Advertisement Image

ትምህርተ ሃይማኖት

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የትምህርተ ሃይማኖት ምዕራፎች

ምዕራፍ ሦስት : ሥነ-ፍጥረት

፫.፩ የሥነ-ፍጥረት ትርጉም
ሥነ ፍጥረት የሁለት ቃላት ጥምረት ነው፡፡ “ሥነ” ያለው “ሠነየ” መልካም ሆነ፣ አማረ፣ ተዋበ፣ በጀ ካለው የግዕዝ ግሰ የተወሰደ ሲሆን መልካምነት፣ መበጀት፣ ውበት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሥነ-ፍጥረት የሚለው ጣምራ ቃል በሁለት መልኩ ሊተረጎም ይችላል፡፡

፩ኛ. በተናባቢ ሲፈታ የፍጥረት መበጀት፣ የፍጥረት ማማር ማለት ይሆናል
፪ኛ. በቅጽል ሲፈታ /ሥነ የሚለው ቃል ፍጥረት ለሚለው ቃል ገላጭ ሲሆን/ የበጀ ፍጥረት ያማረ ፍጥረት ማለት ይሆናል፡፡

እግዚአብሔር በከሃሊነቱ፣ ወሰን ድንበር በሌለው ዕውቀቱ የፈጠረው ፍጥረት ሁሉ የበጀ በየሁኔታውም ብቁ ያማረ ፍጥረት ነውና ሥነ-ፍጥረት ተብሏል፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም የፈጠረውን ሁሉ እጅግ መልካም እንደሆነ አየ›› እንዲል፡- /ዘፍ. ፩፥፴፩/

ሥነ-ፍጥረት ስንዐ ፍጥረት የፍጥረት መስማማት፣ የተስማማ ፍጥረት ተብሎም ይተረጎማል፡፡ ይህም የፍጥረት መገኛ የሆኑት ፬ቱ ባሕርያት /እሳት፣ ውኃ፣መሬትና ነፋስ/ የማይስማሙ ሲሆኑ በእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል ተስማምተው ስለሚኖሩ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለነዚህ ባሕርያት መስማማት እንዲህ ብሏል፡፡

‹‹ወአስተነዓዎሙ በበይናቲሆሙ እንዘ ዘዘዚአሁ ግእዘ ጠባይዒሆሙ - የየጠባያቸው ሥራ የተለያየ ሲሆን እርስ በእርሳቸው አስማምቷቸዋል›› /ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን ፪/

እግዚአብሔር ፍጥረታትን ለምን ፈጠረ?

እግዚአብሔር ፍጥረታትን ከመፍጠሩ በፊት በቅድምና የነበረ ነው፡፡ በቅድምናም ሲኖር ፍጥረትን ከመፍጠሩ በፊት አንዳች የጎደለበት ነገር አልነበረም፡፡ በገዛ ባሕርይውም ይመሰገን ነበረ፡፡ ይህም ፍጥረትን የፈጠረው የጎደለበት ኖሮ ፍጥረት እንዲሞላለት አለመሆኑን ያስረዳል፡፡

‹‹እምቅድመ ይፈጥር መላእክተ ለቅዳሴ አኮ ዘተጸረዐ ስብሐተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፤ መላእክትን ለምስጋና ከመፍጠሩም በፊት የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ምስጋናቸው የተቋረጠ አይደለም›› /ቅዳሴ ዘሰለስቱ ምዕት/

በመጽሐፈ ቀሌምንጦስም እንዲህ የሚል ተጽፏል፡፡ ‹‹ይቅርታዬንና ክብሬን አሰጣቸው ዘንድ ነው እንጂ ከነሱ እጠቀም ብዬ አልፈጠርኳቸውም›› /ቀሌምንጦስ/

እግዚአብሔር ፍጥረታትን የፈጠረበት ዓላማ የሚከተሉት ናቸው፡-

፩ኛ.ሰውና መልእክት ስሙን እንዲቀድሱት ክብሩን እንዲወርሱት ፈጥሯቸዋል፡፡ /ኢሳ. ፵፫፥፯/፤ ኢፌ. ፪፥፲/

፪ኛ.የቀረውን ፍጥረት ለአንክሮ ለተዘክሮ /የሕልውናው መታወቂያ እንዲሆኑ/ እና ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ እንዲሆኑ ፈጥሯቸዋል፡፡ ለአንክሮ ለተዘክሮ ተፈጥረዋል ማለት ሥነ-ፍጥረትን በመመልከት፣ በመመራመር ሥራው እንዲደነቅ ህልውናው እንዲታወቅ ተፈጥረዋል ማለት ነው፡፡ ይኽውም ሸማን ስናይ ሸማኔ፣ ሸክላን ስናይ ሸክላ ሠሪ፣ ሕንፃን ስናይ ሐናጺ መኖሩን እንደምናውቅ ሁሉ በጥበብ የተፈጠረውንም ፍጥረት ስናይ ፈጣሪ እንዳላቸው ያስረዳልና ነው፡፡
‹‹የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኃይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል››እንዳለ፡፡ /ሮሜ. ፩፥፳/

ለምግበ ሥጋ ተፈጥረዋል የተባሉትም አዝዕርቱን፣ አትክልቱን፣ ፍራፍሬውን የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ለምግበ ነፍስ የተፈጠሩትም እንደ ስንዴውና፣ ወይኑ ያሉት ናቸው፡፡ የሕይወት /የነፍስ/ ምግብ ሥጋውና ደሙ ይዘጋጅባቸዋልና፡፡

፫.፪ የስድስቱ ቀናት ፍጥረታት
እግዚአብሔር ፍጥረታትን ለመፍጠር የተጠቀመባቸው ዕለታት ፮ ናቸው፡፡ እነርሱም እሁድ፣ ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረብዕ፣ ኅሙስና አርብ ናቸው፡፡ እነዚህን ዕለታት ቀድመን መዘርዘራችን በየዕለቱ በየተራ የተፈጠሩትን ለመመልከት ያስችለን ዘንድ ነው እንጂ ዕለታቱ ከፍጥረታቱ ቀድመው ተገኝተዋል ለማለት አይደለም፡፡ ዕለታቱ በእያንዳንዳቸው ፍጥረታት ሲፈጠሩባቸው የተፈጠሩና የተገኙ ናቸው፡፡

