ምዕራፍ አራት : አዕማደ ምሥጢር
፬-፩ የምሥጢር ፍቺ በቤተ ክርስቲያን
ምሥጢር፡- አመሠጠረ ሠወረ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ዘይቤያዊ ፍቺው ለልብ ጓደኛ ብቻ የሚነገር በሁለት ሰዎች መካከል የሚቀር ማለት ነው፡፡
ይህን ዘይቤያዊ ፍቺ ግን ቤተ ክርስቲያን ምሥጢር አትለውም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የማያውቀው በሰዎች መካከል ብቻ ተወስኖ የሚቀር ነገር የለምና ነው፡፡ ሐናንያና ሰጲራ ከሰው ሁሉ ሠውረው የሠሩትን እግዚአብሔር ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደገለጸለት፡፡ (ሐዋ ፭፥፩-፰)
በቤተ-ክርስቲያን አፈታት ምሥጢር ማለት፡-
በምርምር ጥልቀት፣ በእውቀት ብዛት ሊደርስበት የማይችል፣ በሥጋ አእምሮ ሳይሆን በመንፈስ አእምሮ የሚረዱት ረቂቅና ጥልቅ ኀቡዕ (የተሰወረ) ነገር ማለት ነው፡፡
፬.፪ ምሥጢር የተባሉበት ምክንያት
ምሥጢር ማለት ከዕውቀት በላይ የሆነ በእምነት ብቻ የሚረዱት መሆኑን ተመልክተናል፡፡ አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትም ምሥጢር መባላቸው ከመምህራን ተምረው በልቦና መርምረው የሚያምኗቸው በዓይን የማይታዩ፣ በእጅ የማይጨበጡ ነገሮች የሚነገሩባቸው በመሆናቸው ነው፡፡ ሰው እነዚህን ምሥጢራት የሚረዳው የማይታየውን በምታስረዳና ተስፋን በምታስረግጥ በእምነት ነው፡፡ አዋቂ ፍጥረት የሆነው የሰው ልጅ ሁሉን የመመርመርና የመረዳት ሥልጣን ከአምላኩ የተሰጠው ቢሆንም የፈጣሪውን ባሕርይውንና ግብሩን በሞላ ለመረዳት ውሱን ከሆነው አቅሙ በላይ ስለሚሆንበት በእምነት መቀበል ብቸኛ አማራጩ ነው፡፡
፬.፫ አዕማድ የተባሉበት ምክንያት
አዕማድ፡- የሚለው ዐምድ የሚለው የግዕዝ ቃል ብዙ ቁጥር ነው፡፡ ዐምድ ማለት ትክል፣ ምሰሶ ማለት ነው፡፡ አዕማድ ማለት ደግሞ ምሰሶዎች ማለት ይሆናል፡፡
ምሥጢራቱ ምሰሶዎች መባላቸው ምሰሶ ቤትን ደግፎ እንደሚያጸና እነዚህም ቤተ-ልቡናን ከኑፋቄ /በክህደት መውደቅ/ የሚያጸኑ ስለሆነ ነው፡፡ ምሰሶ የሌለው ቤት ይፈርሳል፤ ይወድቃል፡፡ የቀና ሃይማኖት ያልተማረ፣ አምስቱን አዕማደ ምሥጢር ያላወቀ ክርስቲያንም በክህደት በጥርጥር ይያዛል፣ ሃይማኖትን ባለመያዙ ምግባር ባለመሥራቱ በመንጸፈ ደይን ይወድቃልና ነው፡፡
፬-፬ የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ዝርዝር አከፋፈል
፭ቱ አዕማደ ምሥጢራት የሚባሉት፡-
፩. ምሥጢረ ሥላሴ
፪. ምሥጢረ ሥጋዌ
፫. ምሥጢረ ጥምቀት
፬. ምሥጢረ ቁርባን
፭. ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡
ምሥጢረ ሥላሴና ሥጋዌ ነገረ መለኮት የሚነገርባቸው ምስጢራት ናቸው፡፡ ይህም የመለኮት ስሙን ግብሩን፣ ባሕርዩን እንዲሁም ምስጢረ ትስብእትን /ሰው የመሆንን ምስጢር/ የምንማርባቸው ናቸው፡፡
ምሥጢረ ጥምቀትና ምስጢረ ቁርባን የቤተ-ክርስቲያን ሀብታት ናቸው፡፡ ከ፯ቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን መካከልም የሚመደቡ ናቸው፡፡
ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ደግሞ ስለ ነገረ ሕይወት ማለትም ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት የምንማርበት ነው፡፡
በ፭ቱ አዕማደ ምሥጢራት ሁሉን አካቶ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይና ጠባይዓት፣ ስለሰው ልጅ በኃጢአት መውደቅና ዳግመኛ መዳን እንዲሁም ስለ ጽድቅና ኩነኔ መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእነዚህ በ፭ቱ አዕማደ ምሥጢራት ሃይማኖትን መግለጥ የመረጠው፡፡
‹‹…ሌሎችን አስተምር ዘንድ በቋንቋ ከሚነገር ብዙ ቃል ይልቅ በቤተ-ክርስቲያን በአእምሮዬ አምስት ቃላትን ልናገር እሻለሁ››/ቆሮ፲፬፣፱/
፬-፭ ምሥጢረ ሥላሴ
ሥላሴ፡- ሠለሰ ሦስት አደረገ ካለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ሦስትነት፣ ሦስት መሆን የሚል ፍቺ አለው፡፡ የምሥጢርን ፍቺ በገጽ 32 ተመልከት፡፡
ምሥጢረ ሥላሴ ስንልም የአንድነትን የሦስትነትን ነገር የሚነገርበት ምሥጢር ማለት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን አብነት በማድረግ ከቅዱሳን አባቶቻችን በተላለፈልን ትምህርት መሠረት እግዚአብሔርን በአንድነት በሦስትነት እናምነዋለን፤ እናመልከዋለን፡፡
፬.፭.፩ የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት
እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፣ ሦስት ሲሆን አንድ ነው፡፡
፬-፭-፩-፩ አንድነት በምን?
