Advertisement Image

ትምህርተ ሃይማኖት

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የትምህርተ ሃይማኖት ምዕራፎች

ምዕራፍ አንድ ፡ የትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ

፩.፩ የሃይማኖት ትርጉም
ሃይማኖት በአንድ ቃል ወይም ብያኔ እንዲህ ነው ብሎማስቀመጥ አይቻልም፡፡ ይኸውም ሊቃውንት በየተረዱበት መንገድ በልዩ ልዩ አገላለጽ አስቀምጠውታልና ነው፡፡

የሃይማኖትን ትርጉም በመጠኑ ለመቃኘት በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው መዝገበ ቃላታዊ ፍቺ ሲሆን ሁለተኛውም ምስጢራዊ ፍቺ ነው፡፡

፩. መዝገበ ቃላታዊ ፍቺ
መዝገበ ቃላታዊ ፍቺውን ስንመለከት ለምሳሌ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ሃይማኖትን በተለያዩ ቃላት ጠርቶታል ከነዚህም መካከል፡- ሃይማኖት ፣ ሀይመነ ፣ አሚን ፣ እምነት የሚሉት ይገኙበታል ፤ የቃላቱም ትርጉም ፡-

፩.፩. ሃይማኖት ማለት፡- ማመን፣ መታመን፣ እምነት፣ ጽኑ ተስፋ፣ የአምልኮ በሕል፣ በልብ በረቂቅ የሚሣል ማለት ነው፣ እንዲሁም የሚያምኑት የሚያሳምኑት ነው፡፡
፩.፪ ሃይመነ ማለት ፡- አመነ ታመነ በሚል ይተረጎማል፡፡
፩.፫ አሚን ማለት፡-ማመን፣መቀበል፣ተስፋ ማድረግ፣አለመጠራጠር፣መናዘዝ እውነት መናገር፣መመስከር በማለት ገልጦታል፡፡
፩.፬ እምነት ማለት ፡- በቁሙ በመውሰድ ሃይማኖት ፣ማመን ፣መተማመን ማለት እንደሆነ ብርም ሰፍሮ ይገኛል፡፡

፪. ምስጢራዊ (ጽንሰ ሃሳባዊ ) (ሃማኖታዊ) ፍቺ

፪.፩ ሃይማኖት ማለት፡- በባሕርይው የማይታይና የማዳሰስ አምላክ አንድ እግዚአብሔር መኖሩን፣ እርሱም የዓለም ፈጣሪ ሠራኢ ዓለማት፣ መጋቢ ፍጡራን፣ አዳኝ መሆኑን እና በባህርየ መለኮቱ፣ በልዩ ሶስትነቱ እና አንድነቱ፣ በምልአተ አካሉ… በፍፁም እምነት በኅሊና እና በልቦና ተገንዝቦ ያለመጠራጠር እውነት ነው፣ እርግጥ ነው ብሎ መቀበል ማለት ነው፡፡ዕብ11÷1-3፣ ሮሜ 10÷10
፪.፪ ሃይማኖት ማለት፡- ከእግዚአብሔር ጋር ሚያገናኝ ረቂቅ መንገድ (ፍኖተ እግዚአብሔር) ማለት ነው፡፡ ኤር 6÷16
፪.፫ ሃይማኖት ማለት፡- ተስፋ የምናደርገውን የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው፡፡ ዕብ 11÷1

በተጨማሪም የሚከተሉት ነጥቦች የሃይማኖትን ምንነት የሚገልጡ የሚያብራሩ ናቸው፡፡

ሀ. ሃይማኖት መሠረት ነው፡-

‹‹አሚንሰ መሠረት ይእቴ ወካልኣኒሃ ሕንጻ ወንድቅ እሙንቱ - እምነት መሠረት ናት ሌሎቹ ግን ሕንፃና ግንብ ናቸው›› (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

ቅዱስ ዮሐንሰ አፈወርቅ በሕንፃና በግንብ መስሎ የተናገራቸውና ሌሎቹ ብሎ የጠቀሳቸው ምግባርንና ትሩፋትን ነው፡፡ እምነት/ሃይማኖት ግን የእነዚህ መሠረት ናት፡፡ ይህም ሕንፃን ከመገንባት በፊት ሀልዎተ ፈጣሪን /የፈጣሪን መኖር/ ማመንና በሚሰሩት ምግባር ትሩፋት የሚያምኑት ፈጣሪ የማያልፍ የማይጠፋ ዋጋን እንደሚሰጥ በእምነት መቀበል ይቀድማል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ እንዳለ፡-

‹‹ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው አስቀድሞ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጣቸው ሊያምን ይገባዋል፡፡››/ዕብ ፲፩÷፮/

በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፮ ÷ ፲፮ ላይ ዐለት በተባለው በቅዱስ ጴጥሮስ እምነትና ምሥክርነት ማመን (ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ መሆኑን ማመን) የሁሉ መሠረት እንደሆነና ከዚህ በኋላ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን በፈተና ጸንቶ ለዋጋ የሚያበቃ ሥራን መሥራት እንደሚገባ እንደሚከተለው አብራርቷል፡፡

