Advertisement Image

ክርስቲያናዊ ስነምግባር

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የክርስቲያናዊ ስነምግባር ምዕራፎች

ምዕራፍ አንድ : ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር

1.1 ትርጉም
+ ክርስቲያን፡- የተጠመቀ ፣ በክርስቶስ ስም የተጠራ፣ የክርስቶስን ትምህርት የተቀበለ ፣ የክርስቶስ ቤተሰብ የሆነ የክርስቶስ ወገን ተብሎ ይተረጎማል፡፡

+ ሥን፡- መልክ ፣ ውበት ፣ ደምግባት ፣ ጌጥ ፣ ጥራት ፣ ጥዳት፣ መልካምነት ፣ ደግነት ፣ በጎነት ማለት ነው፡፡

+ ምግባር ፡- ሥራ ፣ ፈጠራ ፣ ክንውን ማለት ነው፡

+ ሥነ ምግባር፡- የሥራ መልካምነት ፣ መልካም ሥራ ፣ የሥራ ደግነት ፣ ደግ ሥራ ፣ የሥራ በጎነት ፣ በጎ ሥራ ፣ ማለት ነው፡፡

+ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፡- የክርስቶስ ቤተሰብ ሊሠራው የሚገባ በጎ ስራ፤
o ከክርስቶስ ወገን የሚጠበቅ መልካም ሥራ፤
o ከተጠመቀና በክርስቶስ ስም ከሚጠራ አማኝ የሚጠበቅ ደግ ሥራ ማለት ነው፤

ከትርጉሙ መረዳት እንደሚቻለው ክርስቲያን የሆነ ሰው የሚጠበቅበት መልካም (ደግ) ሥራ አለ ማለት ነው፡፡ ይህንኑ መልካምና የተወደደ ሥራ የምንማርበት ክፍለ ትምህርት መሆኑን ጭምር የቃላቱ ትርጉም ያስረዳናል፡፡

1.2 የክርስቲያን ሥነ ምግባራት መለኪያዎች
ከላይ በትርጉሙ እንዳየነው ከማንኛውም ክርስቲያን የሚጠበቀው መልካም ሥራ መልካምነቱ የሚመዘነው ወይም የሚለካው በዓለማዊ ሚዛን አይደለም፡፡ የሚለካበት የራሱ የሆነ መንፈሳዊ ሚዛን አለው፡፡ እነዚህንም በአጭሩ እንደሚከተለው እናያቸዋለን፡፡

ሀ. ሕገ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ሕግ)

የእግዚአብሔር ሕግ የሚባለው ሰዎች እንዲያደርጉት ያዘዘበትንና እንዳያደርጉት የከለከለበትን ነው፡፡ እንደ አጥርና እንደ ድንበር ያለ ሲሆን እንዳይጥሱትና እንዳያፈርሱት እግዚአብሔር የወሰነውና በቅዱሳን አባቶቻተን በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ ያስተላለፈው ትእዛዝ ነው፡፡

አንድ ክርስቲያን የሠራው ሥራ በራሱም ሆነ በሌሎች ዘንድ መልካም መሆን አለመሆኑ መመዘን የሚገባው ከእግዚአብሔር ሕግ አንጻር (አኳያ) ነው፡፡ የፈጸመው ተግባር አድርግ ብሎ ካዘዘው ውስጥ ከሆነና አታድርግ ብሎ ከከለከለው ውስጥ ከሌለ ሥራው ያማረና የተወደደ ነው ማለት ነው፡፡ የጽሑፍ ሕግ ከተሰጠበት ከኦሪት ዘመን ጀምሮ ስናይ የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መመዘኛዎች 1ኛ. ሕገ ኦሪትና 2ኛ. ሕገ ወንጌል ናቸው፡፡ አንድ ክርስቲያን ሥነ ምግባሩ ያማረ ነው የምንለው ከሕገ እግዚአብሔር አኳያ ከነዚህ ከሁለቱ ሕግጋት ጋር ተስማምቶ እስከተገኘ ድረስ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር (የክርስቶስ) ቤተሰብ ሆኖ ሳለ ሥራው ግን ከአባቱ ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ካልተስማማ ቤተሰብነቱ (ክርስቲያንነቱ) ያጠራጥራል ማለት ነው፡፡

ይህንን በምሳሌ ማየቱ የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ አንድ ልጅ አባቱ የሚያዘውን ሰምቶ የከለከለውን ትቶ የፈቀደለትን ብቻ እያደረገ ከኖረ አባቱ ደስ ይለዋል፡፡ ልጁም በአባቱ ዘንድ የተወደደና የተመሰገነ ልጅ ይሆናል፡፡