ሥላሴ በህልውና፣ እግዚአብሔር በመባል፣ በአምላክነት፣ በአገዛዝ፣ በሥልጣን፣ በመለኮት፣ በባህርይ፣ በልብ፣ በቃል በእስትንፋስ አንድ ናቸው፡፡ እነዚህንም በመሳሰሉት ሁሉ አንድ ናቸው፡፡ ‹‹እኔና አብ አንድ ነን፡፡›› እንዲል፡፡/ዮሐ. ፲፥፴/
እግዚአብሔር በአንድነቱ የሚታወቅበቸው ስሞች ፈጣሪ፣ አምላክ፣ ጌታ፣ መለኮት፣ እግዚአብሔር፣ አዶናይ፣ ኤልሻዳይ፣ ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ሀ. ሥላሴ በህልውና /በአኗኗር/ አንድ ናቸው፡፡
ህልውና ማለት አንዱ በአንዱ መኖር ማለት ነው፡፡ ይኽውም በኩነታት /በሁኔታዎች/ የሚገናዘብ ረቂቅ ምሥጢር ነው፡፡ ‹‹እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምኑምን?....እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ›› /ዮሐ ፲፬፥፲ እና ፲፮/
ሥላሴ በህልውና አንድ ስለሆኑ /አንዱ በአንድ ስላለ/ አብ ተጠራ ማለት አብን በተለየ አካሉ መጠቆም ቢሆንም ወልድና መንፈስ ቅዱስም በአብ ህልውና አሉ፡፡ ለወልድም ለመንፈስ ቅዱስም እንዲሁ ነው፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ሥራው የሦስቱም ሆኖ ሳለ ለአንዱ አካል ሰጥቶ የሚናገረው፡፡
ለአብ ሰጥቶ ሲናገር
‹‹እኔ የምነግራችሁን ይህ ቃልም ከራሴ የተናገርኩት አይደለም፤ በእኔ ያለ አብ እርሱ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ›› /ዮሐ. ፲፬፥፲/
ሥራውን ለአብ ሰጥቶ መናገሩ ቅድመ ዓለም በአብ ልብነት የታሰበውን በእኔ ቃልነት እናገራለሁ ለማለት ነው፡፡ ሥራው የሦስቱም ሆኖ ሳለ ለአብ ሰጥቶ መናገሩ በአብ ህልውና ወልድና መንፈስ ቅዱስ ስላሉ በአብ የሁሉንም መናገር ነው እንጂ አብ ብቻውን ይሠራል ማለት አይደለም፡፡ አብ ያለ ወልድ ምንም ሥራ እንደማይሠራ ‹‹… ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም ተብሎ ለእግዚአብሔር ወልድ ተነግሯል /ዮሐ. ፩፥፫/
ለወልድ ሰጥቶ ሲናገር
‹‹እንደገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና…እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና፡፡›› /ዮሐ. ፲፥፲፰/
ሥልጣን የሁሉም ሲሆን ለወልድ ሰጥቶ ይናገራል፡፡ በወልድ ህልውና አብና መንፈስ ቅዱስ ስላሉ የእነርሱንም የሥልጣን ባለቤትነት መናገር ነው፡፡ ለዚህ ነው ሥልጣኑ የአብም ሥልጣን ስለሆነ እንዲህ የተባለው፡- ‹‹እርሱ ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው›› /ሐዋ. ፪፥፴፪/
ለመንፈስ ቅዱስ ሰጥቶ ሲናገር
‹‹ያ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ እርሱ ከራሱ አይናገርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል፡፡ እርሱ እኔን ያከብረኛል ከእኔ ወሰደ ይነግራችኋልና፡፡ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው ስለዚህም ከእኔ ወሰዶ ይነግራችኋል አልኋችሁ፡፡›› /ዮሐ. ፲፮፥፲፫-፲፭/
መሪነት የሁሉም ሆኖ ሳለ ለመንፈስ ቅዱስ ሰጥቶ ይናገራል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ህልውና አብና ወልድ ስላሉ የእነርሱንም መሪነት መናገር ነው፡፡ በህልውናም አንድ ስለሆኑ “ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው” ይላል፡፡
የህልውና አንድነት በዮርዳኖስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅም ተገልጧል፡፡ ሦስቱ አካላት በዮርዳኖስ በአንድ ጊዜ ሲገኙ ህልውናቸው ደግሞ አብ በወልድ ቃልነት በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ‹‹ የምወደው ልጄ እርሱ ነው እርሱን ስሙ ብሎ›› በመናገሩ ታውቋል፡፡
የሥላሴን የህልውና አንድነት በሰው ልጅ ባሕርይ ምሳሌነትም ይረዱታል፡፡ ለእኛ ለሰው ልጆች ሦስት ነገር አለን፡፡ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ፡፡ በልቦናችን አብ፣ በቃላችን ወልድ፣ በእስትንፋሳችን መንፈስ ቅዱስ ይመስላሉ፡፡ በልቦናችን እንደምናስብ ሥላሴም በአብ ልቦናነት ያስባሉ፤ በቃላችን ቃል እንድንናገር በወልድ ቃልነት ይናገራሉ፤ በእስትንፋሳችን እንደምንተነፍስ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ይተነፍሳሉ፡፡
ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ የሥላሴ የባህርይ ከዊን /ሁኔታ/ ስማቸው ነው፡፡ ይህም የኩነታት /የሁኔታዎች/ ሦስትነት በህልውና የሚገናዘቡበት /አንዱ በአንዱ ውስጥ የሚገኙበት/ ስም ነው፡፡
o አብ ለራሱ ለባዊ /አዋቂ/ ሆኖ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልብ ዕውቀት ነው፡፡ በእርሱ ልብነት ወልድ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው፤ ያስቡበታል፡፡
o ወልድ ለራሱ ነባቢ /ቃል/ ሆኖ ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ ቃል ነው፡፡ በእርሱ ቃልነት አብ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው፤ ይናገሩበታል፡፡
o መንፈስ ቅዱስ ለራሱ ህያው ሆኖ ለአብ ለወልድ ህይወት ነው፡፡ በእርሱ እስትንፋስነት አብ ወልድ ህልዋን ናቸው፤ ሕያዋን ሆነው ይኖሩበታል፡፡
ከዚህ ወጥቶ ግን ለሦስቱ አካላት ለየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አላቸው ማለት ክህደት ነው፡፡
ለ. ሥላሴ በእግዚአብሔርነት /እግዚአብሔር በመባል/ አንድ ናቸው፡፡
አብ እግዚአብሔር ይባላል፤ ወልድ እግዚአብሔር ይባላል፤ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ይባላል፡፡ ነገር ግን አንድ እግዚአብሔር ቢባል እንዲ ሦስት እግዚአብሔር አይባልም፡፡ ‹‹…አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡›› እንዲል፡፡(ዘዳ ፯÷፬)
የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ሦስቱም አካላት እግዚአብሔር እንደሚባሉ /እግዚአብሔር በመባል አንድ እንደሆኑ/ ያሳያሉ፡፡
አብ እግዚአብሔር ተብሎ እንደሚጠራ፡-
‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርሰቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም አንድነት…›› /፪ቆሮ. ፲፫፥፲፬/
ወልድ እግዚአብሔር እንደሚባል፡-
‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ-ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ…›› /ሐዋ. ፳፥፳፰/ አማናዊት ቤተ-ክርስቲያንን በደሙ ፈሳሽነት የዋጃትና የመሠረታት እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ተብሎ እንደሚባል፡- /ሐዋ. ፭፥፫-፮/
‹‹ጴጥሮስም፡- ሐናንያ ሆይ መንፈስ ቅዱስን ታታልለው ዘንድ የመሬትህንም ዋጋ ከፍለህ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ እንዴት አደረ?... እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አላታለልህም አለው›› ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናንያን ያታለለው /የዋሸው/ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን እንደሆነ ነግሮታል፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ አግዚአብሔር እንደሚባል ያሳያል፡፡ በተጨማሪም ዕብ. ፫፥፯ እና ዘፀ. ፲፯፥፯ በማገናዘብ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሚባል ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር ሦስቱንም አካላት እግዚአብሔር ብሎ በመጥራትና የህልውናቸውን ቅድምና በመመስከር ነው፡፡
‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፡፡ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡›› /ዮሐ. ፩፥፩-፪/ ሦስት ጊዜ እግዚአብሔር ማለቱ ሦስቱም አካላት እግዚአብሔር መባል የሚገባቸው በመሆናቸው ነው፡፡
ሐ. ሥላሴ በፈጣሪነት አንድ ናቸው፡፡
‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ›› በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል “ፈጠረ” አለ እንጂ “ፈጠሩ” አለማለቱ ሥላሴ በፈጣሪነት አንድ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ /ዘፍ. ፩፥፩/፡፡ በተጨማሪም ልበ አምላክ ዳዊት ‹‹ አንተ ከጥንት ምድርን መሰረትህ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው፡፡›› ብሎ አንድ ፈጣሪ ብቻ መኖሩን ገልጧል፡፡ /መዝ. ፪፩፥፳፭/
ሥላሴ በመፍጠር አንድ በመሆናቸው ‹‹ እግዚአብሔር ፈጠረ›› ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ፈጣሪ መኖሩን እየተናገረ በሌላ መልኩ በህልውና አንድ ናቸውና ፈጣሪነትን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሰጥቶም ይናገራል፡፡ /ስለህልውና አንድነት በገጽ 23 የተሰጠውን ማብራሪያ ተመልከት/
- /ኢዮ. ፴፫፥፬/ ‹‹ የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ›› ሲል መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ መሆኑን
- /ዮሐ. ፩፥፫/ ‹‹ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም ሲል ወልድ ፈጣሪ መሆኑን››
- /መዝ. ፴፪፥፮/ ‹‹የእግዚአብሔር ይቅርታው ምድርን ሞላ፣ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፣ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፡፡” ሲል ሦስቱም አካላት ፈጣሪ መባል የሚገባቸው መሆኑን ያሳያል፡፡
መ. ሥላሴ አምላክ በመባል አንድ ናቸው
አብ አምላክ ይባላል፤ ወልድ አምላክ ይባላል፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ይባላል፡፡ ነገር ግን አንድ አምላክ ቢባል እንጂ ሦስት አምላክ አይባልም፡፡ /፩ጢሞ. ፩፥፲፯፤ ኢሳ. ፵፥፳፰/
፬-፭-፩-፪ ሦስትነት በምን?
