Advertisement Image

ክርስቲያናዊ ስነምግባር

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የክርስቲያናዊ ስነምግባር ምዕራፎች

ምዕራፍ ሁለት : ዐሠርቱ ቃላት ትእዛዛት

ከላይ እንደተመለከትነው የተጻፈው የእግዚአብሔር ሕግ በኦሪትና በወንጌል የሚገኝ ነው፡፡ በቅድሚያ የምንመለከተው በኦሪት ዘመን ለእስራኤል በሙሴ አማካኝነት የተሰጡትን አሥሩን ቃላት (ትዕዛዛት) ነው። እነዚህ የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መለኪያዎች (መመዘኛዎች) በመሆናቸው ባጭሩም ቢሆን ማወቅ ከእያንዳንዱ ክርስቲያን ይጠበቅበታል። አሥሩ ቃላት የሥነ ምግባር መለኪያ ብቻም ሳይሆኑ ለሃይማኖትና ለክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ሕጎች መሠረቶችም ናቸው። እነሆ÷ እንደሚከተለው ባጭሩ እናያቸዋለን።

ሀ. ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክትን አታምልክ$ (ዘጸ.20÷3)
ሰዎች በምድር ላይ ሲኖሩ የተለያዩ ፍጥረታትን እንደ አምላክ እንዳያመልኩና እንዳይቀበሉ የተሰጠ ትዕዛዝ (ሕግ) ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን ሕግ የሰጠው ለራሳችን ጥቅም ነው፡፡ የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም (ፍጥረት) የፈጠረ ፣ አምነው ለሚያመልኩት ዋጋ የሚሰጥ ፣ የማያምኑበትንና የሚያመልኩትን እሱን ትተው ሌሎች በሰማይና በምድር የሚገኙ ፍጥረታትን የሚያመልኩትንና የማያመልኩትን ደግሞ ለዘለዓለም የሚቀጣ ፣ ሁሉን ማድረግ የሚችል የሚሳነው (ሊያደርገው የማይችለው) የሌለ እሱ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን አምነን እንድንገዛለትና የሕይወት ባለቤት እንድንሆን ነው ይህን ትዕዛዝ (ሕግ) የሰጠን፡፡

ለ. የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጠራ (ዘጸ.20÷7)
ይህ ሁለተኛ ሕግ የእግዚአብሔርን ስም እንድናከብር የተሰጠ ነው፡፡ በሆነ ባልሆነው ማለትም በሐሰት ፣ በመሐላ ፣ በመርገም ፣ በጨዋታ ፣ በቀልድ ፣ በድፍረትና በመሳሰሉት ጊዜዎችና ቦታዎች ስሙን እንዳንጠራ የሚከለክል ሕግ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ #አምላክህ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራው አያንጻውምና$ በማለት አያይዞ ነግሮናል፡፡ ይህም ማለት ስሙን በከንቱ የሚጠራ ሰው ይቀጣል፤ ይፈረድበታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስሙን በጸሎት ፣ በምስጋና ፣ በዝማሬ ፣ በትምህርትና በመሳሰሉት ጊዜዎችና ቦታዎች በክብር በመጥራት ምሕረትና ይቅርታውን ደጅ ልንጠና ይገባናል፡፡

ሐ. የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አስብ (ዘጸ.20÷8)
ይህ ሕግ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ.2 ቁ2-3 በተጻፈው ላይ የተመሠረተ በስድስተኛው ቀን ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሠራዉ ሥራ ሁሉ አረፈ፡፡ እግዚአብሔር ሰባተኛዋን ቀን ባረካት ቀደሳትም፤ ሊፈጥረው ከጀመረው ሥራ ሁሉ በእርስዋ ዐርፎአልና፡፡ በማለት የሰፈረውን የሚያስታውስና ሰውም ሥራውን በሌሎቹ ቀናት ሠርቶ በሰንበት ማረፍ እንዳለበት የሚያሳስብ ነው፡፡ ሰንበትን ከሥጋዊ ሥራ በተለየ ሁኔታ መንፈሳዊ ሥራ እንድንሠራበት ነው የተፈቀደልን፡፡ #ትቀድሳት ዘንድ አስብ$ ማለትም የተቀደሰ ሥራ ሥራባት የሚል መልእክትን የያዘ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ የተቀደሰ ሥራም፡- ምስጋና ፣ ቅዳሴ ፣ የተራበን በማብላት ፣ የተጠማን በማጠጣት እንግዳ መቀበል የታመመና የታሰረ መጠየቅ የታረዘ የተራቆተ ማልበስ ቃለ እግዚአብሔርን መስማትና ማሰማት የመሳሉትን መንፈሳዊ ተግባራት ማከናወን ነው፡፡ ከኃጢአት ተለይቶ ንስሐ ገብቶ ቅዱስ ቁርባን ተቀብሎ የሚዋልባት ቀን ናት ሰንበት፡፡ ይቺ ሰንበት ቀዳሚት ሰንበት ቅዳሜ ስትሆን በሐዲስ ኪዳን የተጨመረችን የክርስቲያኖች ሰንበት የተባለች እሑድም ከሲኦል ባርነትና ከአጋንን ስቃይ የዳንንባትና ያረፍንባት ፣ ክርስቶስ በትንሣኤ ያከበራት ቀን ናት፡፡ ሁለቱንም በመንፈሳዊ ተግባራት አጊጠን ውስጣችንንና ውጪያችንን በንስሐና በቅድስና አሳምረን ልናከብራቸው የሚገቡ የተቀደሱ ዕለታት ናቸው፡፡

