ምዕራፍ አራት : ክርስቲያናዊ ግዴታዎች (ተግባራት)
ከላይ የጠቀስናቸ ሁሉ ክርስቲያናዊ ግዴታዎች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጅ በዚህ ንዑስ ርእስ ልናያቸው የሚገቡ ጥቂት ነጥቦችን ክርስቲያኖች ግዴታዎች በማለት አቅርበናቸዋል፡፡ ግዴታዎች ሰዎች መብቶቻቸውን ለማግኘት (ለማስከበር) የግድ ሊፈጽሟቸው የሚገቡ ተግባራትን የሚገልጡ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ጉዞው እያንዳንዱ ክርስቲያን ክርስቶስ በነፃነት የሰጠውን ሰማያዊ መብቱን (መንግሥተ ሰማያት መግባትን) ማግኘት ሊፈጽማቸው የሚገቡ ክርስቲያናዊ ግዴታዎች አሉት፡፡ ዋና ዋናዎቹን ብቻ እንደሚከተው እናያቸዋለን፡፡
ሀ. ጸሎት
ጸሎት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት መንገድ መሰላል ነው፡፡ ሰው አምላኩን በነገሮች ሁሉ ማመስገን ይጠበቅበታል፡፡ ጸሎትሰ ተናግሮ ምስለ እግዚአብሔር ልዑል ጸሎትስ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገሯት ቋንቋ ናት ስለዚህ ባለፊው እያመሰገንን በሚመጣው እየለመን ስለመግቦቱና ጠብቆቱ መመስከር ይገባዋል፡፡ እያመሰገነም ይለምነዋል፡፡ ጧት በሰላም ስላሳደረው ሲያመሰግን በሰላም እንዲያውለው ደግሞ ይማጸነዋል ይለምነዋል፡፡ በሌሎች ጉዳዮችም እንዲሁ ነው፡፡ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ነውና ይህን መሥዋዕት ከማቅረብ ወደ ኋላ እንዳንል ያስፈልጋል፡፡
ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ እሱ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ አውቀን በማንኛውም ጉዳይ ወደ እሱ መጮህ ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ከተቋረጠ ከእሱ የሚጠበቀው (የሚሰጠው) ሁሉም ነገር አብሮ መቋረጡ የግድ ነው፡፡ በተለይም ሰማያዊው ስጦታ በተቋረጠ ግንኙነት ውስጥ ይገኛል ብሎ ማሰብ ከብት ካልዋለበት ቦታ ኩበት አገኛለሁ ብሎ የመድከም ያህል ነው፡፡ ስለዚህ ዘወትር በጸሎት ከፈጣሪያችን ጋር መገናኘት ይገባናል፡፡ እንድንጸልይ ያዘዘንም እሱው ፈጣሪያችን ክርስቶስ ነው፡፡ (ማቴ.6÷5-16)
እንደ ቅዳሴ በመሳሰሉት የማኅበረ ጸሎቶች መሳተፍ ደግሞ ታላቅ ጸጋ የሚያስገኝ ስለሆነ የቅዳሴውና የመሳሰለው ሁሉ ተሳታፊ በመሆን ከካህናት ጋር አብሮ መጸለይ ይገባናል፡፡ ጸልየን ፣ አስቀድሰን ፣ ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ተባርከን ስንመጣ ለመንግሥተ ሰማያት የበለጠ ራሳችንን ማዘጋጀታችን እንደሆነ አንርሳ፡፡ የቤተሰብ ጸሎትን በጋራ በቤት ውስጥ ማድረስ ይገባል፡፡ የግል ጸሎትም እንደ አቅማችን ስንችል በቤተክርስቲያን አለበለዚያም በመኖሪያና በሥራ ቤታችን (አካባቢያችን) ማቅረብ ይገባናል፡፡
ለ. ጾም
ጾም በታወቀ (በተወሰነ) ጊዜ ሰውነታችን ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከልና መወሰን ማለት ነው፡፡ ይህ ክርስቲያናዊ ግዴታ መመሪያዎቹ ሰዎች ለአባታችን ለአዳምና ለእናታችን ለሔዋን በገነት የተሰጣቸው መመሪያ (ትዕዛዝ) ነው፡፡ ይህም ማለት ከምስጋና ጸሎት ጋር አብረው እንዲፈጽሙት የተሰጣቸው ነው እንጅ ብቻውን አይደለም፡፡ እንዲበሉት የተፈቀደላቸው የመኖሩን ያህል እንዳይበሉ የተከለከሉትም ዕፅ ነበር፡፡ ያንን መጠበቅ አቅቷቸው (ጾም አፍርሰው) ትዕዛዙን በመጣሳቸው አስቀድሞ እንደነገራቸው በሞት ተቀጥተዋል፡፡ ዛሬም ጾም ለመጾም ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች መቀጣታቸው አይቀርም፡፡