፬-፭-፩-፪ ሦስትነት በምን? ሥላሴ በስም በአካል፣ በግብር፣ በኩነት እና በመሳሰሉት ሦስት ናቸው፡፡
አካልና ስም ቋንቋዊ ፍቻቸውን ስንመለከት፡-
o አካል፡- ከራሰ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር በሥጋ በአጥንት በጅማት በቁርበት የተያያዘ ገጽን መልክዕን አቋምን ያሳያል፡፡
o ገጽ፡- ልብስ የማይሸፍነው ከአንገት በላይ ያለውን መገለጫ ወይም በአጭሩ ፊትን ያመለክታል፡፡ መለያ መታወቂያ ማለት ነው፡፡
o መልክዕ፡- ኅብርን፣ ቅርጽን፣ ደም ግባትን፣ ያመለክታል፡፡ ይኽውም ቀይ መልክ፣ ጥቁር መልክ፣ መልከ መልካም፣ መልከ ክፉ ሲል ይታወቃል፡፡
o ስም፡- ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር ያለው አካል ከሌላ አካል ተለይቶ ማን እንደሆነ ታውቆ የሚጠራበት ነው፡፡
ስም ስንል ሦስት ዓይነት ነው፡፡
ሀ. የተጸውዖ ስም፡- አንዱ ከሌላው ተለይቶ የሚጠራበት ቁጥራቸው ከአንድ በላይ ለሆኑ ተመሳሳይ ባሕርይ ላላቸው የሚሰጥ ስም ነው፡፡
ከሌላ ሁለተኛ ወገን የሚሰጥ ስለሆነ በአብዛኛው ዋናው አገልግሎቱ ከብዙዎቹ ተመሳሳይ አካላት አንዱን ለይቶ ለመጥራት ነው፡፡
ለ. የግብር ስም፡- በአካል ተቀድሞ የአካልን እንቅስቃሴ ጠባይና ሥራ የመሳሰሉትትን የሚያመለክት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-ገበሬ፣ ሰዓሊ. . .
ሐ. የአካል ስም፡- ይህ ስም የሚነሳው ከባሕርይ በመሆኑ ከአካል የሚቀድም ሳይሆን ከአካል ጋር እኩል ህላዊ ያለው ስም ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ሰው፣ ፈረስ፣ አንበሳ እንደ ማለት ሲሆን ይህን ስም ያገኙት አካል ሲገኝ ጀምሮ ነው እንጂ ኖረው ኖረው አይደለም፡፡
ሀ. የሥላሴ የአካል ሦስትነት
ሥላሴ በአካል ሦስት ናቸው፡፡ ይህም ማለት ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም መልክ ፍጹም ገጽ አለው፡፡ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም መልክ ፍጹም ገጽ አለው፡፡ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም መልክ ፍጹም ገጽ አለው፡፡
ሰው በአርአያ ሥላሴ ተፈጥሯልና የሥላሴ መገለጫ ነው፡፡ ለዚህ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ለእግዚአብሔር በሰው አካል አምሳል እጅ እግር፣ አይን፣ ጆሮ እንዳሉት የተጻፈው፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃኑ ጆሮዎቹም ወደ ልመናቸው ናቸውና፡፡››/መዝ. ፴፫፥፲፭/ ‹‹. . .ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት›› /ኢሳ. ፰፮፥፩/
ይህ ማለት ግን በእግዚአብሔር አካልና በሰው አካል መካከል ልዩነት የለም ማለታችን አይደለም፡፡ ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ይህንንም ልዩነት በሠንጠረዥ ተመልከት፡፡
የሰው አካል የሥላሴ አካል
ግዙፍ ነው በዓይን አይታይም፣ በህሊናም አይታሰብም፣ ረቂቅ ነው
ውሱን ነው በሰማይና በምድር በአየር በዕመቅ የመላ ነው፣ በሁሉም ቦታ አለ
ጠባብ ነው ሰፉህ /ሰፊ/ ነው፡፡ ለስፋቱም ልክና መጠን የለውም፣ ላይና ታች ቀኝና ግራ የለውም
ፈራሽ በስባሽ ነው /ዘፍ. ፫፥፲፱፤ መዝ. ፻፪፥፲፬/ ይህ የሌለበት ሕያው ባሕርይ ነው፡፡ /ራዕ. ፩፥፲፰/
ደካማ ነው ሁሉን ቻይ ድካም የሌለበት ነው፡፡ /ኢሳ. ፵፥፳፲/
አስገኚ አለው አስገኝ የሌለው ነው፡፡
በአጭሩ ሰው ሥጋ ለባሽ ስለሆነ ግዙፍና ተዳሳሽ አካል ሲኖረው እግዚአብሔር ግን መንፈስ በመሆኑ ረቂቅና የማይዳሰስ አካል አለው፡፡ የእግዚብሔርን የአካል ሦስትነት ስናሰብ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ለእየራሳቸው ፍጽም አካል ስላላቸው ሦስቱም በተለየ አካላቸው እኔ ማለት የሚቻለውና እርሱ የሚባልላቸው ናቸው፡፡
‹‹እኔ ፊተኛው ነኝ፤ እኔም ዘላለማዊ ነኝ…ከሆነበትም ዘመን ጀመሮ እኔ በዚያ ነበረሁ፡፡ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል፡፡›› በቅዱስ ወንጌልም እንዲህ የሚል ተጽፏል፡፡
‹‹እኔም አብን እለምነዋለሁ፡፡ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር ይኖር ዘንድ ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፡፡ እርሱም ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው›› /ዮሐ. ፲፬፥፲፮-፲፯/
‹‹ሌላ አጽናኝ››መባሉም፡- አብ አጽናኝ ነው ልጁን ወደ ዓለም የላከ ነውና፤ ወልድም አጽናኝ ነው ዓለምን ለማዳን የመጣ ነውና፤ ከሁለቱም ሌላ ፍጹም አካል ያለው አጽናኝ ለማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፡፡
‹‹ሌላ አጽናኝ››መባሉም፡- አብ አጽናኝ ነው ልጁን ወደ ዓለም የላከ ነውና፤ ወልድም አጽናኝ ነው ዓለምን ለማዳን የመጣ ነውና፤ ከሁለቱም ሌላ ፍጹም አካል ያለው አጽናኝ ለማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፡፡
‹‹ከእናንተም ጋር ሳለሁ ይህን ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፡፡››/ዮሐ. ፲፬፥፳፭-፳፮/
ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ ሦስቱም አካላት በአንድ ቦታ በአንድ ሰዓት ማገኘታቸውም ሥላሴ በአካል ፍጹማን ለመሆናቸው /ለእየራሳቸው አካል ያላቸው ለመሆኑ/ ተጨማሪ ማስረጃ ነው፡፡ /ማቴ. ፫፥፲፮ እና ፲፯/
ለ. የሥላሴ የስም ሦስትነት
ሥላሴ በአካላዊ ግብረ ስም ሦስት ናቸው፡፡ የስም ሦስትነታቸውም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
- አብ ማለት አባት፣ አሥራፂ ማለት ነው፡፡ ወልድን የወለደ፣ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ ነውና
- ወልድ ማለት ልጅ ማለት ነው፤ የአብ የባሕርይ ልጅ ነውና
- መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ /የተገኘ፣ የወጣ/ ማለት ነው፡፡ ከአብ አብን መስሎ ወልድን አህሎ የሠረፀ ነውና፡፡
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚለው የሥላሴ የአካል ሰማቸው ነው፡፡ ምንም እንኳ ሥላሴ በዚህ ጊዜ ተገኙ ባይባልም፣ ጥንት መሠረት ሳይኖረው ቅድመ ዓለም ሲኖር የኖረ ነው እንጂ እንደ ተጸውዖ ስም ኖሮ ኖሮ የወጣ አይደለም፡፡ የሥላሴ አካል ጥንት እንደሌለው ሁሉ ለስሙም ጥንት የለውም፡፡
