በእግዚያብሔር ስላመኑ ጺሩጻይዳ የተባለ የከላዉዲያን ንጉስ ያደረሰባቸዉ መከራ
ከምዕራፍ 13-21 የመቃቢስ ዘሞዓብ ልጆች አብነት አድርጎ ትንሳኤ ሙታን የተሰጠ መልስ የያዘ መጽሐፍ ነዉ ፡፡

4.2.14.2 መጽሐፈ መቃቢስ ሣልስ
አስር/10/ ምዕራፎች ሲኖሩት በዋነኝነት መጽሐፍም የብሉይ ኪዳን ታሪኮች እየጠቀሰ የጽድቅና የኩነኔን፣ የትንሳኤ ሙታንን፣ ዲያቢሎስ የሰዉ ልጆችን የሚያሰናክልባቸዉ መንገዶች የያዘ ነዉ ፡፡ በግሪክ ቋንቋ እንደተጻፈ ይታመናል፡፡ ይህ መጽሐፍ ከመቃቢያን ሁለት ጋር እንደ አንድ ይቆጠራላ ፡፡

ይዘት፡- ከአዳም ጀምሮ የነበሩትን አበዉ ለአብነት እየጠቀሰ ሰዉን በዚህ ምድር መልካም ከሰራ በወዲያዉም ዓለም መልካም እንደሚገጥመን መጥፎም ነገር ስንሰራ እንዲሁ እንደሚገጥሙንና ስለንስሐና ስለመንግስተ ሰማያት የገልፃል ፡፡

አከፋፈል:- በ3 ዓበይት ምዕራፎች ይከፈላል ፡-

ከምዕራፍ 1-3 ስለሰይጣን ስለ አዳምና ሔዋን ዉድቀት
ከምዕራፍ 4-6 ስለ ሰይጣን ዉድቀት ስለ ጌታችን ማዳንና ጻድቃንና ኃጥኣን
ከምዕራፍ 7-10 በእግዚያብሔር ስለ ማመንና ስለ ኢዮብ ይናገራል ፡፡

4.2.15. መጽሐፍ ዮሴፍ ወልደ ኮሪዮን / መቃቢያን ራብዕ /
ዮሴፍ ማለት ይጨምር ይዲገም ማለት ነዉ ፡፡ የኮሪዮን ልጅ ዮሴፍ እንደጻፈዉ ይታመናል ፡፡ ይህ መጽሐፍ ዜና አይሁድ/ መጽሐፍ ስርዉ / በመባል ይታወቃል ፡፡ በጣም ረጅም መጽሐፍ ነዉ ፡፡ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ ያለዉን ታሪክ ይተርካል ፡፡

ይዘት ፡- ከአዳም ጀምሮ 70 ዓ.ም በጥጦስ መሪነት እየሩሳሌም እስከ ጠፋችበት ድረስ ያለዉን አይሁድ ታሪክ ይተርካል ፡፡

የመጽሐፉ አከፋፈል፡- መጽሐፉ 8 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን በ 8 አበይት ክፍሎች ይከፈላል ፡፡

1. ስለ አዳም
2. ስለ ንጉስ እንጥያኮስ ፡ መቄዶናዊ ፡ ስለዮናናዉያን ንጉስ
3. ስለ እስክንድርያ ንግስት የህርቃልና የአስትሮ በሎስ ልጅ
4. የህርቃል ከፋርስ መግባቱና መገደሉ
5. ስለ አስቴር ንግስና ስለ አርኬለአስ ታሪክ
6. የሄሮድስ ልጅ አደርኬላኦስ ታሪክ
7. ስለ ስምኦን ያረብሃዊ
8. ስለ ቤተ መቅደስ የሮማዉያን ከአይሁድ ጋር መጣላታቸዉ ይተርካል ፡፡

ይህ መጽሐፍ ከትልቅነቱ የተነሳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ ዉስጥ አይገኝም ፡

4.2.16 መጽሐፈ ኩፋሌ ፡-
ኩፋሌ ማለት የተከፈለ /መከፈል/ ማለት ነዉ፡፡ መከፈሉም ለኦሪት ነዉ፡፡ በኦሪት መጽሐፍ ዉስጥ የምናገኘዉን ታሪኮች አስፋፍቶ ይተርካል፡፡ ከሥነ-ፍጥረት ጀምሮ እስከ እስራኤላዉያን ከግብፅ መዉጣት ይተርካል ፡፡ ይህንን መጽሐፍ የጻፈዉ ነብዪ ሙሴ እንደሆነ ይታመናል ፡፡ ኩፋሌ 1 ፡ 1-4 ቦታደዉም ደብረ ሲና እንደሆነ ይነገራል ፡፡

