ክፍለ ትምህርት ፫ : ንዋየ ቅድሣት
ታቦት፡- ታቦት ማለት እግዚአብሄር አስርቱ ትዕዛዛትን በእጁ ፅፎ ያስቀመጠበትና ለሙሴ የሰጠው ቅዱስ ንዋይ ነው፡፡ በቤተክርስቲያንም ፃህሉን እና ፅዋውን በዚህ ላይ በማስቀመጥ መስዋዕቱን እናከብርበታለን፡፡ ይህም ማለት ቅዱስ ስጋውና ክቡር ደሙ የሚዘጋጀው በዚህ ላይ ነው፡፡ ዘጸ 31 ፥ 18 / ዘዳ 20
መስቀል፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶ በቀራንዩ የተሰቀለበት ሰይጣን ድል የተነሳበት የመዳናችን አርማ ነው፡፡ መስቀል ምዕመናንን እና ንዋየ ቅዱሣትን ለመባረክ ያገለግላል፡፡ የተለያዩ የመስቀል አይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ፦
የእጅ መስቀል፡- ይህ የክህነት ማዕረግ ያላቸው።
-አባቶች ብቻ የሚይዙት ሲሆን ምዕመናንን ለመባረክ ይጠቀሙበታል፡፡
የመፆር መስቀል፡- ይህ ዲያቆናት በቅዳሴ ጊዜ የሚሠብኩበት ሲሆን በመጠኑም ከፍ ያለ ነው፡፡
መብራት፡- መቅረዝ የሻማ ማብሪያ ነው፡፡ ቀንዲል ደግሞ ሻማ ወይም የዘይት መብራት ነው፡፡ የመቅረዙ አገልግሎት ለሻማ ማብሪያነት ሲሆን ቀንዲሉ ደግሞ ቅዱሣት መፃህፍት፣ መልዕክታት፣ ወንጌል ሲነበቡ ይበራሉ።
አልባሳት፡- በቤተክርስቲያን የአገልግሎት ልብስ እንደ ግለሠቡ የስልጣን ሁኔታ ይለያያል፡፡ የመነኮሣት ልብስ፣ ከካህናት ልብስ የካህናትና ዲያቆናት ይለያል።
፦ የጳጳሳት ልብስ ፣ የመነኮሳት ልብስ ፣የካህናት ልብስ ፣ የዲያቆናት ልብስ
ማኅፈድ፡- የጨርቅ መሸፈኛ ነው፡፡ ታቦቱን እና ጻህሉን ለመሸፈን ያገለግላል፡፡ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ፤ ከሠሜን ወደ ደቡብ፤ ከመስዕ/ ከሰሜን ምሥራቅ /ወደ አዜብ /ደቡብ ምዕራብ/ ሆኖ ይለበሳል፡፡
መንጦላዕት፡- በሶስቱም የመቅደስ በር የሚጋረዱ መጋረጃዎች ናቸው፡፡ ቀለማቸውም ቀይ ነው፡፡
መጎናፀፊያ፡- ይህ በቅዳሴ ጊዜ መንበሩ (መሠዊያው) የሚለብሰው ሲሆን፤ ታቦት በሚወጣበት ጊዜ የሚጎናፀፈው ነው፡፡
መንበር፡- የጽላቱ (የታቦቱ) መቀመጫ ዙፋን ነው፡፡ ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙ የሚዘጋጀውም በዚህ ላይ ሆኖ ነው፡፡ ካህን ያልሆነ ሠው መንበሩን መንካት የማይችል ሲሆን መንበሩ እና ታቦቱ ወዳለበት ክፍል (መቅደስ) መግባት የሚችሉት ዲያቆናት፣ካህናት፣ኤጲስ ቆጳሳት ጳጳሳት ናቸው፡፡
ጻህል፡- የቅዱስ ሥጋው ማስቀመጫና ማክበሪያ ነው፡፡ ከወርቅና ከብር፣ ከነሀስና ከብረት የሚሠራ ሲሆን የተለየ ቅርፅና የተለየም ምልክት ያለው ነው፡፡