አብ ተለውጦ ወልድ መንፈስ ቅዱስን እንደማይሆን የአብ ስሙ ተለውጦ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ ለአብ የአባትነት ስም የአባትነት ክብር አለውና፡፡ ወልድም ወልድ ቢባል እንጂ አብ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፣ የባሕርይ ክብሩ ከአብ ሳያንስ የልጅነት ክብር የልጅነት ስም አለውና፡፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ቢባል እንጂ አብ ወልድ ተብሎ አይጠራም፡፡ የባሕርይ ክብሩ ከአብ ከወልድ ሳያንስ መንፈስ ቅዱስ ተብሎ ይጠራል እንጂ፡፡
የሥላሴ የስም ሦስትነት በብሉያትም በሐዲሳትም ተመስክሯል፡፡
በብሉይ ኪዳን
‹‹እግዚአብሔር አለኝ፡- አንተ ልጄ ነህ እኔም ዛሬ ወለድሁህ›› /መዝ. ፪፥፯/
ቅድመ ዓለም አካል ዘእምአካል፣ ባሕርይ ዘእምባሕርይ የወልድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ ዛሬም በተዋህዶ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ ብሎ አብና ወልድን ያነሳል፡፡ ተናጋሪው ወልድ ነው፤ እግዚአብሔር ብሎ አብን አንስቷል፡፡
‹‹ይህን ታውቅ እንደሆንህ፤ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?›› /ምሳ. ፴፥፬/ ይህ ቃል አብ የአባትነት፣ ወልድ የልጅነት ስም እንዳላቸው ያሳያል፡፡
በሐዲስ ኪዳን
‹‹ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃኋችሁ አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ፡፡››/ማቴ. ፳፰፥፲፱/
‹‹ያ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡…ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው ስለዚህም ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋል አልኋችሁ፡፡›› /ዮሐ. ፲፮፥፲፫-፲፭/
ሥላሴ በክብር በሥልጣን አንድ ስለሆኑ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ተብለው ሲጠሩ የሥልጣን ቅደም ተከተልን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወልድን አስቀድሞ፤ አብና መንፈስ ቅዱስን አስከትሎ ሲጠራ በሚከተለው ጥቅስ ማየት ይቻላል፡፡
‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔር ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም አንድነት ከሁላችሁ ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡›› /፪ቆሮ. ፲፫፥፲፬/
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ አብን አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስንና ከዚያም ወልድን አስከትሎ ሲጠራ የሚከተለው ምንባብ ያሳያል፡፡
‹‹. . .እግዚአብሔር አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስ ቅዱስም እንደሚቀዱሱ፣ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርሰቶስ ደም ይረጩ ዘንድ…›› /፩ጴጥ. ፩፥፪/
ሐ. የሥላሴ የግብር ሦስትነት
ግብር ማለት ሥራ ማለት ነው፣ ሥላሴ በግብር ሦስት ናቸው፡፡
- የአብ ግብሩ ወልድን መውለድ መንፈስ ቅዱስን ማሥረጽ ነው፡፡
- የወልድ ግብሩ ከአብ መወለድ ነው፡፡
- የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ ከአብ መስረጽ ነው፡፡
አብ ቢወልድ ቢያሠርፅ እንጂ እንደ ወልድ አይወለድም፤ እንደ መንፈስ ቅዱስ አይሠርፅም፡፡ ወልድም ቢወለድ እንጂ እንደ አብ አይወልድም አያሠርፅም፤ እንደ መንፈስ ቅዱስም አይሠርፅም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቢሠርፅ እንጂ እንደ አብ አይወልድም አያሠርፅም እንደ ወልድም አይወለድም፡፡
ወላዲ አሥራፂ፣ ተወላዲ፣ ሠራፂ የሚለው የሥላሴ የአካል ግብር ስማቸው ነው፡፡ ይህም በቅድሳት መጻሕፍት ምስክርነት የተረጋገጠ ነው፡፡
‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው›› /ማቴ. ፫፥፲፯/ ይህ ቃል አብ ወልድን እንደ ወለደ ያሳያል፣ ልጄ ብሎ ጠርቶታልና፡፡
‹‹እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ…›› /ዮሐ. ፲፭፥፳፮/ ይህ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ከአብ እንደ ሰረፀ ያሳያል፡፡
አብ ወልድን ቢወልድ መንፈስ ቅዱስን ቢያሠርፅ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ በፊት የነበረ አያሰኝም፡፡ በእኛ ግዕዝ /ልማድ/ አባት ሲበልጥ ሲቀድም፤ ልጅ ሲተካ ሲከተል ነው፡፡ በሥላሴ ግን አብን አባት ወልድን ልጅ መንፈስ ቅዱስን ሠራፂ ስላለን መቅደም መቀዳደም፤ መከተል መከታተል፤ መብለጥ መበላለጥ የለባቸውም፡፡ የውስጥ የባሕርይ ግብር ነውና፡፡
ሐ. የሥላሴ የኩነት ሦስትነት
ኩነታት በህልውና /በአኗኗር/ እየተገናዘቡ በአንድ መለኮት የነበሩ ያሉና የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነርሱም ልብነት ቃልነትና እስትንፋስነት ናቸው፡፡
- ልብነት፡- በአብ መሰረትነት ለራሱ ልባዊ /አዋቂ/ ሆኖ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልብ /ዕውቀት/ መሆን ነው
- ቃልነት፡- በወልድ መሠረትነት ለራሱ ነባቢ /ቃል/ ሆኖ ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ /ቃል/ መሆን ነው
- እስትንፋስነት፡- በመንፈስ ቅዱስ መሠረትነት ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብ ለወልድ ሕይወት መሆን ነው፡፡
የኩነታት ሦስትነት ከአካላት ሦስትነት ይለያል፡፡ ኩነታት ያለተፈልጦ በተጋብኦ በአንድነት አካላትን በህልውና እያገናዘቡ በአንድ መለኮት ያሉና የሚኖሩ ናቸው፡፡ አካላት ያለተጋብኦ በፍጹምነት ያሉ በህልውና እያገናዘቡ በአንድ መለኮት ያሉና የሚኖሩ ናቸው፡፡ አካላት ያለተጋብኦ በፍጹምነት ያሉ ናቸው፡፡ ሥላሴ በአካላት ፍጹም ሦስት ሲሆኑ በልብ፣ በቃል፣ በእስትንፋስ ግን ተገናዛቢዎች ስለሆኑ በአንድ ልብ ያስባሉ፣ በአንድ ቃል ይናገራሉ፣ በአንድ እስትንፋስ ሕያዋን ሆነው ይኖራሉ፣ አንድ ፈቃድ ይፈቅዳሉ፣ አንድ አሳብ ያስባሉ፣ በአንድነት አንድ ሥራ ይሠራሉ፣ በአንድነት ይመለካሉ፡፡
ከላይ በዝርዝር የተመለከትነው የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት በብሉያትና በሐዲሳት እንዴት እንደተገለጠ ደግሞ ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን፡፡
በብሉይ ኪዳን
ጥቅስ አንድ፡-
‹‹እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር፡፡››/ዘፍ. ፩፥፳፮/