‹‹መሠረቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ላይ በወርቅና በብር በከበረ ድንጋይ በእንጨት በሣርና በአገዳ የሚያንጽ ቢኖርም የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ እሳትም በፈተነው ጊዜ ቀኑ ይገልጠዋል፤ የእያንዳንዱም ሥራ እሳት ይፈትነዋል፡፡ ሥራው ጸንቶ የተገኘለት ሰው ዋጋውን የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ ሥራው የተቃጠለበት ግን ዋጋውን ያጣል፡፡››/፩ኛ ቆሮ፫÷፲፩-፲፭/

ለ. ሃይማኖት ከዕውቀት በላይ ነው

ሰው በስሜት ሕዋሳቱ መርምሮ ያውቃል፡፡ ሻካራውን ከለስላሳው በእጁ ዳስሶ፣ ጨለማውን ከብሩሁ በዓይኑ አይቶ፣ ጣፋጩን ከመራራው በምላሱ ቀምሶ፣ መልካም መዓዛ ያለውን ከሌለው በአፍንጫው አሽትቶ ለይቶ ያውቃል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በርህቀት /ከእርሱ በመራቅ/ እና በርቀት /በረቂቅነት/ ያሉትን በስሜት ሕዋሳቱ መርምሮ በእውቀት ሊደርስባቸው አይችልም፡፡ ይህም ሰው ለእውቀቱ ድንበር ለአእምሮው ወሰን እንዳለ ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ወሰን የሌለው መንፈስ እንደመሆኑ ሰው በስሜት ሕዋሳቱ ሊረዳው ሊደርስበትም እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ወሰን ያለው ሰው ወሰን የሌለውን እግዚአብሔርን የሚያውቀውና ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኘው በእምነት ከሆነ እምነት /ሃይማኖት/ ከእውቀት በላይ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ ማመን ከማወቅ በፊት እንደሆነ የመሰከረው፡፡
‹‹እኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ እንደሆነህ አምነናል፤ አውቀናልም›› /ዮሐ. ፮.፥፷፱/

ሐ. ሃይማኖት ተስፋ የምናደርገውን የሚያስረግጥ ነው

‹‹እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት፡፡›› /ዕብ. ፲፩÷፩/ ሰው በረቂቅነቱ ምክንያት በዓይነ ሥጋ የማያየውን የእግዚአብሔርን ህልውና የሚረዳው በእምነት ነው፡፡ እንደዚሁም ከእርሱ በመራቋ ምክንያት የማያያትን ነገር ግን ተስፋ የሚያደርጋትን መንግስተ ሰማያትን በእውነት ለባልዋ እንደ አጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ እንዳለች የሚያረጋግጠው በእምነት ነው፡፡ /ራዕ. ፳፩፥፪/:: ስለዚህ እምነት የማናየውን የምታስረዳ ተስፋ የምናደርገውን የምታስረግጥ ናት፡፡

፩.፪ የሚያምኑ ፍጥረታትና የሃይማኖት አጀማመር የሚያምኑ ፍጥረታት
እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት እያንዳንዱ ቢቆጠር ፍጡር ተናግሮ አይፈጽመውም፡፡ ነገር ግን ብዙውን አንድ እያሉ በየወገኑ ቢቆጥሩት 22 ፍጥረታት ይሆናል፡፡ ከእነዚህም ፍጥረታት መካከል ሁለቱ ማለትም ሰውና መላእክት የእግዚአብሔርን ስም ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ሲፈጠሩ ቀሪዎቹ ግን ለአንክሮ፣ ለተዘክሮ፣ ለምግበ ሥጋ፣ ለምግበ ነፍስ እንዲሆኑ ተፈጥረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከ22 ፍጥረታት ሃይማኖት የሚያስፈልጋቸው ሰውና መላእክት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት፡-

1. ሰውና መላእክት ሃይማኖት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ዕውቀት ስላላቸው 2. ሕያዋን ስለሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት እንደሌሎቹ ፍጥረታት ፈርሰው በስብሰው የማይቀሩ፣ ለዓላማ የተፈጠሩ በመሆናቸው ከፈጣሪያቸው ጋር እንዳይጣሉና ከክብሩ እንዳይለዩ ሃይማኖትን መያዝ ምግባርን ምሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

የሃይማኖት አጀማመር
ሃይማኖት ከማን ለማን እንዴት ተሰጠች
ሃይማኖት ከእግዚአብሔር አክብሮ ለፈጠራቸው መላእክት እና ለሰው ባለማዳላት የተሰጠ ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ ቅ/ ጳውሎስ ይህን ሲያመለክት በአፌ 2÷8 ‹‹ፀጋው በእምነት አድኖአችኋልና ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለምና›› በማለት ገልጾታል ፡፡

ከፍጥረታት ውስጥ ሃይማኖት ያላቸው መላእክት እና ሰዎች እንዲሁም አጋንንት ብቻ ናቸው፡፡ የአጋንንት እምነት ግን በስራ የማይገለጽ በመሆኑ ለድኅነት አያበቃቸውም ፡ስለ አጋንንት እምነትም ሐዋርያው ቅ/ያእቆብ በያዕ2÷19 ‹‹አጋንንት ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል›› በማለት ገልጾታል፡፡