ስለዚህም የጾምን ጥቅም በማወቅ (በመረዳት) በሰው ዘንድ ለመታየት (ጾመኛ ነው ለመባል) ሳይሆን እግዚአብሔር ያዘዘውና ቅዱሳን ጾመው የተጠቀሙበት ስለሆነ እኔም ብጾመው አምላኬን ደስ አሰኝበታለሁ ብሎ መጾም ይጠቅመናል፡፡ ጾም ፡-
+ የሥጋን ምኞት ፈቃድ ለማስታገስ (ለማብረድ)፤
+ ሰውነታችን ለመልካም ሥራ የተመቻቸ እንዲሆን ለማድረግ፤
+ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ትሑት ለመሆን፤
+ መብልና መጠጥን ተጠግቶ ከሚመጣ ፈተና ለመዳንና ለመሳሰሉት የሚጠቅም የሥጋንና የነፍስን ቁስል የሚፈውስ መድኃኒት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስለ ጾም ቶሎ የሚታየንና የሚገባን ከሥጋ ፣ ከወተትና ከተዋጽኦዎቻቸው እንዲሁም ከሌሎች ምግቦች ተከልክሎ መቆየት ብቻ ነው፡፡ የጾም ትርጉም ግን ከዚህም የተሰፋና የጠለቀ ምሥጢር ያለው ነው፡፡
ጾም በውስጡ የሚይዛቸው ቁም ነገሮች ሕዋሳትን ክፉ ከሆነ ድርጊቶች (ሐሳቦች) መከልከልን የሚጨምር ነው፡፡ ይህን ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊው ሊቅ በጾመ ድጓው በሚገባ አብራርቶታል፡፡ ዓይን ክፉ ከማየት ፣ ጆሮ ክፉ ከመስማት ፣ ልብ ክፉ ከማሰብና ሕዋሳት ሁሉ እጅ ፣ እግር ፣ ምላስ ፣ አፍንጫን ሌሎችም ከክፉ ስሜቶች እንዲርቁ አሳስቧል፡፡ ጾም የሚባለው እነዚህን ሁሉ ይጨምራል፡፡
ውጪን ያዋረዱ መስለው ከእህልና ከውሃ እየከለከሉ ግፍ የሚሠሩ ፣ ድሃ የሚበድሉ ፣ ፍርድ የሚያጓድሉ ፣ ጉቦ የሚቀበሉና የርኀራኄ ሥራን ለማድረግ የማይፈልጉ ጨካኞች የሆኑ ሰዎች ጾም ከንቱ መሆኑን ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ አስተምሮናል፡፡(ኢሳ.58÷1-13) ነቢዩ ዘካርያስም እውነተኛውን ፍርድ በመፍረድ ፣ ምጽዋትንና ምሕረትን በማድረግ መበለቲቱንና ድሃ አደጉን ስደተኛውንና ችግረኛውን ባለመበደል ፣ እንዲሁም አንዱ በአንዱ ላይ ክፉ ሐሳብ ባለማሳብ የሚጾመውን ጾም እንጂ ከዚህ ውጪ የሆነውን ጾም እግዚአብሔር እንደማይቀበል ነግሮናል፡፡ (ዘካ7÷1-ፍጻሜ)
ስለዚህ ለሚጠፋ መብል አትሥሩ (ዮሐ.6÷26) ብሎ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ለዚህ ዓለም ምግብ በመሳሳት እና ጣፋጭ ምግቦች በመውደድ እንዲሁም የሥጋን ፍላጐት ሁሉ ለማሟላት በመጨነቅ ከጾም ትዕዛዝና ሥርዓት ውጪ ሆነን በሠይጣን ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅና ከፈጣሪያችን እንዳንጣላ ጾምን ከሙሉ ትርጉምና ምሥጢሩ ጋር እናዘውትር (እንጹም) ፡፡
ሐ. ስግደት
ስግደት ማለት ማጎንበስ ፣ ራስን ዝቅ ማድረግ ፣ መንበርከክ እና ግንባርን መሬት ማስነካት (በግንባር መውደቅ) እና ስሞ መመለስ ማለት ነው፡፡ ይህም ለፈጣሪ ክብር የመስጠትን ራስን ዝቅ የማድረግ የትሕትና ምልክት ነው፡፡ (ዕዝ.9÷15) ስግደት ፡-
1ኛ. የባሕርይ የአምልኮት ስግደትና
2ኛ. የጸጋ የአክበረት ስግደት በመባል በሁለት ይፈከላል