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል “እግዚአብሔርም አለ” ብሎ አንድነቱን፣ ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር ብሎ ብዛቱን ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም “እንፍጠር” የሚለው በፈጣሪነት ሥልጣን ትክክል /እኩል/ የሆኑ አካላት የሚነጋገሩ መሆኑን ያሳያል፡፡
ጥቅስ ሁለት፡
‹‹እግዚአብሔር አምላክም አለ፡- እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፡፡››/ዘፍ ፫፥፳፪/
እግዚአብሔር አለ ብሎ አንድነቱን ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ብሎ ከሁለት አካል በላይ እንደሆኑና ሥላሴ አንድ አካል አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡
ጥቅስ ሦስት፡-
‹‹ እግዚአብሔርም አለ…ኑ እንውረድ አንዱም የሌላውን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው፡፡›› /ዘፍ. ፲፩፥፮/
‹‹እግዚአብሔርም አለ›› በሚለው አንድነቱን፣ ‹‹ኑ እንውረድ›› በሚለው ደግሞ አንዱ አካል ከአንድ በላይ ለሆኑ ሌሎች አካላት መናገሩን እንገነዘባለን፡፡ በተጨማሪም ‹‹ቋንቋቸውን እንደባልቀው›› የሚለው የመፍረድ የመቅጣት ስልጣናቸው እኩል /አንድ/ የሆኑ አካላት እንዳሉ ያሳያል፡፡
ጥቅስ አራት፡
/ዘፍ. ፲፰፥፩-፲/ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍለ ንባብ እግዚአብሔር ለአብርሃም በሦስት ሰዎች አምሳል መገለጹ ተመልክቷል፡፡ ይህም ቀደም ባሉት ጥቅሶች ግልጽ ሆኖ ያልተቀመጠውን የእግዚአብሔር ሦስትነት ገሃድ ያደርገዋል፡፡
አብርሃምም ይናገረው የነበረው አንድነትና ሦስትነትን የሚያሳይ ነው፡፡
- ‹‹አቤቱ በፊትህ ባለሟልነትን አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈው›› ማለቱ ሦስቱ ሰዎች በጌትነት አንድ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ቀጠል አድርጎ…
- ‹‹ውኃ እናምጣላችሁ›› ማለቱ በሦስትነታቸው መናገሩ ነ
> - ‹‹ሦስት መስፈሪያ ዱቄት አዘጋጂ›› ብሎ ሚስቱን ሣራን ሲያዛት ሦስትነትን ‹‹ለውሽውም እንጎቻ አድርጊ›› ብሎ በአንድ ለውሳ አንጎቻ እንድትጋግር ማዘዙ ደግሞ የሦስቱን አንድነት ያጠይቃል፡፡
ጥቅስ አምስት፡-
‹‹የእስራኤልን ልጆች ስትባርኳቸው እንዲህ በሏቸው፡፡ እግዚአብሔር ይባርክህ ይጠብቅህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ ይራራልህም፡፡ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሳ ሰላምንም ይስጥህ›› /ዘኁ ፮፥፳፫-፳፮/ ሦስት ጊዜ እግዚአብሔር መባሉ ሦስትነትን፤ ቃሉ አንድ መሆኑ እንድነትን ያመለክታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ፪ኛ ቆሮ. ፲፫፥፲፬ ላይ ከተናገረው ቃል ጋር በማቆራኘት እንደሚከተለው ይተረጎማል፡፡
‹‹እግዚአብሔር ይባርክህ ይጠብቅህም›› የሚለው ለእግዚአብሔር ወልድ የተነገረ ነው፡፡ ይህም ማለት ቡሩክ እግዚአብሔር መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አርቆልህ በረከተ ሥጋንና በረከተ ነፍስን ይስጥህ፣ በነፍስም በሥጋም ይጠብቅህ፣ ከክህደት ከጥርጥር ከሥጋዊ ጠላት፣ ከጸብአ አጋንንት ከመርገም ከኩነኔ ከገሃነም ይጠብቅህ ማለት ነው፡፡ ይህም ያለ እግዚአብሔር ጸጋ አይገኝምና ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርሰቶስ ጸጋ›› ብሎ ጠቅሶታል፡፡‹‹ጸጋሰ ሥርየተ ኃጢአት ይእቲ›› እንዲል ሰው ከኃጢአት እስራት የተፈታ፣ከሲኦል የወጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ነውና፡፡
‹‹እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፣ ይራራልም›› ሰው ወዳጁን በብሩህ ገጽ በፈገግታ ይቀበለዋል፡፡ ብሩህ ገጽ የፍቅር መግለጫ ነው፡፡ ርህራሄ ደግሞ ከፍቅር የሚመነጭ ነው፡፡ ምስጢሩም እግዚአብሔር እኛን በፍቅር አይን ተመልክቶ በርህራሄው ከመከራ እንደሚያድነንን የሚያስረዳ ነበረ፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ፍቅር›› ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ለጠቀሰው ነው፡፡ /በተጨማሪም ዮሐ. ፫፥፲፮፤ ፩ዮሐ. ፫፥፲፱ ተመልከት/
‹‹እግዚአብሔር ፊቱን ወዳንተ ያንሳ ሰላምንም ይስጥህ›› ይህም በምሕረት ዓይን ይመልከትህ፤ በውስጥ በአፍአ፣ በነፍስ በሥጋ ሰላምን ይስጥህ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ሕብረት›› ያለው ነው፤ የመንፈስ ቅዱስ ሰላም ሲል፡፡ ሰላም የሚገኘው ሕብረት ባለበት ነውና፡፡ ሰላምና ሕብረት፤ ጸብና መለያየት አይነጣጠሉምና፡፡
ጥቅስ ስድስት፡-
‹‹የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች፤ የእግዚአብሐር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገች፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች›› /መዝ. ፻፲፯፥፲፮-፲፯/ የእግዚአብሔር ቀኝ የሚለው ሦስት ጊዜ መነገሩ የሦስትነት፤ ቃሉ አለመለወጡ የአንድነት ያመለክታል:፡
ጥቅስ ሰባት፡-
‹‹እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ኃይሉም ታላቅ ነው፤ ለጥበቡም ቁጥር የለውም›› /መዝ. ፻፵፮፥፭/
ይህም ማለት፡- እግዚአብሔር አብ ገናና ነው፤ ኃይሉ እግዚአብሔር ወልድም ገናና ነው፤ ኃይሉ አለው ኃይሉ ስለተገለጸበት፣ በኃይል አንድ ስለሆኑ፡፡ ጥበቡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ሀብቱ ፍጹም ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሀብቱ ብዙ ነውና ስፍር ቁጥር የሌለው ጥበብ ብሎ መንፈስ ቅዱስን አነሳ፡፡ /ኢዮ. ፱፥፬/
ጥቅስ ስምንት፡-
‹‹አንዱም ለአንዱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድርም ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበረ፡፡››/ኢሳ. ፮፥፫/
ሦስት ጊዜ ቅዱስ መባሉ የሦስትነት ቃሉ አለመለወጡ የአንድነቱ ምሳሌ ነው፡፡ በሌላም መልኩ ሦስት ጊዜ ቅዱስ መባሉ የሦስትነት ቃሉ አለመለወጡ ሦስቱ አካላት በምስጋና ትክክል መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
ድግግሞሽ ነው እንዳይባል መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት በዕብራውያን የአነጋገር ዘይቤ ደጋም ቃል ሁለት ጊዜ ነው እንጂ ሦስቴ አይደለም፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን ማስረጃዎች ተመልከት፡፡ /ዘፍ. ፳፪፥፲፩፤ ዘፀ. ፫፥፬፤ ፩ሳሙ ፫፥፲/
ጥቅስ ዘጠኝ፡-
