Advertisement Image

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች

ምዕራፍ አምስት : የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ዝርዝር ጥናት

5.1 የቃሉ ትርጉም
ሐዲስ ኪዳን፡- ማለት አዲስ ውል፣ አዲስ ስምምነት፣ አዲስ የመተማመኛ መሐላ ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኪዳን የሚለው ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠ ሰዎችም በእምነት የሚቀበሉት ውል ማለት ነው፡፡ ሐዲስ ኪዳን ስንል ደግሞ ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠ የድኀነት ውል ማለት ሲሆን ይኸውም በወልደ እግዚአብሔር በወልደ ማርያም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲያገኝ የሚያረጋግጥ ኪዳን ነው፡፡ (ማር 16፣16 ዮሐ 3፣36 ዮሐ 6፣47 …)

የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት የሚባሉት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት(ወንጌል) እና ቅዱሳን ሐዋርያት የጻፏቸው መጽሐፍቶች ናቸው፡፡ ሐዲስ ኪዳን ሲባል ፊተኛ ወይም የቀደመ ኪዳን እንደነበረ ያስገነዝባል፡፡ ይህ ፊተኛ ኪዳን ብሉይ ኪዳን ተብሎ ይጠራል፡፡ የሐዲስ ኪዳን መመሥረት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት በትንቢት የተነገር ነበር፡፡“እንሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል እግዚአብሔር“ ትን ኤር 31፣31-34 (ዕብ 8፣6-13)

የሐዲስ ኪዳን የተመሠረተችው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡ “…ይህ ጽዋ ስለ እናንት የሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፡፡ “ሉቃ 22፣19-20 1ኛ ቆሮ 11፣ 23-26

እግዚአብሔር ዓለምን የሚያስተዳድረው በቃል ኪዳኑ ስርዓት ነው፡፡ ሰዎች ቃልኪዳኑን ተቀብለው ቢታዘዙለት የቃል ኪዳኑን በረከት ይቀበላሉ፡፡ ይህንን የቃልኪዳኑን በረከት ለማግኘት ከሰዎች የሚጠበቀው ነገር መታዘዝ ነው፡፡ በቃል ኪዳኑ ውስጥ ሰጪ፣ ተቀባይ፣ የአቀባበል ምልክት፣ ተስፋ እና የተስፋ ምልክት አለ፡፡

_ የሐዲስ ኪዳን ሲጪ - ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
- የሐዲስ ኪዳን ተቀባይ - በክርስቶስ የባሕሪ አምላክነት የሚያምኑ ክርስቲያኖች
- የሐዲስ ኪዳን ማኀተብ - ጥምቀት
- የሐዲስ ኪዳን ተስፋ - የዘላለም ህይወት / መንግስተ ሰማያት/
- የተስፋው ምልክት - ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡

የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት አከፋፈል በምዕራፍ አራት የተመለከትን ሲሆን በዚህ ምዕራፍ ዝርዝር የሐዲስ ኪዳን ጥናትን እንመለከታለን፡፡

5.2የወንጌል መጽሐፍት
ወንጌል የሚለው ቃል ኢቫንጌልዮን ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም በግእዝ ብስራት በአማርኛ ምሥራች ማለት ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምርህት ወይም ዜና ሠናይ የያዘ ስም ወንጌል ተብሎ ይጠራል፡፡ ትምህርቱን ወንጌል ብሎ ለመጀመርያ ጊዜ የጠራው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ማር 1፣15 ማቴ 24፣14 ማቴ 26፣13 ማር 16፣15 ‹‹ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግስት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፡፡›› ማቴ 24፣1

ከዚህ የክርስቶስ ቃል በመነሳት ሐዋርያት ስለክርስቶስ የጻፉት እና ያስተማሩት ሁሉ ወንጌል ይባላል፡፡ (ሮሜ 1፣16 ማር 4፣23 ማር9፣35 ወንጌል እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ ማርያም እንደተገለጠ፣ ስለሰው ልጆች ኃጢአት ሲል መከራ መቀበሉን፣ መራቡን፣መጠማቱን፣ መገረፉን፣ በማዕከለ ምድር በቀራንዮ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ሞት ድል አድርጎ መነሳቱን፣ በይባቤ መላዕክት ወደ ሰማይ ማረጉን እንዲሁም ዳግም ዓለምን ለማሳለፍ መምጣቱን የምታስተምር ብርሃናዊት ህግ ናት፡፡ የእግዚአብሔርን ሰው መሆን እና የሰው ልጆችን ድኅነት ስለምታበስር ወንጌል ምስራች ትባላለች፡፡ በወንጌል የተገለጸ ድኅነት በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘ ድኅነት በመሆኑ ያለን ወንጌል አንድ ወንጌል እንጂ የተለያየ ወንጌል አይደለም፡፡ ነገር ግን ወንጌላት ብለን በብዙ ቁጥር ስንጠራ በአራቱ ወንጌላዊያን የተጻፉት የወንጌል መጽሐፍት ማለታችን ነው፡፡ሉቃ 1፣1-4

በወንጌል ስለ ክርስቶስ የተጻፈው ሙሉ በሙሉ ክርስቶስ የሰራው የማዳን ስራ ሳይሆን ከሰራው ስራ ጥቂቱን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው አራቱ ወንጌላዊያን ከልደቱ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ያለውን አቅማቸው እስከ ፈቀደ ጻፉት፡፡ ‹‹ጌታ ኢየሱስ ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጽሐፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ነበር፡፡›› ዮሐ 21፣25 እንዳለ፡፡

አራቱ ወንጌላዊያን ሁለቱ ከሐዋርያት ወገን ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ከአርድዕት ወገን ናቸው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ሐዋርያት ብቻ ጽፈውት ያልሆነስለምን ነው ቢሉ ስለክብረ አርድዕት ነው፡፡ አርድዕት ለማስተማር በወጡ ጊዜ አይሁድ እነዚህማ የወጪ /ተሪታ/ ሰዎች ናቸው በማለት ትምህርታቸውን ከመቀበል ይከለከሉ ነበር፡፡ አርድዕት ብቻ ያልጻፉት ስለምን ነው ቢሉ ሰለክብረ ወንጌል ነው፡፡ አርድዕት ብቻ ጽፈውት ቢሆን ኖሮ ‹‹ ይህቺማ ተርታ ህግ ናት ደጊቱ ህግ ምሥጢር ተአምራትን በቤተ ኢያኤሮስ፣ ምሥጢር መንግስትን በደብረ ታቦር፣ ምሥጢር ምጽአትን በደብረ ዘይት፣ ምሥጢር ጸሎትን በጌቴሴማኒ በተመለከቱ አዕማደ ምድር /የምድር ምሶሶዎች/ በተባሉ በሐዋርያት ልብ ቀርታለች ብለው አይሁድ ወንጌልን ከመቀበል በተከለከሉ ነበርና ሁለት ከሐዋርያት ሁለት ከአርድዕት ወገን ሆነው ጽፈውታል፡፡

5.2.1 የወንጌል ጸሐፊዎች አራት የመሆናቸው ምስጢር
ሀ. በአራቱ እንስሳት ይመሰላል፡- የሥላሴ መንበር የሚሽከሙ አራቱ እንስሳት ማለት የአንበሳ፣ የላህም፣ የንስር እና የሰው ገጽ መልክ ባለቸው በአራቱ እንስሳት ይመሰላሉ፡፡

- ቅዱስ ማቴዎስ በሰው ይመሰላል፡-የዳዊት ልጅ ፣ የአብርሃም ልጅ እያለ የጌታን ምድራዊ ልደት በመጻፍ ሰለሚጀምር በሰው ይመሰላል፡፡
- ቅዱስ ማርቆስ በአንበሳ ይመሰላል፡- አንበሳ ኑሮው በምድር በዳ ነው፡፡ ከዚህ ሆኖ አንድ ጊዜ ድምፁን ሲያሰማ እንሰሳት ይገሰጻሉ፣ አራዊት ይደነግጣሉ፡፡ ቅዱስ ማርቆስ ከአምልኮተ እግዚአብሔር ተራቁታ ምድረ በዳ በሆነች በግብፅ ምድር ጣዕር ስብከቱን ሲያሰማ ምዕመናን ተገስጽዋል አጋንንት መናፈቃን ደንግጠዋል፡፡አንድም አንበሳ ለላህም ጌታው ነው፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በትምህርተ ወንጌል አምላኮተ ላህም ከግብፅ ምድር አጥፍቶዋል፡፡
- ቅዱስ ሉቃስ በላህም ይመሰላል፡- ከሌሎች በተለየ መልኩ የጌታን በከብቶች በረት መወለድ ፤እንስሳት እስትንፋሳቸውን መገበራቸው ይጽፋል፡፡
- ቅዱስ ዮሐንስ በንስር ይመሰላል፡- ንስር በእግሩ ይሽከረከራል በክንፉ ይበራል፡፡ በእግሩ እንደመሽከረከሩ እንደ ወንደሞቹ የጌታን ከሰማይ ሰማይት መውረዱን ከድንግል ማርያም መወለዱን ይጽፋል፡፡ በክንፍ እንደ መብረሩ ንጽሐ ሰጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቦና ተሰጥቶት የሥላሴን የአንድነት እና የሦስትነት የወልደ እግዚአብሔር በቅድምና መኖር ጽፏል፡፡

