Advertisement Image

ትምህርተ ሃይማኖት

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የትምህርተ ሃይማኖት ምዕራፎች

ምዕራፍ ሁለት : ሀልወተ ፈጣሪ - የፈጣሪ መኖር

2.1 የሃይማኖት መሠረት - ፈጣሪን ማመን
ሃይማኖት ማለት የ፳፪ቱ ሥነ-ፍጥረት አስገኚ፣ የሚታየውና የማይታየውን ዓለም መጋቢ፣ ሁሉን ማድረግ የሚችል ረቂቅ ምሉዕ ሰፋሕ፣ ሕያው ባሕርይ የሆነ እግዚአብሔር ነው ብሎ ማመን ነው፡፡ የዚህ እምነት መሠረቱ የፈጣሪ መኖር /ሀልዎተ ፈጣሪ/ ነው፡፡ የፈጣሪ መኖር ስንል ግን ለአኗኗር ጥንት ወይም ፍጻሜ አለው ማለት ሳይሆን ዘመኑ የማይለካ ከጥንት በፊት የነበረ ጥንት ከመጨረሻም በኋላ የሚኖር መጨረሻ ብለን ለመናገር መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ሃይማኖትን ያጸኑ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች በጸሎተ ሃይማኖት እንዲህ ብለዋል፡፡

‹‹ሁሉን በፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን ሰማይንና ምድርን ፈጠረ የሚታየውንና የማይታየውን›› /ሰለስቱ ምዕት/

በመሠረቱ ዓለም ያለ አስገኚ የተገኘ፣ ከተገኘም በኋላ ያለ መጋቢ በራሱ የሚኖር አይደለም፡፡ ሸክላ ያለ ሰሪ፣ ቡቃያ ያለ መሬት፣ ልጅ ያለ እናት አባት እንደማይገኙ ሁሉ ዓለምም ያለ አስገኚ የተገኘ አይደለም፡፡ ለተፈጥሮው አስገኚ፣ ለኑሮው ሠራዒ መጋቢ፣ ለጉዞው መነሻና መድረሻ አለው እንጂ፡፡ ይህንንም በልቡና መርምረን በቃለ እግዚአብሔር ምስክርነት በእምነት እናውቃለን፡፡ “ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ፣ የሚታየው ነገር ከማይታይ እንደሆነ በእምነት እናውቃለን” /ዕብ. ፲፩፥፫/

2.2 የፈጣሪ መኖር የሚያስረዱ ነገሮች
ሀ. ሥነ-ፍጥረት
የማይታይና የማይዳሰሰው አምላክ በሚታይና በሚዳሰሰው ሥራው /ሥነ-ፍጥረት/ ራሱን ስለገለጠ ሥነ-ፍጥረት ለፈጣሪ መኖር አንድ አስረጂ ነው፡፡ ሥነ ፍጥረት የፈጣሪ መኖር የሚያስረዳው በሁለት ወገን ነው፡፡ እነሱም፡-

፩. ከፍጥረታት መካከል በራሱ የተፈጠረ በራሱም ላይ ብቻውን ሙሉ ሥልጣን ያለው ፍጥረት አለመኖሩ፡፡ ይህም ለተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ አስገኚ ፈጣሪ በተፈጠረውም ፍጥረት ላይ ሥልጣን ያለው ኃይል እንዳለ ያሳየናል፡፡

. በተፈጠረው ፍጥረት መካከል ያለው አብሮ የመኖር ስምምነት ለምሳሌ፡- ከእንስሳት የሚወጣውን የተቃጠለ አየር በመጠቀም በምትኩ ለእንስሳት በሕይወት መኖር የሚያሰፈልገውን አየር ተክሎች መለገሳቸው፣ በዚህም በከባቢ አየር ውስጥ ለሁሉም በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጉ አየራት መጠናቸው ሳይዛባ የሚኖር መሆኑ በቂ አስረጂ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን እንስሶችም ተክሎችም ፈልገው አስበውት የሚያደርጉት አለመሆኑ ፍጥረታትን ፈጥሮ በሥርዓት የሚያስተዳድር ኃይል /አምላክ/ እንዳለ ያስረዳል፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍትም በሥነ-ፍጥረት የፈጣሪ ህልውና የሚታወቅ መሆኑ ይመሰራክሉ