መ. አባትህንና እናትህን አክብር (ዘጸ.20÷12)፡-
ወላጆች ለልጆቻቸው መገኛዎች ፣ አሳዳሪዎች ፣ መጋቢዎች ፣ አሳዳጊዎች ፣ ጠባቂዎችና አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ልጆቻቸው ሊወዷቸው ፣ ሊያከብሯቸው እና ሊታዘዙዋቸው ይገባል፡፡ ይህ ሕግ ይህን የሚያስገነዝብ ሲሆን እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር እድሜህ እንዲረዝም በሚል ማስጠንቀቂያ ያስረዋል፡፡ ይህ ማለት አባት እናትን ማክበር በምድርም ዕድሜ ያረዝማል ነው፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነታችንን ሁሉ የሚወስነውና መሠረት የሚሆነው የመከባበር ሕግ የሚመነጨው ከዚህ ትዕዛዝዝ ነው፡፡ ትኩረት የምንሰጥበት ዋነኛው ነገር እግዚአብሔር ወላጆቻቸውን በሚያከብሩና በሚታዘዙዋቸው ልጆች ደስተኛ መሆኑን መግለጡ ነው፡፡ ይህን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቄላስያስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ሲገልጠው ልጆቼ ሆይ ለወላጆቻችሁ በሁሉ ታዘዙ እንዲህ ማድረግ ይገባናል ይህም እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና በማለት ነው፡፡ ቄላ.3÷20 ኤፌ 6÷1-4 ይህ ትዕዛዝ በሥጋ የወለዱንን አባትና እናቶቻችንን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ እንደ አባትና እንደ እናት የሚሆኑንን የዕድሜ ባለጸጋዎች ፣ የክርስትና አባትና እናት ፣ መምህሮቻችንንና የመሳሰሉትን ሁሉ የሚመለከት ትዕዛዝ ቃል ነው፡፡ እኛም ይህን አውቀን እንደሰማንና እንደተማርን በዕለት ተዕለት ማኅበራዊና ቤተሰባዊ ሕይወታችን ይህን ተግባር ለመፈጸም መጣር ይጠበቅብናል፡፡

ሠ. አትግደል (ዘጸ.20÷13) ፡-
ይህ ትዕዛዝ በቀጥታ ክቡር ከሆነው ሕይወት ጋር የተገናኘ የተያያዘ ነው፡፡ ድርጊቱ ከሟች በበለጠ የገዳዩን ዕድሜ ፣ ሕይወት 2 ኅሊና ፣ ሞራልና መጨረሻ የሚያበላሽ ታላቅ ኃጢአት ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሔር ሕንፃ (እጅ ሥራ) ነው፡፡ በዚህ ዓለም የሚገኝ ማንም ሰው የሠራውን ሥራ ሌላው ተነስቶ ዝም ብሎ ቢያቃልልበትና ቢያፈርስበት ፀጥ የሚለው የለም፡፡ እግዚአብሔርም የእጅ ሥራውን (ሕንፃውን) የፈለገውን ያህል አመፀኛ እንኳን ቢሆን ከሕግ ውጪ ማንም እንዲያፈርስበት አይፈልግም፡፡ የሚያደርጉት ሰዎች ካሉም እንኳን የፈጠራቸው አምላክ እግዚአብሔር ይበቀልላቸዋል እንጂ ቸል ብሎ አይመለከትም፡፡ ሰው አየኝ አላኝ ተብሎ በድብቅ እንኳን ግድያው ቢፈጸም፡-

- የሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር፤
- የአጥፊው (የገዳዩ) ሰው ኅሊና፤
- በደሉ የተፈጸመበት ሰው ደም (ነፍስ)፤
- በዚያው የሚኖሩ ሥነ ፍጥረቶች ሁሉ ይመሰክሩበታል፡፡ እግዚአብሔርም እነዚህን ምስክር አድርጎ ይቀጣዋል (ይበቀለዋል)፡፡

ሰው ሰውን የሚገድለው በሥጋው በአካሉ ብቻ አይደለም፡፡ ያለውን ጥራቱን በማሳጣት ፣ ሞራሉን በስደብ… በመስበር ፣ ከሃይማኖት በማውጣት በማጠራጠር ፣ ታሪኩን በሐሰት በማበላሸ ወዘተ በመሳሰሉ ሕገ ወጥ ተግባራትም ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ እነዚህ ሁሉ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው እኛም ተመሳሳይ በሆኑና በተጠቀሱ የግድያ ተግባራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዳንሳተፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡

ረ. አታመንዝር (ዘጸ.20÷14)
ይህ ሕግ የሰዎችን የኅሊና ነፃነትና የቤታቸውን ሰላም ለመጠበቅ ሲል እግዚአብሔር የሰጠው ነው፡፡ ማመንዘር ወይም ዝሙት ማለት ነው ሰው አንድ ለአንድ በተቀደሰ ጋብቻ ከተፈቀደለት የትዳር አጋሩ ጋር ከሚያደርገው ውጪ የሚሠራ የነውር እና የርኩሰት ሥራ ነው፡፡ ሥጋዊ ፍላትን ካልተቆጣጠሩትና በአግባቡና በተፈቀደው መስመር ብቻ እንዲስተናገድ ካላደረጉት ነፍስንም ሥጋንም ከሚጎዳ ዝሙት ይደርሳል፤ ወይም የዝሙት ምርኮኛ ያደርጋል፡፡

ማመንዘር በዚህ ዓለም ሥጋዊ ጤንንትንና ሕይወትን ለታላቅ ችግር ከማጋለጡም በላይ ቤተሰብን የሚበትን ፣ ሰላምን የሚያናጋና ለማኅበራዊ ቀውስ የሚያጋልጥ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ ከሚስት ውጪ ወንዱ የሚፈጽመውና ሴትም ከባልዋ ውጪ የምትሠራው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ነው ዝሙት የሚባለው፡፡ ያላገቡም ከማግባታቸው በፊት የሚያደርጉት የጾታ የወንድና የሴት ግንኙነት በእግዚአብሔር የተፈቀደ አይደለም፡፡ ይህ ድርጊት በወዱየኛው በሰማያዊው ዓለምም ወነደል ሆኖ መንግሥተ ተሰማይትን የሚከለክል እና ከእግዝአብሔር ጋር የማይጣት ታላቅ በደል ኃጢአት ነው፡፡ ስለዙህ የተሳሳቱ በንስሐ ታርመው በቀጣይ ሕይወታቸው እንዲስተካከሉ፤ ያልተሳሳቱም እንዳይሰሳቱና በቤተከርስትየን ሕግ መሠረተ ጋብቻቸውን መሥርትው አንደሉ አንድ ተወስው በመጠንቀቅ እነዲኖር ልንነግራቸውና እኛም ሠርተን በማሳየት ምሌ ልንሆናቸወ ይገባል፡፡

ሰ. አትስረቅ (ዘጸ.20÷÷15)
ይህ ሕግ በዚህ ዓለም ሰዎች ሠርተው የማግኘት መብታቸውን እንዳያጡ ፣ የንብረት (የሀብት) ባቤትነት መብትና ነጻነታቸውን እንዳይገፈፉ የሚከራከር (ጥብቅና የሚቆም) ነው፡፡ አንዱ የሌላውን ሀብትና ንብረት ባለሥልጣን ፣ ባለ ጉልበት ፣ ባለ ወገን ፣ ባለ ገንዘብ ፣ ባለ ጊዜ ነኝ ብሎ ገፍቶ እንዳይቀማው የሚከለክል ሕግ ነው፡፡ በሌላም መንገድ አታሎም ሆነ ተደብቆ አንዱ የአንዱን ንብረት (ሀብት) እንዳይወስድ ይከለክላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ደግሞ እንዳስታወቀው ሰው በላቡ (በወዙ) ወጥቶ ወርዶ በሚያገኘው ሀብት ብቻ እንዲተዳደር እንጂ የሌላውን እጅ ጠባቂ እንዳይሆን የሚያሳስብ ሕግ ነው፡፡ አንድ ሰው ያልለፋበትን የሌላውን ሰው ንብረት በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን ከቀማ እንደ ነፍስ ገዳይ መሆኑ ነው፡፡