ለ. በተጨማሪ በአራቱ አፈላጋት፣ በአራቱ ክዋክብት፣በአራቱ ወቅታት ወዘተ…ይመሰላሉ፡፡

5.2.2 የአራቱ ወንጌላውያን ይዘት
አራቱ ወንጌላት ከይዘታቸው አንጻር ሲጠኑ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ይህ ማለት አንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩበት የታሪክ፣ የትምህርት እና የተአምራት አመዘጋገብ ስላላቸው ነው፡፡ እነሱም፡-

1. ሲኖፕቲክ ወንጌላት
2. አራተኛው ወንጌል

1 ሲኖፕቲክ ወንጌላት

ሲኖፕቲክ/synoptic/ ከግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአራቱ ወንጌላት መካከል ለሦስቱ ወንጌላት ማለት ለማቴዎስ፣ ለማርቆስ እና ለሉቃስ ወንጌል የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ሲኖፕቲክ ማለት በአንድ የሚታዩ /seen together/ ማለት ነው፡፡ ሦስቱ ወንጌላት በይዘታቸው ሰለሚመሳሰሉ እና አንዱ ከአንዱ ማስተያየት ስለሚቻል የተሰጣቸው ስያሜ ነው፡፡

2 አራተኛ ወንጌል

አራተኛው ወንጌል የተባለው የዮሐንስ ወንጌል ነው፡፡ በዚህ ወንጌል የተመዘገበ እንደ ሌሎቹ ወንጌላት የጌታን ታሪክ እና ትምህርት ቢሆንም በሦስቱ ወንጌላት ያልሰፈሩ የጌታችን ትምህርቶችን ይዞ ይገኛል፡፡

ሦስቱ ወንጌላት:- ሰለ ጌታ የምድር መዋዕለ ዘመን /የሰውነት ነገር/ አጉልተው ይጽፋሉ፡፡ /ማቴ 1፣1-17 ማር 8፣32 ሉቃ 3፣ 23-38/
አራተኛ ወንጌል፡- የጌታን ከሰማይ መውረድ /መለኮትን ነገር/ አጉልቶ ይጽፋል፡፡ /ዮሐ 1፣1-3 3፣13፣6፣41-51 8፣23/
በዚህ ምክንያት ሦስቱ ወንጌላት ወንጌላተ ዘበምድር /Earthly Gospels/ ሲባሉ አራተኛ ወንጌል ደግሞ ሰማያዊ ወንጌል /Heavenly Gospel/ ይባላል፡፡

1. የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል
የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው በሐዋርያው በቅዱስ ማቴዎስ ነው፡፡ በ325 ዓ.ም በኒቂያ ጉባኤ የተሰበሰቡ 318 የቤ/ክ ሊቃውንት ለመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ፣ቁጥርና ምዕራፍ ሲሰጡ ‹‹ብስራተ ማቴዎስ ሐዋርያ አሐዱ እም ዐሠርቱ ወክልኤቱ ሐዋርያት… ›› በማለት የወንጌሉ ጸሐፊ ቅዱስ ማቴዎስ እንደሆነ አሰቀምጠዋል፡፡ ከሐዋርያት አበው መካከል የሆነው ፓፒዮስ /60-130 ዓ.ም/ ‹‹ማቴዎስ የጌታን ነገር በዕብራይስጥ ቋንቋ ጻፈ፡፡›› በማለት የወንጌሉ ጸሐፊ ቅዱስ ማቴዎስ እንደሆነያስቀምጣል፡፡

የስሙ ትርጓሜ እና መጠራቱ፡-ማቴዎስ ማለት የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ የቀድሞ ሰሙ ሌዊ ይባል ነበር፡፡ ቁጥሩ ከ12 ሐዋርያት ወገን ነው፡፡ /ማቴ 9፣9-13 ማር 2፣13-17/ ማቴዎስ አባቱ ዲቁ እናቱ ከሩትያስ ይባላሉ፡፡ በማርቆስ ወንጌል ላይ የማቴዎስ አባት እልፍዮስ አንደሆነተመዝግቧል፡፡ /ማር 2፣14/

በእስራኤላዊያን ባህል በሁለት ስም መጠራት ልማድ ሰለሆነ የማቴዎስ አባት ዲቁ ሌላው ስሙ እልፍዮስ ይባላል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ከነገደ ይሳኮር ወገን ሲሆን በገሊላ አውረጃ በምትገኘው በቅፍርናሆም ከተማ ተቀምጦ ለሮማዊያን/ ሄርድስ አንቲጳስ/ ቀረጥ ይሰበስብ ነበር፡፡ /ማቴ 1፣1 13/

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዚህች ከተማ በሄደ ጊዜ በመቅርጫው ተቀምጦ አገኘውና ተከተለኝ ብሎ ጠራው፡፡ ለጊዜው ጌታችንንበእግር ተከተለው፤ ፍጻሜው ግን በግብር መሰለው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ገንዘቡን ሁሉ ለድሆች በማብላት ጌታችንን እና ደቀ-መዛሙርቱ በቤቱ ጠርቶ የቁም ተስካሩን ያወጣ ሐዋርያ ነው፡፡

ያስተማረበት ሀገር

ቅዱስ ማቴዎስ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስጸጋን ከተቀበለ በኃላ ወደ ሐዋርያዊ አገልግሎቱ ተሰማርቷል፡፡ በፍልስጤም/ለዕብራዊያን/፣ በፋርስ፣ በባቢሎንና በኢትዮጵያ ወንጌልን እንዳስተማረ የቤ/ክ የታሪክ ጽሐፊው አውሳቢዮስ ዘቂሳርያ እና ሩፊኖስ በመጽሐፍቶቻቸው አስቀምጠዋል፡፡ ጥንታዊ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሊቃውንት በምዕራብ ትግራይ በአድዋ አዋራጃ ውስጥ ናዕዴር በተባለ ቦታ እንዳስተማረ ይናገራሉ፡፡ /መዝ 71(72)፣40/ በመጨረሻም ጥቅምት 12 ቀን ብስባውሪ በምትባል ቦታ አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ በሰማዕትነት አርፏል፡፡ /ስንክሳር ጥቅምት 12/

የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈበት ዘመን

የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል የተጻፈበት ዘመን በተመለከተ እየሩሳሌም በ70 ዓ.ም ከመጥፋቷ በፊት የተጻፈ መሆኑን አብዛኞቹ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ በግእዝ የመጽሐፍ ቅዱስትርጓሜ ላይ ጌታ ባረገ በ8ኛው ዓመት ተፈጽሞ የ9ኛው ዓመት ሲጀመር ቀላውዴዎስ ቄሳር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህም በ41 ዓ.ም ማለት ነው፡፡ በአንዳንድ መጽሐፍት ከቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ቀጥሎ በ58 ዓ.ም እንደተጻፈ ይገለጻል፡፡

ወንጌሉ የተጻፈበት ቦታ፣ ቋንቋ እና የተጻፈላቸው ሰዎች

ቅዱስ ማቴዎስ በምድር ፍልስጤም ከአይሁድ እምነት ወደ ክርስትና ለተመለሱ አይሁዳዊያን/ዕብራዊያን/ ጽፎላቸዋል፡፡ ትምህርቱን አስተምሮ ወደ ሌላ ቦታ ለማስተማር በሚሄድበት ጊዜ አባታችን በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል እና ጻፍልን ብለውት ጽፎላቸዋል፡፡ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉንስለጻፈበት ቋንቋ ሶስት አይነት አስትምህሮች አሉ፡-

ሀ. በዕብራይስጥ፡- የቤ/ክ ሊቃውንትን ጨምሮ አብዛኞቹ ምሑራን የሚስማሙበት ወንጌሉን በዕብራይስጥ ቋንቋ እንደጻፈው ነው፡፡ ነገር ግን የዕበራይስጥ ቅጂ እስከ አሁን ድርስ አልተገኝም፡፡

ለ. አረመይክ፡- የአረማይክ ቋንቋ በመጀመራያ መቶ/ክ/ዘመን በፍልስጤማዊያን የሚነገር ቋንቋ ሲሆን ጌታም ያሰተማረው በዚህ ቋንቋ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ ወንጌሉ በአረማይክ ቋንቋ ጽፎታል ይላሉ፡፡ ፓፒዮስ የተባለ የቤ/ክ አባት በ2ኛ መ/ክ/ዘ እንደአስቀመጠው ሎጂያ ተብሎ በሚጠራው ስብስብ ውስጥ የጌታችን ታሪክ ትምህርት እና ታምራት እንደተመዘገብ ይተርካል፡፡ በዚህም ወንጌሉ በአረማይክ ቋንቋ ጽፎታል ይላሉ፡፡

ሐ. በግሪክ፡- አብዛኞቹ የማቴዎስ ወንጌል ቅጅዎች በግሪክ ቋንቋ ይገኛሉ ይህንም በመያዝ ወንጌሉ በግሪክ ቋንቋ ጽፎታል ይላሉ፡፡

የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈበት ምክንያት

1. ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብርሃም እና ከዳዊት ዘር የተወለደ ፍጽም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለማጠይቅ፡፡ የሰው ልጅ፣ የዳዊት ልጅ እያለ ጌታ እራሱ የተናገራቸውን ይጠቅሳል፡፡ /1፣1-17 9፣6 16፣1317፣12…/