የባሕርይ (የአምልኮት) ስግደት የባሕርይ አምላክ ለሆነ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብ ሲሆን የጸጋ የአክብሮት ስግደት ደግሞ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለቅዱሳን ሁሉ የሚቀርበው ነው፡፡ ስግደቱ የባሕርይ ወይም የጸጋ መሆኑ የሚታወቀውም በሰጋጁ (ስግደቱን በሚያቀርበው ሰው) ልብ እና ልብን በሚመረምር በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው እንጂ ሌላ ምልክት የለውም፡፡
ስለዚህ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ሲሰግዱ አምላክነቱን በማሰብ ለፈጣሪ የሚቀርብ የመገዛት መገለጫ በሆነ መንገድ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ #ኑ÷ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ$ እንዲል (መዝ.94÷5) ለእርሱ የሚቀርብ ስግደት ለሌላ ለማንም ስለማይቀርብ ይህንኑ በማመንና በልብ በማሰብ የራስን ክብር ሁሉ ለሱ አምላካዊ ክብር በማስገዛት በመስጠት በፍርሃት መስገድ ይገባል፡፡ በዚሁ አንጻር ለቅዱሳን ስንሰግድ ደግሞ እግዚአብሔር በቸርነቱ ያከበራቸውና የቀደሳቸው መሆኑን በማመን መስገድ ይገባል፡፡ ከእግዚአብሔር ስለተሰጣቸው የጸጋ ቅድስናና ክብር የጸጋ (የአክብሮት) ስግደት ነው የምንሰግድላቸው፡፡ ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልአክ #እንድናከብርህ ስምህ ማነው$ ብሎ ጠይቆ ማንነቱን ካወቀ በዟላ ከሚስቱ ጋር ሰግዶለታል፡፡ (መሳ.13÷17-21) የቅዱሳንን ክብር ከምንገልጥባቸው መንገዶች አንዱ ስግደት ስለሆነ የሚገባቸውን ስግደት በመስገድ የአማላጅነታቸውንና የቃል ኪዳናቸው ተጠቃሚዎች መሆን የኛ ድርሻ ነው፡፡
መ. ምጽዋት
ምጽዋት ማለት ስጦታ ፣ ችሮታ ፣ ልግስና ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት በተለያዩ ምክንያቶች ምግብ ላጡ ምግብ ፣ ልብስ ላጡ ልብስ ፣ መጠለያ ላጡ መጠለያ እና ማናቸውንም አላስፈላጊ ነገሮች መርዳት ነው፡፡ ይህም በሚታይና በሚቆጠር (በሚሠፈር) ስጦታ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ሰው ያጣውን የሌለውን ነገር ሁሉ መስጠትን ያካትታል፡፡ ለምሳሌ፡- ምክር ለሚያስፈልጋቸው ምክር መስጠትና የዕውቀትና የሙያ እገዛ (ድጋፍ) ለሚያስፈልጋቸውም መርዳት ምጽዋት ነው፡፡
ይህ ተግባር ጾም ፣ ጸሎትንና ስግደትን የበለጠ የሚያሳምራቸው እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያስችላቸው ነው፡፡ (ኢሳ.58÷6-7፣ሆሴ6÷6) መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የምሕረት ሥራ ክርስቲያኖች ሁሉ እንዲሠሩት ደጋግሞ አዟል፡፡ (ማቴ.5÷4 ፣ማቴ.26÷11 ሉቃ.14÷12-15) ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች ምንም ልዩነት ሳናደርግ ለሰዎች ሁሉ ልንራራላቸው ይገባል፡፡ #ለድሃ የሚሰጥ አያጣም አይቸገርም ነዳያንን እንዳያይ ዓይኑን የሚጨፍን /የሚመልስ/ ግን እጅግ ይረገማል (ይቸገራል) በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን እንዳስተማረን በዚህም በዚያም በወዲያኛውም ዓለም እንዳንቸገርና እንዳይፈረድብን አዛኞችና ለመርዳት የተዘጋጀን እንሁን፡፡ (ምሳ.28÷27 ምሳ.21÷12-14መዝ.40÷1-2) በፍርድ ቀንም ጻድቃን እንዲፈረድላቸው ኃጥአንም እንዲፈረድባቸው የሚያደርገው መሠረታዊ ጉዳይ ምጽዋትን መሠረት ያደረገ ሆኖ ይገኛል፡፡ (ማቴ.25÷31-ፍጻ ፣ መዝ.111÷9፣2ቆሮ 9÷6 ፍጻ) በዚህ መሠረት ምጽዋት መስጠት ክርስቲያኖች ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት በሚያደጉት ጉዞ አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማወቅ በእግዚአብሔር፣ በእመቤታችን በቅዱሳንም ስም መመጽወት ይገባናል፡፡