‹‹የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኃይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፡፡›› /ሮሜ. ፩፥፳/
‹‹አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ ያስተማሩህማል፣ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ ይነግሩህማል፣ ለምድር ንግራት እርሷም ትተረጉምልሃለች፣ የባህርም ዓሳዎች ያስረዱሃል፣ የእግዚአብሔር እጁ ይህን ሁሉ እንዳደረገ›› /ኢዮ. ፲፯-፲/
‹‹ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል››/መዝ. ፲፰፥፩/
ሌላው ግዕዛን /አእምሮ/ የሌላቸው ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው መፈራረቃቸው በዚህም ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ በምድር ላይ ምግበ ሥጋን አግኝቶ መኖር መቻሉ ወቅቶችን የሚያፈራርቅ ኃይል መኖሩን የሚያስረዳ ምስክር ነው፡፡
‹‹ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራን እየሠራ ከሰማይ ዝናምን፣ ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፣ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም፡፡›› /ሐዋ. ፲፬፥፲፯/

ለ. የሕሊና ምስክርነት
ሰው የተጻፈ ሕግ ባይኖረውም እንኳ መጽሐፍትንም ባያነብ አዋቂ ፍጥረት በመሆኑ መልካምና ክፉውን በሕሊናው አመዛዝኖ መለየት ይቻለዋል፡፡

‹‹ሕግ የሌላቸው አሕዛብስ እንኳ ለራሳቸው ሕግ ይሠራሉ. . .በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ፣ ከሥራቸውም የተነሳ ይታወቃል ሕሊናቸውም ይመሰከርባቸዋል ይፈርድባቸዋልም፡፡›› /ሮሜ. ፲፬ ና ፲፭/

ሰው የሁሉ ፈጣሪና ገዥ መኖሩን አምኖ ከሞት በኋላ ያለውንም ሕይወት ተስፋ አድርጐ ሲኖር በሕሊናው ፍጹም ስላምን ያገኛል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እግዚአብሔርን ቅር የሚያሰኝ ሥራ ሲሠራ /ሲገድል፣ ሲሰርቅ. . . ./ ሠሪው የሃይማኖት ሕግ ባይኖረውም እንኳ የተፈጥሮ ዳኛ ሕሊናው ስለሚፈርድበት በጭንቀት ይኖራል፡፡ ይህም ማለት ሰው በሕሊናው አንድ ቅንና እውነተኛ ፈራጅ መኖሩን ያውቃል ማለት ነው፡፡

ሐ. እግዚአብሔር ከሰው ጋር ባደረገው ንግግር
እግዚአብሔር ከሰው ጋር በራዕይ በሕልምና በገሃድ ቃል በቃል ያደረገው ንግግር ህልውናውን ያረጋግጣል፡፡

‹‹እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበረ፡፡›› /ዘፀ. ፴፫፥፲፩/
‹‹የሙሴ እህት ማርያምንና አሮንንም በዐምደ ደመና ተገልጦ እንዳነጋገራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡›› /ዘኁ. ፲፥፭-፲/ቀደምት አበው ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የእግዚአብሔርን መኖር በስፋት እና በጥልቀት አስተምረዋል ፣ ትንቢት ተናግረዋል ትንቢታቸውም በጊዜው ፍጻሜን አግኝቶም አልፏል፡፡