2. አይሁድ ጌታን ከነብያት አንዱ ነው ይሉት ነበርና ወልደ እግዚአብሔር መሆኑን ለማስረዳት፡፡ /3፣17 8፣29 11፣25-27…./

3.በሕግና ነብያትስለመሲሁ የተናገሩት ስለጌታ መሆኑን ለማስተማር ጽፎላቸዋል፡፡/ 1፣22-23 2፣4 16፣ 11-25 12፣17-21…/

የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል 28 ምዕራፎች እና 1061 ቁጥሮችን በውስጡ የያዘ ወንጌል ነው፡፡ ከ1061 ቁጥሮች ውስጥ 644 የጌታ ትምህርቶችንይዟል፡፡ በዚህ ከዮሐንስ ወንጌል ጋር ሲዛመድ ከሉቃስ እና ከማርቆስ ወንጌል ጋር ይለያል፡፡የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ከ150 በላይ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ይጠቅሳል፡፡

በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ላይ ከ150 በላይ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች መጠቀሱ ወንጌሉ ትንቢት ለተነገረላቸው ሱባኤ ለተቆጠረላችሁ ለአይሁዳዊያን መጻፉን ያሳያል፡፡

የወንጌሉ አከፋፈል

የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል 28 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን እንደሚከተለው ይከፈላል፡-

ከምዕራፍ 1-4 - የጌታችንመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የትውልድ ሐረጉን፣ልደቱን፣ስደቱን ጥምቀቱን እና በዲያቢሎስ መፈተኑን
ከምዕራፍ 5-7 - የተራራው ስብከት
ከምዕራፍ 8-12 - የኃይል ስራው /ተአምራቱ/፣ 12 ደቀ-መዛሙርቱን መምረጡ፣የሠጣቸውን ስልጣን እና ትዕዛዝ ይዟል፡፡
ከምዕራፍ 13-20 - በደብረ ታቦር የጌታችን ክብር መገለጡ፣ ሐዋርያትን ማስተማሩ
ከምዕራፍ 21-27 - ወደ እየሩሳሌም በክብር መግባቱ፣ ስለ ዳግም ምጽአቱ ማስተማሩ፣ ከአይሁድ መጣላቱ ሕማሙ፣ስቀለቱ ና ሞቱ
ከምዕራፍ 28 - ስለ ጌታችን ትንሳኤና መገለጥ ያትታል፡፡

2. የቅዱስ ማርቆስ ወንጌል
የማርቆስ ወንጌል የተጻፈው በቅዱስ ማርቆስ ነው፡፡ የቤ/ክ የታሪክ ጽሐፊው አውሳቢዮስ ዘቂሳርያ /339/ የቤ/ክ ታሪክ በሚለው መጽሐፉ ላይ ቅዱስ ማርቆስ እንደ ጻፈው ይናገራል፡፡ /መጽሐፈ ስንክሳር ሚያዝያ 30/

የሰሙ ትርጉም፡-ቅዱስ ማርቆስ ሁለት ሰሞች እንዳሉት ቅዱሳት መጽሐፍት ይናገራሉ፡፡ ዮሐንስ ና ማርቆስ፡፡ ዮሐንስ አይሁዳዊ ስሙ /ዮሐ 12፣12-25 13፣5-13/ ሲሆን ማርቆስ ደግሞ የሮማዊ ስሙ ነው፡፡ማርቆስ /የሐዋ 15፣19 2ጢሞ 4፣11 1ጵጥ 5፣13/ ማርቆስ ማለት ታላቅ መዶሻ ወይም ካህን ማለት(ልዑክ) ማለት ሲሆን ዮሐንስ ማለት ፍስሃ ወይም ደስታ ማለት ነው፡፡

የቅዱስ ማርቆስ ቤተሰቡ፡- የማርቆስ እናቱ ማርያም ከ36ቱ ቅድሳት አንስት መካከል የምትቆጠር ናት፡፡ ቤቷን ለሐዋርያት መሰብስቢያ፣ ጸሎት ማድርጊያ፣ ስርዓት መሠራያ ሰለሰጠች ቤ/ክ ተብሎ ተጠረቷል፡፡ /የሐዋ 12፣5/ ጌታም የመጨረሻውን እራት የበላው በማርቆስ እናት ቤት ነው፡፡ /የሐዋ 1፣26/ ቅዱስ ማርቆስ በልጅነቱ በእየሩሳሌም ውስጥ የተፈጹምት ድርጊቶች ያወቃል አብሮ ነበርና፡፡ /ማር 14፣51-52/ ጌታ በተያዘ ጊዜ እርቃኑ የሸሸው እሱ ነበር፡፡

ወንጌል ያሰተማረበት ሀገር

ቅዱስ አውሳቢዮስ ዘቂሳርያ ማርቆስ በሮም ውንጌልን እንደሰበከና ወደ እስክንድርያ ሄዶ እንዳስተማር የመጀመርያ የእስክንድርያ ጳጳስ እንደሆነ ጽፏል፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት በአፍሪካ ሀገራት ተዞዋውሮ እንዳስተማረ ይገልጻሉ፡፡

ውንጌሉ የተጻፈበት ቦታ፣ ቋንቋ እና ዘመን

ውንጌሉን ለሮማዊያ ሮም ላይ ሆኖ በሮማይስጥ/ላቲን/ ቋንቋ ጽፎታል፡፡ እንደ ቤ/ክ አስተምሮ ውንጌሉን የጻፈበት ዘመን ጌታ በዐረገ 11ኛው ዓመት ተፈጽሞ 12ኛው ዓመት ሲጀመር ቀላውዲዎስ ቄሳር በነገሰ በአራተኛው ዓመት ነው፡፡ 44 ዓ.ም አካባቢ ጽፎታል፡፡

ቅዱስ ማርቆስ ውንጌሉ የጻፈላችው ሮማዊያን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት እውቅት ስለሌላቸው በውንጌሉ ውስጥ ስለአይሁዳ ባህልና ስለዕብራዊያን አንዳንድ ቋንቋ በመተርጎም አሰቀምጧል፡፡ /3፣17 5፣41 7፣12 7፣34 14፣36…/በወቅቱ አብዛኛው ዓለም ያስተዳድሩ የነበሩት ሮማዊያን ከእነሱ በላይ ኃያል እንደሌለ አድርገው ይመኩ ሰለነበር የጌታችን የመድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅነትና ሁሉ ማድርግ የሚችል አምላክ መሆኑ ለማስተማር የጌታን ታምራት በውንጌሉ ውስጥ ከሌሎቹ ወንድሞቹ በተለየ ተቀሷቸዋል፡፡

ወንጌሉ የተጻፈበት ዓላማ

1. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለሮማዊያን ለማስረዳት/ለማሰተማር/፡፡ (1፣1-11 3፣11 9፣7 12፣35-37)
2. ጌታችን ካስተማራችው ትምህርት ይልቅ የሰራቸውን የኃይል ሥራ/ታምራት/ አብዝቶ በመግለጥየጌታችን አምላክነት፣ሁሉቻይነት እና ኃያልነት ለማስተማር፡፡

የማርቆስ ወንጌል አጠቃላይ ይዘቱ ስንመለከት 16 ምዕራፎች እና 678 ቁጥሮች ያሉት ከወንጌላዊያ ሁሉ ትንሽ ምዕራፍ ያለው ወንጌል ነው፡፡ወንጌሉ ሲጻፍ የሚጀመርው በማስተማር ዘመኑ የተፈጸሙ የጌታ ትምህርትና ታምራት በመጥቀስ ነው፡፡ በዚህ ከሌሎችን ወንጌላዊያን ወንድሞቹ ይለያል፡፡ ማቴዎስና ሉቃስ ከልደቱ ሲጀምሩ ዮሐንስ ከቀዳማዊነቱ ይጀምራል፡፡ ማርቆስ ግን በማሰተማር ዘመኑ ይጀምራል፡፡

የቅዱስ ማርቆስ ወንጌል አከፋፈል

ከምዕራፍ 1-6 የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት፣ የጌታ ጥምቀት፣ ሽባውን ስለመፈወሱ፣ ጌታ በገሊላ ተመስግኖ እንዳስተማረ
ከምዕራፍ 7-9 ሰውን ስለሚረክሱ ስራዎች፣ እንጀራን አበርክቶ ሰለመመገቡ፣ በደብረ ታቦር ክብሩን ሰለመግለጹ
ምዕራፍ 10 የጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ፣ በይሁዳ ስለማስተማሩ፣ በኢያሪኮ ዓይነ ስውር ስለመፈወሱ
ከምዕራፍ 11-13 ወደ ኢየሩሳሌም በክብረ ስለመግባቱ፣ ስለወይን ቦታ ስራተኞች፣ ሰለዓለም ፍጻሜ ማስተማሩ
ከምዕራፍ14-16 ስለ ጌታ እራት፣ ስለ ጌቴሴማኔ ጽሎት፣ ስለ ጌታ መያዝ፣ መሰቀል፣ መሞትና መቀበር፣ ሰለትንሣኤው ያትታል፡፡

3. የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል
ሉቃስ ማለት ሊባኖስ /ሉካኖስ/ ማለት ሲሆን ትርጉሙም መብራት ማለት ነው፡፡ በትርጓሜ ወንጌል ላይ ዐቃቤ ሥራይ/ሐኪም/ ትንሣኤ ማለት ነው ይላል፡፡ ሉቃስ ሰሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ወስጥ ሶስት ጊዜ ተጠቅሷውል፡፡ / ቆላ 4፣14 2ኛ ጢሞ 4፣11 ፊል 2፣4 / ቅዱስ ሉቃስ ሀገሩ አንጾኪያ ሲሆን የሁለት ሞያዎች ባለቤት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገል፡፡