፩ኛ. ካለመኖር ወደ መኖር /እምኃበ አልቦ ኅበ ቦ/ በማምጣት፡- በዚሁ መልኩ የተፈጠሩት ፍጥረታት እግዚአብሔር በሥልጣኑ ቀድሞ ካልተገኘ ነገር ያስገኛቸው ናቸው፡፡
፪ኛ. ከተፈጠረው በመፍጠር /ግብር እም ግብር/፡- በዚህ መልኩ የተፈጠሩት ፍጥረታት ደግሞ አስቀድሞ ከተፈጠረ ነገር የተገኙ ናቸው፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ወገኖች የፈጠራቸውን ፍጥረታት ያስገኘባቸው ደግሞ ሦስት መንገዶች አሉ

፩. በማሰብ /በሐልዮ/ :- እግዚአብሔር በዚህ መልኩ ከፍጥረታት ወገን ያስገኛቸውን የፈጠረውን በቃሉ ሳይናገር በእጁም ሳይሰራ በሕሊናው በመፍቀድ ብቻ ነው፡፡

፪ኛ. በመናገር /በነቢብ/ እግዚአብሔር በዚህ መንገድ የፈጠራቸውን ፍጥረታት ያስገኘው ደግሞ ይሁን ብሎ በቃሉ አዝዞ ነው፡፡

፫ኛ. በሥራ /በገቢር/ እግዚአብሔር ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በሥራ /በገቢር/ ያስገኘው አዳምን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመፍጠር ስልጣኑ ‹‹ ሰውን በመልካች እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር›› ብሎ ከምድር አፈር ሠርቶታል /አበጃጅቶታል/፡፡ /ዘፍ. ፪፥፫/ ይህንንም ልበ አምላክ ዳዊት እንዲህ ገልጾታል ‹‹እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም›› /መዝ. ፻፲፰፥፸፫/

፫.፪. ፩ ዕለተ እሑድ
እሑድ የሚለው ስም አሐደ አንድ አደረገ ከሚል የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉምም አንድ፣ አንደኛ፣ መጀመሪያ ማለት ነው፡፡ የፍጥረት የመጀመሪያ ቀን ነውና፡፡

እግዚአብሔር በዚህ ዕለት ራሱን ዕለቱንና ሌሎች ፍጥረታትን ፈጥሯል፡፡ እነዚህም ፍጥረታት፡-
፩ኛ. እሳት ፪ኛ. ነፋስ ፫ኛ. ውኃ ፬ኛ. መሬት
፭ኛ. ጨለማ ፮ኛ. ሰባቱ ሰማያት ፯ኛ. መላእክት ፰ኛ.ብርሃን ናቸው፡፡

እግዚአብሔር ፍጥረታቱን ያስገኘበት ሁኔታ እንደሚከተለው ነው፡፡

በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት /ከሌሊቱ ፩ ሰዓት/፡-

በዚህ ሰዓት አራቱ ባሕርያት የተባሉት (መሬት፣ ውኃ፣ እሳት፣ ነፋስ) እና ጨለማን እምኅበ አልቦ /ካለመኖር/ አምጥቶ በሐልዮ በመፍቀድ ብቻ ፈጥሯቸዋል፡፡

የአራቱ ባህርያት ምሳሌነታቸው

እግዚአብሔር ለፍጥረታት ከሚሰጡት ጥቅም፣ ለአንክሮ ለተዘክሮ ከመፈጠራቸውም ባሻገር በባሕርዬ አራት ነገሮች አሉ ሲል አስቀድሞ አራቱን ባሕርያት ፈጥሯቸዋል፡፡ ይኸውም፡-

1. በባሕርዬ ኃያል ነኝ ሲል ፡- እሳትን ፈጠረ

- እሳት፡- ኃያል ነው ውኃ ካልከለከለው ደረቁንም እርጥቡንም ልብላ (ላጥፋ ) ቢል ይቻለዋል፡፡
- ጌታም ፡- እንዲሁ ከሀሊነቱ፣ ምሕረቱ ካልከለከለው በቀር ትልቁንም ትንሹንም ፣ ክፉውንም መልካሙንም አንድ ጊዜ ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፡፡ ስለዚህኃያልነቱ በእሳት ይመሰላል፡፡
መዝ 7÷11- 12 ፡- እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ ነው ኃይለኛም ታጋሽም ነው ሁል ጊዜም አይቆጣም›› እንዲል፡፡

2. ፈታሒ (እውነተኛ ፈራጅ ) ነኝ ሲል ነፋስን ፈጠረ

- ነፋስ ፡- ፈታሒ ነው ገለባን ከፍሬ ፣ፍሬን ከገለባ ይለያል እንደዚሁም - ጌታም ፡- ጻድቃንን ከኃጥአን ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያልና እውነተኛ ዳኝነቱ በነፋስ ይመሰላል፡፡

- መዝ 7÷11፣ መዝ 9÷16 ‹‹የአምር እግዚአብሔር ገቢረ ፍትሕ / እግዚአብሔር ፍርድን በማድረግ የታወቀ ነው ›› እንዲል፡፡
- ሉቃ 3÷17 ፡- ‹‹መንሹም በእጁ ነው አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል ስንዴውንም በጎተራው ይከታል ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል››
- ማቴ 25÷32 ፡- ‹‹እረኛ በጎቹን ከፍየል እንደሚለይ አርስ በእርሳቸው ይለያቸዋል፡፡ በጎችን በቀኝ ፍየሎችን በግራ ያቆማቸዋል፡፡›› እንዲል፡

3. ርኅሩኅ ነኝ ሲል አንድም መንጽሒ (የማነጻ) ነኝ ሲል ውኃን ፈጠረ

- ውኃ ፡- መንጽሒ (የሚያነጻ) ነው፤ ያደፈውን የሚያነጻ የቆሸሸውን የሚያጠራ ነው፡፡

- ጌታም ፡- ኃጢያተኛ ኃጢአቱን አምኖ ማረኝ ብሎ ቢቀርበኝ ከኃጢያቱ አነጻዋለሁ ሲል ውኃን ፈጥሮታል፡፡
- ቅዱስ ዳዊት፡-መዝ 50÷1 ‹‹ እንደ ቸርነትኅ መጠን ማረኝ እንደ ምህረትህም ብዛት መተላለፊን ደምስስ ከበደሌም ፈጽሞ እጠበኝ ከኃጢያቴም አንጻኝ ››
- በት/ሕቡአትም ‹‹ ወኃበነ ማየ መንጽሔ ዚአነ / ሀብተ ንጽህ ሀብተ ሕይወት የሚሆን ሚያድን የጥምቀት ውኃን አደለን ›› በማየ ጥምቀት ከኃቲአት አዳነን፡፡ ት/ኅቡ/አልመስጦጊያ ምዕ 2÷ 7