መ. የሰው ልጅ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ
ከጥንት ጀምሮ ያለውን የሰው ልጅ ታሪክ ስንመለከት ወይ በእግዚአብሔር ሲያምን አልያም የእግዚአብሔር የእጁ ሥራዎች በሆኑ በፀሐይ፣ በጨረቃ…ወዘተ ሲያምን ወይም ደግሞ በራሱ በእጁ አለዝቦ፣ ጠርቦ ቀርጾ ያዘጋጃቸውን ጣኦታቱን ሲያመልክ መኖሩን እንገነዘባለን፡፡ ይህም የሰው ልጅ ለመኖር ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ የተፈጥሮ ፍላጐቶች ባልተለየ ሁኔታ የእምነት ዝንባሌና ስሜት እንዳለው ያሳያል፡፡ ሰው እንዲህ በተፈጥሮው በራሱ ምሉዕ አለመሆኑ፣ የማይሸነፍ ብርቱ ረዳት መፈለጉ ሁሉን ቻይ፣ ጸባዖች /አሸናፊ/ አምላክ መኖሩን ያሳያል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የሰውን የማመን ዝንባሌ ተጠቅሞ በአቴና ከተማ ‹‹ለማይታወቅ አምላክ›› የሚል ጽሑፍን መነሻ አድርጎ በአቴና ከሚኖሩት አንዳንዶችን ወደ አምልኮ እግዚአብሔር አምጥቷቸዋል፡፡ /ሐዋ. ፲፯፳-፴፬/

ከላይ የተዘረዘሩትን አስረጂዎች ተገንዝቦ ፈጣሪ እንዳለ ማወቅ አእምሮ ለተሰጠው ልጁ ስውር አይደለም፡፡ ሆኖም ይህን አለማስተዋልና የእግዚአብሔር ህልውና መጠራጠር ግን ስንፍና ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም ይህንኑ ያስረዳል፡፡

‹‹ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል››/መዝ. ፲፫፩/ ‹‹እግዚአብሔርን የማወቅ ጉድለት በልቦናቸው ያለባቸው ሰዎች ሁሉ በእውነት ከንቱ ናቸውና፤ በሚታዩ መልካም ነገሮች ያለውን ያውቁ ዘንድ ተሳናቸው፤ ሥራውንም እያዩ ሠሪውን አላወቁትም፡፡››/ጥበ. ፲፫፩/

2.3 የአምላክ ስሞች /አስማተ አምላክ/
ሀለወተ ፈጣሪን ተረድቶ በሃይማኖት የሚኖር ሰው የሚያምነውን አምላኩን እሱነቱንና ስሙን አእምሮው በሚፈቅድለት መጠንና ፈጣሪውንም እሱነቱን በአስታወቀለት መጠን ሊያውቀው ሊረዳው ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ባሕርዩንና ግብሩን የሚገልጸው ስሙ ለሰው ልጅ የታወቀለት በራሱ በእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሙሴ በፊት ለነበሩት አበው እሱነቱን ሲገልጥላቸው ስሙ “ኤልሻዳይ” እንደሆነ በመንገር እንጂ ስሙ እግዚአብሔር መሆኑን አልገለጠላቸውም ነበረ፡፡ የዚህም ስም ትርጉም ሁሉን ቻይ ማለት ነው፡፡ ለሰው ልጅ በቅድሚያ ስለ እግዚአብሔር ግልጥ የሆነው ከሀሊነቱ /ሁሉን ቻይ መሆኑ/ ነውና፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በሊቀ ነብያት ሙሴ ስሙ ማን እንደሆነ ተጠይቆ ሲመልስ ”ያለና የሚኖር” ዳግመኛም የአብርሃም አምላክ፣ የይሰሐቅ፣ የያዕቆብ የሚለው ለዘለዓለም ስሙ እንደሆነ ገልጧል፡፡ /ዘፀ. ፫፥፲፬/ ከዚህ በመቀጠልም በእስራኤላውያን ቋንቋ “ይሆዋ” ወይም “ያህዌ” በሚል ስም እንደሚጠራ ግልጽ አድርጓል፡፡ ይህም ወደ ግዕዝ ሲመለስ “እግዚአብሔር” በሚል ቃል ተተክቷል፡፡

‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ ለአብርሃምም ለይስሐቅም በያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል /አልሻዳይ/ አምላክ ተገለጥሁ፡፡ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበረ፡፡›› እንዲል/ዘፀ. ፮፥፫/

ለነብዩ ለኢሳይያስም ይህንን ስሙን ገልጾለታል፡፡ ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፣ ስሜ ይህ ነው፣ ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጸ ምስሎች አልሰጥም››/ኢሳ. ፵፪፥፰/