ሀ. ባለመድኃኒት ሉቃስ“የተወደደው ባለመድኃኒት ሉቃስ…” / ቆላ 4፣14/

ለ. ሠዓሊ ሉቃስ ፡- በአብዛኞቹ ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያን ትውፊት የቅዱስ ሉቃስን ሰዓሊነት ያሳያል፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳ /የእመቤታችን ልጇን ታቀፋ የተሳለው ስዕል/ ቅዱስ ሉቃስ እንደሳለው ይታመናል፡፡ የቅዱስ ሉቃስ ሰዓሊነት በጻፋቸው ወንጌልና የሐዋርያ ስራ መመልከት ይቻላል፡፡ በአጻጻፉ ቀደም ተከተልን ጠብቆ የጻፈው የሰዓሊነቱ መገለጫ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ የተማረ/ጥበበኛ/ አባት ነው፡፡ ይህንን ትምህርት የተማረው ጠርሴስ አካባቢ እንደሆነና ቅዱስ ጳውሎስን ለትምህርት በሄደበት ወቅት እንደተዋወቅ ይንገራል፡፡

ያሰተማረበት ሀገረና ዕረፍቱ

ቅዱስ ሉቃስ ከዮሐንስ ጋር በመሆን ወደ ጸዕር/ግሪክ/ በመሄድ ዮሐንስ ከፍሎ በሰጠው በመቄዶንያ ወንጌል አስተማሯል፡፡ በተጨማሪ የሮሜ የዳረች ወደ ሆኑት ሀገራት በመሄድ ወንጌልን አስተምሯል፡፡

በኔሮን ቄሣር ዘመን መንግስት ወንጌልን እያስተማር እያለ የጣኦት ካህናት ከሰው ወደ ቄሣር አመጡት፡፡ ንጉሱምእጁእንዲቆረጥ አዘዘ ቀኝ እጁን ከቆርጡት በኃላ ወደ ቀደመው አድርጎ መልሶታል፡፡ በዚህ ዕለት አንገቱን ተቆርጦ ጥቅምት 22 ቀን በ84 ዓመቱ በሰማዕትነት አርፏል፡፡

ወንጌሉ የተጻፈበት ዘመን፣ቦታ፣ እና ቋንቋ

ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉ የጻፈበት ቦታ መቄዶንያ በምትባል ሀገር ነው፡፡ በዚያች ሀገር ገዥ ለነበረው ቴዎፍሎስ ለተባለ ሰው እንደጻፈለት የወንጌሉ መግቢያ ምዕራፍ ይናገራል፡፡/ሉቃ 1፣1/ ወንጌሉ የተጻፈበት ቋንቋ ዮናኒ የሚባል የግሪክ ቋንቋ ነው፡ ወንጌሉ የተጻፈበት ዘመን ጌታ ባዐረገ 21ኛው ዓመት ተፈጽሞ 22ኛው ዓመት ሲጀመር ቀላውዴዎስ ቄሳር በነገሰ በ14ኛው ዓመት ነው፡፡

ወንጌሉ የተጻፈበት ዓላማ

የሉቃስ ወንጌል የተጻፈበት ዓላማ በመግቢያ ላይ በግልፀ ተቀምጧል፡፡ ‹‹ስለተማርከው ቃል እርግጡን እንዲታወቅ በጥንቃቅ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትሎ በተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፡፡›› በማለት አሰቀደሙ ለመኮንኑ ቴዎፍሎስ ያስተማርውን ወንጌል በጥልቀት እንዲረዳው ብሎ እንደጻፈለት ያሰተመራል፡፡ በተጨማሪ፡-

1. ከድንግል የተወለድ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለማሰረዳት /1፣35-43 2፣49 3፣22-38 4፣3-4 10፣22 23፣43/
2. ጌታ ለደኅነት እንደተገለጠ ለማስተማር
3. ስለመዝሙርና ስለጸሎት የተለያዩ ማስረጃዎች በማቅረብ ያስተምራል/1፣46-55 2፣14፣29-34 3፣21 5፣16 6፣12/

የሉቃስ ወንጌል የሚጠራባቸው መጠሪያዎች፡-

- ስለ ሴቶች /እመቤታችን፣ ኤልሳቤጥ …/ ስለሚጽፍ ወንጌል አንስት ተብሎ ይጠራል፡፡ /ሉቃ 8፣1-3/
- ስለመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ደጋግሞ በመጻፉ “ ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ” ይባላል፡፡ / 1፣35 4፣1 11፣13 12፣12 /
- ለአሕዛብ ክርስቶስ የፍቅር አባት እንደሆነ ሰለተጻፈ “ወንጌለ አሕዛብ” ተብሎ ይጠራል፡፡/15፣16/

የወንጌሉ አከፋፈል

የሉቃስ ወንጌል 24 ምዕራፎች እና 1151 ቁጥሮችን በውስጡ ይዟል፡፡

ምዕራፍ 1 መግቢያ፣ የመጥምቁ ዮሐንስ ልደት፣ የእመቤታችን ብስራት
ከምዕራፍ 2-3 የጌታችን ልድትና የሕጻንነት ታሪክ
ከምዕራፍ 4-8ጌታች የማስተማርና የተአምራት ስራውን በገሊላ ስለመጀመሩ እና የደቀ-መዛሙርቱ መጠራት
ከምዕራፍ 9-19 እየሩሳሌም ስለመጓዙና በይሁዳ ሐገረ ስለፈፀመው ስራ፣ ስለ እምነት የሰጠው ትምህርት
ከምዐራፍ 20-23 እየሩሳኤል ገብቶ ስለማስተማሩ፣ ለስው ልጆች ስለተቀበለው መከራ
ምዕራፍ 24 ስለ ትንሣኤና ዕረገቱ ይተርካል፡፡

4. የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል
አራተኛው ወንጌል የተጻፈው በሐዋርያ በቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ በወንጌሉ ላይ ዮሐንስ ጻፈ የሚል ባይኖርም ጌታ ይወደው የነበረ ሐዋርያ ጻፈው ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ /20፣24/ ጌታ ይወደው የነበረ ሐዋርያ ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ስሞች

ቅዱስ ዮሐንስ ከሚጠራበት ዮሐንስ ከሚለው ሰሙ በተጨማሪ ሰባት የተለያዩ ስሞች አሉት፡፡

o ወንጌላዊ ፡- የአራተኛው ወንጌል ጻፊ ስለሆነ
o ፍቁረ እግዚእ ፡- ጌታ ይወደው የነበረ ሐዋርያ
o አብሎቀለምስስ ፡- ባለ ራዕይ
o ቁጽረ ገጽ ፡- /ፊቱ በሀዘን የደመነ/ የጌታን ስቀለት የተመለከት በመሆኑ በህይወት ዘመኑ ፊቱ ሳይፈታ የኖረ በመሆኑ ቁጽረ ግጽ ተብሏል፡፡
o ታኦሎጎስ ፡- ነባቤ መለኮት ማለት ነው፡፡
o ወልደ ነጎድጓድ /ቦአጌርጌስ/ ፡- ከወንድሙ ከያዕቆብ ጋር የሚጠራበት ሰሙ ነው፡፡ ይህንን ስያሜ ያወጣለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ /ማር 3፣17/
o ወልደ ዘብዴዎስ ፡- የዘብዴዎስ ልጅ ተብሎ ይጠራል፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ቤተሰቦዎች

አባቱ ዘብዴዎስ እናቱ ማርያም ባውፍልያ ይባላሉ፡፡ አሣ በማጠመድ ላይ የተሰማሩ ደና ገቢ ያላቸው ቤተሰቦዎች ነበሩ፡፡ አሰቀድሞ ከእድርያስ ጋር በመሆንየመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር፡፡ /ዮሐ 1፣35-43/ ዮሐንስ ማለት ደስታ ፍሣሃ ማለት ነው፡፡ /ማቴ 10፣3 ሉቃ 1፣13-14/

የቅዱስ ዮሐንስ ጥሪ

ቅዱስ ዮሐንስ ከወንድሙ ያዕቆብ ጋር በመሆን አሳ በማጥመድ ላይ ሳለ ጌታችን ወደ ገሊላ ባህር ለማስተማር በመጣ ጊዜ እርሱና ወንድሙ እንዲሁምስሞኦን ጵጥሮስ እና ወንድሙ እንድርያስ ጥርቷቸዋል፡፡/ማቴ 4፣21-22 ማር 1፣19-20 /

ቅዱስ ዮሐንስ የምሥጢር ሐዋርያት ከሚባሉት ወገን ነው፡፡ /ጴጥሮስ፣ያዕቆብ ና ዮሐንስ/ በዚህ ምክንያት ጌታችን ምሥጢረተአምራትን በቤተ ኢያኢሮስ፣ ምሥጢር መንግስትን በደብረ ታቦር፣ ምስጢር ምጽአትን በደብረ ዘይት፣ምስጢረ ጸሎትን በጌቴሴማኒ በገለጸ ጊዜ አብሮ የተመለከተ ሐዋርያ ነው፡፡