4. ባለጠጋ ነኝ ሲል መሬትን ፈጠረ

- መሬት ፡- ሁሉ ነግር ይገኙበታል ለፍጡራን የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ታስገኛለች
- መዝ 64፣9 ፡- ‹‹ ምድርን ጎበኘሃት አጠጣሃትም ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ››
- ጌታም ፡- በባሕርየ ብሰጥ የማይጎድልብኝ ባለጸጋ ነኝ ሲል ምሳሌ ትሆነው ዘንድ መሬትን ፈጠረ፡፡
- በመዝ 84፣12 ‹‹እግዚአብሔርም በጎ ነገርን ይሰጣል ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች›› እንዲል አንድም፡-
- ምድር ፡- ከሀሊ (ሁሉን ቻይ ናት) ናት ፈጣሪዋ እግዚአብሔር በሰጣት ፀጋ ጌታ የፈጠረውን ፍጠርት ሁሉ ችላ ትኖራለች ፡፡ እነደዚሁም፡-
- ጌታም ፡- ሁሉን ችሎ ሁሉን ታግሶ ፀጋውን ለፍጥረቱ ሰጥቶ ይኖራል

ለምሳሌ ፡- ኃጥኡን ከጻድቁ ፣አማኒውን ከኢአማኒው ሳይለይ ሁሉን ችሎ ታግሶ ብርሃኑን እያበራ ፣ዝናሙን እያዘነበ በመግቦቱ እየመገበ ያኖረዋል፡፡በፍርድ ቀን ግን ለሁሉ እንደየስራው ይሰጠዋል እስከዛው ግን በከኃሊነቱ ይታገሳል በዚህም ከኃሊ ነኝ ሲል መሬት ፈጠረ፡፡

እግዚአብሔር አራቱን ባሕርያት ሲፈጥር ሦስት ሦስት ጠባይ (ግብር) እንዲኖራቸው አድርጎ ነው፡፡ይኸውም በባሕርዬ አንድነት ሦስትነት እንዳለ እወቁ ሲል ነው፡፡

- የእሳት ግብሩ ( ጠባዩ) ፡- ማቃጠል፣ ብሩህነት፣ደረቅነት ነው፡፡
- የነፋስ ግብሩ (ጠባዩ) ፡- አርጥብነት ፣ማቃጠል እና ጨለማነት ነው፡፡
- የወኃ ግብሩ ( ጠባዩ) ፡- ብሩህነት ፣እርጥብነት እና ቀዝቃዛነት ነው፡፡
- የመሬት ግብሩ (ጠባዩ) ፡- ደረቅነት ፣ቀዝቃዛነት እና ጨለማነት ነው፡፡

ከሌሊቱ ፪ ሰዓት እስከ ሌሊቱ ፱ ሰዓት

በነዚህ ሰዓታት ከእሳት ዋዕዩን /ማቃጠሉን፣ሙቀቱን/ ትቶ ብርሃኑን ነስቶ /ወስዶ/ ሰባቱ ሰማያትን ፈጥሯል፡፡ የሰባቱ ሰማያት አፈጣጠርም እንደሚከተለው ነው፡፡

፩ኛ. ከሌሊቱ ፪ ሰዓት መንበረ መንግሥትን ፈጠረ፡፡ ከጽርሐ አርያም በታች ከሰማይ ውዱድ በላይ የምትገኛ ናት፡፡ መጠኗ የምንኖርባት ዓለም የሚያህል፣ ከዳር እስከ ዳር የማይደርስ፣ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላት ናት፡፡ በዚህች ሰማይ እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በወደደው መልክ ይገለጥላቸዋል፡፡ /ኢሳ. ፮፥፩፤ ሕዝ. ፩፥፳፮፤ ራዕ. ፬፥፪/

፪ኛ. ከሌሊቱ ፫ ሰዓት ጽርሐ አርያምን ፈጠረ፡፡ ይህች ሰማይ ከሰማያት ሁሉ በላይ ናት፡፡ መጠኗም ይህን ያህላል፣ ድንበሯም እስከዚህ ድረስ ነው ብሎ ከፍጥረታት ወገን የሚያውቃት የለም፡፡

፫ኛ. ከሌሊቱ ፬ ሰዓት ሰማይ ወዱድን ፈጠረ፡፡ ይህች ሰማይ ኪሩቤል የሚሸከማት ለመንበረ መንግሥት እንደ አዳራሽ ወለል የሆነችና መንበረ መንግሥት እንደ ዙፋን የተዘረጋባት ናት፡፡

፬ኛ. ከሌሊቱ ፭ ሰዓት ኢየሩሳሌም ሰማያዊትን ፈጠረ፡፡ ሌላው ስሟ መንግስተ ሰማያት ነው፡፡ ቀዳም ሳጥናኤል የተፈጠረባት፣ ክዶ ቢወጣ ለምዕመናን የተሰጠች ናት፡፡ በመካከሏ የእመቤታችን ምሳሌ የሆነ የብርሃን ታቦት /ታቦት ዘዶር/ ይገኝባታል፡፡ /ራዕ. ፲፩፥፲፱/

፭ኛ. ከሌሊቱ ፮ ሰዓት ኢዮርን ፈጠረ፡፡

፮ኛ. ከሌሊቱ ፯ ሰዓት ራማን ፈጠረ፡፡

፯ኛ. ከሌሊቱ ፰ ሰዓት ኤረርን ፈጠረ፡፡

ኢዮር፣ ራማና ኤረር ዓለመ መላእክት /የመላእክት ከተሞች/ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ምክንያቱም መላእክት በየነገዳቸው የሰፈሩባቸው ቦታ ናቸው፡፡