‹‹የጌታንም ድምጽ፡- ማንን እልካለሁ? ማንስ ወደዚያ ሕዝብ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ›› /ኢሳ. ፮፥፰/ ማንን እልካለሁ? የሚለው አንድነቱን፣ ማንስ ይሄድልናል? የሚለው ደግሞ ሦስትነቱን ያሳያል፡፡
በተጨማሪም የሚከተሉት የብሉይ ኪዳን ምንባባት የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ - ኢሳ. ፵፰፥፲፪-፲፮ - ጦቢ. ፰፥፮ - ሲራ. ፫፥፳፪
- መዝ. ፴፪፥፭-፯ - ዘፍ. ፪፥፲፰
በሐዲስ ኪዳን
የአንድነቱና የሦስትነቱ ነገር በብሉይ ኪዳን በምሥጢር የታወቀ ቢሆንም በሐዲስ ኪዳን ግን በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ጥቅስ አንድ፡-
‹‹ጌታችን ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ ከውኃ ወጣ፡፡ እነሆም ሰማይም ተከፈተለት፡፡ የእግዚአብሔርም መንፈስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ እነሆም በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ፡፡››/ማቴ. ፫፥፲፮-፲፯/
ሰማይ ተከፈተ መባሉ ደጅ በተከፈተ ጊዜ የውስጡ እንዲታይ እስከ አሁን ያልተገለጠ ምስጢር ታየ፣ ተገለጠ ለማለት ነው፡፡ ጌታ ሲጠመቅ ሦስት አካላት በአንድ ሰዓት /ጊዜ/ ተገኝተዋል፡፡ አንዱ አካል ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ሲወጣ፤ መንፈስ ቅዱስ በተለየ አካሉ በአምሳለ ርግብ ሲወርድ፤ አካላዊ አብ በተለየ አካሉ በደመና ሆኖ ሲመለከት፣ የወደደውን ለተዋህዶ ሥጋ ወደ ዓለም የላከው ኢየስስ ክርስቶስ መሆኑን ሲናገር ሦስትነት ተረድቷል፡፡
ጥቅስ ሁለት፡-
‹‹ሂዱና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ፡፡›› /ማቴ. ፳፰፥፲፱/
ይህ ጥቅስ የሥላሴን የስም ሦስትነት /ሥላሴ በስም ሦስት መሆናቸውን/ ይገልጻል፡፡
ጥቅስ ሦስት፡-
‹‹መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል፣ ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው፡፡›› /ሉቃ. ፩፥፴፭/
ጥቅስ አራት፡-
‹‹እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ አየሁ፤ ከእርሱ ጋር ስሙና የአባቱ ስም የመንፈስ ቅዱስም ስም በግንባራቸው የተጻፈባቸው….››/ራዕ. ፲፬፥፩-፪/
በግ ያለው ለሰው ልጆች ቤዛ የሐዲስ ኪዳን መስዋዕት ሆኖ የቀረበውን እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርሰቶስን ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ስለጌታችን ሲመሰክር፡-
‹‹ እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› እንዳለ፡፡ /ዮሐ. ፩፥፴፮/
፬-፭-፪ ስለምስጢረ ሥላሴ የሚያስረዱ ተፈጥሯአዊ ምሳሌዎች
ሀ. የሰው ምሳሌነት
የሰው ነፍስ ሦስትነት አላት፡፡ ልብነት፣ ቃልነት፣ ሕይወትነት፡፡ በልብነቷ የአብ፣ በቃልነቷ የወልድ፣ በሕይወትነቷ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነች፡፡
- ነፍስ እነዚህ ሦስት ነገሮች ስላሏት ሦስት ነፍስ እንደማትባል ሥላሴም በአካል ሦስት ቢሆኑም አንድ እግዚአብሔር አንድ አምላክ ቢባሉ እንጂ ሦስት እግዚአብሔር ሦሰት አምላክ አይባሉም፡፡
- የነፍስ ልብነቷ ቃልነቷ ሕይወትነቷን ከራሷ ታስገኛለች፡፡ ቃልና ሕይወት ከአንዲት ልብ ስለተገኙ በከዊን /በመሆን/ ልዩ እንደ ሆኑ ሁሉ በመነጋገር ይለያሉ፡፡ ቃል ተወለደ እስትንፋስ ሠረፀ /ወጣ/ ይባላል፡፡ እንደዚሁ አብ ወለድን በቃል አምሳል ወለደው፤ መንፈስ ቅዱስን በእስትንፋስ አምሳል አሠረፀው፡፡
- ነፍስ ስትገኝ በሦስትነቷ በአንድ ጊዜ ተገኘች እንጂ ልብነቷ ቀድሞ ቃልነቷና እስትፋስነቷ በኋላ የተገኙ አይደሉም፡፡ እንደዚሁ አብ ወልድን ሲወልደው መንፈስ ቅዱስን ሲያሰርፀው አይቀድማቸውም፡፡
ሰው በነፍሱ በዚህ አኳኋን እግዚአብሔርን ስለሚመስለው እግዚአብሔር ‹‹ሰውን በአርአያችንና በምሳሌአችን እንፍጠር›› ብሎ ተናገረ፡፡ /ዘፍ. ፩፥፳፮/
ለ. የፀሐይ ምሳሌነት
ለፀሐይም ሦስትነት አላት፡፡ ክበብ፣ ብርሃንና ሙቀት፡፡ በክበቧ አብ፤ በብርሃኗ ወልድ በሙቀቷ መንፈስ ቅዱስ ይመስላሉ፡፡
- የፀሐይ ብርሃን የፀሐይ ክበብ፣ የፀሐይ ሙቀት ብለን ሦስት ጊዜ ፀሐይ ፀሐይ ማለታችን ለፀሐይ ሦስትነት እንዳላት ያሳያል እንጂ ሦስት ፀሐይ አለ እንደማያሰኝ እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፤ አብ አምላክ፣ ወልድ አምላክ፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ማለታችንም ሦስት እግዚአብሔር ሦስት አምላክ አያሰኝም፡፡ /መዝ. ፲፰፥፬/
- የፀሐይ ክበቧ ብርሃኗንና ሙቀቷን ያስገኛል፤ ሆኖም ግን ብርሃንና ሙቀትን ቀድሞ የሚገኝበት ጊዜ የለም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ አብ ወልድን ቢወልድ መንፈስ ቅዱስን ቢያሰርፅ ወልድና መንፈስ ቅዱስን ቀድሞ የኖረበት ጊዜ የለም፡፡ በሥላሴ ዘንድ መቅደም መቀዳደም የለም፡፡
- ክበብ ብርሃኑን ፈንጥቆ ጨለማን በማራቁ፣ ዋዕዩን /ሙቀቱን/ ልኮ በማሞቁ ህልውናውን /መኖሩን/ እንዲያሳውቅ የአብም ህልውናውን በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስለተገለጸ አብን ላኪ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስን ተላኪ አልን እንጂ በሥላሴ መብለጥ መበላለጥ ኖሮባቸው አይደለም፡፡
ሐ. የእሳት ምሳሌነት
እሳትም አንድ ሲሆን ሦስትነት አለው፤ አካሉ፣ ብርሃኑና ሙቀቱ፡፡ በአካሉ አብ፣ በብርሃኑ ወልድ፣ በሙቀቱ መፈስ ቅዱስ ይመስላሉ፡፡‹‹እሳት አመጣ›› ሲባል ብርሃኑን ‹‹እሳት አብራ›› ሲባል ብርሃኑን ‹‹እሳት እንሙቅ›› ሲባል ሙቀቱን መናገር ነው፡፡ በዚህም ለእሳት ሦስትነት እንዳለው እንረዳለን፡፡
- እሳት አንድ ሲሆን ሦስትነት እንዳለው፤ ሦስትነት ስላለው እንደ አንድ እንደሆነ ሥላሴም በአካል ሦስት ሲሆኑ በባህርይ በሕልውና አንድ ናቸው፡፡
መ. የባህር /የቀላይ/ ምሳሌነት
የባህር ሦስትነት ስፋቱ ርጥበቱና ሑከቱ /መናወጹ/ ነው፡፡ በስፋቱ አብ፣ በእርጥበቱ ወልድ በሑከቱ መንፈስ ቅዱስ ይመስላሉ፡፡
- ይህ ሦስት ከዊን /ሁኔታ/ ያለው ባሕር አንድ ባሕር ይባላል እንጂ ሦስት ባሕር እንደማይባል ሁሉ ሦስት ከዊን ያላት ባሕርየ ሥላሴ፣ መለኮተ ሥላሴም አንዲት ብትባል እንጅ ሦስት አትባልም፡፡
ሠ. የሦስት ማዕዘን ቅርጽ (Equilaterial Triangle) ምሳሌነት
በማናቸውም ሁኔታ አንድ ዓይነት የሆኑ ሦስት ጎንዎች ጫፍና ጫፋቸው ሲገናኝ ሦስቱም ጎኖቹ ሦስቱም አንግሎቹ እኩል የሆነ ሦስት ማዕዘን (Equilaterial Triangle) ይገኛል፡፡
- ሦስቱ ጎኖች በየራሳቸው ጎን የቆሙ እንደሆነ ሁሉ ሥላሴም በሦስት አካላት፣ በሦስት ገጻት ፍጹማን ናቸው፡፡