፩. የሃይማኖት መሰጠት በዓለመ መላእክት
እግዚአብሔር መላእክት በእለተ እሁድ ልባውያን ነባብያን እና ኅያዋን አድርጎ ከሙሉ ነጻ ፈቃድ ጋር ከፈጠራቸው በኋላ ፈልገው ያግኙኝ በማለት ተሰወራቸው ፤ (ይኸውም ሃይማኖታቸው ይገለጥ ዘንድ ነው ፡፡) መላእክቱም የፈጠረን ማነው፣ ከየት መጣን ፣ በማለት እርስ በእርስ ተጠያየቁ፤ ይህች ሰዓት የመላእክትን አስተዋይነት እና አዋቂነት የሚፈትን እውነተኛ እምነታቸው በተግባር የምትገለጽበት ሠዐት ነበረች፡፡

በዚህችም ሠዐት ከመቶው ነገድ የአንዱ ነገድ አለቃ የነበረው ሳጥናኤል የመላእክትን መታወክ ባየ ጊዜ የፈጠርኳችሁ እኔ ነኝ በማለት የመጀመሪያውን ክህደት ንግግርን አደረገ በዚህም የሃሰት አባትነቱን ገለጠ፡፡ሳጥናኤል ቢያንስ ቢያንስ ራሱን እንኳን እንዳልፈጠረ መረዳት ይችል ነበር በዚህ እንኳን ሊላ አስገኚ ፈጣሪ አምላክ እንዳለ መረዳት በቻለ ነበር እርሱ ግን ክብርን ፈልጎ ክህደትን አመነጨ፡፡

የሣጥናኤል ንግግርም በመላእክት ዘንድ የበለጠ መታወክን ፈጠረ ፤በእርሱ ነገድ ስር የነበረው ከአንዱ ነገድ ገሚሶቹ አዎ አንተ ፈጠርከን ሲሉ ገሚሶቹ ፈጥሮናል ወይስ አልፈጠረንም የሚል ጥርጥር ውስጥ ወደቁ ገሚሶቹም አንተ ሳትሆን እኛ ፈጠርንህ አሉ፡፡ በዚህ ሰዐት የሃይማኖት አርበኛ ቅ/ገብርኤል እነርሱን የፈጠረ አምላክ እንዳለ በማመን እና በመረዳት ‹‹ ንቁም በበኅላዌነ እስከንረክቦ ለአምላክነ / የፈጠረን አምላካችን እስኪገለጥልን ድረስ ፀንተን እንቁም፡፡›› በማለት የሃይማኖት ቃል በመናገር የተቀሩት ዘጠና ዘጠኙ ነገድ ባሉበት እንዲፀኑ ምክንያት ሆነ፡፡ በዚህም ጊዜ ሃይማኖት (እግዚአብሔር አለ )የሚለው እምነት ታወቀ ፤ ሃይማኖት በመላእክት ዘንድ ተገለጠች፡፡

የሚታመን ፈጣሪ እና አማንያን (የሚያምኑ) ፍጡራን ተለዩ፤ ያመኑትም መላእክት እግዚአብሔርን ሳያዩት ከምንም በላይ በባሕሪው ፍፁም ረቂቅ እና ጥልቅ የሆነ አምላክ እንደሆነ በእምነት ተቀበሉት፡፡ ይህንን እምነት እና ጽናታቸውን የተመለከተ እግዚአብሔር ራሱን ለመላእክቱ ገለጠላቸው፡፡ ያመኑት ቅዱሳን መላእክት ተባሉ ያላመኑትም ርኩሳን መላእክት ተብለው ከሃሰት አባታቸው ከሳጥናኤል ጋር ወደ እንጦሮጦስ ወርደትና ጉስቁልናል ተላብሰው ወረዱ፡፡

ሃይማኖት በእግዚአብሔር ማመን መታመን ስለሆነ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ያመኑ የታመኑ ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ ይህም ሃይማኖት የተጀመረው በዓለመ መላእክት በመጀመሪያዋ የሥነ-ፍጥረት ዕለት የመጀመሪያዎቹ አማኝ ፍጥረታት /መላእክት/ በተፈጠሩባት ጊዜ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም እንዴት እንደሆነ ሥነ-ፍጥረት በማለው በሦስተኛው ምዕራፍ የምናየው ይሆናል፡፡

፪. ለሰው ልጆች የሃይማኖት መሠጠት
በሥላሴ በአርያው እና በአምሳሉ አዳምን በፈጠረው ጊዜ የህይወትን እስትንፋስንም እፍ ሲልበት በመንፈሱ አማካኝነት ሃይማኖትን ወይም እግዚአብሔርን የማመን ፀጋ አብሮ ሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም እና ለሄዋን የሰጠው ሃይማኖት በመላእክት ዘንድ ያለችውን ነቅ የሌለባት አንዲቷን ሃይማኖት ናት፡፡

መጽሐፍ ቅዱስም እግዚአብሔር እርሱን የማመን ዝንባሌ (ሃይማኖትን) በውስጣችን እንዳስቀመጠ ይህም የእርሱ ስጦታ እንደሆነ የሐ 17÷25- 27 ‹‹እርሱም (እግዚአብሔር) ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳችም እንደሚጎድለው በሰው ልጅ አይገለገልም፡፡ ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድርም ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰው ወገኖችን ሁሉ ከአንድ ፈጠረ ፡፡›› በማለት ይመሰክርልናል፡፡