ከሌሊቱ ፱ ሰዓት እስከ ፲፪ ሰዓት

በነዚህ ሰዓታት እግዚአብሔር መላእክትን በችሎታው ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ፈጥሯል፡፡ በአንዳንድ መጻሕፍት /መዝ. ፻፫፥፬፤ መቃ. ፲፫፥፲፭፤ ድርሳነ ሚካኤል ዘኅዳር/ ቅዱሳን መላእክት ከእሳትና ከነፋስ ተፈጥረዋል ተብሎ መጠቀሱ መላእክት እሳትና ነፋስን በግብር መምሰላቸውን ለማመልከት ነው፡፡ ይህም ማለት እሳት ረቂቅ ነው፣ መላእክትም ረቂቃን ናቸው፣ ነፋስ ፈጣን ነው መላእክትም ለተልእኮ ፈጣን ናቸው ለማለት ነው፡፡
‹‹ ሶበስ ተፈጥሩ እምነፋስ ወነድ እሞቱ ወእማሰኑ ከማነ - ከነፋስና ከእሳትስ ተፈጥረው ቢሆን እንደ እኛ ታማሚ ሟች በሆኑ ነበረ ››እንዲል፡፡ /አክሲማሮስ/

የተፈጠሩ መላእክት መቶ ነገድ ናቸው፡፡ አፈጣጠራቸውም እንደሚከተለው ነው፡፡

፩ኛ. ከሌሊቱ ፱ ሰዓት በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ያሉትን መላእክት ፈጥሯቸዋል፡፡
፪ኛ. ከሌሊቱ ፲ ሰዓት በኢዮር ያሉትን መላእክት ፈጥሯቸዋል፡፡
፫ኛ. ከሌሊቱ ፲፩ ሰዓት በራማ ያሉትን መላእክት ፈጥሯቸዋል፡፡
፬ኛ. ከሌሊቱ ፲፪ ሰዓት በኤረር ያሉትን መላእክት ፈጥሯቸዋል፡፡

ኢዮር ከላይ ወደታች አራት ከተማ ሲኖራት በእያንዳንዱ አስር አስር ነገደ መላእክትን አስፍሮበታል፡፡

- በመጀመሪያው ከተማ ያሉትን አስሩን ነገድ አጋዕዝት ብሎ ሰየማቸው ሳጥናኤልን በእነሱ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው፡፡
- በሁለተኛው ከተማ ያሉትን ኪሩቤል ብሎ በየስማቸው ኪሩብን አለቃቸው አደረገው፡፡
- በሶስተኛው ከተማ ያሉትን ሱራፌል ብሎ ሰየማቸው ሱራፌን አለቃቸው አደረገው
- በአራተኛው ከተማ ያሉትን ኃይላት አላቸው ሚካኤልን አለቃቸው አደረገው፡፡

ራማ ከላይ ወደታች ሶስት ከተማ ሲኖራት በእያንዳቸው አስር አስር ነገደ መላእክት አስፍሮበታ፡፡

- በራማ በላይኛው (በመጀመሪያዋ) ከተማ ያሉትን አርባብ ብሎ ስየማቸው ገብርኤልን አለቃ አድርጎ ሾመላቸው፡፡
- በሁለተኛው ከተማ ያሉትን መናብርት ብሎ ሰየማቸው፡፡ ሩፋኤልን አለቃቸው አድርጎ ሾመላቸው፡፡
- በሶስተኛው ከተማ ያሉትን ስልጣናት ብሎ ሰየማቸው፡፡ ሱርያልን አለቃቸው አድርጎ ሾመላቸው፡፡

ኤረርንም እንደ ራማ በሶስት ከተማ ከፍሏት በእያንዳንዱ ከተማ አስር አስር ነገድ አስፍሮባታል፡፡

- በኤረር በመጀመሪያዋ ከተማ ያሰፈራቸውን መኳንንት በሁለተኛዋ ከተማ ያሉትን ሊቃናት በሶስተኛዋ ከተማ ያሉትን መላእክት ብሎ ሰይሟቸዋል፡፡ ለመኳንንት ስዳካኤልን ለሊቃናት ሰላታኤላን ለመላእክት እናንኤልን አለቃ አድረጎ ሾሞላቸዋል፡፡

እሑድ ቀዳማይ ሰዓተ መዓልት (እሑድ ከንጋቱ ፩ ሰዓት)

እግዚአብሔር አምላክ ቅዱሳን መላእክትን ከፈጠራቸው በኃላ በባሕርዩ ረቂቅ ነውና አብሯቸው ሳለ ተሰወረባቸው፡፡ ይህም መላእክቱ ከእግዚአብሔር በአገኙት እውቀት ተመራምረው እርሱን ፈጣሪያቸውን እንዲያውቁ ነው፡፡ ከዚህ በኃላ መላእክት "ማን ፈጠረን?" "ከወዴት መጣን?" እያሉ መመራመር ጀመሩ፡፡ ሳጥናኤልም ከሁሉም የበላይ ሆኖ ተፈጥሯልና ከወደታች መላእክት ይህን ሲነጋገሩ ቢሰማ ከወደ ላይ ግን ድምፅን ቢያጣ "እኔ ፈጠርኳችሁ" ብሎ ሐሰትን ከራሱ አመንጭቶ ተናገረ፡፡ በዚህ ሰዓት በመላእክት ዘንድ ታላቅ ሽብር ሆነ፡፡ ከዲያብሎስ የሐሰት ልቦና መንጭታ የወጣች ይህች የአመጽ ንግግር በአለቅነት የተሾመላቸው ፲ሩን ነገድ በሶስት ወገን ከፋፈላቸው፡፡ (ሄኖክ ፲፩÷፫፤ ዮሐ ፰)

፩ኛ. አዎን ሳጥናኤል ፈጥሮናል ያሉ አንድ ወገን
፪ኛ. ፈጥሮን ይሆን ወይስ አልፈጠረን ይሆን እያሉ የተጠራጠሩ ሁለተኛ ወገን
፫ኛ. ከዚያም ከዚህም ሳይሆኑ እንዲሁ ፈዘው የቀሩ ሶስተኛ ወገን

የቀሩት ፮ቱ ነገድ ከነገደ ሚካኤል ተጨምረው እርሱ በቦታ በበላይነት ስለሆነ ፈጠረን ካለ እኛም የበታቾቻችንን ፈጠርናችሁ እንባልን? ይህስ አይሆንም አሉ፡፡ በዚህ ሰዓት መላእከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ንቁም በበህላዌነ እስከ ነአምር ፈጣሪነ-ፈጣሪያችንን እስከምናውቅ ድረስ በያለንበት ጸንተን እንቁም ›› ብሎ መላእክቱን አረጋጋቸው፡፡