ይህም እግዚአብሔር የሚለው ስም የሁሉ ፈጣሪ፣ አስገኚና መጋቢ ከነባሕርዩና ግብሩ እሱነቱን በጠቅላላ የሚገልጽ ስም በመሆኑ ክቡር ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካዊ ግብሩን የሚገልጡ ስያሜዎች ‹‹ አምላክ፣ ፈጣሪ፣ ጌታ፣ ከሃሊ፣ መጋቢ፣ አዳኝ፣. . . ወዘተ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ አምላካዊ ባሕርዩንም በሚገልጡ ‹‹ ሕያው፣ ዘላለማዊ፣ ያለና የሚኖር፣ መሐሪ፣…›› በሚሉ ሰያሜዎች ይጠራል፡፡ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜ ግን እርሱነቱን ከነባሕርይውና ግብሩ የሚገልጽ በመሆኑ ይህ ስም ለፈጣሪ የመጨረሻው /የመጠሪያ ስም/ ነው፡፡ በዚህም ስም አምልኮታችንን እንፈጽማለን፡፡ ይህም ስለሆነ ከዐሥርቱ ሕግጋት ኦሪት አንዱ ይህንን ቅዱስና ክቡር ስም በከንቱ መጥራትን ይከለክላል፡፡

‹‹የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና››/ዘፀ. ፳፥፯

“ያሆዋ” ወይም “ያህዌ” የሚለው ስም በአይሁድ ዘንድ በዓመት ውስጥ በተወሰነ ጊዜ ያውም በሊቀ ካህናቱ ብቻ ካልሆነ በቀር በማንኛውም ጊዜ፣ በማንኛውም ሰው በግልም ይሁን በማኅበር ጸሎት ላይ አይነሣም፡፡ በዚህ ፋንታ ግን ኤሎሄ/ኤሌሂም /አምላክ/አምላኬ/፣ አዶን/አዶኒ/አዶናይ /ጌታ/ጌታዬ/ ኢሊዮን/ኤል /ልዑል/ በሚል የተጸውዖ ስም እግዚአብሔርን ይጠሩታል፡፡ እነዚህንም የተጸውዖ ስሞች እግዚአብሔር/ያህዌ ከሚለው ጋር እያጣመሩ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ

‹‹ጌታ እግዚአብሔር›› /ሕዝ. ፪፥፬/
‹‹ልዑል እግዚአብሔር›› /ዘፍ. ፲፬፥፲፰/
‹‹እግዚአብሔር አምላክ››
በዚህም መሠረት ለልጅም ይሁን ለድርጅት ስያሜ ሲያወጡ ይህንን ቅዱስ ስም በቀጥታ መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡

2.4 የእግዚአብሔር ባሕርያት /ባሕርያቱ ለእግዚአብሔር/
በዚህ ርዕስ ሥር የምንመለከተው እግዚአብሔር ስለ ባሕርይው የሰው ልጅ እንዲያውቀው በቅዱሳት መጻሕፍት በኩል ከተገለጠው ጥቂቱን ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ግን ሰው የፈጣሪውን ባሕርይ መርምሮ የሚደርስበት አእምሮ የሚገልጽበትም ቋንቋ አይኖረውም፡፡ ከዚህ በታች የምንመለከታቸውን የእግዚአብሔር ባሕርያት ናቸው ስንል ከሌላ ከማንም ያላገኛቸው ማንም ደግሞ ከእርሱ ሊወስዳቸው የማይቻለው የራሱ ገንዘቦቹ ናቸው ማለታችን ነው፡፡ ከዚህ ከባሕርይ ገንዘቡም ለፍጡር ቢሰጥ አንዲት ሻማ ብርሃንን ለሌሎች ሻማዎች ብትሰጥ የራሷ ብርሃን እንደማያልቅባት የእርሱም ገንዘቡ የማያልቅበት ነው፡፡