ሠ. አሥራት
ከአሥር እጅ አንዱን (አሥራት) ለቤተክርስቲያን መስጠትም የታዘዘ ሕግ መሆኑን ማወቅና ዘጠኙን እጅ ለራስ አስቀርቶ ከአሥሩ አንዱን ከመቶው አሥሩን ለእግዚአብሔር መስጠት ተገቢ ነው ይኽውም፡-
ሀ. በረከተ ሥጋን ለማግኘት (ምሳ.3÷9-10)
ለ. የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ለመፈጸም (ዘዳ.14÷22)
ሐ. ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን መፈጸሚያ
- ዘይት (ሰም) መብራት ዘጸ.27÷20
- እህል ለቁርባን (ስንዴ) ዘሌ.2÷1-3
- ዕጣን ለማዕጠንት (ዘጸ.30÷36) እና የመሳሰሉት
መ. ካናትን አገልጋዮች ለመርዳት
ሠ. ቤተክርስቲያንን ተጠግተው ለሚኖሩ ችግረኞች መርጃ እንዲሁም ለመሳሰሉት ተግባራት ሰው ጥሮ ግሮ ካገኘው ገንዘብም ሆነ እህል ወይም እንስሳ ለእግዚአብሔር አሥራቱን እና በኩራቱን ለቤተክርስቲያን መስጠት አለበት፡፡
ከዚሁ ጋር ወደ ተቀደሱ ቦታዎች (አብያተ ክርስቲያናት) አቅም በፈቀደ መጠን ከስጦታ ጋር በግልም ሆነ በጋራ እየተጓዙ መሳለምና በረከተ ሥጋ በከረተ ነፍስ ለማግኘት ይገባል፡፡ ይህም በሃይማኖትና በምግባር የሚያጠነክር ስለሆነ መለማመድና መተግበር ጥሩ ነው፡፡
ታላላቅና ንዑሳን በዓላትን እንደ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ ማክበር የማይረሣ ጉዳይ ነው፡፡ በበዓላት ቀን ከሥጋዊ ሥራ ተለይቶ እየዘመሩ ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እየተማሩ ፣ እየቆረቡ ፣ እየጸለዩ ፣ እየሰገዱ ፣ እየመጸወቱና መልካም ሥራ አየሠሩ በመዋል ሥርዓቱ ሲጠናቀቅ መመለስ ይገባል፡፡
ቤተክርስቲያን ቅዳሜና እሑድን (ሰንበትን) ጨምሮ በርካታ የበዓል ቀናት ቢኖሩዋትም በወር ውስጥ የቅዱስ ሚካኤል በዓል በ12 ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓል በ21 እና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ በ29 ቀን ማንኛውም ክርስቲያን እንዲያከብራቸው ታዛለች፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ በዓመቱ ውስጥ የሚከበሩ ዋና ዋናዎቹ በዓላትም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ብሥራት (ፅንሰት)፡- መጋቢት 29 ቀን ቅዱስ ገብርኤል እግዚአብሔር ከእሷ እንደሚወለድ ለድንግል ማርያም የምሥራች የነገረበት ቀን ነው፡፡
2. ልደት፡- እግዚአብሔር ከእመቤታችን ሰው ሆኖ የተወለደበት ቀን ነው፡፡ በዓሉም ታህሣሥ 29 ቀን ይውላል፤
3. ጥምቀት፡- ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀበት ቀን ነው፡፡ በዓሉም ጥር 11 ቀን ይውላል፤
4. ደብረ ታቦር፡- ክርስቶስ የመለኮቱን ብርሃን አምላክነቱን የገለጠበት ቀን ነው፡፡ በዓሉም ነሐሴ 13 ቀን ይውላል፤
5. ሆሳዕና፡- ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ (ኢየሩሳሌም) የገባበት ቀን ነው፡፡ በዓሉም ትንሣኤ 1 ሳምንት ሲቀረው በሚውለው እሑድ ቀን ይውላል፤