ፅዋ፡- የክርስቶስ ክቡር ደም የሚቀርብበት ነው፡፡ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከመዳብ፣ከነሀስ፣ ከብረት የሚሠራ ነው፡፡
ዕርፈ መስቀል፡- ማንኪያ ዓይነት ሆኖ ጫፉ ላይ መስቀል ያለው ነው፡፡ ፅዋው ከተሠራበት ቁስ የሚሠራ ሲሆን አገልግሎቱም የክርስቶስን አማናዊ ደም ለመቀበል የሚያገለግል ነው፡፡
ዐውድ፡- በድርገት ጊዜ ጻህል የሚቀመጥበት ሰፋ ያለ ጻህል ነው፡፡ ሥጋው እንዳይነጥብ መጠበቂያ ነው፡፡ የሚሠራው ከብረት፣ከነሀስ፣ከእንጨት ነው፡፡
ጽንሃ፡- የዕጣን ማሣረጊያ ነው፡፡ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከብረት፣ ይሠራል፡፡ ይህን ንዋይ ምዕመናን መጠቀም (መንካት) አይገባቸውም፡፡ ዲያቆናት ይይዙታል ይነኩታል ነገር ግን ካህናት የሚይዙበት ቦታ ላይ መያዝ አይችሉም(አያጥኑም)።
መሶበ ወርቅ፡- የአነስተኛ መሶብ ቅርፅ አለው፡፡ አገልግሎቱም ቅዱስ ቁርባኑን ከቤተልሄም ወደ ቤተ-መቅደስ ለማምጣት ነው፡፡ በሚመጣበት ጊዜም በመጎናፀፊያ ተሸፍኖ ነው፡፡
ሙዳይ፡- ለማዕጠንት አገልግሎት የሚያስፈልግ ዕጣን የሚቀመጥበት ነው፡፡
ቃጭል፡- በቅዳሴ ጊዜ የሚቃጨልና ድምፅ የሚሠጥ ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ አራት ጊዜ ቃጭል ይደወላል፡፡
1.ቅዳሴ ሲገባ
2.ፃኡ ንዑሰ ክርስቲያን ሲባል
3.በእግዚኦታ ጊዜ
4.ድርገት በሚወርድበት ጊዜ
ጥላ፡- ይህ ከተለመደው ጥላ የሚለየው የተለያየ አንፀባራቂ ቀለም ባላቸው ጨርቆች መሠራቱ ነው፡፡ አገልግሎቱ በቅዳሴ ጊዜ ምስባክ ሲሰበክ እና ወንጌል ሲነበብ ይዘረጋል፡፡ ንግስ በሚሆንበት እለትም ከፊት እና ከኋላ በታቦቱ ዙሪያ ይዘረጋል፡፡
ድባብ፦ በመጠኑ ከጥላ ሠፋ ያለ ሲሆን በንግስ በዓላት ቀን በታቦቱ ላይ ይዘረጋል፡፡ ይዞ በታቦቱ አጠገብ መቆም የሚችለው ካህን ብቻ ነው፡፡
ከበሮ፡- ከበሮ ከእንጨት እና ከበሬ ቆዳ ተሠርቶ በጨርቅ የሚሸፈን ከፍተኛ ድምፅ የሚሠጥ መሣሪያ ነው፡፡ ይሁንና ከነሃስ እና ከብርም ተሠርቶ ቆዳው ሊወጠር ይችላል፡፡ ሁለት ጎኖች ሲኖሩት በእነዚህ ሁለት ጎኖች የሚወጣው ድምፅ የተለያየ ነው፡፡ አገልግሎቱም በማህሌት ጊዜ ለመዝሙር ማጀቢያነት ነው፡፡
ፅናፅል፡- ከነሃስ ወይም ከብር ሊሠራ ይችላል፡፡ ድምፅ የሚሠጡት በውስጡ ያሉት 5 ወይም 7 የሚሆኑ የነሀስ ወይም የብር ቁርጥራጮች ናቸው፡፡ አገልግሎቱም በእጅ ተይዞ ወደ ላይ እና ወደታች በማወዛወዝ መዝሙሩን ማጀብ ነው፡፡
መቋሚያ፡- ከእንጨት ከነሀስ ከብር ይሰራል፡፡ አገልግሎቱም በመዝሙር ጊዜ በትከሻ በመሸከም ወይም በእጅ በማወዛወዝ መዝሙሩን ይጅባል፡፡ ለመደገፊያነትም ያገለግላል፡፡