እግዚአብሔር በባሕርዩ፡-

፩. ዘላለማዊ /ሕያው/ ነው
እግዚአብሔር የሌለበት ጊዜ የለም፡፡ ፍጥረታትን ከመፈጠሩ በፊት በባሕርዩ የኖረ ነው፡፡ የሚታዩትና የማይታዩት ፍጥረታት ከእርሱ ተገኙ እንጂ እርሱን የፈጠረ/ያስገኘ ማስገኘትም የሚቻለው ሌላ ኃይል የለም፡፡እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ነበረ፡፡ የጊዜና የዘመን ፈጣሪንና ባለቤት እንጂ ዕለትና ጊዜ እርሱን አይቀድሙትም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ስለዚህ ምስክር ነው፡-

‹‹ተራሮች ሳይወለዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ መቼም መች አንተ ነህ›› /መዝ. ፹፱፥፪/

እግዚአብሔር በራሱ የነበረ ያለና የሚኖር ስለሆነ በጊዜ አይወሰንም ጊዜም እርሱን አይወስነውም፡፡ በባሕርይውም እርጅናና መለወጥ የለበትም፡፡

‹‹አቤቱ አንተ አስቀድመህ ምድርን መሠረትህ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው፡፡ እነርሱ ይጠፋሉ አንተ ግን ትኖራለህ፡፡ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃል እንደ መጎናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፣ ይለወጡማል፡፡ አንተ ግን ያው አንተ ነህ ዓመትህም ከቶ አያልቅም››/መዝ. ፻፩፥፳፭-፳፯/
ከእግዚአብሔር በፊት የነበረ መጀመሪያ አልነበረም፡፡ ከእርሱም በኋላ የሚኖር መጨረሻ አይኖርም፡፡ እርሱ መጀመሪያና መጨረሻ ፊተኛና ኋለኛ ነው፡፡

‹‹የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- እኔ ፊተኛ ነኝ እኔ ኋለኛ ነኝ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም፡፡›› /ኢሳ. ፵፬፥፮/
በተጨማሪም የሚከተሉት ጥቅሶች የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነት ይገልጣሉ፡፡ /ራዕይ. ፩፥፲፰፤ ፩ኛ/፣ ጢሞ.፩፥፲፯፣ ዘፀ. ፫÷ ፲፬/

፪ኛ. ምሉዕ ነው
እግዚአብሔር የሌለበት/የማይኖርበት ቦታ የለም፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው በጊዜ እንደማይወሰን ሁሉ በቦታም አይወሰንም፤ በሁሉም ቦታ እርሱ አለ፡፡ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ሙሉ እንደሆነ ልበ አምላክ ዳዊት እንደዚህ ገልጾታል፡፡
‹‹ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ፡፡ ወደ ጥልቁም ብወርድ አንተ በዚያ አለህ፡፡ እንደ ንስር ክንፍን ብወስድ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበር በዚያ እጅህ ትመራኛለች ቀኝህም ታኖረኛለች››/መዝ. ፻፴፰-፯-፲/

በነብዩ ኤርምያስም አድሮ እግዚአብሔር ምሉዓ ባሕርይነቱን ገልጧል፡፡
‹‹እኔ ቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ ሩቅ አምላክ አይደለሁም ይላል እግዚአብሔር ሰው በስውር ቦታ ቢሸሸግ እኔ አላየውምን? ሰማይና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን ይላይ እግዚአብሔር›› /ኤር. ፳፫፥፳፫ እና ፳፬/

በተጨማሪም የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ተመልከት፡፡ /ኢሳ. ፰፥፩፤ መዝ. ፻፪፥፲፱፤ ኢሳ. ፮፥፫/

፫ኛ.ሁሉን ማድረግ የሚቻለው /ከሀሌ ኩሉ ነው/
እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚቻለው የሚሳነው የሌለ ነው፡፡ የተፈጠረ ፍጥረት ሁሉ የሚታየውም የማይታየውም ዓለም የችሎታው ውጤት ነው፡፡ ከተፈጠረው ፍጥረት አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ የሆነ የለምና፡፡ /ዮሐ. ፩፥፫/ እግዚአብሔር ሁሉን ያለአማካሪና ረዳት ያስገኘ ስለሆነም ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው፣ ሁሉም በሥልጣኑ ሥር ነው፣ ሁሉን የመወሰን ስልጣን ያለውም እርሱ በቻ ነው፡፡ /ኢሳ. ፵፥፲፪-፲፯፣ ፵፫፥፲፫፤ ፵፬፥፯/