እውነተኛ ሰው ክርስቲያን ለሌላው ይረዳል እንጂ የሌላውን አይቀማም ፣ አይዘርፍም አያታልልም፡፡ አጋጣሚዎችን ተገን ምክንያት አድርጎ ጉቦ አይቀበልም፤ አራጣ ወለድ አይቀበልም፤ በሚዛን አይበደልም የተበደረውን አያስቀርም አይክድም፡፡ እነዚህ ሁሉ ተግባራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የስርቆት መንገዶች ናቸውና፡፡ ስለዚህ የአንድን ሰው አካላዊም ሆነ አእምሮአዊ ንብረቶች እውቅና ሰጥቶና አክብሮ መኖርና የግድ አስፈላጊ ከሆነም ገዝቶም ሆነ በቀጥታ ለምኖ ወይም አስፈቅዶ ባለቤቱን በማክበርና በማመስገን በሠላምና በፍቅር መጠቀም እንጂ የስርቆትን መንገድ መከተል በዚህም ምድር በረከትን ያሳጣል፤ በወዲያናውም ዓለም ከእግዚአብሔር ያጣላል፡፡ ክርስቲያኖችን ይህን በማወቅ ራሳቸውንና ወገኖቻቸውን ከዚህ አሳፋሪ ኃጢአት ለማራቅ መታገል አለባቸው፡፡

ሸ. በባለእንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር (ዘጸ.20÷16)
ባልንጀራ የሚለው ቃል መሰሎቻችን የሰውን ዘር ሁሉ የሚመለከት ቃል ነው፡፡ ሐሰት ማለት የሆነውን አልሆነም፤ ያልሆነውን ደግሞ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ይህም የእውነት ተቃራኒ (ጠላት) ነው፡፡ እንደሌሎቹም ሁሉ በሥጋና በነፍስ የሚያስጎዳ ኃጢአት ነው፡፡ አዳምና ሔዋንን ከገነት ያስወጣቸው ሐናንያና ሰጲራን ያስቀሰፋቸውን ሰዎችን በዓለማችን በርካታ ታላላቅ ኃጢአቶችን ያሠራቸው ሐሰት ነው፡፡ የሰውን መብት ፣ ሕይወት ፣ ነጻነት ፣ የሚያሳጣ፣ ቤተሰብን የሚያፈርስ ማኅበራዊ ቀውስን የሚያመጣ ሀገርንም የሚጎዳ ተግባር ነው፡፡ የሚወዱትን ለመጥቀም የማይወዱትን ለመጉዳት ተብሎ የሚፈጸም ምስክርነት ብቻ ሳይሆን በእውነተኛ መሠረት ላይ ያልቆመን ክስ ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ በሐሰት ለጊዜው እውነተኞች የተጎዱና የጠፉ ቢመስሉንም ዘላለማዊ ጥፋትን ተቀብለው የሞት ሞትን የሚሞቱት ግን ዛሬ እንደጧት ጤዛ በማያረፍደው የሐሰት ደስታ የሚቀማጠሉት ኃጢአተኞች ናቸው፡፡ ይህንን አውቆ እውነተኛ ሆኖ ከእውነት ጋር መከራ እየተቀበሉም ቢሆን ዘላለማዊዉን ደስታ ለማግኘት ከሐሰት ተግባራት ሁሉ መራቅ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡

ቀ. የባልንጀራህን ሚስት ፣የባልንጀራህን ቤት አትመኝ (ዘጸ.20÷17)
አንድ ሰው የሱ ያልሆነውን ማንኛውንም ነገር (ሀብት) የራሱ እንዲሆን እንዳያስብ (እንዳይመኝ) የሚያስጠነቅቅ ሕግ ነው፡፡ ክፉ ምኞች ከላይ በዝርዝር የያናቸውን ኃጢአቶች ለመሠራት የሚያበቃቸው በልብ የሚጠነስስ ኃጢአት ነው፡፡ በሕግ የተከለከለውን ሁሉ ለማድረግ የሚገፋፋ ፣ የሕግን ዳር ድንበር ለማስፈረስ አጥሩንም ለማስጣስ የሚያነሳሳ ታላቅ በደል ነው፡፡

የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ሰው ከፍተኛውን ውጊያ እዚህ ላይ ካደረገና ካሸነፈ በሌሎች ኃጢአቶች ላይ ድል አድራጊ ለመሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኃጢአቶች በልብ ተፀንሰው በማደግ የሚወለዱ ስለሆኑ ነው፡፡ አዳምን ከገነት ያወጣው ፣ አክአብ ናቡቴን እንዲገድል ያደረገው ኤሳው ብኩርናውን እንዲሸጥ ያደረገውና ሌሎች ተመሳሳይና ታላላቅ ኃጢአቶች እንዲሠሩ ያደረጋቸው የራስ ያልሆነውንና የሌላውን ሀብትና ንብረት መመኘት ነው፡፡