በጥቅሱ ውስጥ ፡- ‹‹እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ›› እና ‹‹ የሰው ወገኖችን ከአንድ ፈጠረ ›› የሚለው ሐረግ ሰው ሃይማኖታዊ ፍላጎት ያለው መሆኑን ይኸውም ‹‹ከአንድ ፈጠረ›› በማለቱ ሃይማኖት ተፈጥሮአዊ መሆኑን ያሳያል፡፡

በሃይማኖት መንገድነት ሰው እግዚአብሔርን ይፈልጋል እግዚአብሔርም ወደ ሰው ይቀርባል ራሱንም ይገልጥለታል፡፡ አዳም ኣባታችን ሕገ እግዚአብሔርን ጥብቆ በገነት ለሰባት አመታት በሃይማኖት ከቆየ በኋላ በዲያብሎስ አማካኝነት የቀረበለትን ፈታና በወደቀ ጊዚ እግዚአብሔርን ፈርቶ በገነት ዛፍ ሥር ከሄዋን ጋር ሲሸሸግ እግዚአብሔር አምላክ ማዕምሬ ህቡአት (የተሰወረውን የሚያውቅ ) ሁኖ ሳለ አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ በንስሃ ሊመልሰው አስቦ በሰኮና ብእሲ ዳናውን እያሰማ (የእርምጃ ድምጽ) እያሰማ በገነት እየተመላለሰ ይፈልገው ይጠራው ጀመር፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፍለጋም ‹‹ ዴሬክ የህዌ ›› (ፍኖተ እግዚአብሔር) ሃይማኖት በመባል ይታወቃል ፡፡ ሃይማኖት የሰው እግዚአብሔርን ፍለጋ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ፍለጋንም ያካትታል፡፡

በዓለመ መላእክት የተመሰረተች እና እግዚአብሔር በሰው ልቦናም ያሳደራት በሎም አዳም በበደለ ጊዜ በእግዚአብሔር አዳምን ፍለጋ ባደረገው ጉዞ (ዴሬክ ያህዌ) የተገለጠችው ሃይማኖት ከአዳምም በኋላ በተነሱ ደጋግ አባቶች በልቦና ታስባ በምግባር ስትገለጥ ቆይታለች፡፡ የተጻፈ ሕግ የሃማኖት መመሪያ ባልነበረበት ዘመን የሰው ልጅ በልቦናው በተጻፈ ህግ እና ዝንባሌ በመታገዝ በህሊናው ተጠቅሞ እግዚአብሔርን ያመልከው ነበር፡፡ ለዚህም ከአዳም እስከ ሙሴ ድረስ ያሉ ደጋግ አባቶች ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህ ዘመንም ህገ ልቦና ብለን የምንጠራው ነው

በዚህች ሃይማኖት፡-

- ይህች ሃማኖት አዳም በንስሃ ከአምላኩ ታርቆባታል፣
- ይህች ሃማኖት አቤልን ከቃየል የጥፋት መንገድ ለይታዋለች
- ይህች ሃማኖት ኣባታችን ኖህን በአምላኩ እንዲታመን እና ከጥፋት ውሃ እንዲድን አስችላዋለች፣
- ይህች ሃማኖት አባታችን አብርሃምንም ከሀገሩ እንዲወጣ እና ወደተስፋይቱ ምድር ወደ ከነአን እንዲገባ ለበረከትም እንዲሆን አስችላዋለች፡፡…ወዘተ
- በዘመነ ብሉይም በተሰጠ ሕገ ኦሪት ሰዎች እየተመሩ በነቢያት መመህርነት እየታገዙ በአንዲቷ ሃይማኖት ፀንተው እግዚአብሔርን ያመልኩ የነበረ ሲሆን ፤ በሃዲስ ኪዳንም በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ እና በሶስቱ አካላት መገለጥ ከበፊት ይልቅ ጎልታ ልትገለጥ ልትፀና ችላለች ፡፡ እስከ ፍጻሜ ዓለምም በሰዎች ልቡና እየታሰበች መከፈል መለወጥ ሳኖረርባት በስራ እየተገለጠች ትኖራለች፡፡ ለክብር ለመንግስተ ሰማያት እና ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት እና ለመኖር አማራጭ የሌላት አንዲት እና ብቸኛ የድኅነት መንገድ ሆና ትኖራለች፡፡