ያስተማረበት ሀገረ

ቅዱስ ዮሐንስ የማስተማረ ስራው በኢየሩሳሌምና በአካባቢያም በመጀመረ ከዚህ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በመሆን በአንጾኪያ አስተምሮል፡፡ በዋነኝነት ግን ያስተማረው በእስያ አህጉር በኤፌሶን ከተማ ነው፡፡ በኤፌሶን ከተማ ብዙ ታምራትን በማድርግ ወንጌል አስተምሯል፡፡ ከኔሮን ቄሣር በመቀጠል የነገሰው ድምጢያኖስ የእራሱን ምስል አስርቶ ወደ ከተማይቱ በመላኩ ህዝቡ እንዲሰግድለት አዋጅ አስንገሯል፡፡ ይህ ድርጊት ቅዱስ ዮሐንስ በመቃውሙ ምክንያት ወደ ሮም ተውስዶ በዚህ መንግስት ላይ ያመጹ ስዎች በእስር ወደ ሚቀመጡበት ወደ ፍጥሞ ደሴት በግዞት ተውስዶዋል፡፡ በዚያም ሳለ ራዕይ ተገልጦለት ራዕይ ዮሐንስ ጽፏል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ለሰባት ዓመታት ያል ከታሰረ በኃላ ንጉሱ ሲሞት ነጻ ወጧል፡፡

ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ዕረፍት

ስለ ቅዱስ ዮሐንስ የመጨረሻ ህይወት የተለያዮ አስተምሮዎች አሉ፡፡

1.እንደ ሄኖክ እንደ ኤልያስ ሞተ ስጋ አልቀመሰም፡፡ የሚለው የመጀመሪያ አስተምሮ ነው፡፡ ጌታችን በውንጌል “እኔ እስከመጣ ድረስ በህይወት ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ?” /ዮሐ 21፣20-25/‹‹እውነት እላችኃለሁ የስው ልጅ በመንግስቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድርስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ እንዳንድ አሉ፡፡›› /ማቴ 16፣28/ እነዚህ ዮሐንስ መሰወሩን የሚያለክቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፡፡

2. በማቴ 20፣22-23 እና ማቴ 10፣38-39 የተጻፈውን በመጥቅስ ሞቷል የሚሉ አሉ፡፡

ወንጌሉ የተጻፈበት ቦታ፣ቋንቋ ና ዘመን

የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል የተጻፈብት ቦታ ኤፌሶን ሲሆን የተጻፈበት ቋንቋ ደግሞ የግሪክ /የፅርዕ/ ቋንቋ ነው፡፡ወንጌሉ የጻፈበት ዘመን ጌታ ባዐረገ በ30 ዘመን ኔሮን ቄሳር በነገሰ በ7ኛ ዓመት ነው፡፡ ይህ ማለት በ63 ዓ.ም ተጽፏል ማለት ነው፡፡ ወንጌሉ የተጻፈላቸው ህዝቦች የኤፌሶን ህዝቦች ናቸው፡፡

ቅዱሰ ዮሐንስ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምርማንነቱ በመግለጥ ላይ ያተኩራል፡፡ በዚህ ምስክሮችን አንስቷል፡፡ ካነሳቸው ምስክሮች መካከል፡-

1. የአባቱን ምስክርነት /5፣34 8፣18/
2. የራሱ የወልድ ምስክርነት /8፣18-58/
3. የመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት / 15፣36 10፣25/
4. የሥራዎቹ ምስክርንት /5፣36 10፣25/
5. የቅዱስን መጽሐፍት ምስክርነት / 5፣39-46/
6. የመጥምቁ መለኮት ዮሐንስ ምስክርነት /1፣7 5፣33-35/
7. የተማሪዎቹ ምስክርነት /15፣27 19፣35/ ናቸው፡፡

ጌታችን የእሱን ማንነት ያስታወቀባቸው ሰባት ቃላት በዚህ ወንጌል ውስጥ ይገኛል፡፡ እነርሱም “እኔ ነኝ” በመባል የታወቃሉ

1 የሕይወት እንጅራ እኔ ነኝ /6፣35/
2 የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ /8፣12/
3 የበጎች በር እኔ ነኝ /10፣7/
4 መልካም እረኛ እኔ ነኝ /10፣11/
5 ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ /11፣25/
6 መንገድና ህይወት እኔ ነኝ /14፣6/
7 እወነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ /15፣1/ የሚባሉት ናቸው፡፡

5.3የታሪክ መጽሐፍ ክፍል
በሐዲስ ኪዳን ቅዳሳት መጽሐፍት ጥናት አከፋፈል መሰረት ከወንጌል መጽሐፍት ክፍል ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የምናገኘው የታሪክ መጽሐፍት ክፍል ነው፡፡

ከጌታ ዐረገት በኃላ የመጀመሪያቱ የቤ/ክ ታሪክ የሚናገር ክፍል ከ34 ዓ.ም እስከ 64 ዓ.ም ድርስ ያለው የቤ/ክ ታሪክ የሚናገረው የሐዲስ ኪዳን የመጽሐፍ ክፍል “የሐዋሪያት ስራ” የሚባለው ነው፡፡ በይዘቱ ከክርስቶስ ዕረገት በኃላ ሐዋርያት ያደርጉት የወንጌል ትምህርት እና ሐዋርያዊ ጎዞ የሚተርክ በመሆኑ የሐዲስ ኪዳን የታሪክ መጽሐፍ ወይም የቤ/ክ ታሪክ ተብሎ ተጠርቷል፡፡

ሐዋርያ፡- ማለት የተላክ፣መልክተኛ፣ደጃዝናች፣ቀላጤ፣ምጥው፣ፈንው፣ሒያጅ ማለት ነው፡፡ ይህ ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጣቸው ለ12ቱ ሐዋርያት ነው፡፡ ከእነሱ ውጪ

ሀ. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ /ዕብ 3፣1/
ለ. በርናባስና ጳውሎስ በአንድነት /ሐዋ 14፣4/
ሐ. ጳውሎስ /ሮሜ 1፣1 1ቆሮ 9፣1-2 15፣9 /

1.የሐዋርያት ስራ
የሐዋርያት ስራ በግእዝ ግብረ ሐዋርያት በመባል ይጠራል፡፡ ለመጽሐፉ የተሰጠው ሌላው ስም መጽሐፍ ግብረ ልዑካን፣ዜና ሐዋርያት ይባላል፡፡ ይህ መጽሐፍ እውነተኛ የክርስትና ጠባይን ሰለሚገልጥ የተለየ የክርስትና መጽሐፍ ይባላል፡

የሐዋርያት ስራ ጻፊና የተጻፈለት ስው

የሐዋርያት ስራ ጽሐፊ ቅዱስ ሉቃስ ሲሆን የተጻፈለት ሰው ወንጌሉን ለጻፈላት ለቴዎፍሎስ ነው፡፡ ይህንን የሚደገፉ ነጥቦች

- ቴዎፍሎስ የተባለ ሰው በመገለጡ /ሐዋ 1፣1/
- የሉቃስ ወንጌል መድምደሚያ ቃላትና የሐዋርያት ስራ መነሻ ቃላት በብዛት አንድ መሆናቸው፡፡ /ሉቃ 24፣44-53 ሐዋ 1፣1-2/
- በመጽሐፈ ስንክሳር ይንን የሚደግፍ/የሚመሰክር/ ቃል መገለጹ፡፡ ጥቅምት 22

የተጻፈበት ዘመን፣ ቦታና ቋንቋ

የሐዋርያት ስራ ቅዱስ ሉቃስ በሮም ከተማ ሆኖ በግሪክ ቋንቋ እንደጻፈው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይህ መጽሐፍ የተጻፈበት ዘመን ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በሮም ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሰረበት ወቅት ስለኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ እናዳስተማረ በመጨረሻ ክፍሉ ላይ ይገልጻል፡፡ ይህም ዘመን 62-64 ዓ.ም ድረስ ያሉት ሁለት ዓመታት ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት የተጻፈበት ዘመን 64 ዓ.ም መጨረሻ 65 ዓ.ም መጀመሪያ ሊሆን ይችላል፡፡

የሐዋርያት ስራ ይዘት፡- ጻፊ ቀድሞ ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ ዕረገቱ ከጻፈ በኃላ ከጰራቅሊጦስ ጀምሮ የመጀመሪያውን የቤ/ክ መሠረትና ኅብረት፣ የቤ/ክ ተአምራት፣ የመጀመሪያውን ጥምቅት፣ ስደት፣ እንዲሁም መጀመሪያዎቹ ሰማዕታት… በማንሳት ቤተ ክርስቲያን ከምን ተነስታ ከምን እንደደረሰች የሚያስገነዝብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መጽሐፍ ነው፡፡

የመጽሐፉ አከፋፈል

የሐዋርይት ስራ 28 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን እንደሚከተለው ይከፈላሉ