ስለዚህ የራሳችን በሆነው (በተሰጠን) መርካትን ትተን የሌላው ሚስት ፣ ሀብት ፣ ሥልጣን ፣ ዕውቀት ፣ ቤትና የመሳሰሉትን ለማግኘት መመኘት በራሱ ኃጢአት መሆኑንና ወደ ባሰው የድርጊት ኃጢአት የሚያሸጋግር መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ በዚች ኃላፊና ጠፊ በሆነች ምድር ላይም ሳንረካና ስንባዝን ከበረከትና ከሰላም ተራቁተን እንደምንኖርና ይቺ ዓለም ስታልፍ እኛም ስንጠራ ዘላለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያሳጣን መሆኑን አውቀን ይህን ከባድ ኃጢአትና የኃጢአቶች ሁሉ ምንጭ የሆነውን ክፉ ምኞት በየጊዜው በመዋጋት ስንሸነፍም ንስሐ እየገባን ልናስወግደው ይገባል፡፡

በ. ባልንጀራህን እንደራስ አድርገህ ውደድ (ዘሌ.19÷18)
ሰው ለመሰሉ (ለሰው) ሊኖረው ስለሚገባ ፍቅርና አክብሮት የሚገልጽ ትዕዛዝ ነው፡፡ መቼም ራሱን የሚጠላ የለም፡፡ ሰው ራሱን የሚወደውን ያህል ሌላውን (መሰሉን) ከወደደ ማኅበራዊ ቀውስ የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ መለያየትና ጥላቻም ሥፍራ (ቦታ) አያገኙም፡፡ እግዚአብሔር በአርአያውና በመልኩ የፈጠረው የሰው ልጅ እርስ በርሱ በመዋደድ እንዲከባበርና እንዲረዳዳ ያዘዘበት ይህ ሕግ የዐሠርቱ ቃላተ ኦሪት መደምደሚያ ሆኖ ነው የተቀመጠው፡፡ ሰው መሰሉን እንደሱ ከወደደ ከላይ አባት እናትህ አክብር ከሚለው ጀምሮ ያየናቸው ትዕዛዛት ሁሉ ቅዱስ ጳውሎስ #ባልንጀራውን የወደደ ግን ሕግን ሁሉ ፈጸመ… ያለው ሮሜ (14÷8-11)

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህን በመልእከቱ ሲገልጠው #እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት ይህች ናት.. እኛ ግን ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃን፤ ባልንጀራችንን እንወዳለንና ባለንጀራውን የማይወድ ግን በጨለማ ይኖራል፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይ የሆነም ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳማይኖር ታውቅላችሁ፡፡ እያለ ነው፡፡ (1ዮሐ3÷11-19) ቅዱስ ዮሐንስ እርስ በእርስ መዋደድ የሚያስገኘውን ሰማያዊ ጥቅምና ጉዳት ገልጦ ካስቀመጠ በኋላ ቁጥር 16 ላይ #በዚህም ፍቅርን አወቅነው፤ እርሱ ራሱን ስለእኛ አሳልፎ ሰጥቷልና፤ እኛም ስለባልንጀሮቻችን ራሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል በማለት ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀውንም ተግባር (ሥራ) ገልጦ አስተምሮናል፡፡

እንግዲህ ፍቅራችን ግብዝነት የሌለበት (የይስሙላ ያልሆነ) እና በሥራ የተገለጠ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ወገኖቻችን ተቸግረው እያለ ከንፈር መጠንና ኀዘናችንን በቃል ብቻ ገልጸን የምንሄድ ከሆነ ክርስትናችን ከንቱ መሆኑ ነው፡፡ ክርስቲያን ተብለን ከተጠራን የክርስቶስን ምሳሌት ተከትለን ልንሠራና የወገኖቻችንን ችግር በማቃለል ያለንን ፍቅር በሥራ መግለጥ ይጠበቅብናል፡፡ አለበለዚያ ነፍሰ ገዳዮች ናችሁ የተባልነውን አንርሳ፡፡ ነፍሰ ገዳይ ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን አይወርስም ተብሏልና መንግሥቱን ወርሰን የዘለዓለም ሕይወት እንድናገኝ እርስ በርሳችን በምግባርና በእውነት እንዋደድ፡፡ (ዮሐ.3÷18)