እርሱ ራሱ እግዚአብሔርም ከሣራ ጋር በአደረገው የቃል በቃል ንግግር ሁሉን ቻይነቱን ገልጧል፡፡ ‹‹በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን›› /ዘፍ. ፲፰፥፲፬

ጻድቁ ኢዮብም፡-
‹‹ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንህ የሚሳንህም እንደሌለ አወቅሁ›› ብሏል፡፡/ኢዮ. ፵፪፥፪/ ተጨማሪ ጥቅሶች፡- /ሉቃ. ፲፰፥፳፯፤ ፩፥፴፯፤ መዝ. ፻፴፬፥፮/

፬ኛ. ቅዱስ ነው
እግዚአብሔር በባሕርይው ልዩ ክቡር ነው፡፡ ርኩሰት የማይስማማውም ፍጽም ንጽሕ ነው፡፡ እግዚብሔር የባሕርይ ገንዘቡ በሆነ በዚህ ቅድስናው ከማንም ጋር የማይነጻጸር የሚመስለውም የሌለ ነዉ፡፡

‹‹አቤቱ፡- በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማነው በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማን ነው ?››እንዲል፡፡ዘፀ ፲፭÷፲፩ የሳሙኤል እናት ሐናም ይህን የእግዚአብሔርን ልዩ ቅድስና እንዲህ ትገልጸዋለች፡፡ ‹‹እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና›› /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፪/

ቅዱሳን መላእክትም ይህን የእግዚብሔርን ዘላለማዊ ቅዱስና በመግለጥ ያለማቋረጥ እንዲህ እያሉ ያመግኑታል፡፡ ‹‹ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የነበረውና ያለው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ›› /ራዕ. ፬፥፰/

ለዚህም ነው ቅዱስና ገናና ንጹሐ ባሕርይ እግዚአብሔር ሰውን በአርአያውና በምሳሌው በንጽሐ ባሕርይ ለክብር ስለፈጠረዉ የሰው ልጅ ከማንኛውም ርኩሰት ራሱን እንዲያነጻና በቅድስና እንዲኖር የታዘዘው፡፡ ‹‹የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁሉ፡፡›› /፩ኛ ጴጥ. ፩፥፲፭/

ለግንዛቤ ያህል ከላይ ያሉትን ስለ እግዚአብሔር ባሕርያት አነሳን እንጂ የእግዚአብሔር ባሕርያት እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው ፍጡር የፈጣሪውን ባሕርይ ሰፍሮ ቆጠሮ ዘርዝሮ የሚጨርሰው አይደለምና፡፡

፭ኛ. እግዚአብሔርን ማየትና ሙሉ ለሙሉ ማወቅ አለመቻሉ፡-
እግዚአብሔር በባህርይው ፍፁም መንፈስ ስለሆነ ሊታይና ሙሉ ለሙሉ ሊታወቅ አይችልም፡፡ እግዚአብሔርን የሚመስል ከቶ ምንም ነገር የለም፡፡

ሐዋ 17÷29 “አምላክን በሰው ብልኀትና ሐሣብ የተቀረፀውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባም፡፡” ተብሎ እንደተፃፈ እግዚአብሔርን ማንም ያየው ሰው እንደሌለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አረጋግጦአል፡፡ ሉቃ 10÷22 “ውሱን የሆነው የሰው ዐይን ውሱንነት የሌለውን እግዚአብሔርን ማየት አይቻለውም፡፡ ፀሐይን እንኳ ትኩር ብለን በዐይናችን ለማየት የማንችል ከሆነ እንዴት አድርገን በባህሪው ፍፁም ረቂቂና ምሉዕ የሆነውን መለኮት ልናየው እንችላለን? መላዕክት እንኳን ከሰው በበለጠው ረቂቃን ሆነው ቢገኙም ረቂቁን (በባሕርዩ) የሆነው እግዚአብሔርን አይተውት አያውቁም፡፡ ነገር ግን ሰው እና መላዕክት እግዚአብሔርን በባሕርየ መለኮቱ አይተውት ባያውቁም አቅማቸው ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውን ያህልና ሊረዱት በሚችሉበት ሁኔታ እግዚአብሔር ራሱን በዘፈቀደ በልዩ ልዩ ምሣሌዎች ይገልጽላቸዋል፡፡