ምዕራፍ 1 የጌታ ዕረገት፣በይሁዳ ምትክ ሐዋርያ ቅዱስ ማትያስመተካቱ
ከምዕራፍ 2-7በበዓለ ሃምሳ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ለሐዋርያት መወረዱን፣ በአንድ ስብከት ሶስት ሺ ሰዎችን ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳሳመነ፣ቅዱስ ጴጥሮስ ለ40 ዓመት ሙሉ ሽባ የሆነን ሰውማዳኑን፣ የመጀመሪያ የቤ/ክ አንድነት እና አኗኗር፣ የሰባቱ ዲያቆናት ምርጫ እንዲሁም ሰለ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ
ከምዕራፍ8-12 የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በፈሊጶስ መጠመቁ ፣የሳውል መጠራት፣የአንጾኪያ ቤ/ክመመሠረትና ማደግ፣ የሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ስማዕትነት
ከምዕራፍ 13-18 የቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያ ጉዞና ስራዎቹ፣ የመጀመሪያበኢየሩሳሌም የተደረገ ጉባኤ፣50 ዓ.ም
ከምዕራፍ 19-28 የቅዱስ ጳውሎስ በቂሣርያ ለሁለት ዓመት ታሰሮ መቆየቱ ወደ ሮም በይግባኝመመለሱ፣ ጳውሎስ ታስሮ ሳለ ስለክርስቶስ ማስተማሩ ይተረካል፡፡

5.4 የሥርዓት መጽሐፍት ክፍል
እግዚአብሔር አምላክ ያለ ሥርዓት እንዲሁን የፈጠረው ፍጥረት የለም ፡፡ ብሉይና ሐዲስ ኪዳን የሚያወሱት እግዚአብሔር ሁሉ በአግባብና በሥርዓት የሚከናውንና ያከናወነ አምላክ መሆኑን ነው፡፡ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይ እና ምድር ፈጠረ” ዘፍ 1፣1 ይህ የሥነ-ፍጥረት መጀመሪያ ቃል በዘፍጥረት ላይ እንደተመዘገበ እግዚአብሔር ስድስት ቀናት ውስጥ ፍጥረታትን ሲፈጥር ሁሉ በሥርዓት እንዳከናውነ የሚሳይ ቃል ነው፡፡

የሰው ልጅ ለመዳን ከጉስቁልና የጸዳ ህይወት እንዲኖርው እግዚአብሔር ባስቀመጠለት ሥርዓት መጓዝ እንደሚገባው ቅዱሳት መጽሐፍት ይመሰክራሉ፡፡

“ከሥርዓት የሚርቁትን አጎሳቀልካቸው” መዝ 118፣118
“ምድር ከሚቀመጡባት በታች ረክሳለች ሕጉን ተላለፈዋልና ሥርዕቱንም ለውጠዋልና፡፡” ት ኢሳ 24፣5
“ያለሥርዓት የሚሆዱትን ገስጹአቸው ፡፡” 1 ተሰ 5፣14 2 ተሰ 3፣6

5.4.1 ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው
ሥርዓት ማለት “ሠርዐ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ሕግ፣ደንብ፣አሠራር ማለት ነው፡፡ ሥርዓት ማለት የመንፈሳዊ አገልግሎት ሕግና ደንብ ወጥቶለት የአስራር ሂደቱን የተስተካከለ፣ መነሻና መደረሻ ያለው እንዲሁም ሊጠበቅ፣ እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የተቀደሰ አሠራር ማለት ነው፡፡በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ “ሲኖዶስ ዘቅዱሳን ሐዋርያት ተብሎ ይጠራል፡፡” ሲኖዶስ ማለት የአባቶች ጉባኤ ማለት ነው፡፡

5.4.2 የሥርዓት መጽሐፍት በማን፣መቼና በምን ቋንቋ ተጻፉ
የሥርዓት መጽሐፍት ከትንሣኤ እስከ ዕረገት በነበረው ወቅት ጌታ ያስተማረውን ትምህርትና ሥርዓተ ቤተ-ክርስቲያን፣ጳጳሳትና ምዕመናን አንዴት መመራት እንዳለባቸው ያስተምራል፡፡ የሥርዓት መጽሐፍት የተጻፉት በሐዋርያትና በሐዋርያን አበው ነው፡፡ የተጻፉበት ዘመን ከትንሣኤ በኃላ (ከክርስቶስ ዕርገትና ከርደተ መንፈስ ቅዱስ በኃላ) ባሉት ወቅታት ነው፡፡ የተጻፈበት እናት ቋንቋ የሱርስት ቋንቋ(ጥንታዊ የሶርያ ቋንቋ) ሲሆን አንዳንዶች የጽርዕ(የግሪክ ቋንቋ) ቋንቋ ነው ይላሉ፡፡

5.4.3 የሥርዓት መጽሐፍት አከፋፈል እና ይዘት
የሥርዓት መጽሐፍት በሶስት አቤት ክፍሎች ይክፈላሉ፡፡ እነሱም፡-

ሀ. የቤተ-ክርስቲያን አመሠራረት፣ አወቃቀር፣አጠቃላይ የአገልግሎት ሥርዓትና ትምህርት ክፍል የሚያተኩሩ ናቸው፡፡

በዚህ ስር የሚካተቱ መጽሐፍት አራት ናቸው፡፡ እነሱም ዲዲስቅልያ፣ግጽው፣ አብጥሊስና ሥርዓተ ጽዮን ናቸው፡፡ እነዚህ 85ቱ የሐዋርያት ቀኖናዎች ተብለው የሚጠሩት ናቸው፡፡

ለ. ኪዳን ክፍል

በዚህ ስር የሚገኙት ሁለቱ የኪዳን መጽሐፍት (መጽሐፈ ኪዳን ቀዳማዊና መጽሐፈ ኪዳን ካልዕ) የሚባሉት ጌታ ከትንሣኤ እሰከ ዕርገት ያስተማራችው ትምህርት የያዙ ናቸው፡፡ጌታችን ከትንሣኤ በፊት ያስተማራቸው ትምህርት፣ ታምራት እና ታሪክ ወንጌል ተብሎ ሲጠራ ከትንሣኤ እስከ ዕርገት ያለውኪዳንተብለው ይጠራል፡፡

ሐ. የአገልጋዮች አበው ነብያት፣ሐዋርያትና አርድዕት ወ.ዘ.ተ የሚመለከት ክፍል ነው፡፡ አገልጋዮች በሥርዓት መጓዝ እንደሚገባቸው ይተነትናል፡፡

8ቱ የስርዓት መጽሐፍት ከ81 ቅዱሳት መጽሐፍት እንዲካተቱ የወሰኑት 318 ሊቃውንት በኒቃያ ጉባኤ ተሰብሰበው ባለበት ውቅት ነው፡፡

1. መጽሐፈ ኪዳን ቀዳማዊ
መጽሐፋ 59 አንቀጾች ያሉት ሲሆን በዮሐንስ፣በጴጥሮስና ማቴዎስ እንደተጻፈ ይንገራል፡፡ ሌላው 11ዱ ሐዋርያት እንደጻፉትም ይንገራል፡፡ ኪዳን የሚለው ቃል በዚህ አገባብ ትምህርት፣ ምስጋና ማለት ሲሆን ጌታችን ለሐዋርያት ከትንሣኤ በኃላ ለ40 ጊዜ እየተገለጠ ያሰተማራቸው ትምህርት ማለት ነው፡፡

የመጽሐፈ ኪዳን ቀዳማዊ ይዘት ሥርዓት ጸሎትና ሥርዓት ቅዳሴ ነው፡፡ ሶስቱ ኪዳን ዘዘወትር በቤ/ክ የሚደረሱ የምስጋና ጸሎቶች ናቸው፡፡ አጠቃላይ በውሰጡ የሚገኙት፡-

- ኪዳን ዘዘወትር (ኪዳን ዘመንፈቀ ሌሊት፣ ኪዳን ዘነግህና ኪዳን ዘሠርክ)
- ቅዳሴ እግዚእ- በእንተ ቅዳሳት
- ትምህርት ኅቡአት - ፍተሐት ዘውልድ
- በሰማይ ይሐሉ ልብክሙ - እግዚአብሔር ዘብርሃናትናቸው፡:

2. መጽሐፈ ኪዳን ካልዕ
ሁለተኛ መጽሐፍ ኪዳን በስድ ንባብ መልክ የተጻፈ ነው፡፡ አጠቃላይ ይዘቱ ሰለ ዳግም ምጽአት፣ ስለሐሳዊ መሲሕ፣ ሰለ ካህናት ከፍተኛ ና ዝቅተኛ ሹመት/አገልግልት/፣ ሰለ ምዕመናን ንዑሰ ክርስቲያን ሥርዓት ጥምቅትና ምሥጢረ ቁርባን የሚናገረ ነው፡፡ በዚህ ይዘቱ ከራዕይ ዮሐንስ ጋር ይመሳሰላል፡፡ እንደአባቶቻችን አስተምሮ ሁለቱ ኪዳናት 60 አንቀጾች በጋራ ያለቸው ሲሆን 59 አንቀጾች ኪዳን ቀዳማዊ ሲባሉ 1 አንቀጽ በስድ ንባብ መልክ የተዘጋጀ ኪዳን ካልዕ ነው፡፡

3. ሥርዓተ ጽዮን ሲኖዶስ
ጽዮን ማለት አንባ መጠጊያ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያት የመንፈስቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኃላ በጽርሐ ጽዮን ተሰባሰብው ባለበት ውቅት ስለ ሶስቱ የክህነትማዕረጋት፣ ስለአገልግሎትና ሥነ-ምግባር፣ ስለበዓላትአከባበረ፣ ስለስማዕታት መታሰቢያ፣ ስለ ቅድመ ፍሲካ ላለውጾም ፣ሰለ ቅዱስ ቁርባን፣ ስለቅዱሳት መጽሐፍት ምንባብ ወዘተ ሥርዓት የደንገጉበት መጽሐፍ ነው፡