ሳጥናኤልንም ፈጠርኳችሁ ካልከን ፈጥረህ አሳየን አሉት፡፡ መፍጠር ተሳነው፡፡ በዚህ ጊዜ መላእክቱን ፈጽሞ እንዳያስታቸው ብሎ እሑድ በነግህ (ጠዋት ፩ ሰዓት) ‹‹ ለይኩን ብርሃን - ብርሃን ይሁን›› ብሎ ብርሃንን ፈጠረ፡፡ ብርሃኑን መዓልት ጨለማውን ሌሊት ብሎ ጠራው (ዘፍ ፩÷፭):: መላእክትም ብርሃኑ ዕውቀት ሆኗቸው ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ አሸናፊ እግዚአብሔር ምስጋናህ በሰማይና በምድር የመላ ነው›› ብለው አመስግነውታል፡፡ ዲያብሎስና ያመኑበት መላእክት ግን ከክብራቸው ተዋርደዋል፣ ወደ ጥልቁም ተጥለዋል (ኢሳ ፲፬÷፲፪-፲፮)

እሑድ ከጠዋቱ ፪ ሰዓት

በዚህ ሰዓት መንፈስ ቅድስ አንዱን ክንፉን ወደ ላይ አንዱን ክንፉን ወደታች አድርጎ ለመላእክት ታያቸው፡፡ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ ቅዱስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብለው ምስጢረ ሥላሴን አምልተው አስድተው ተናገሩ፣ ሃይማኖታቸውንም አጸኑ፡፡››

እሑድ ከቀኑ ፫ ሰዓት እስከ ቀኑ ፲፪ ሰዓት

እሑድ ከቀኑ ፫ ሰዓት እስከ ቀኑ ፲፪ ሰዓት በነዚህ ሰዓታት ቅዱሳን መላእክትን በየነገዳቸው ከአጋዕዝት ጀምሮ እስከ መላእክት ያሉትን ቀባቸው፣ ማለትም አእምሮን፣ የማያቋርጥ ምስጋናን ሰጣቸው፤ ሕማም ሞት ድካም እረፍት የሌለባቸው አደረጋቸው፡፡

፫.፪. ፪ ዕለተ ሰኑይ (ሰኞ ዕለት)
ሰኑይ ሰነየ ካለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ሁለት መሆንን ፣ ሁለት ማድረግን ያመለክታል፡፡ሰኑይ (ሰኞ)ሁለተኛ ዕለት ማለት ነው፡፡

በዚህ ዕለት እግዚአብሔር ራሱን ዕለቱንና ጠፈርን ፈጥሮአል፡፡ ጠፈርን የፈጠረ በመጀመሪያው ሰዓት ሌሊት (ከሌሊቱ በ ፩ ሰዓት) ነው፡፡ ጠፈር ከመፈጠሩ በፊት በዕለተ እሑድ የተፈጠረው ውኃ ከምድር እስከ ኤረር መልቶ አድሮ ነበረ፡፡ ያንን ውኃ ከ፫ ወገን ከፍሎታል፡፡

፩ኛ. አንዱን እጅ በዚህ ዓለም አስፍሮታል
፪ኛ. ሁለተኛውን እጅ ከላይ አሳፍሮታል፡፡ ይህም ውኃ ሐኖስ ይባላል፡፡
፫ኛ. ሦስተኛውን እጅ ‹‹ለይኩን ጠፈር ማዕከል ማይ ወማይ- በውኃና በውኃ መካከል ጠፈር ይሁን›› ብሎ በመካከል አጽንቶታል፡፡
‹‹በሁለተኛይቱም ቀን በሐኖስና በውቅያኖስ መካከል ጠፈርን አድርጓልና፡፡ በዚያችም ቀን ውኃዎች ተከፋፍለው እኩሌቶቹ ወደ ላይ ወጥተዋልና፣ እኩሌቶቹ ከጠፈር በታች ወደአለው ወደ ምድር መካከል ወርደዋና፣ በሁለተኛው ቀን ይህን ስራ ብቻ ሠራ›› እንዲል (ኩፋ ፪÷፱)

የሰኞ ፍጥረት ምሳሌ

ከላይ የሚገኙት ሁለቱ እጅ የውኃ ክፍሎች በላይ ተወስነው መኖራቸው እና አንዱ አጅ በዚህ ምድር መስፈሩ ምሳሌነቱ የሶስቱ አካላት የአብ፣የወልድ ፣ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነውይኸውም፡-

ከላይ የቀረው ሁለቱ እጅ ውኃ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲሆን በዚህች ምድር የሰፈረው ደግሞ የወልድ ምሳሌ ነው፡፡ አብና መንፈስ ቅዱስ ሥጋ ለብሰው በዚች ምድር አልተመላለሱም ፤ ወልድ ግን የሰውን ልጅ ለማዳን በመወለድ ግብሩ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ለሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ለመመላለሱ ምሳሌ ነው፡፡

፫-፪-፫ ዕለተ ሠሉስ (ማክሰኞ ዕለት)
ሠሉስ ሠለሰ ሦስት አደረገ ካለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ሦስተኛ ማለት ነው፡፡

በዚህም ዕለትም እግዚአብሔር ራሱን ዕለቱንና ፫ፍጥረታትን ፈጥሯል፡፡ (ዘፍ፩÷፩፪) እነዚህም፡-

፩ኛ. በመጥረቢያ የሚቆረጡ ዕፀዋትን /ዛፎችን…/
፪ኛ. በማጭድ የሚታጨዱ አትክልትን /ሣር መሰል ነገሮችን…../
፫ኛ. በጣት የሚለቀሙ አትክልትን /ፍራፍሬዎችን…./

ከላይ የተጠቀሱትን ፍጥረታት እግዚአብሔር በዚህ ዕለት ከመፍጠሩ በፊት አስቀድሞ የተፈጠሩትን እንደሚከተለው አደላድሏል፡፡

፩ኛ. ከሰኞ እስከ ማክሰኞ ከጠፈር በታች ምድርና ውኃ ተቀላቅለው ነበረ፡፡ ምድር ላይ የቀረውን አንድ እጅ ውኃ ለሦስት ከፍሎ አንዱን እጅ መሬት በታች አደረገው፤ ሁለተኛውን ደግሞ መሬትን አጎድጉዶ ውቅያኖስ አደረገው፡፡
፪ኛ. በዚህ ዕለት ከላይ ካየነው በተጨማሪ አምስቱ ዓለማተ መሬትን አደላድሏል፡፡