፩.፫ የሃይማኖት አስፈላጊነት (በነፍስ በስጋ)
ሀ. ሃይማኖት ለሥጋዊ ሕይወት የሚሰጠው ጥቅም
፩ኛ. ሰላምን ያሰጣል

ሰላም ፍጹም የሆነ ውስጣዊ ዕረፍት ነው፡፡ ሰው በሃይማኖት ከኖረ ውስጣዊ ሰላሙን የሚያደፈረሱ ፈተናዎችን፣ አእምሮ የሚያልፉ ጭንቀቶችን ሁሉ በተአምኖ እግዚአብሔር ድል ስለሚያደርግ ዕረፍት የሚያሳጡ ኃጢአቶችንም በንሰሐ ስለሚያስወግድ ዘወትር ሰላም አይለየውም፡፡ ይህ ደግሞ ለሥጋዊ ሕይወት መሠረታዊ ጥቅም አለው፡፡ ምክንያቱም ሰው በሥጋዊ ሕይወቱ ውጤታማ የሚሆነው ተማሪውም ተምሮ መመረቅ፣ ነጋዴው ነግዶ ማትረፍ፣ ሙያተኛው ሠርቶ ራስንና ወገንን መደገፍ የሚቻለው እያንዳንዱ ውስጣዊ ሰላም ሲኖረው ነው፡፡ ሰላም የሌለው ሰው ግን ዘወትር ከራሱ ጋር ስለሚያጋጭና ስለሚጣላ በማኝኛውም ቦታ የተሰጠውን ኃላፊነት የሚጣበት አቅም አይኖረውም፡፡ በሃይማኖት የሚኖር ሰው ሁሉን ማድረግ የሚቻለው በእግዚአብሔር በመደገፍ እውነተኛውን ሰላም ያገኛል፤ ልቡናውም ከጭንቀት ይጠበቃል፡፡ የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ይህንን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ ልባችሁ አይደንግጥ አትፍሩም፡፡›› /ዮሐ. ፲፬፥፳፯/
‹‹ሁሉ የሚገኝባት ከልቡናና ከአሳብ ሁሉ በላይ የምትሆን የእግዚአብሔር ሰላም በኢየሱስ ክርሰቶስ ልባችሁንና አሳባችሁን ታጽናው›› /ፊል. ፬፥፯/
‹‹በአንተ ላይ ታምናለችና በአንተ የምትደገፍ ነፍስን ፈጽመህ በሰላም ትጠበቃለህ››/ኢሳ. ፳፮፥፫

፪ኛ. መንፈሰ ጠንካራ ያደርጋል

ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር ብዙ ተግባራት አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እጅግ አድካሚ፣ እልህ አስጨራሽና ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በሃይማኖት /በአሚነ እግዚአብሔር/ የማይኖረው የሚታመነው ስለሌለው ተመርሮና ተስፋ ቆርጦ ሲተዋቸው በሃይማኖት የሚኖረው ግን ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› ብሎ በጠንካራ መንፈስ ሊወጣቸው ይቻለዋል፡፡ /ፊል. ፬፥፲፫/

የከነዓን ምድር እንዲሰልሉ ከተላኩት ጉበኞች /ሰላዮች/ የምንረዳው ይህንኑ ነው፡፡ የከነዓንን ምድር እንዲሰልሉ በተላኩበት ጊዜ ፲፪ቱም ሰላዮች ምድሪቱ መልካም እንደሆነች ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን እጅግም ግዙፋን መሆናቸውን አይተዋል፡፡ ነገር ግን ፲ሩ ተአምኖ እግዚአብሔር የጎደላቸው በመሆናቸው ተስፋ ቆርጠዋል፤ ፈተናውን ማለፍ ተስኗቸዋል፡፡ ሕዝቡንም በአመጡት ወሬ አሸብረዋል፡፡ ሕዝቡም የተስፋይቱን ምድር መውረስ ዓላማ አድርገው ብዙውን መከራ ተቀብለው በበረሃ አልፈው መጥተው ጥቂት መንገድ ሲቀራቸው ‹‹ኑ አለቃ ሾመን ወደ ግብጽ እንመለስ ›› የሚሉ ሆነዋል፡፡ /ዘኍ. ፲፬፥፬/፡፡ በእምነት ጽኑአን የነበሩት መንፈስ ጠንካሮቹ ኢያሱና ካሌብ ግን ‹‹አይደለም ማሸነፍን እንችላለንና እንውጣ እንውረሳት ›› /ዘኍ ፲፫፥፴/ ብለዋል፡፡

በሃይማኖት የሚኖር ሰው ኃያሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር መሆኑን ስለሚያምን ምንም ያህል ከባድ ፈተና ቢገጥመው ያጋጠመውን ፈተና አግዝፎ፣ ራሱን እንደ አንበጣ አሳንሶ አይመለከትም፡፡ /ዘኍ. ፲፫፥፴፪/ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን ከማለፍ በኋላ ያለውን መልካም ነገር ስለሚያይ በፈተናው ውስጥ በብርቱ መንፈስ ሆኖ ያልፋል፡፡

፫ኛ. ታማኝና ተወዳጅ ያደርጋል

በሃይማኖት የሚኖር መንፈሳዊ ሰው በሁሉ ነገር በሰው ፊት ይታመናል፡፡ ይህም በሁሉ ፊት ሞገስ እንዲያገኝ ስለሚያደርገው የሚቃወመው፤ ጉዳት ሊያደርስበት የሚፈልግ፣ የሚጠላው ሰው አይኖርም፡፡ ሰይጣን በቅንዓት አንዳንዶችን በክፋት ቢያስነሳበት እንኳን በፈተናው ስለሚጸና ፈተናውን ሲያልፍ ከፊት ይልቅ የሚበልጥ ታማኝነትንና ተወዳጅነት ያተርፋል፡፡ ይህንንም ከቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት መማር ይቻላል፡፡ ለባርነት በተሸጠበት በባዕድ ሀገር ሀገርን እስከ መምራት ድረስ ታማኝነትንና ተወዳጅነትን ያገኘው ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ አሚነ እግዚአብሔር ስለነበረው ነው፡፡ /ዘፍ. ፴፱/፡፡