6. ስቅለት፡- ክርስቶስ ስለ ዓለም (ስለ እኛ) ድኅነት በቀራንዮ አደባባይ የተሰቀለበት መታሰቢያ በዓል ነው፡፡ ከትንሣኤ በፊት ያለው ዓርብ ላይ ይውላል፤
7. ትንሣኤ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን የተነሣበት ቀን ነው፤
8. ዕርገት፡- ክርስቶስ ከሙታን በተነሣ በአርባኛው ቀን የሚውል ወደ ሰማይ የወጣበት በዓል ነው፡፡
9. ጰራቅሊጦስ፡- በተነሣ በሃምሳኛው ቀን ባረገ በአስረኛው ቀን መድኃኔዓለም ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለደቀመዛሙርቱ የላከበት ቀን ነው፡፡
እነዚህና ሌሎችም በዓላት በመማርና ከቅዱሳት መጻሕፍት አንብቦ በአግባቡ በመረዳት ከላይ እንደገለጽነው በመልካምና መንፈሳዊ ሥራዎች ማክበር አቅም በፈቀደ መጠን የርኀራሄ ሥራን በመሥራት ራስን ለሰማያዊው መንግሥት ማዘጋጀት የክርስቲያኖች ሁሉ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የትና እንዴት ይፈጸማል?
በዚህ ዐቢይ ርእስ ስር ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ተራ በተራ ባጭር እናያቸዋለን፡
ሀ. የት ይፈጸማሉ?
በዝርዝር ያየናቸውን ክርስቲያናዊ ተግባራት ሁሉ የምንፈጽማቸው በቅድስናው ሥፍራ (በቤተክርስቲያን) ብቻ የሚመስላቸው ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ዳሩ ግን የክርስትና ሃይማኖት ማዕከላዊ (ዋነኛ) ቦታ ቤተክርስቲያን ትሁን እንጂ ክርስትያናዊ ሥነ ምግባራት ግን በሁሉም ቦታ እንደ አስፈላጊነቱ ሊፈጸሙ ይገባቸዋል፡፡ ስለዚህም ክርስቲያዊ ሥነ ምግባራትን ክርስቲያን የሆነ ሰው
- በመኖሪያ ቤት (በቤተሰቡ መካከል)
- በመኖሪያ አካባቢ
- በሥራ አካባቢ (በመሥሪያ ቤት)
- በተለያዩ ማኅበራት
- በሠርግ (ጋብቻ) ቦታ
- በሐዘን (ለቅሶ) ቤትና በመሳሰሉት ሁሉ በመፈጸም ታማኝነቱን መግለጥ (ማሳየት) ይገባዋል
ለ. እንዴት ይፈጸማሉ?
ለዚህ መልስ የሚሆነውን በዝርዝር ለማየት በጣም ስለሚበዛ በአጭሩ እናየዋለን፡፡ ለእያንዳንዳቸው የየራሳቸው የሆነ አፈጻጻም አላቸው፡፡ ለምሳሌ፡- የጾም ፣ የጸሎት ወዘት ቀደም ባሉት ገጾች የአንዳንዶቹ አፈጻጸም አብሮ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ አሁን በዚህ ክፍል ጥቅም (የጋራ) የሆነውን አፈጻጸም ነው የምንመለከተው፡፡
- እግዚአብሔርን በመፍራትና በመውደድ፣
- የመንግሥተ ሰማያትን ጣዕም በማስታወስ፣
- የገሃነመ እሳትን ስቃይ በማሰብ፣
- የዚችን ዓለም ኃላፊነትና ጠፊነት ባለመርሳት፣
- በትሕትናና በታማኝነት፣
- በትዕግሥት በታታሪነት፣
- ራስን ለሰማዕትነት በማዘጋጀት፣
- በመንፈሳዊ ቅንዓት፣
- የሰይጣንን ክፋትና የእግዚአብሔርን ቸርነት በማነጻጻር፣
- ተስፋ ባለመቁረጥና በመሳሰሉት መንፈሳዊ ተግባራት በመታጀብ (በመታገዝ) ሁሉንም ለእግዚአብሔር ክብር ብለን እንድናደርጋቸው ቤተክርስቲያን አስተምራናለች፡፡ ስለዚህ እኛም ከቅድስት ቤተክርስቲያን ጀምሮ ክርስትያናዊ ሥነ ምግባራትን በምንከውንባቸው (በምንፈጽማቸው) ቦታዎች ሁሉ ከላይ የተገለጹትን በአዕምሮአችን እያወጣንና እያወረድን በሕይወታችንም (በኑሮአችን) ለመግለጥ እየታገልን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡
የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አስፈላጊነት ለምንድን ነው?