የማክሰኞ ፍጥረት ምሳሌነታቸው

ቅዱስ ኤፍሬም በውደሴ ማርያም ምስጋናው ‹‹ አንቲ ውዕቱ ገራህት ዘኢተዘራ ዘር ውስቴታ ዘር ወጻ እምኔኪ ፍሬ ሕይወት / አንቺ ዘር ያልተዘራብሽ እረሻ ነሽ ካንቺ የሕይወት ፍሬ ወጥቶብሻልና ›› በማለት እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዳመሰገናት ፡-

- ዘር ሳይዘራባት ፣ሳትታረስ፣ ፍሬ የስገኘችው ምድር ፡- በእመቤታችን ትመሰላለች፤ ይኸውም እመቤታችን የለሩካቤ (ያለ ወንድ ዘር) እውነተኛ የሕይወት ፍሬ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የማስገኘቷ ምሳሌ ነው፡፡ - እግዚአብሔር እነዚህን የማክሰኞ ፍጥረታት በሦስቱ ዓለማተ መሬት ማለትም፡- በምንኖርባት ምደር፣ በገነት እና በብሔረ ብፁአን አስገኝቷቸዋል፡፡

፫.፪. ፬ ዕለተ ረቡዕ (ረቡዕ ዕለት)
ረቡዕ ማለት አራተኛውን ዕለት የሚያመለክት ነው፡፡ በግዕዝ ራብዕ ማለት ነውና፡፡

በዚህ ዕለት እግዚአብሔር ራሱ ዕለቱን እንዲሁም በመጀመሪያው ሰዓት ሌሊት ቀኑንና ሌሊቱን ይለዩ ዘንድ ፫ ብርሃናትን በሰማይ ጠፈር ላይ ፈጥሯል፡፡ (ዘፍ ፩÷፲፬) እነርሱም ፀሐይ ጨረቃና ከዋክብት ናቸው፡፡

የፀሐይ ተፈጥሮ ከእሳትና ከነፋስ ነው፡፡ ጨረቃና ከዋክብትን ግን ከነፋስና ከውኃ አርግቶ ፈጥሯቸዋል፡፡ ከዚህ በኃላ ‹‹ለይኩን ብርሃን›› ብሎ ከፈጠረው አንደኛው ብርሃን የስንዴን ቅንጣት ያህል አምጥቶ ያንን ከ7 እጅ ከፍሎ 6ቱን እጅ ለፀሐይ አደረገ፡፡ የቀረውን አንዱን እጅ እንደገና ከ7 ከፍሎ 6ቱን እጅ ለጨረቃ አደረገ፡፡ ቀሪውን አንድ እጅ ክዋክብትን እንደየ መጠናቸው ቅብቷቸዋል፡፡ ከዋክብትንም በብርሃን ሲቀባ አላልቅ ብለው ነበር፡፡ ‹‹ኮከብ ከኮከብ ይበልጣልና ›› እንዲል፡፡ (፩ ቆሮ ፩፮)

የረቡዕ ስነፍጥረት ምሳሌነታቸው

1. በ1ኛ ቆሮ 15፣40 ‹‹የፀሀይ ክብር አንድ ነው ፤የጨረቃም ክብር ሌላ ነው፤የካክብትም ክብር ሌላ ነው፡፡አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያያልና›› እንዲል የረቡዕ ፍጥረታት በክብር መበላለጣቸው ምሳሌነቱ የአንዱ ቅዱስ ክብር ከአንዱ ቅዱስ ክብር የመበላለጡ ምሳሌ ነው፡፡

ጌታ በወንጌል‹‹ … አንዱ መቶ አንዱ ሥልሳ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ፡፡›› ብሎ እንዳስተማረ
- ፀሐይ፡- የባለ መቶ
- ጨረቃ፡- የባለ ስልሳ
- ክዋክብት፡- የባለ ሠላሳ የሃይማኖት እና ምግባር ፍሬ የሚያፈሩ የቅዱሳን ምሳሌዎች ናቸው፡፡

2. አንድም ፀሀይ በምሳሌነቷ ለጻድቃንም ለሀጥአንም ምሳሌ ሆና ትነገራለች ይኸውም፡-

- ፀሀይ የጻድቃን ምሳሌ ናት ሲባል ፡- ፀሀይ ሁል ጊዜ ሙሉ እንደሆነች ጻድቃንምምግባር እና በሀይማኖት ምሉአን ናቸውና በፀሀይ ይመሰላሉ፡፡
- ፀሀይ የኃጥአን ምሳሌ ናት ፡- በዋዕይነቱ ፀንታ እንድትኖር ኃጥአንም በኃጢአታቸው ፀንተው የመኖራቻ ምሳሌ ነው፡፡ እንድም ፀሀይ ብርሃኗን ሳትለውጥ በምልአት እንደምትኖር ሁሉ ኃጥአንም በኃጢአት በክህደት ምሉዐን የመሆናቸወ ምሳሌ ናት፡፡

3. አንድም፡-ጨረቃ የጻድቃንም የኃጥአን ምሳሌ ሆና ትነገራለች

- ጨረቃ የጻድቃነ ምሳሌ ናት ሲባል፡- ጨረቃ ከብርሃኗ እንድ ጊዜ ስትጎድል አንድ ጊዜ ስትሞላ እንደምትኖር ፃድቃንም አንድ በሃጢያት ሲሰናከሉ በንስሃ እየሞሉ የመኖራቸው ምሳሌ ናት፡፡ - ጨረቃ በሃጥአን መመሰሏ፡- ጨረቃ በመጠኗ እያነሰች እንደምትሄድ ኃጥአንም ከእውቀትና ከምግባር እያነሱ የመሄዳቸው ምሳሌ ነው፡፡

፫.፪. ፭ ዕለተ ሐሙስ (ሐሙስ ዕለት)
ሐሙስ ሐምስ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን አምስተኛ የሚል ትርጉም አለው፡፡

በዚህ ዕለተ ራሱን ዕለቱንና ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ፍጥረታት እንድታስገኝ ትአዛዝ በመስጠት በደመ ነፍስ ሕይወት ሕያዋን የሆኑ ፫ ፍጥረታትን ፈጥሯል፡፡ እነዚህም፡-

፩ኛ. በልብ የሚሳቡ (ምሳሌ፡- ዓሣ አንበሪ)
፪ኛ. በእግር የሚሽከረከሩ(ምሳሌ፡- ዳክዬ)
፫ኛ. በክንፍ የሚበሩ (ምሳሌ፡- ዓሣ አውጭ) ናቸው፡፡