በተቃራኒው አታደርግ ሲለው እያደገ፤ አድርግ ሲለው ደግሞ እምቢ ማለት ከጀመረ በአባቱ ዘንድ የተጠላና የተረገመ ሆኖ ይቀራል፡፡ ተመክሮ ተመክሮ ካልተስተካከለም አባቱ ልጄ አይደለህም ብሎ ከቤት ያባርረዋል፡፡ እግዚአብሔርም አባታችን ስለሆነ እንደዚሁ በሰጠን ትዕዛዝ ሕግ መሠረት እንድንመላለስና ደስ እንድናሰኘው ይፈልጋል፡፡ በሕጉ መሠረት የሚሄድ ልጅ ክርስቲያን ካገኘም እሱም ያከብረዋል፡፡ አመጸኛና የማይታዘዝ ልጅ ከሆነ ደግሞ መክሮ አስመክሮ እንዲስተካከል ይጠራዋል፡፡ ከተመለሰና ሥራውን ካሳመረ ይወደዋል፤ ይምረዋልም፡፡ እምቢተኛ ከሆነ ደግሞ ከቤቱና ከርስቱ ከመንግሥተ ሰማያት ያባርረዋል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ማንኛውም ክርስቲያን በእግዚአብሔር ሕግ ሲመዘን ዋጋ ቢስ እንዳይሆን ቀሎ እንዳይገኝ ሥራዎቹን ሁሉ የእግዚአብሔር ሕግ በኦሪትም ሆነ በወንጌል ምን ይላል ብሎ እየተጠነቀቀ እና ራሱን እየለካ እየመዘነ መሥራት አለበት ማለት ነው፡፡ ሥራው እግዚአብሔርን ደስ ካሰኘ ሰዎችንም ደስ ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ ደስ የማይላቸውም ሰዎች እንኳን ቢኖሩ እነሱን ለማስደሰት ሲባል የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ አይገባም

ለ. የኅሊና (የአዕምሮ) ሕግ፡-

ሰው በተፈጥሮው ክፉውን ደጉን የሚለይበት ኅሊና (አዕምሮ) ከእግዚአብሔር ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ኅሊናው ወይም አዕምሮው አውጥቶና አውርዶ የሚፈጽመው ሕግ የኅሊና ሕግ ይባላል፡፡ እግዚአብሔር ሕጉን በጽሑፍ ከመስጠቱ በፊት የነበሩ ሰዎች እነ አብርሃም ይመሩ የነበሩበት በኅሊና ሕግ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ፈጣሪያቸውን እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙ ሰውንም ሳይበድሉና ሳያሳዝኑ መልካም ሥራን የሠሩ ብዙ የቀደሙ አባቶችና እናቶች አሉ፡፡ በዚህ ሥራቸውም ተጠቅመውበታልእንጂ አልተጎዱበትም፡፡ ለምሳሌ ያህልም ፡- ሄኖክ ፣ ኖኅ ፣ አብርሃም ፣ ሣራ ፣ ይስሐቅ ፣ ርብቃ ፣ ያዕቆብ ፣ ዮሴፍና የመሳሰሉትን ቅዱሳን አባቶች ታሪክ ማንበብ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ መልካም ሥራን የሚሠራ ሰው በዚህም ምድር በሰው ዘንድ በወዲያኛውም ዓለም በመንግሥተ ሰማያት ተጠቃሚ እንደሚሆን በማወቅ ለመልካም ሥራ መነሣሣት ያስፈልጋል፡

በኅሊናችን የሚመላለሰውን ሃሳብ በመመርመር መልካም መስሎ የታየንንም ከላይ ባየነው የእግዚአብሔር ሕግ ዳግመኛ ለክተነው መዝነነው የተስማማ ሆኖ ካገኘነው ብንሠራው እንጠቀምበታለን፡፡ እዚህ ላይ መጠንቅቅ የሚገባው ሥጋችንን ደስ የሚያሰኝ ሐሳብ መልካም የሆነ የኅሊና ሕግ ነው ብለን እንዳናስተናግደው (እንዳንፈጽመው) እና እንዳንሳሳት ነው፡፡ የኅሊና ሕግ ማለት የሥጋ ፈቃድ ማለት አይደለም፡፡ ከአዕምሮ የሚመነጭ ፣ የሥጋ ፈቃድን የሚቃወመውና ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ተስማምቶ የሚኘውን ነው የኅሊና ሕግ የምንለው በሌላ አነጋገር አንድ ሰው ጉቦ ሲበላ ፣ ሚስቱ ካልሆነች ሴት ጋር ሲማግጥ ሲያመነዝር ፣ በፍርድ ሲያዳላ ፣ የሰው ገንዘብ ሲሰርቅና ተመሳሳይ ተግባራትን ሲፈጽም ከውስጡ (ከኅሊናው) ተው ልክ አይደለህም ተሳስተሃል እያለ የሚነግረው ነው የኅሊና ሕግ የሚባለው፡፡

ስለዚህ ማንኛውም ክርስቲያን ውስጡን (ኅሊናውን) እያዳመጠ መልካም የሆነውን ሥራ በቤተሰቡ ፣ በሥራ ቦታና በማኅበራዊ ሕይወት በሕብረተሰቡ መካከል ሁሉ ለመሥራት መቻል አለበት፡፡ ቢሳሳትም እንኳን ንስሐ እየገባ በቀረው ጊዜ መልካም ለመሥራት መነሳሳት ይገባዋል፡፡ ከዚሁም ጋር ከአባት ፣ ከአያት ፣ ከቅድመ አያቱ እና ከሽማግሌዎቹ በቃል የተላለፈለት መልካም ሕግ ትዕዛዝ ካለ እንደተለመደው ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር መስማማቱን አረጋግጦ ሊተገብረው ይገባል፡፡