ለምሣሌ ፡- ኢሣ 6÷2 “ሱራፌል ፊትህን ማየት አይቻለንም ብለው በክንፋቸው ፊታቸውን እንደሚሸፍኑ ተገልጿል፡፡”

ለሙሴ በእሳት ነበልባል መልክ ዘፀ 3
ለኢሳያስ በዘፍን ላይ ባለ ንጉሥ አምሳል ኢሳ 6
ለዳንኤል በራዕይ በሽማግሌ ዳን 7÷13-14
ለብርሃም በሦሥትነት እና አንድነት እንደ ሰው በሽማግሌ አምሳል ዘፍ 1÷9፡18 በመሆን ተገልጦላቸዋል፡፡

ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ በሀዲስ ኪዳን ባሕርየ መለኮትን ከባሕርየ ሰብእ አካለ መለኮቱን ከአካለ ሰብእ ጋር በተዋህዶ አንድ እስካረገበት ጊዜ ድረስ አካለ መለኮትን ያየው አንድስ እንኳን የለም በተዋህዶ አየነው እንጂ፡፡ በተዋሕዶ አምላክ ሰው በመሆኑ ሰውና መላእክት እግዝአብሔርን አዩት፡፡

፮ኛ. የእግዚአብሔር በራሱ መኖር፡-
ይህ ባህሪ (ጠባይ) በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ እንጂ ለማንኛውም ፍጡር የሌለው የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ የእግዚአብሔር በራሱ መኖር ስንል ለአኗኗሩ ምንም ምን ምክንያት ያለው ሲሆን ለመኖሩ ምንም ምክንያት የሌለው ለራሱ የሚኖር ነው፡፡ እርሱ በራሱ የሚኖር ሲሆን ፍጥረታት ግን በእግዚአብሔር አስገኝነት የሚኖሩ ናቸው፡፡

ጌታችን መድኀነ ዓለም እየሱስ ክርስቶስ በዮሐ 5÷26 ላይ አብና ወልድ በእነርሱም ህልው ሆኖ ያለው መንፈስ ቅዱስ በራሳቸው እንደሚኖሩ ወይም በራሳቸው ሕይወት እንዳላቸው የገለጠው በማያሻማ ቃል ነው፡፡ ዮሐ. 5÷26 “አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና›› በማለት አስተምሮናል፡፡

፯ኛ. የማንም ዕርዳታ የማያስፈልገው መሆኑ፡-
እግዚአብሔር አምላክ ለሀሣቡ አማካሪ ለድርጊቱ አጋዥ የማይሻ ሁሉን እንዳሠበ እንደወደደ ያለከልካይ ያለ አማካሪ ያለረዳት መፈፀም የሚቻለው ሁሉን በራሱ ፈቃድ፣ኃይል፣ሥልጣን ያለ እንከን እና ጉድለት የሚያከናውን ነው፡፡

ቅዱሳን መጽሐፍም የእግዚአብሔርን ያለማንም አጋዥነት ሁሉን አድራጊ መሆን እንደሚከተለው ይገልጹታል፡-

ሐዋሥ 17÷25 “ሕይወትና እስትንፋስን ÷ሌሎችንም ነገሮች ለሰው ሁሉ የሚሰጥ እርሱ ስለሆነ ምንም ነገር አይጐድለውም ÷ የሰውም እርዳታ አያስፈልገውም”
ሮሜ 11÷34 “የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም የእርሱ አማካሪ የሚሆን የለም››
ኢሳ 40÷13-14 “የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ ወይም አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማነው? ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንግድ ማን አስተማረው? ዕውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው?”