፬ኛ. ትዕግስተኛ ያደርጋል

በሃይማኖት የሚኖር ሰው ሁሉ በፈቃደ እግዚአብሔር የሚከናወን መሆኑን ስለሚያምን በሥጋዊ ሕይወቱ ድንገተኛ ችግሮች ቢያጋጥሙት (ሀብት ንብረት ቢወድም፣አካል ቢጎድል፣…) ይታገሳል እንጂ መድኃኒት ጠጥቼ፣ ገደል ገብቼ ልሙት አይልም፡፡ ይልቁንም እንደ ጻድቁ ኢዮብ ‹‹ እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ፣ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን›› እያለ እግዚአብሔርን ከማመስገን አይቦዝንም፡፡ /ኢዮ. ፩፥፳፮/፡፡ በሌላ መልኩ በሃይማኖት የሚኖር ሰው ከሰዎች የሚሰነዘሩበትን ፈተናዎች ሁሉ በትዕግስት ይቋቋማል፡፡ ክፉውን ሁሉ በመልካም /በትዕግስት/ ያሸንፋል እንጂ በክፉ ስለማይሸነፍ ለበቀልም ስለማይነሣሣ ወንጀል ፈጽሞ በሥጋው ላይ መከራን አይመጣም፡፡ /ሮሜ. ፲፪፥፳፩/፡፡

፭ኛ. ከመከራ ሥጋ ያድናል ይሰውራል

በሃይማኖት የሚኖር ሰው በሥጋ መከራ ቢደርስበት የሚያምነው አምላኩ በክንፈ ረድኤቱ ከመከራ ይሰውረዋል፡፡ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ክብርን፣ ዐስበ ሰማዕታትን /የሰማዕታት ዋጋ/ ያገኝ ዘንድ ፈቅዶ ካልተወው በቀር እሳቱን፣ ሰይፈ ስለቱን ሁሉ ያርቅለታል፡፡

- ዳንኤልን ከተራቡ አናብስት አፍ እንዳዳነው /ዳን. ፮፥፲-፳፰/
- ሠለስቱ ደቂቅን ከሚነድ እሳት እንደታገዳቸው /ዳን. ፫፥፰-፴/
- ሶስናን በድጋይ ተወግራ በእሳት ተቃጥላ ከመሞት እንዳዳናት /ዳን. ፲፫፥፴/

፮ኛ. በረከተ ሥጋን ያሰጣል

በሃይማኖት የሚኖር ሰው እግዚአብሔርን በማመኑ በሥጋዊ ሕይወቱ ያሉት ነገሮች ሁሉ የተባረኩ ይሆናሉ፡፡ በተቀደሰ ጋብቻ ኖሮ የተባረከ ልጅ ይወልዳል፤ አሥራቱን አውጥቶ ሀብቱ ንብረቱ የተባረከ ይሆናል፤ ጥቂቱ ይበዛለታል ጐዶሎው ይሞላለታል፡፡

- አብርሃም በቅዱስ ጋብቻ ኑሮ ዘሩ የተባረከ እንደሆነ /ዕብ. ፲፮፥፳/
- የሰራፕታዋ ሴት በእግዚአብሔር አምና የነብዩ የኤልያስን ቃል ስምታ እንደተባለችው ስላደረገች ቤቷ በበረከት እንደተሞላ /1ኛ ነገ. ፲፯፥፲-፲፮/
- የዶኪማስ የሠርጉ ቤት በጌታ ተአምራት ሥራ፣ በእመቤታችን ምልጃ በበረከት እንደተጎበኘ /ዮሐ. ፪፥፲፮/

7ኛ. ድኅነተ ሥጋን ያሠጣል

ሰው በተለያየ ምክንያት የሥጋ ሕመም /ደዌ/ ሊያገኘው ይችላል፡፡ በሃይማኖት የሚኖር ከሆነ ግን በእምነቱ ብቻ ፍጹም ፈውስን ሊያገኝ ይችላል፡፡ ሃይማኖት ለደዌ ነፍስ /ኃጢአት/ በንሰሐ ፈውስን እንደምትሰጥ ለደዌ ሥጋም በተአምር ፈውስን ታስገኛለች፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ብዙዎችን በእምነታቸው ምክንያት ከተለያየ ደዌ ሥጋ እንደ ፈወሳቸው በወንጌል ተጽፎ እናነባለን፡፡ /ማር. ፪፥፭፤ ሉቃ. ፲፯፥፲፱፤ ማቴ. ፱፥፳፪፤ ማቴ. ፰፥፲፫/

ለ. ሃይማኖት ለነፍስ የሚሰጠው ጥቅም
ሃይማኖት ለሥጋ ያለውን ጥቅም ስናነሳ ሥጋን የሚጠቅሙ ነገሮች ነፍስንም የሚጠቀሙ፣ ሥጋን የሚጎዱም ነገሮች ነፍስን የሚጎዱ መሆናቸው ሊስተዋል ይገባል፡፡ ነፍስ ያለ ሥጋ አትቆምምና፡፡ በሥጋዊ ሕይወቱ ውስጣዊ ደስታ የሌለው ሰላም የተሞላበትና ሰኬታማ ኑሮን መምራት ያልቻለ ሰው ስለነፍሱ ደኅነት የማይጨነቅ ለመንፈሳዊ ሕይወት ግድ የለሽ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን በሃይማኖት የሚኖር ሰው በነፍሱ የሚከተሉትን ጥቅሞች ያገኛል፡፡