የዚህ መጽሐፍ መሪ ምልክቱ “ዓይን” ይባላል፡፡ የሥርዓተ ጽዮን ሌላው ስያሜ”ሲኖዶስ ቀኖናት ዘጽዮን” ወይም “መጽሐፈ ዜናሆሙ ለሐዋርያት” ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ መጽሐፍ ትዕዛዛቱ የሚፈጸሙት በዘመን ሐዋርይት ብቻ ሳይሆን ከእነሱ በኃላ ለሚመጣው ዘመን የተደነገገ ነው፡፡ በመጨረሻ ቅዱሳን ሐዋርያትና አረድዕት ተከፋፍለው ያስተማሩበትን ሀገረ በዝርዝር ያሰቀምጣል፡፡

4. አብጥሊስ ሲኖዶስ
ይህ መጽሐፍ 82 ቀኖናት/አንቀጾች/ያለበት የመጽሐፍ ሲኖዶስ ክፍል ነው፡፡

አብጥሊስ ማለት አፖስቶሊ ከሚለው የግሪክ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም “የሐዋርያት ቀኖናት” ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ በ1ኛ መ/ክ/ዘመን ሐዋርያት ስለቅዱስ ሲኖዶስ ድንጋጌዎች ይናገራል፡፡ የሲኖዶስ ስብስባ ክርስቲያን ሁለት ወይም ሶስት ኤጵስ ቆጶሳት በተገኙበት ይደረጋል ይላል፡፡

በተጨማሪ ሰለ 81 ቅዱሳት መጽሐፍት ይዘረዝራል፣ ሌላ ስለ ካህናት ጋብቻ፣ ስለአርብና ረቡዕ ጾም ፣ስለሐሰተኛ መጽሐፍ ወዘተ የሚወስንና የሚከለከሉ ቀኖናት አሉት፡፡ ቅዱስ ቀሌምንጦስ በኩሉ ለአሕዛብ የላኩት መጽሐፍ ነው፡፡

መጽሐፈ አብጥሊስ መሪ መልክቱ “ረስጠአ” የሚል ምኅጻረ ቃል ነው፡፡ ረስ ማለት በአረብኛ “ሐዋርያ” ማለት ሲሆን ጠ “ቀኖና ትዕዛዛት፣ አ “አንድኛ ቀዳማዊ” ማለት ነው፡፡

5. ትዕዛዘ ሲኖዶስ
ይህ መጽሐፍ72 ቀኖና /አንቀጽ/ያለበት የሲኖዶስ መጽሐፍ ክፍል ነው፡፡ ትዕዛዝ ማለት በቁሙ ከሥራ አስቀድሞ የሚሰጠ ደንብ፣ሥርዓት ወይም ሕግ አድርግ አታድረግ የሚል ፈቃድ ማለት ነው፡፡ ይህም መጽሐፍ በቀሌምንጦስ እጅ ሐዋርያት ህገ ቤ/ክን ለአሕዛብ ለማሳወቅ ጽፈውታል፡፡

መጽሐፉ(ትዕዛዘሲኖዶስ) ሰለ ሢመተ መላዕክት፣ ዐሥረት፣ መባዐ፣ ሥርዓተ ቁርባን፣ጸሎት ና ሰንበት በሰፊው ያትታል፡፡ የዚህ መጽሐፍ መሪ ምልክቱ “ረስጠብ” ሲሆን ትርጉሙ እንደቀደመው ነው፡፡ በግብጽ ቋንቋ “ሁለተኛ፣ ዳግማዊ” ማለት ነው፡፡ “ሐዋርያት ቀኖናት ቀሌምጦንስ ዳግማዊ” ማት ነው፡፡

6. ግጽው ሲኖዶስ
ይህ መጽሐፍ57 ቀኖና /አንቀጽ/ ያለበት መጽሐፍ ነው፡፡ ግጽው ማለት የታየ፣የተገለጠ፣ ጉልሕ፣ ሥዕል ማለት ነው፡፡

ሰለሢመተ ክህነት ሲያብራራ ቢያንስ ለአንድ ኤጵስ ቆጶስ በሠመቱ ጊዜ መገኝት አንዳለባቸው ያሰረዳል፡፡ 81 ዝርዝር መጽሐፍት አምላካዊት/ቅዱሳት መጽሐፍት/ ያስቀምጣል፡፡

በተጨማሪ ሰለ ህዝባዊያን ተልዕኮ፣ሰለ ትህትና፣ ሰለ 10ቱ ቃላት፣ ሰለ ዐሥራት፣ስለ ሰንበት፣ ስለሙታን ተዘካር፣ሰለ ቁርባንና ጋብቻ በዝርዝር የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡

መሪ ምልክቱ “ረሰጠጅ” ሲሆን ይህ ማለት ሐዋርያት ለቀሌምጦንስ የሰጡት ሦስተኛ መጽሐፍ ማለት ነው፡፡

7. መጽሐፈ ዲዲስቅልያ
ዲዲስቅልያ ማለት ትምህርት ማለት ነው፡፡ ይህንን ስያሜ ያገኘው ከመጽሐፉ ይዘት አንጻር ነው፡፡ በ43 አንቀጾች የተከፈለ ትምህርቶች እናተግሳጾችን የያዘ መድብል ነው፡፡ በሌላ አጠራር “ዲዲስቅልያ ዘሐዋርያት” ይባላል፡፡ ዲዲስቅልያ በአጠቃላይ ይዘቱ ስለ ሥርዓተ ቅዳሴ፣ስለ ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር ትምህርቶች ያዞ የሚገኝ መጽሐፍ ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ መሪ ምልክቱ “ድስቅ” ይባላል፡፡

8. መጽሐፈ ቀሌምንጦስ
ይህንን መጽሐፍ የጻፈው ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሲሆን ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ጌታ የተናገረው በመመስረት የጻፈው ነው፡፡ ቅዱስ ቀሌምንጦስ በ90 ዓ.ም የሮም ሊቀ ጳጳስ ሆኖ የተሾመ ቅዱስ አባት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በህይወት መጽሐፋ ላይ ስሙ መጻፋን በፊልጵስዮስ መልእክቱ ላይ ጠቅሷል፡፡ (ፊል 4፣3)

መጽሐፉ ከአዳም ጀምሮ ስለነበሩ አበው ቅዱሳን ይዘረዝራል፡፡ እንዲሁም ስለገነትና ከገነት ወጥተው ደብረ ቅዱስ ስለገቡ ሰዎች ሁኔታ ይተነትናል፡፡ በተጨማሪም ይዘቱ ስለ ሥርዓተ ቅዳሴ እና ቀኖናዊ ቅርጽ ያለው ነው፡፡

አዲስ ቤ/ክ የሚባረክበት ሥርዓት አንዲሁም በሰሞነ ሕማማት ምዕመናን ከሥጋዊ ስራዎች ማረፍ እንደሚገባቸው ያትታል፡፡ በስተ መጨረሻም ቅዱስ ቀሌምንጦስ ስለአየው ራዕይ ይናገራል፡፡

የመጽሐፉ ልዩ ምልክት “ጵጥ” ነው፡፡ ይህም ጵጥሮስ ማለት ነው፡፡

5.5 የመልዕክት መጽሐፍት ክፍል
ሐዋርያት በአይን ላልተመለከቷቸው እና ለተመለከቷቸው ምዕመናን መልዕክት እየጻፉ ይልኩላቸው ነበር፡፡ ከሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ አብዛኞቹ የመልዕክት ይዘት ያላቸው መጽሐፍት ናቸው፡፡ ከ35ቱ የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ 21 የመልዕክት መጽሐፍት ሲሆኑ ከእነዚህ(ከ21) ውስጥ 14ቱ የቅዱስ ጳውሎስ፣ 3ቱ የቅዱስ ዮሐንስ፣ 2ቱ የቅዱስ ጴጥሮስ 1 የቅዱስ ይሁዳ እና 1 የቅዱስ ያዕቆብ መልዕክታት ናቸው፡፡ እነዚህ 21 መልዕክታት ከተቀባዮቹ አንጻር በሁለት ይከፈላሉ፡፡

ሀ. ለማኅበረ የተላኩ መልዕክታት /ለአማኝ ምዕመናን/ ሲሆኑ በቁጥራቸው 15 ናቸው፡፡ እነርሱም ሮሜ፣ 1ኛ ና 2ኛ ቆሮንጦስ፣ ገላቲያ፣ ኤፌሶን፣ ፈልጵስዮስ፣ ቆላሲስ 1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ፣ዕብራዊያን፣ 1ኛ ና 2ኛ ጴጥሮስ እና 1ኛ የይሁዳ መልዕክት ናቸው፡፡
ለ. ለግለሰብ የተላኩ መልዕክታት፡፡ እነርሱም በቁጥር 6 ሲሆኑ 1ኛ ና 2ኛ ጢሞቲዮስ፣ቲቶ፣ ፊልሞና፣ 2ኛና 3ኛ ዮሐንስ ናቸው፡፡

5.5.1 የመልዕክት መጽሐፍት አጠቃላይ ይዘት
ሃያ አንዱ መልዕክታት በዋነኝነትትኩረት አድርገው የተጻፉት የሃይማኖት፣የሥርዓተ ቤ/ክ እና የስነ-ምግባር ትምህርቶች ላይ ነው፡፡ በተጨማሪ በሌሎች አካላት የሐሰተኛ መምህራን/የተማሩት የስህተት ትምህርትና የስነ ምግባር እርምት ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