ይዘቱ ፡- ስለ ስነ-ፍጥረት፡ አርስተ አበዉ የነበሩትን በሱባኤ ይገልፃል ፡፡ እንዲሁም እስራኤላዉያን ከግብፅ ስለመዉጣታቸዉ ይነገራል፡፡

መጽሐፉ አከፋፈል ፡- መጽሐፉ 34 ምዕራፎች ሲኖሩት በ 4 ዓበይት ክፍሎች ይከፈላል ፡፡

1. ምዕራፍ 1 የሙሴ ከእግዚያብሔር ጋር መገናኘቱን /መነጋገሩን/
2. ከምዕራፍ 2-7 ከአዳም ጀምሮ እስከ አብርሃም ድረስ ያለዉን ታሪክ
3. ከምዕራፍ 8-32 የያዕቆብና የልጆቹ ታሪክ
4. ከምዕራፍ 33-34 የሙሴ አነሳስና በግብጻዉያን ላይ ድል ይገልጻል ፡፡

4.2.17 መጽሐፈ ሄኖክ፡-
ይህ መጽሐፍ የአዳም ሰባተኛ ትዉልድ በሆነዉ በሄኖክ የተጻፈ መጽሐፍ ነዉ፡፡ በመጀመሪያ የተጻፈዉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነዉ፡፡ ሄኖክ ማለት አዲስ /ተሐደተሶ/ ማለት ነዉ፡፡ ይህ መጽሐፍ በዉስጡ 42 ምዕራፎች የያዘ ሲሆን ስለክርስቶስ ስለ መልአክት ስለ ፀሐይና ጨረቃ ዑደት ስለ እፅዋት ስለ ጻድቃን እና ኃጥአን በኖህ ዘመን ስለተፈጸመዉ ኃጢያትና ቅጣት ያወሳል፡፡

የመጽሐፈ ሄኖክ አከፋፈል :- 42 ምዕራፎች ያሉት መጽሐፈ ሄኖክ በ 4 አበይት ክፍሎች ይከፈላል ፡፡

ከምዕራፍ 1-20 ስለ ቅዱሳን መልዕክትና ስለ ጌታችን
ከምእራፍ 21-26 ስለ ፀሐይና ጨረቃ ስለ ከዋክብት ወቅቶች ይናገራል ፡፡
ከምዕራፍ 27-35 ስለ እስራኤል የተነገረ ተንቢት
ከምዕራፍ 36-42 ፃድቃንና ኃጥአን ዋጋና ቦታ ይገልጻል ፡፡

4.3 የመዝሙርና የጥበብመጽሐፍት ፡
የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት አከፋፈል መስረት በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የመዝሙር እና የጥብበ መጽሐፍት ይባላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳት መጽሐፍት ቀኖና እና አቆጣጠር መሰረት የመዝሙርና የጥበብ መጽሐፍት የሚባሉት በአጠቃላይ 8 /ስምንት/ መጽሐፎች ሲሆኑ እነርሱም እንደሚከተለዉ ይዘረዘራሉ ፡

1. መጽሐፈ ኢዮብ
2. መዝሙረ ዳዊት
3. መጽሐፈ ምሳሌ
4. መጽሐፈ ተግሳፅ
5. መጽሐፈ መክብብ
6. መኃልየ መኃልየ ዘሰሎሞን
7. መጽሐፈ ጥበብ
8. መጽሐፈ ሲራክ ናቸዉ ፡፡

እነዚህ የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት የራሳቸዉ የሆነ አከፋፈልና የራሳቸዉ የሆነ ይዘት አላቸዉ ፡፡ ወደ አከፋፈላቸዉ ከመሄዳችን በፊት የመዝሙርና የጥበብ መጽሐፍት ምን ማለት እንደሆነ /ትርጓሜዉን/ እንመልከት ፡፡