፩ኛ. በነፍሱ ደኅነትን ያገኛል

ሰው በነፍሱ ደኅነትን አገኘ የምንለው ከዘለዓለም ፍርድ አምልጦ ገነት መንግስተ ሰማያትን መውረስ ሲችል ነው፡፡ ለዚህ ደኅነት ነፍስ ለመብቃትም ርቱዕ ሃይማኖትን መያዝ በጐ ምግባር መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ያለ ሃይማኖት ደኅነተ ነፋስን ማግኘት የለም፡፡ ‹‹በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን ፈጽሞ ተፈርዶበታል››/ዮሐ ፫፥፲፰/

እምነት ወደ ደኅንነት ለመድረስ ለሚደረገው የሕይወት ሙሉ ጉዞ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ሮማዊውን የእስር ቤቱን ዘበኛ እንዲህ ያሉት፡- ‹‹በጌታችን በኢየሱስ ክርሰቶስ እመን አንተና ቤተሰቦችህ ትድናላችሁ››/ሐዋ. ፲፮፥፴፩/

፪ኛ. በነፍሱ ዘላለማዊ ዋጋን ያገኛል

ሰው ሃይማኖትን ጠብቆ በምግባር ጸንቶ በነፍሱ ድኅነት ሲያገኝ ነፍሱ የማይጠፋ ዘላለማዊ ሽልማትን ትቀዳጃለች፡፡ ይህም የነፍስ ሰማያዊ ዋጋዋ ነው፡፡ ይህ ዋጋ፡-

የሕይወት አክሊል ነው
‹‹መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄአለሁ፡፡ እንግዲህ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል ይህንንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባሉ፡፡ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡›› /፪ጢሞ ፬፥፮- ፲/

የክርስቶስ መለኮታዊ ክብር ተካፋዮች መሆን ነው ይህም ክርስቶስን መምሰል ነው
‹‹እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት፤ ከዚያም እርሱን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን እንጠባበቃለን፡፡ እርሱም እንደ ከኃሊነቱ ረዳትነት መጠን የተዋረደውን ሥጋችንን የሚያድሰው ክቡር ሥጋውንም እንዲመስል የሚያደርገው፣ የሚያስመስለውም ሁሉም የሚገዛለት ነው፡፡››/ፊል ፫፥፳ እና ፳፩/

እግዚአብሔር መንግስት መውረስ ነው
ሰው በቀናው ሃይማኖቱና በበጐ ምግባሩ ሐዘን፣ ጩኽት፣ ሕማም፣ መከራ፣ ሞት የሌለባትን የእግዚአብሔር ክብር የሞላበትን መንግስቱን ይወርሳል፡፡ /ራዕ. ፳፩፥፩-፳፯/

፩.፬ ስለ ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተላልፈው መልእክት
በአንዲቷ ሃይማኖት እስከመጨረሻው መጽናት

ሃይማኖታችንን እስከመጨረሻው አጽንተን ልንጠብቃው የሚገባ ቁም ነገር ነው፡፡ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስም ‹‹ የመጀመሪያ እምነታችንን እስከመጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፡፡ ›› ዕብ 3÷14 እንዲሁም ቅ/ጳውሎስ እረፍቱ (ሞቱ) በተቃረበ ጊዜም ‹‹ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል ›› በማለት በሃይማኖታችን መጽናት እንደሚገባ በቃሉም በህይወቱም ያስተምረናል፡፡

በሃይማኖታችን እስከመጨረሻው ድረስ መጽናት በመጽሐፍ ቅዱስ ገድላቸው በክብር በፈፀሙ አባቶች እና እናቶች የህይወት ጉዞ የምንረዳው ሲሆን እኛም በአምነታችን ብንፀና ድህነትን እንደምናገኝ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ እስከ መጨረሻ የሚፀና እርሱ ይድናል ›› ማቴ 24÷13 በማለት አባታዊ ምክሩን ሰጥቶናል፡፡ እኛም በ1ኛ ቆሮ 16÷13 ‹‹ ንቁ በሃይማኖት ቁሙ ›› የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርትን በማሰብ በየትኛውም መንገድ የሚመጣውን ፈተና እየታገስን ድል በመንሳት በሃይማኖታችን ፀንተን ልንቆም ይገባል፡፡

ሃይማኖት በሥራ የምትገለጽ መሆን አለባት

በመልካም ስራ የማትገለጥ ሃይማኖት በራሷ የሞተች ጥቅምም የሌላት ናት፤ በቅ/ያእቆብ መለእከት ያዕ2÷18-19 ‹‹ ወንድሞች ሆይ እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን ›› በማለት እምነት ያለስራ ከንቱ የሆነ ነገር እንደሆነ ይመክረናል፡፡ በስራ ያማይገለጥ ሃይማኖት ከአጋንንት እምነት ጋር ልንመስለው እንችላለን፡፡ ያዕ 2÷19 ‹‹ አጋንንት ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል ›› እንዲል፡፡