የሐሙስ ስነፍጥረት ምሳሌነታቸው

ለሚስጥረ ጥምቀት ነው
ባህር ፡- የጥምቀት 1ኛ ቆሮነ10÷2 ከባሕር ውስጥ የተገኙት ፍጥረታት የሰዎች ምሳሌ ሲሆኑ
ከባህር ወጥተው በየብስ የቀሩት የኢ-ጥሙቃን (ያልተጠመቁ) ሰዎች ፣
በባህር ውስጥ የቀሩት የጥሙቃን (የተጠመቁ) ሰዎች
አንዴ ከውኃ አንዴ ከየብስ የሚመላለሱ ደግሞ አንዴ ወደ ክርስትና አንዴ ወደ ኑፋቄ የሚወላውሉ ሰዎች ምሳሌ ናቸው፡፡

፫.፪. ፮ ዕለተ ዓርብ (ዓርብ ዕለት)
ዓርብ ዓርብ ካለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መካተቻ ማለት ነው፡፡ ይህም ዕለቱ የፍጥረት መካተቻ ፣ ማብቂያ/መፈጸሚያ መሆኑን ያመለክታል፡፡

በዚህም ዕለት እግዚአብሔር ራሱን ዕለቱንና በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት ከደረቅ ምድር በደመ ነፍስ ሕይወት ሕያዋን የሆኑ እንደ ሐሙስ ያሉ ፫ ፍጥረታትን ፈጥሯል፡፡ እነዚህም፡-

፩ኛ. ሣር ነጭተው ውኃ ተጎንጭተው የሚኖሩ እንሰሳት
፪ኛ. ሥጋ ቦጭቀው ደም ተጎንጭተው የሚኖሩ አራዊት እና
፫ኛ. ፍሬ ለቅመው ውኃ ጠጥተው የሚኖሩ አዕዋፍ ናቸው፡፡

የዓርብ ሦስቱ ስነፍጥረታት ምሳሌነታቸው

ለ ትንሳኤ ሙታን ነው እነዚህ ፍጥረታት የትንሳኤ ሙታን ምሳሌዎች ናቸው ፡፡ይኸውም እነዚህ ፍጥረታት መሬት ሁነው ሳለ እግዚአብሔር እንዲነሱ ሲያዝ ከመሬት ተነስተው ደመነፍስ ያላቸው ተንቀሳቃሽ እንደሚሆኑ ሁሉ በእለተ ምጽአትም እግዚአብሔር ሲያዝ ትብያ የነበሩ፣ አፈር ሁነው የነበሩ የሰው ልጆች ሕይወት ተዘርቶባቸው የመነሳታቸው (የትንሳኤ ሙታን) ምሳሌ ነው፡፡

በዕለተ ሐሙስና በዕለተ ዓርብ የተፈጠሩ ፍጥረታት ‹‹እንሰሳት›› በመባል አንድ ቢሆኑም በአኗኗራቸው ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ የሐሙስ ፍጥረታት በየብስ የአርብ ፍጥረታት በውኃ መኖር አይሆንላቸውምና፡፡

በዚሁ ዕለት በነግህ እግዚአብሔር ‹‹ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር›› ብሎ 4ቱን ባሕርያተ ሥጋ 5ኛ ባሕርየ ነፍስን አዋህዶ አዳምን ፈጥሮታል፡፡(ዘፍ ፩÷፳፮) ከፈጠረውም በኃላ የሕይወት እስትንፋስን እፍ ብሎበታል፡፡ በዚህም ሰውን ከሌሎች በደመ-ነፍስ ሕያዋን ሆነው ከሚኖሩበ እንሰሳት ለይቶ ክብርን ልጅነትን ሰጥቶ ለዘለዓለም ሕያው ፍጥረት አድርጎታል፡፡ (ዘፍ ፪÷፯)

እግዚአብሔር እስከ 6ኛው ዕለት የፈጠራቸው ፍጥረታት ፳፪ ናቸው፡፡ ብዙውን አንድ እያለን ብንቆጥር፡፡ እነዚህን ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ በ7ኛው ቀን አረፈ፡፡ (ዘፍ ፪÷፪፣ ኩፋ ፫÷፪-፫) አረፈ ማለት ደክሞት አረፈ ማለት ሳይሆን መፍጠሩን ተወ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኃላ አዳም በተፈጠረ በ፰ተኛው ቀን በሁለተኛው ዓርብ ረዳት የምትሆን ሔዋንን ፈጠረለት፡፡ (ዘፍ ፪÷፲፰)

፫.፫ ሃያው ዓለማት
እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት ብዙውን አንድ እያለን ብንቆጥር ፳፪ ሥነ-ፍጥረት እንዳለ ከላይ ተመልክተናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ (እሳት፣ ውኃ፣ መሬት፣ ነፋስ) ፳ ዓለማትን ፈጥሯል፡፡ ፈጥሯል ስንልም አደላድሏል፣ አከናውኗል ማለት እንጂ ሌላ አዲስ ፍጥረትን አስገኝቷል ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ሃያው ዓለማት ከ ፳፪ቱ ሥነ-ፍጥረት ውስጥ ተካተው የሚቆጠሩ ናቸው እንጂ ከ፳፪ቱ ሥነ-ፍጥረት ውጭ ሌላ ፍጥረታት አይደሉም፡፡ ሃያው ዓለማት የተፈጠሩት ከእሑድ አስከ ማክሰኞ ነው፡፡ ሃያው ዓለማት የሚባሉት

የዓለማቱ ስም ብዛት
፩ ዓለማተ እሳት ፱
፪ ዓለማተ ነፋስ ፪
፫ ዓለማተ ማይ ፬
፬ ዓለማተ መሬት ፭
ጠቅላላ ድምር ፳

፩ኛ. ዓለማተ እሳት

ዓለማተ እሳት የተፈጠሩት ከእሳት ግብር፣ ጠባይ (ብሩህነት፣ ውዑይነት፣ ይቡስነት) ነው፡፡ የተፈጠሩበት ዕለትም ዕለተ እሑድ ነው፡፡ ዓለማተ እሳት በቁጥር ዘጠኝ ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