፰ኛ.የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት፡-
እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት፡- - እግዚአብሔር ከዘመን በላይ የሆነ ዘላለማዊ በመሆኑ ያለፈውን የአሁነንና የወደፊቱን በግልጥ የሚያውቅ የሚሆነው ነገር ከመሆኑ አስቀድሞ የሚያውቅ በፊቱ አንዳች የሚሰወር ነገር የሌለ ኃያል አዋቂ አምላክ ነው፡፡ አንድን ነገር ከመታሠቡ በፊት አስቀድሞ የሚያውቅ አዋቂ ነው፡፡
- እግዚአብሔር የሚሆነውን አስቀድሞ በጐውንም ክፉውንም ያውቀዋል ሲባል የሰውን ልጅ ነፃ ፈቃድና ፍላጐት አይገድበውም፡፡ የእግዚአብሔር አስቀድሞ ማወቅ ደግሞ እርሱ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራዋል ማለት አይደለም ወይም ሰው ሁሉ እግዚአብሔር የወሰነለትን እንጂ ሌላ ነገር ለማድረግ ነፃነት የለውም ማለት አይደለም፡፡
- በእግዚአብሔር ዘንድ ያለው የባሕርይ እውቀት እጅግ ፍፁምና ከፍጹምነት በላይ የሆነ ነው፡፡ በእርሱም በባሕር ያለውን አዋቂነት ቅዱሣት መጽሐፍት እንዲህ ሁሉ አዋቂነቱን በፊቱም የሚሸሸግ የሌለ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

1ኛ ዜና 28÷9 “እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራል፤የነፍስንም ሀሳብ ሁሉ ያውቃል፡፡” መዝ 139÷15-16 “አጥንቶቼ በመሠራት ላይ እንዳሉ በእናቴም ማሕፀን በጥንቃቄ በመገጣጠም ላይ እንዳሉ፤ እዚያም በስውር በማድግበት ጊዜ በዚያ መሆኔን አንተ ታውቅ ነበረ ከመወለዴ በፊት አየኸኝ ለእኔ የተወሰኑልኝ ቀኖቼ ገና ከመጀመራቸው በፊት በመዝገብ ሠፍረዋል፡፡” ኤር 23÷24 “ሰው በስውር ቢሸሸግ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርን የሞላሁ እኔ አይደለሁምን፣ ይላል እግዚአብሔር፡፡” ዕብ 4÷13 “ከእግዚአብሔር ፊት የሚሰወር ምንም ፍጥረት የለም ለእርሱ ፊት ሁሉ ነገር ግልጥና እርቃኑን ሆኖ የሚታይ ነው፡፡” ኤር 17÷10 “እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ እንድመራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኩላሊትንም እፈትናለሁ፡፡”

2.5 የምዕራፉ ማጠቃለያ
የሃይማኖት መሠረት የፈጣሪ መኖር ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም የፈጠረ እግዚአብሔር ነው ብሎ ማመን ነው፡፡

ፈጣሪ በባህርዩ በፍጥረታት የማይመረመር ቢሆንም ራሱን ግን ያለምስክር አልተወም፤ ማለትም ህልውናውን የሚያስረዱ ምስክሮችን ሰጥቷል፡፡ ከነዚህም ውስጠ ሥነ-ፍጥረት፣ የሰው ልጅ የሕሊና ምስክርነት፣ ፈጣሪ ከሰው ጋር ያደረገው ንግግርና የሰው ልጅ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የገለጠው ህልውናውን ብቻ ሳይሆን ባሕርይውን /ሕያውነቱን፣ ምሉዕነቱን፣ ቅዱስነቱን፣…/ እና ግብሩን /ፈጣሪነቱን፣ ከሃሊቱን፣ መጋቢነቱን፣ አዳኝነቱን፣…/ እሱነቱን በጠቅላላ የሚገልጥ ስሙንም ነው፡፡ ይህም ስም በእስራኤላውያን ቋንቋ “ያህዌ” ሲሆን በግዕዝ “እግዚአብሔር” በሚለው ተተክቷል፡፡