- በሦስቱ ጎኖች መካከል የርዝመት የውፍረት ልዩነት እንደሌለ በማናቸውም ነገር እኩል እንደሆኑ ሥላሴም በክብር አንድ ናቸው፡፡
- ከሦስቱ ጎን አንዱ ከሌላ ሦስት ማዕዘን አይባልም እንደዚሁም ሁሉ ከሥላሴ አንዱ ፍጡር የሚል በአምላክ ሕልውና ላይ ምን ያህል የክህደት ትምህርት እንዳስተማረ ከምሳሌው እንረዳለን
- የሦስቱ ጎን ግራ ቀኙ እንዳይታወቅ ለሥላሴም ግራ ቀኝ የላቸውም
‹‹ተቀዳሚና ተከታይ ቀኝና ግራ የለብንም፣ ጠፈር የለብንም መሠረትም የለብንም ጠፈርም መሠረትም እኛው ነን›› /ቅዳሴ /
፬-፮ ምሥጢረ ሥጋዌ
፬.፮.፩ ትርጉም
ሥጋዌ የሚለው ቃል ተሠገወ = ሥጋ ሆነ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ሠው መሆን፣ ሥጋ መልበስ ማለት ነው፡፡
ምሥጢረ ሥጋዌ ስንልም ሰው የመሆን፣ ሥጋ የመልበስ ነገር የሚነገርበት፤ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል በከዊን ስሙ ቃል የሚባለው ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋ የመልበሱ ነገር የሚነገርበት ምሥጢር ማለት ነው፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹ቃል ሥጋ ሆነ›› ብሎ የገለጸው ነው፡፡ /ዮሐ. ፩፥፲፬/
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ እግዚአብሔር ወልድ ሰው የመሆኑን ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ፡፡›› /ገላ. ፬፥፬/
፬-፮-፪ የሰው ልጅ ተፈጥሮና ክብር
እግዚአብሔር ፭ ቀን ሙሉ ዓለምን በሥነ-ፍጥረት እያስጌጠ ካዘጋጀ በኋላ ዓርብ በነግህ ‹‹ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር›› ብሎ ተናገረ፡፡/ዘፍ. ፩፥፳፮/እንዲህ ተናገረና ግዙፍ አካል ሥጋን ከ፬ ባሕሪያት ከመሬት፣ ከውኃ፣ከነፋስና ከእሳት ከፍሎ አገናኝቶ በሥጋ አለስልሶ በደም አርሶ በጅማት አያይዞ ባጥንት አጽንቶ፣ ረቂቅ አካል ነፍስን ካለመገኛ አስገኝቶ ዕውቀት ቃል ሕይወት ሰጥቶ፣ እነዚህን ሥጋንና ነፍስን አዋሕዶ ሰውን በምሳሌው ፈጠረ፡፡ /ዘፍ. ፪፥፮፤ ዘፍ. ፩፥፳፯/
ሰው የሚለው በግእዝ ስብእ የሚለውን ቃል ነው፡፡ ሰብእ ማለት ፯ ሁኔታ /ጠብዓይት፣ ግብራት/ ያለው አካል ማለት ነው፡፡ የተለየ ስሙን ግን አዳም ብሎ ሰይሞታል /ዘፍ. ፭፥፪/፡፡ አዳም በተፈጠረ በ፰ኛው ቀን (በሁለተኛው ዓርብ) የምትረዳውን የምትስማማውን ረዳት እንፍጠርለት እንጂ ‹‹ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም›› ብሎ ከአዳም ጎን አንድ አጥንት ወስዶ የምትረዳውን ሴት ፈጠረለት፡፡/ዘፍ. ፪፥፲፰ እና ፳፩፥፳፫፤ ኩፋ. ፬፥፬‐፮/፡፡ አዳምም ከጎኑ ለተገኘች ሴት ሔዋን ብሎ መጠሪያ ስም አወጣላት /ዘፍ. ፫፥፳/፤ ትርጉሙም የሕያዋን እናት ማለት ነው፡፡
ሰው ክቡር ፍጥረት መሆኑ፡-
- በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ በመፈጠሩ
- ከአምላክ በታች በተሰጠው የገዥነት ሥልጣን ታውቋል፡፡ /ዘፍ. ፩፦፳፰-፴፤ መዝ.፰፥፮‐፰/
፬-፮-፫ የሰው ልጅ የተሰጠው ነጻ ፈቃድና አምላካዊ ትዕዛዝ
የሰው ልጅ ሙሉ ነጻነት ያለው ፍጡር ነው፡፡ ይህም የሚታወቀው በተሰጠው አእምሮ የወደደውን /ክፉውን ከሻተ ክፉውን መልካሙን ከሻተ መልካሙን/ እንዲመርጥ የመምረጥ መብት የተሰጠው በመሆኑ ነው፡፡ የሚከተሉት ምንባባት ይህን የሰው ልጅን ነጻነት ያሳያሉ፡፡
‹‹እነሆ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና ሞትን መልካምንና ክፋትን አኑሬአለሁ፡፡ ዛሬ እኔ የማዝህን የአምላክንህ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ብትሰማ፣ አምላክህን እግዚአብሔርንም ብትወድድ፣ በመንገዶቹም ሁሉ ብትሄድ፣ ሥርዓቱንና ፍርዱንም ብትጠብቅ በሕይወት ትኖራለህ…ልብህ ግን ቢስት አንተም ባትሰማ፣ ብትታለልም ለሌሎች አማልክትም ብትሰግድ ብታመልካቸውም ፈጽመህ እንደምትጠፋ እኔ ዛሬ እነግርሃለሁ…አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖር ዘንድ ሕይወትን ምርጥ…እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመትና ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ውደደው፣ ቃሉን ስማው፣ አጥናውም፡፡››/ዘዳ. ፴፥፲፭-፳/
‹‹እሺ ብትሉና ብትሰሙኝ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉና ባትሰሙኝ ግን ሰይፍ ይበላችኋል›› /ኢሳ. ፩፥፲፱/
‹‹ ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ›› /ዮሐ. ፲፬፥፲፭/
እግዚአብሔርም ለአዳም ‹‹ከገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፡፡ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና›› ብሎ አምላካዊ ትእዛዝ ሰጠው፡፡ /ዘፍ. ፪፥፲፯/ ውድ ተማሪዎች ይህም አምላካዊ ትእዛዝ የተሰጠበት ምክንያት እንደ ሚከተለው እንመለከተዋለን፡-
፩ኛ. አዳም ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር እንዲገለጥ
እግዚአብሔር ለአዳም ያለው ፍቅር ከመፍጠር እስከ መግቦት ባለው ተገልጧል፡፡ የአዳም ፍቅር የሚታወቀው ደግሞ የፈጣሪውን ሕግና ትእዛዝ በመጠበቅ ነው፡፡ ‹‹ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለ፣ የሚጠብቀውም የሚወደኝ እርሱ ነው፡፡››እንዲል፡፡ /ዮሐ. ፲፬፥፳፩
ይህንን ትእዛዝ በማክበር አዳም ከክብሩ ሳይጎድልበት፤ ከጸጋው ሳይቀነስበት ለ፯ ዓመታት እርሱ በእግዚአብሔር ቤት እግዚአብሔርም በእርሱ ልቦና ኖሩ፡፡ ‹‹ትእዛዙን የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል፣ እርሱም ይኖርበታል››እንዲል /፩ዮሐ. ፫፥፳፬/
፪ኛ. ፍጡርነቱ ይታወቅ ዘንድ
ዕፀ በለስ አዳም የሚገዛለት ፈጣሪ እንዳለው የምታሳውቅ የተገዥነት ምልክት ነበረች፡፡ አዳም ‹‹ሁሉን ግዛ›› ቢባልም ካስገዛለት በታች መሆኑን ያውቅ ዘንድ አድርግ አታድርግ የሚል ሕግ ተሰጥቶታል፡፡
፫ኛ. ነጻ ፈቃዱ ይገለጥ ዘንድ
የአንድ ሰው ነጻ ፈቃዱ የሚታወቀው የመምረጥ መብት ሲኖረው ነው፡፡ በመሆኑም ለአዳም ሁለት ምርጫ ተሰጠው፤ ሌሎችን ዛፎች ቢበላ በሕይወት የመኖርና ዕፀ በለስን ቢበላ የመሞት ምርጫ፡፡ ዕፀ በለስን ባይፈጥርለት ኖሮ አዳም ወዶ ፈቅዶ መርጦ መታዘዙን ማውቅ ባልተቻለ ነበረ፡፡
፬-፮-፬ የሰው ልጅ አወዳደቅ
አዳምና ሐዋን በገነት ፯ ዓመት ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው በሕይወት ከኖሩ በኋላ ሰይጣን በእባብ አድሮ አስቀድሞ ‹‹ለእመ ትበልዑ ኢንትኮ በለሰ ሞተ ዘትመውቱ›› ያላቸውን “ለእመ ትበልዑ ኢንትኮ በለስ አኮ ሞተ ዘትመውቱ አላ አማልክተ ትከውኑ” ብሎ አስቷቸው በሉ፡፡ የአምላካቸውንም ሕግ ሻሩ፡፡ /ዘፍ. ፫፥፩/፡፡ ክብሩ የሰው ልጅ ወደቀ፡፡