አባታችን ቅ/ያዕቆብ ሊያጸድቅ ሚችለው እምነትም እንደ አባታችን አብርሃም ያለ በስራ የተገለጠ እምነት እንደሆነ የአብርሃምን ታሪክ እያስተወሰ ያስተምረናል፡፡ ያዕ2÷2-26 ‹‹ ኣባታችን አብርሃም ልጁን በመሰዊያው ባቀረበ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን ; ›› እንዲል፡፡ እምነት ያለ ምግባር ምውት እንደሆነ ሁሉ ስራም ያለእመነት ( ሃይማኖት ) ከንቱ ነው ፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኘው የምንችለው ሁለቱን አዋህደን መኖር ስንችል ብቻ ነው፡፡

ሃይማኖት የተጋድሎ ሕይወት ነው

ሃይማኖትና ተጋድሎ የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ አንድ ሰው በሃይማኖት ውስጥ አለ የሚባለው ዘወትር በሃይማኖቱ የሚመጣበትን ፈተና በተጋድሎ (በድል) ሲወጣ ነው፡፡ የዚህን ዓለም ምኞት፣ ከራስ የሚመነጭ ፈተና፣ ከዲያብሎስ የሚሰነዘርን የኃጢአት ጦር የምንዋጋው (እስከመጨረሻው የምንጋደለው) ድል የምንነሳው በተሰጠን አንዲት ሃይማኖት ሆነን ስንኖር ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም በልዩ ልዩ መልኩ እንዲህ ያስተምረናል፡- 1ኛ ጢሞ 6÷12 ፡- ‹‹ መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል የተጠራህለትንም በብዙ ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የተመንህለትን የዘላለም ሕይወት ያዝ ››

ይሁ 1÷3 ፡- ‹‹ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠች ሃማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ ››

ገንዘብን ከመውደድ እና ከሃሰተኛ መናፍቅ መምህራን የሃሰት ትምህርትም ልንጠነቀቅ የሚገባ ነገርም እንደሆነ ማስተዋል የተገባ ነው ፡፡ ብዙዎች ገንዘብን ከመውደድ እና በአጋንንት እና በመናፍቃን ትምህርት በመታለል ከሃይማኖት ክደው ወጥተዋል መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ይመሰክራል፡፡
1ኛ ጢሞ 6÷10 ፡- ‹‹ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና አንዳንዶች ይህን ሲመኙ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ስቃይ ራሳቸውን ወጉ ›› እንዲል፡፡

1ኛ ጢሞ 4÷2 ፡- ‹‹በውሸተኞት ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንት ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖት ይክዳሉ›› ስለሆነም በዚህ ዓለም ስንመላለስ በሃይማኖት ሆነን የሃጢአትን ሥራ ልንቃወም እና ልንታገል ኃይለ እግዚአብሔርንም ተላብሰን የፅድቅ ጦር እቃ እምነቱን፣ ፀሎቱን፣ ስግደቱን የንስሃ ህይወቱን በሥጋ ወደሙ ታትሞ የመኖርን ዝግጅት ገንዘብ አድርገን ድል ልንነሳ ይገባናል፡፡ ኤፌ 6÷16 ፡- ‹‹በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን ክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ ምትችሉበትን ጋሻ አንሱ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡›› ይህንን ማድረግ ስንችል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኛ ለማስተማር ስለ ራሱ ሲናገር 2ኛ ጢሞ 4÷7 ‹‹ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ ሩጫየን ጨርሻለው ሃማኖቴን ጠብቄአለሁ ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል ›› እንዳለ እኛም የተጋድሎአችንን ዋጋ የጽድቅን አክሊል በመንግስተ ሰማያት ከጌታችን ዘንድ እንቀበላለን ፡፡

፩.፭ የምዕራፉ ማጠቃለያ
ሃይማኖት ማመን እና መታመን በሚሉ ሁለት ቃላት ይተረጎማል፡፡ ማመን ስንል የተማሩትን በልብ መቀበል ሲሆን መታመን ማለት ደግሞ እውነት ነው ብለው የተቀበሉትን በአፍ መመስከር በተግባር መግለጥ ነው፡፡

ሃይማኖት የምግባር፣ የትሩፋት መሠረት ነው፤ ምግባር ትሩፋት ከመሥራት በፊት ሃይማኖትን መያዝ ይገባልና፡፡ ሃይማኖት ከእውቀት በላይ ነው፤ በስሜት ሕዋሳት መርምረው የማይደርሱባቸውን ያስረዳልና፡፡ ሃይማኖት ከዚህ በተጨማሪ ተስፋን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል ሃይማኖት የሚያስፈልጋቸው ሰውና መላእክት ብቻ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እውቀት ስላላቸውና ሕያዋን ፍጥረታት ስለሆኑ ነው፡፡

በእግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ ያመኑ ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ ለዚህም ሃይማኖት የተጀመረው በዓለመ መላእክት ነው፡፡ በተጨማሪም ሃይማኖት ለነፍስም ለሥጋም በረካታ ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