መዝሙር ፡- ማለት ምስጋና ማለት ነዉ ፡፡ ጥበብ፡- ማለት ማስተዋል ፤ መንፈሳዊ እዉቀት ፤ ማንኛዉንም ነገር ለማግኘት የመመርመር ችሎታ ማለት ነዉ ፡፡ ስለዚህ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የሚገኙት መጽሐፍት እግዚአብሔር መለመኛ፣ መማፀኛና ማመስገኛጸሎቶችና የእግዚአብሔር ድንቅ ስራ ምስጋና ጥበቡን አካተው ይዘዋል፡፡(መ/ር “ቸሬ አበበ እና ዲ/ን ቴዎድሮስ በየነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ገጽ 49 2001 ዓ.ም)

ይህንን መጽሐፍ ተከፍሎ ከመተርጎሙ በፊት በዕብራይስጡ የቅኔ መጽሐፍ በመባል ይታወቅ ነበር፡፡በስምና ወርቅ በምሳሌም የተጻፉ በመሆናቸዉ አቀራረባቸዉ ቅኔያዊ በመሆኑ ይህን ስያሜ አግኝቷል ፡፡

1. መጽሐፈ ኢዮብ
ኢዮብ፡- ማለት አበባና ጨረቃ ማለት ነዉ ፡፡ በቩልጋታና ነሰብዓ ሊቃናት ዮብ/ጆብ/ ይባላል ፡፡ ይህ መጽሐፍ 42 ምዕራፎች አሉት፡፡ መጽሐፉን በእርግጠኝነት ማን እንደፃፈዉ አይታወቅም ፡፡ ሊቃዉንቱ ኤልሁ በሚለዉ ይስማማሉ /ኢዮብ 9፡23/፡፡ የተፃፈበት ዘመን ከ 1500 ዓ.ዓ. በፊት /ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ነዉ / ተብሎ ይገመታል፡፡ የተጻፈበት ቋንቋ ሱርስት ነዉ፡፡ መጽሐፉ በስድ ንባብ /ጽሑፍ/ መልክ ከተጻፉት የመጀመሪያዉና የመጨረሻዉ ክፍሎች በስተቀር አብዛኛዎቹ በግጥም መልክ ነዉ፡፡

አጠቃላይ ይዘቱ፡- እግዚአብሔርን በሚወዱና በሚታዘዙ ሰዎች ላይ ሊደርስ እንደሚችልና በትዕግስት ካሳለፉት መከራዉ እንደሚወገድና በረከትንም ከእግዚአብሔር በእጥፍ እንደሚያገኙ የሚያስተምር መጽሐፍ ነዉ ፡፡ የዚህ ታሪክ ባለቤትየሆነዉ ጻድቁ ኢዮብ ስለደረሰበት መከራ እና መከራዉን በመታገሱ ስላገኘዉ በረከት በሰፊዉ የሚገልጽ መጽሐፍ ነዉ ፡፡

የመጽሐፉ አከፋፈል፡-

መጽሐፉን በ3 ዋና ዋና ክፍሎች ከፍሎ ማጥናት ይቻላል፡፡

1ኛ. ከምዕራፍ 1 እና 2
- በእነዚህ ምዕራፎች ዉስጥ ኢዮብ 7 ወንዶች እና 3 ሴቶች ልጆቹን የነበረዉን ሃብት ማጣቱ፣ በጎቹን ግመሎቹን በሬዎቹንና አህዮቹን በሞት በመነጠቁ የደረሰበትን ፈተና እናገኛለን /በሰይጣን መፈተኑን/
2ኛ. ከምዕራፍ 3 እስከ 37
- ከደረሰበት መከራ የተነሳ ምነው ባልተወለድኩ ብሎ ሕይወቱን ማማረሩን
- አልፋዝና በልዳስ ሰፈር በኢዮብ ላይ የደረሰው መከራና ችግር ከኃጢያት ነው በማለት ያቀረቡት ወቀሳ /ያደረጉት ምልልስ/
3ኛ ከምዕራፍ 38 እስከ 42
- የእግዚአብሔር ትምህርት በዐውሎ ነፋስ ሆኖ ለኢዮብ ስለ ሰዎች ንግግር ከንቱነት የሰጠው መልስ
- እግዚአብሔር የሚያደርገውን ያውቃል ብሎ ከብስጭቱ ስለማረፉ
- ከእግዚአብሔር ቁጣ ይድኑ ዘንድ ስለወዳጆቹ መጸለዩ
- ኢዮብ የጠፋበትን ሃብት በእጥፍ ማግኘቱ ልጆቹን እስከ አራት ትውልድ ድረስ እንዳየና እድሜ ጠግቦ እንደሞተ እናገኛለን፡፡