በየርእሱ ስር መጠነኛ ጥቅሙም አብሮ ተገልጿል፡፡ ዋና ዋናዎቹን ደግመን ጥቅል በሆነ መልኩ ባጭሩ እንደሚከተለው እናያለን፡-
- እምነት ያለ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ብቻውን የሞተ ስለሆነና ምንም ጥቅም ስለማይሰጥ፤ (ያዕ.2÷14-ፍጻ) የሰዎች ሩጫ ከንቱ እንዳይሆን፡፡
- ሥርዓት አልበኝነት እዳይስፋፋ (ሰዎች ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ውጪ እንዳይሆኑ)፤
- የማኅበራዊ ሕይወት ቀውስ እንዳይስፋፋ፣
- ትዳር እንዳይፈርስና ቤተሰብ እንዳይበተን፣
- የተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች እንዳይከሰቱ፣
- ክርስቲያኖች ከቤተክርስቲያን እቅፍ እንዳይወጡ፣
- መተሳሰብና መረዳዳት ጠፍቶ ግለኝነት እንዳይነግሥ፣
- ሠላምና አንድነት ጠፍቶ ዘረኝነትና መለያየት እንዳይሰፍን ያደርጋሉ የሚሉትንና የመሳሰሉትን ዋና ዋናዎቹ ጥቅሞች ሲሆኑ ዋናውና መሠረታዊው ጥቅሙ ሰዎች ሁሉ የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ባለቤት ሆነው የርስተ መንግሥተ ሰማያት ወራሾች እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥቅሞች የተዘረዘሩ በመሆናቸው እና ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም በሥጋ እንዳንጎዳና በወዲያኛውም ዓለም ነፍሳችንን ለማዳን እንችል ዘንድ በሃይማኖታችን ጸንተን (ጠንክረን) ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራትን ልንተገብራቸው ይገባል እንላለን፡፡
ማጠቃለያ
አባቶቻችን በተለያዩ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳስተማሩን ሃይማኖት መሠረት ሲሆን ሕንፃው (ግንቡ) እና ጣሪያው ደግሞ ሥነ ምግባር ነው፡፡ አንድ ቤት ጥሩ መሠረት ኖሮት ግድግዳና ጣሪያ ከሌለው ቤት አይባልም፡፡ ምክንያቱም ከሌሊት ብርድና ከቀን የፀሐይ ግለት ሊያድን አይችልምና፡፡ ምግባር የሌለውም ሃይማኖት እንዲሁ ከሰይጣን ፈተና ከኃጢአት ወጥመድና ከሲኦል (ገሃነመ እሳት) ሊያድን በዚህም ዓለም በረከተ ሥጋን ሊያስገኝ አይችልም፡፡
ግድግዳውና ጣሪያው ያማረ ሆኖ መሠረቱ ያልጸና ቤትም ከነፋስ ፣ ከኃይለኛ ዝናብ ፣ ከጎርፍና ከማዕበል ሊያድንና የሚኖርበትን ሊያድን አይችልም፤ ጥሩ ሥነምግባር ይዘው ትክክለኛ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከሰይጣን የተንኮል ነፋስ ፣ ከኃጢአትም ማዕበል፣ ከፈቃደ ሥጋም ጎርፍ በተነሳባቸው ጊዜ ጸንተው ሊቋቋሙት አይችሉም፡፡ መልካም ምግባራቸው ሁሉ ቢደማመር መሠረት (ሃይማኖት) ሆኖ ከጥፋት ሊያድናቸው አይችልም፡፡ (ማቴ.7÷24-28)
ስለዚህ ሁለቱንም ማለትም የቀናች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትንና የታዘዙትን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት አጣጥሞ መያዝና በመተግበር ራስን ከሥጋዊና መንፈሳዊ (ምድራዊና ሰማያዊ) ጥፋት ማዳን (ማትረፍ) ይጠበቅብናል፡፡