- ጸጋው ተገፈፈ - ባሕርይው ጎሰቆለ ማለት ነው፡፡
፩ኛ. ጸጋው ተገፈፈ ስንል፡-
+ ራቁቱን ሆነ
አዳምና ሔዋን ለብሰውት ከነበረው በጸጋ ከተሰጣቸው የብርሃን ልብስ ተራቆቱ፡፡ ‹‹የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደሆኑ አወቁ፡፡›› እንዲል፡፡ /ዘፍ. ፫፥፯/
+ ኃይልን አጣ
አዳም ከበደል በኋላ ፈቃደ ነፍሱ በፈቃደ ሥጋው ላይ የነበራትን ኃይል አጣች፡፡ እንስሳን ይመስል ለመብላት ባማረ፣ ለዓይን በሚያስጎመጅ፣ ለጥበብ መልካም መስሎ በሚታይ ነገር ተሸነፈ፡፡ ‹‹ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሶች ሆነ፤ መሰላቸውም፡፡›› /መዝ. ፵፰፥፲፪/
ይህም ብቻ ሳይሆን የአምላኩን የፍቅር ድምፅ እንኳ የሚያዳምጥበት መንፈሳዊ ኃይል አጥቷል፡፡ ‹‹በገነት ስትመላለስ ድምፅህን ሰማሁ ዕራቁቴንም ስለሆንኩ ፈራሁ ተሸሸግሁም፡፡›› /ዘፍ. ፫፥፲/
+ እንግዳ ሆነ
የገነት ባለርስት የዚህ ዓለም ጌታ የነበረው የሰው ልጅ ከበደል በኋላ ይህንን ሁሉ አጥቶ እንግዳ ሆነ፡፡ ‹‹እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፤ እንደ አባቶችም ሁሉ እንግዳ ነኝና፡፡›› /መዝ. ፴፰፥፲፫፤ ዘፍ. ፵፯፥፰/
፪ኛ. ባሕርይው ጎሰቆለ ስንል፡-
+ ሰላሙን አጣ
አዳም ከበደል በኋላ በባሕርይው የነበረውን ፍጹም ሰላም አጥቷል፡፡ የኃጢአት ፍጻሜው ሰላምን ማደፍረስ፣ ፍርሃትን ማንገስ ነውና አዳም ኃጢአትን ከፈጸመ በኋላ “ፈራሁ ተሸሸግሁ” የሚል ሆኗል፡፡ መጽሐፍ እንዲህ እንዲል፡:
‹‹ኃጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ተማምኖ ይኖራል›› /መጽ. ተግ ፬፥፩/በግሪኩ ምሳሌ ፳፰፥፩/
+ ሕያውነትን አጣ
እግዚአብሔር ሰውን በንጹሕ ባሕርይ ያለ ሞት ፈጥሮት ነበረ፡፡ሕያው ፍጥረት አዳም ግን በነጻ ፈቃዱ ተጠቅሞ “አትብላ” የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ በማፍረሱ በነፍስ በሥጋ ሟች ሆነ፡፡በሥጋው ርደተ መቃብር በነፍሱ ርደተ ሲዖል ተፈረደበት፡፡
- እግዚአብሔርን መምሰል አጣ
አምላክ ዘበጸጋ የነበረ ሰው ከአለቆች እንደ አንዱ /ዲያብሎስ/ በኃጢአት በመውደቁ እግዚብሔርን የመምሰል ክብር አጣ፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት ይህን እንደተናገረ
‹‹እኔ ግን እላለሁ አማልክት ናችሁ፤ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፡፡ እናንተ ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ፡፡››/መዝ. ፹፥፩-፮/
+ ገነትን አጣ
እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለምና /ማቴ. ፳፪፥፴፪/ ሞትን የተሸከሙ አዳምና ሔዋን ከገነት ተባረሩ፡፡
+ ባለዕዳ ሆነ
ነጻ ፍጥረት የነበረው አዳም ሞትን ያህል ዕዳ ተሸከመ፡፡
ለአዳም መውደቅ ተጠያቂ ማን ነው?
፩ኛ. የዕፀ በለስ መኖር ነውን?
ዕፀ በለስ ቀድሞውን የተፈጠረችው ለአዳም መሳሳት ምክንያት እንድትሆን ሳይሆን የአዳም ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር፣ እንዲሁ ነጻ ፈቃዱ እንዲገለጥባት፣ ፍጡርነቱ እንዲታወቅባት መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ስለሆነም ዕፀ በለስ መታዘዝን የምትገልጥ የምልክት ዛፍ ነበረች እንጂ በራሷ ተጉዛ መጥታ አዳምን ብላኝ ብላ አላስገደደችውም፤ በአዳም ላይ ሞትን ያመጣችው ባለመታዘዙ እንጂ ሞትን የሚያመጣ መርዝ በመያዟ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ዕፀ በለስ ልትሆን አትችልም፡፡
፪ኛ. ዲያብሎስ ነውን?
ዲያቢሎስ ክፉን ምክር ለአዳምና ለሔዋን መከራቸው እንጂ እጃቸውን ይዞ ዕፀ በለስን አላስቆረጣቸውም፡፡ አመዛዝኖ መወሰን የእነርሱ ድርሻ ነበረ፡፡ ዲያብሎስ ምክንያተ ስህተት ይሆናል እንጂ ስህተት እንድናደርግ የማስገደድ ሥልጣን የለውም፡፡ እርሱን የመቃወም ሥልጣን የእኛ ነው እንጂ፡፡
‹‹ለእግዚአብሔር እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔር ቅረቡት ይቀርባችሁማል›› እንዲል፡፡/ያዕ. ፬፥፰/
አዳም እግዚአብሔር የታመነ አምላክ እንደሆነ ሰባት ዓመት በገነት ሲኖር ፈትኖ አውቋል፡፡ በእነዚያ “አትብላ” የሚለውን የአምላኩን ትእዛዝ በጠበቀባቸው ዓመታት እግዚአብሔር እንደነገረው ጸጋው ሳይለየው፣ ባሕርይው ጉስቁልና ሳያገኘው በሕይወት ኖሮ ነበረና፡፡ የዲያብሎስ ምክር ግን ለአዳም ሁለተኛና እንግዳ ትምህርት ነበረ፡፡ ሰባት ዓመት ፈትኖ ከሚያውቀው ከእግዚአብሔር ሕግም የሚጻረር ነበረ፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ግን አዳም በነጻ ፈቃዱ ወስኖ በዲያብሎስ ምክር ተመራ፡፡ ስለዚህ ለሰው ልጅ መሳሳት ተጠያቂው ራሱ የሰው ልጅ ነው ማለት ነው፡፡
፬-፮-፭ አምላክ ለምን ሰው ሆነ?
አዳምና ሔዋን ከበደል በኋላ እግዚአብሔርን እውነቱን የሰይጣንን ሐሰቱን በተረዱ ጊዜ አዝነዋል፣ አልቅሰዋል፣ ንሰሐም ገብተዋል፡፡ እግዚአብሔርም ንሰሐቸውን ተቀብሎ የሚድኑበትን ተስፋ ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት አምላክ ሰው የሆነው እንደ ተስፋው ቃል ከፍርድ በታች የሆነውንና በሞት ቀንበር የተያዘውን የሰውን ልጅ ለማዳን ነው፡፡ ሰውን ሊያድነው የሚቻለው ከአምላክ ሌላ ማንም ወይንም ምንም አልነበረምና፡፡
፩ኛ. ነቢያት - ሊሆኑ አልቻሉም
ከክርሰቶስ መምጣት በፊት የነበሩት ነቢያት ቀድሞውኑ ወደ ሕዝቡ ይላኩ የነበሩት ለትምህርት፣ ለተግሣጽ እና መጻኢያቱን እየነገሩ ለመምከር ነበረ፡፡ በመሆኑም በየዘሙኑ ከሚደርሰው መከራ በትምህርታቸውና በጸሎታቸው ሕዝቡን ከመዓት ከቁጣ ታድገዋል /መዝ. ፻፭፥፫/ነገር ግን አዳምን ከጥንተ አብሶ ሊያላቅቁት፣ የሞትን ዕዳ ሊከፍሉለት ግን አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም በአዳም በደል ምክንያት ወደ ዓለም የገባው ሞት በአዳም ባሕርይ የተወለዱትን ሁሉ ስለገዛ ነብያት ራሳቸውም ከዚህ የሞት ዕዳ ሊከፍሉለት ግን አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም በአዳም በደል ምክንያት ወደ ዓለም የገባው ሞት በአዳም ባሕርይ የተወለዱትን ሁሉ ስገዛ ነብያት ራሳቸውም ከዚህ የሞት ዕዳ ነጻ ስላልነበሩ ነው፡፡ ባለ ዕዳ ሌላኛውን ባለዕዳ ሊክሰው ዋስ ሊሆነው አይችልምና፡፡ /ሮሜ. ፭፥፲፪-፲፬/
፪ኛ. መላዕክት - ሊሆኑ አልቻሉም
ምክንያቱም የሞትን ፍርድ የፈረደ እግዚአብሔር ነውና ያንን ፍርድ መላዕክት ማንሣት አይቻላቸውም፡፡ በመሆኑም ከገነት አዳምን ያስወጣው በመልዕኩ ሰይፍ ገነትን ያስጠብቀ እግዚአብሔር ስለሆነ እርሱ ያስወጣውን መላዕክት ሊመልሱት አልቻሉም፡፡