2. መዝሙረ ዳዊት
መዝሙረ ዳዊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ከፍተኛ አገልግሎት /አስተዋጽኦ/ አለው፡፡ መዝሙረ ዳዊት መዘምራን በዜማ ስልት የሚገለግሉበት መነኮሳትና ካህናት በሌሊት በቤተ-ክርስትያን እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ምስባክ ነው፡፡ ምእመናን በያሉበት ሁነው እየጸለዩ መላእክት ብርሃንን የሚያቀርቡበት መላእክተ ጽልመትን የሚያርቁበት ሕሙማን የሚፈወሱበት እጅግ ጠቃሚ የሆነ መጽሐፍ ነው፡:

ዳዊት፡- ማለት ልበ አምላክ፣ ኅሩይ ማለት ነው፡፡ መዝሙረ ዳዊት በውስጡ 150 መዝሙር፣ጸሎት፣ ትምህርትና ቅኔ ይገኝበታል፡፡ በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ያሉት መዝሙሮች በአብዛኛው የእርሱ በመሆናቸው የዳዊት መዝሙር ሲባሉ መዝ. 146 እና 148 ግን የሐጌና የዘካሪያስ ናቸው፡፡

- በቶራ ልጆች ስም የሚጠሩ 11 መዝሙሮች አሉ፡፡
- የአሳፍ መዝሙሮች የሚባሉት 12 መዝሙሮች መዝ 50.73.79.90.96 ወዘተ
- በኢታን የምትደረስ መዝ 93.

መዝሙረ ዳዊት አሁን ባለበት ደረጃ ያዘጋጀው ካህኑ እዝራ ነው፡፡ መዝሙሮቹ በተለያየ እንጂ በአንድ ዘመን ብቻ የተዘጋጁ አይደሉም፡፡ መዝ. 74.24 መዝ.3.30 እና መዝ70 የተዘጋጁት ከእስራኤላውያን ምርኮ በኋላ ነው፡፡

አጠቃላይ ይዘቱን ስንመለከት የሰውን የሕይወት ዘመን የሚያሳይ ነው፡፡ በሕይወቱ የሚያጋጥሙትን ኃዘንና ደስታን፤ መልካምና ክፉ፤ መውደቅና መነሳትን፤ ችግርና ምቾትን፤ ከእግዚአብሔር መራቅና ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ዳዊት ስለራሱ የተናገረው፣ ስለክርስቶስ፤ ጻድቃንና ኃጥአን በመዝሙር መልክ ይገልጻል፡፡

1ኛ. አከፋፈሉ

1ኛ. ከመዝ. 1 እስከ መዝ 40
2ኛ. ከመዝ. 41 እስከ መዝ.71
3ኛ. ከመዝ.72 እስከ መዝ 88
4ኛ. ከመዝ 89 እስከ መዝ. 105
5ኛ. ከመዝ. 106 እስከ መዝ. 150

2ኛ. አከፋፈሉ በአስር አርዕስት ሲከፈል

1ኛ. መዝ. 1፤1 ለሁሉም የሚሆን ተግሳፅና ምክር
2ኛ. መዝ. 2፤1 ስለክርስቶስ
3ኛ. መዝ. 3፤1 ስለራሱ (ቅዱስ ዳዊት)
4ኛ. መዝ. 4፤1 ስለመናናዊያን
5ኛ. መዝ. 5፤1 ስለትሩፋት
6ኛ. መዝ. 13፤1 ስለ ሕዝቅያስ
7ኛ. መዝ. 34፤1 ስለ ኤርሚያስ
8ኛ. መዝ 43፤1 ስለ መቃቢያን
9ኛ. መዝ. 71፤1 ስለ ልጁ ሰሎሞን፡፡ የቀሩት 140ዎቹ በእነዚህ ስር ይካተታሉ፡፡

ከላይ በመጀመሪያው ላይ ያለው አከፋፈል ላይ እያንዳንዱ ክፍል ፍጻሜው የሚታወቀው ከዘላለም እስከ ዘለዓለም እግዚአብሔር ይባረክ አሜን የሚሉ ቃላት ስለተጻፈባቸው ነው፡፡