5.5.2 የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት
ቅዱስ ጳውሎስ አይሁዳዊ ስሙ ሳውል ይባል ነበር፡፡ ሳውል የሚለው ስም ሰኦል ከሚለው ስም ጋር በትርጉም ተመሳሳይነት ሲኖረው በእግዚአብሔር የተለመነ ማለት ነው፡፡ ጳውሎስ የሚለው ስም በቤተ ክርስቲያን ብርሃን ተብሎ ይተረጎማል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ነገዱ ከአይሁዱ ወገን ከነገደ ብንያም ነው፡፡ ሮሜ 11፡1 ፊል 3፡5 የተወለደው ኪልቅያ ዋና ከተማ በጠርሴስ ነው፡፡ ሐዋ9፡11 21፡39፤22፡3 ነገር ግን የሮሜ ዜግነት ነበረው፡፡ ሐዋ 16፡3፤22፡25፤23፡37 ትምህርቱንም ፈሪሳዊ ሆኖ እንደነበር ተገልጧል፡፡ ሐዋ 23፡6፤26፡5 ፊል 3፡5

ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ ከማመኑ በፊት ክርስትያኖችን ያሳድድ ነበር፡፡ ይህንንም ያደርግ የነበረው ባለማወቅ ነበር፡፡ ሐዋ 26፡9 1ኛ ጢሞ 1፡13 ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት በሞተ ጊዜ በእርሱ መወገር ተስማምቶ የገዳዮቹን ልብስ ይጠብቅ ነበር፡፡ ሐዋ7፡60 22፡20 ከእስጢፋኖስም ሞት በኋላ በእየሩሳሌም ቤተ-ክርስቲያን ላይ በነበረው ስደት ዋነኛው አሳዳጅ ነበር፡፡ ሐዋ፡8፡3

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ክርስትና የተጣራው በሐዋርያት ወንጌል ተሰብኮለት ሳይሆን በራሱ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ገላ 1፡11 ሐዋ 9

የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ጉዞዎች

የክርስቶስን ወንጌል በዓለም ለመስበክ ያደረጋቸው ሐዋርያዊ ጎዞዎች በሐዋርያት ስራ ውስጥ የተመዘገቡት የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ጉዞዎች ሦስት ናቸው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ 14 መልእክታት ጽፏል፡፡

1. የመጀመሪያ ጉዞው በደሴተ ቆጶሮስና በታናሽ ኢስያ ውስጥ በቋንፍልያ እንዲሁም በደቡባዊ ገላትያ በሚገኙ ከተሞች ነበር፡፡
2. ሁለተኛ ሐዋርያዊ ጉዞው መቄዶኒያ እና አካያ በተባሉት አውራጃዎች ነበር፡፡
3. በሦስተኛው ሐዋርያዊው ጉዞው በእስያ መቄዶኒያና አካያ አስተምሯል፡፡

1. የሮሜ መልእክት
ቅዱስ ጳውሎስ የሮሜ መልእክት የጻፈው በቆሮንጦስ ከተማ ሲሆን በሦስተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ መጨረሻ በቆሮንጦስ ለሦስት ወራት በተቀመጠበት ወቅት ነው፡፡

መልእክቱ የፃፈበት ምክንያት ሁለት ሲሆን፡- የመጀመሪያው በሮሜ ቤተ-ክርስትያን ውስጥ ቢጸ ሐሳውያን አይሁድና ከአሕዛብ ክርስቶስን ባመኑ ወገኖች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት በትምህርት ለማስወገድ፡፡ ሮሜ 1፡16፤2፡9፤3፡9/31 ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በወቅቱ ጳውሎስ ቅድሚያ ወደ ሮሜ ከዚያም ወደ እስጳንያ ለመሄድ የነበረው ዕቅድና የጉዞውን አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉለት የነበረውን ተስፋ አስቀድሞ ሊጽፍላቸው ስለወደደ ነው፡፡ ሮሜ 1፡19/15

የሮሜ የመልእክቱ አጠቃላይ ይዘት ስንመለከት በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት የተደገፈ ጥልቅ መረጃ የያዘ መልእክት ነው፡፡

የመልእክቱ አከፋፈል

የሮሜ መልእክት 16 ምዕራፎችን የያዘ ሲሆን ይህንንም በ7 ከፍሎ መመልከት ይቻላል

1. መግቢያ ሮሜ 1፡1/11
2. የእግዚአብሔር ጽድቅ ለአይሁድም ለአሕዛብም የሚያስፈልግ ስለመሆኑ የጻፈው ትምህርት ሮሜ 1፡16/4፡23
3. ጽድቅን ያገኙ ሰዎች ለጽድቅ እንጂ ለኃጢያት መገዛት እንደሌለባቸው የጻፈው ትምህርት ሮሜ5፡1/6፡23
4. በክርስቶስ ስለተገኘው አርነት የፃፈው ትምህርት ሮሜ 7፡1/8፡39
5. መዳን ለእስራኤልም ለአሕዛብም እንደሆነ የፃፈው ትምህርት ሮሜ 9፡1/11፡36
6. ስለ ክርስትያናዊ ሥነ-ምግባር የፃፈው ትምህርት ሮሜ 12፡1/13፡5
7. ማጠቃለያ ሮሜ 15፡1/16፡27

2. የመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ መልእክት
በአጠቃላይ ወደ ቆሮንጦስ የተላኩት መልእክታት ሁለት ሲሆኑ እነዚህ መልእክታት የተፃፈላቸው ክርስትያኖች በሚኖሩበት የቆሮንጦስ ከተማ በግሪክ ሀገር ውስጥ ያለችው የአካያይ አውራጃ ዋና ከተማ ናት፡፡ በዚህ ከተማ ወንጌልን የሰበከውናቤተ-ክርስትያኒቱን የመሰረተው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከው በሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞው ወቅት ሲሆን መልእክቱ የተፃፈው በኤፌሶን በ3ኛ ሐዋርያዊ ጉዞው ላይ ሳለ በኤፌሶን ነው፡፡ ይህም በ55ዓ.ም ገደማ ነው፡፡

መልእክቱ የተፃፈበት ምክንያት ሁለት ሲሆን፡- አንደኛው በቆሮንጦስ ቤተ ክርስትያን ምዕመናን ዘንድ እኔ የጳውሎስ ነኝ እኔ የአጵሎስ ነኝ እኔ የኬፋ ነኝ እኔ የክርስቶስ ነኝ የሚል መለያየት ተፈጥሮ ስለነበር ይህም ልዩነት እንዲያስወግዱ ለመግለጽ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከቆሮንጦስ ምዕመናን በጽሑፍ ተልከው ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ነበር፡፡

የመልአክቱ አጠቃላይ ይዘት ሥነ-ምግባርን ሥርዓትንና ሃይማኖትን ያጠቃለለ የተግሳፅ ትምህርት ነው፡፡

የመልእክቱ አከፋፈል

1ኛ. የቆሮንጦስ መልእክት 16 ምዕራፎች ሲኖሩት እነዚህ በስድስት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡-

1. መግቢያ 1፡1/9
2. በመካከላቸው ስለነበረው ክርክርና መለያየት የጻፈላቸው ተግሳጽ 1፡9/4፡/21
3. ከዝሙት ርቀው በድንግልና ወይንም በጋብቻ እንዲኖሩ የጻፈው ትምህርት 5፡1/7፡40
4. ለጣዖት የተሰዋን መስዋእት መብላት እንደማይገባ የፃፈላቸው ትምህርት 8፡1/10፡33
5. በማኅበር ሲሰበሰቡ ለሚያደርጓቸው ነገሮች የደነገገላቸው ሥርአት 11፡1/15፡58
6. መደምደሚያ 16፡1/24

3. ሁለተኛይቱ የቆሮንቶስ መልእክት
ሁለተኛይቱ የቆሮንጦስ መልእክት የተፃፈው ከመቄዶንያ ሲሆን ጊዜውን በ3ኛው የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት የመጀመሪያይቱ መልእክት የተፃፈው ከዓመት በኋላ ነው፡፡ ይህም በ56ዓ.ም ገደማ ነው፡፡ ሁለተኛይቱ የቆሮንጦስ መልእክት ተፃፈችበት ምክንያት ሦስት ሲሆን፡- አንደኛው ምክንያት የቆሮንጦስ ክርስትያኖች ከስህተታቸው ተመልሰው ንስሐ በመግባታቸው የተሰማውን ደስታ ለመግለጽ ንስሐ ያልገቡትንም ንስሐ እንዲገቡ ሊመክራቸው ስለፈቀደ 2ቆሮ 5፡6/7 12፡19/21 ሁለተኛው ምክንያት በመካከላቸው ገብተው ልዩ የሐሰት ትምህርት ያስተምሩ ከነበሩ ሐሰተኛ መምህራን እንዲጠበቁ ለማስጠንቀቅ 1፡1/15 እና ሦስተኛው ምክንያት ቀደም ሲል ለኢየሩሳሌም ክርስትያኖች እንዲሰጥ ጀምረውት የነበረውን የአስተዋፅኦማሰባሰብ አጠናቀው እንዲጠብቁት ስለ ልግስና ስጦታ ሊጽፍላቸው ስለወደደ 8፡1 9፡7