- ሰባቱ ሰማያት
- ምጽንዓተ ሰማይና
- ገሃነመ እሳት ናቸው

እግዚአብሔር ከእሳት ባሕርይ ብሩህ ብሩሁን ወስዶ ሰባቱን ሰማያትንና ምጽንዓተ ሰማይን ፈጥሯል፡፡ ምጽንዓተ ሰማይ (የሰማይ መጽኛ ወይ መሠረት) እግዚአብሔር ሁሉም ሰማያት እንዲጸኑበት አድርጎ የፈጠረው የእሳት ጉዛጓዝ ነው፡፡ከዚህ በኋላ የእሳቱን ዝቃጭ (ጨለማውንና ፍሙን) ወደ ታች አውርዶ ገሃነመ እሳትን ፈጥሮበታል፡፡

፪ኛ. ዓለማተ ነፋስ

ዓለማተ ነፋስ በነፋስ የተመሉ በነፋስ የረጉ የጸኑ ናቸው፡፡ የተፈጠሩትም በዕለተ ሰኑይ ነው፡፡ዓለማተ ነፋስ የሚባሉት ሁለት ናቸው፡፡

ሀ- ባቢል፡- ይህ የረጋ ነፋስ ከጠፈር በላይ የሚገኝ ሲሆን ሐኖስ ተብሎ የሚጠራውን ውኃ የሚሸከመው ነፋስ ነው፡፡ ለ- ይህንን ዓለም የሚሸከመው ነፋስ፡፡

፫ኛ. ዓለማተ ማይ

እነዚህ ዓለማት ከውኃ የተፈጠሩ ውኃ የመላባቸው ዓለማት ናቸው፡፡ የተፈጠሩትም በዕለተ ሰኑይና በዕለተ ሠሉስ ነው፡፡ዓለማተ ማይ የሚባሉት ፬ ናቸው፡፡

፩ኛ. ሐኖስ፡- ይህ ብጽብጽ ውኃ የመላበት ከኤረር በታች የሚገኝ የውኃ ዓለም ነው፡፡ ይህን የውኃ ዓለም ባቢል የሚባል ነፋስ ይሸከመዋል፡፡
፪ኛ. ጠፈር፡- ይህ ግግር ውኃ ነው፡፡ ጥንተ ባሕርዩን በመጠኑ ስለለቀቀ እንደ አንድ ፍጥረት ተቆጥሯል
፫ኛ. ውቅያኖስ፡- ይህ መሬትን የሚከባት ውኃ ነው
፬ኛ. ከምድር በታች የሚገኝ ውኃ ፡- ልበ አምላክ ዳዊት የምድር መሠረት ስለሆነው ስለዚህኛው የውኃ ዓለም እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ምድርን በውኃ ላይ ያጸና›› (መዝ ፻፴፭፥፮)

ከአራቱ ዓለማተ ማይ ሐኖስና ጠፈር የተፈጠሩት በዕለተ ሰኑይ ሲሆን ውቅያኖስና የምድር መሠረት የሆነው የውኃ ዓለም የተፈጠሩት ደግሞ በዕለተ ሠሉስ ነው፡፡

፬ኛ. ዓለማተ መሬት

እነዚህ ዓለማት ከመሬት (ከአፈር) የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ዓለማተ መሬት የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፡፡

፩ኛ. ገነት፡- ቀድሞ ከበደል በፊት አዳምና ሔዋን የኖሩባት፤ ዛሬ በሃይማኖት ጸንተው ምግባር ሠርተው በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም የተለዩ ቅዱሳን በአካለ ነፋስ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የሚቆዩባት የዕረፍት፣ የሕይወት፣ የታደለና የደስታ ቦታ ናት፡፡ በዚች በገነት በፍሬ የተሞላች ፍሬዋን ለቅመው የማይጨርሷት፣ መዓዛ ጣዕሟ ልብን የሚመስጥ እፀ ሕይወት፤ ከወተት ይልቅ እጅግ የምትነጣ፣ ከማር ሰባት እጅ የምትጣፍጥ ማየ ሕይወት፣ በአራቱ ማዕዘን ዞረው ገነትን የሚያመጡ 4ቱ አፍላጋት (ወንዞች) ይገኙበታል፡፡

፪ኛ. ብሔረ ሕያዋን፡- አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ቅዱሳን በአካለ ሥጋ እያሉ ከዚህች ዓለም እየተነጠቁ በመሄድ የሚኖሩባት ናት፡፡ ከነዚህ ቅዱሳን ሰዎች መካከል ጻድቁ ሄኖክንና፣ ነቢዩ ኤልያስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ (ዘፍ፭÷፳፬-፪ ነገ ፪÷፩)

፫ኛ. ብሔረ ብጹዓን፡- ይህች ዓለም ከገቢረ ኃጢያት ፍጹም የተለዩ የጽድቅ ሥራን ብቻ የሚሠሩ ብጹዓን ሰዎች በሕይወተ ሥጋ የሚኖሩባት ናት፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ የብርሃን ምድር ናቸው፡፡ ከጠፈር ዝቅ ከምንኖርባት ምድር ከፍ ብለው የሚገኙ ሲሆን በዓይነ ሥጋ የማይታዩ (የተሠወሩ) ናቸው፡፡ ገነት በምሥራቅ ብሔረ ሕያዋን በሰሜን ብሔረ ብጹአን በደቡብ አቅጣጫ ይገኛሉ፡፡

፬ኛ. የምንኖርባት መሬት፡- ከአዳም በደል በኃላ ለሰው ልጆች መኖሪያ ሆና የተሰጠች ናት፡፡

፭ኛ. ሲዖል፡- የፀና ጨለማ የሞላበት፣ የሚያቃጥል እሳት ያለበት በምዕራብ አቅጣጫ ያለ ቦታ ነው፡፡ ኃጢያትን ሲሠሩ የኖሩ ሰዎች ከሞተ ስጋ በኃላ በአካለ ነፍስ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ እየተቀጡ የሚቆዩባት የቅጣት ቦታ ነች፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት 5ቱ ዓለማተ መሬት በብርሃን መጠን፣ በጥራትና በንጽሕና ይበላለጣሉ፡፡ ከሲኦል እኛ ያለንበት ዓለም ብሩህ ጥሩና ንጹሕ ነው፡፡ እኛ ካለንበት ዓለም ብሔረ ብጹዓን፣ ከብሔረ ብጹዓን ብሔረ ሕያዋን፣ ከብሔረ ሕይዋን ገነት ብሩህ ጥሩና ንጹሕ ነው፡፡