ምዕራፍ አንድ : የቤተ-ክርስቲያን ታሪክ መግቢያ
1.1 የቤተክርስቲያን ታሪክ ማለት ምን ማለት ነው?
ታሪክ ማለት በቀደሙት ዘመናት የተፈፀሙ ክንዋኔዎች ስብስብ ወይም በቀደሙት ዘመናት የነበሩ ሰዎች አከናውነውት ያለፉት ሥራ ነው፡፡[ የቤተክርስቲያን ታሪክ ቁጥር ፩ ፤ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ እና መ/ር ቸሬ አበበ ፤በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤ/ማ/መ ማኅበረ ቅዱሳን ፤ ሰኔ ፳፻ ዓ.ም.፤ገጽ 1] ይህ ማለት ግን ታሪክን በቀደመው ዘመን ብቻ ተወስኖ የሚቀርና በመጣውና በሚመጡት ዘመናት ላይ ተጽዕኖም ሆነ አስተዋጽኦ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ታሪክ ( History) ምንም እንኳን በቀደመው ዘመን የተሠራ ቢሆንም የታሪክ ጥናት (Hisetriography) ከአሁኑ ( present) እና ከሚመጣው ( future) ዘመን ጋር ያጣምረዋል፡፡ ስለዚህ ታሪክን ስንማማር የቀደመውን ዘመን እናጠናለን (studying the past)፣ የአሁኑን ዘመን ከቀደመው የታሪክ ዘመን በማነፃፀር እንተነትናለን (analyzing the present) እንዲሁም የቀደሙትንና ያለውን ከግምት በማስገባት መጭውን እንተነብያለን (predicting the future )፡፡ ከቤተክርስቲያን የታሪክ ምሁራን (Histeriographers) አንዱ የሆኑት ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል “ታሪክ ሁለት አጠቃላይ መልኮች አሉት፡፡ እነዚህም አምላካዊና ሰብዓዊ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ልዑል እግዚአብሔር በጊዜ ውስጥ ለዓለም መገለጡን ወሰን የሌለው ጥበቡን፣ ፍርዱንና ምሕረቱን፣ እንዲሁም ክብሩንና ለሰው ልጅ የሚሰጠውን ደስታ የሚገልጠው በታሪክ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ታሪክ በአጠቃላይ የሰው ዘርን መልካሙን ሆነ ክፉ ኑሮውን፣ ቁሳዊውንም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወቱን ክፉውንም ሆነ በጎ ምግባሩን የሚገልጥ ሐተታ ነው፡፡ ዓለሙን ሁሉ የፈጠረና እስከ መጨረሻ ድረስም የሚያስተዳደር አንድ እግዚአብሔር ስለሆነ ታሪክ ዓለም-አቀፋዊ ጠባይ አለው፤ ይህም የእግዚአብሔርን አንድነት ይገልጣል” ይሉናል፡፡
የቤተክርስቲያን ታሪክ ማለት ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ቤተክርስቲያን ያከናወነቻቸውን ሠርታቸው ያለፈችውን በዘመናት ሁሉ የተፈጸመባትን ማንኛውንም ነገር ማለታችን ነው፡፡[የቤተክርስቲያን ታሪክ ፤ ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የታተመ ፤ ከሉሌ መላኩ አዲስ አበባ ፤ 1986 ዓ.ም. ፤ ገጽ 8] የቤተክርስቲያን ታሪክ የክርስትና አምልኮ ታሪክ ነው፡፡ ክርስትና ሃይማኖት ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የሚያጠና የትምህርት ክፍል ነው፡፡ በምድር ያለች የመንግሥተ ሰማያት ምሣሌ ወይም በምድር ያለች ሰማያዊት አካል የሆነች ቤተክርስቲያንን የምናጠናበት በመሆኑ የቤተክርስቲያን ታሪክ መንፈሳዊ ትጋትና አትኩሮት የሚያስፈልገው የእውቀት ዘርፍ ነው፡፡
“የቤተክርስቲያን ታሪክ የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ እንዴት እንደተመሠረተና እንደተስፋፋ የሚገልጥ ሐተታ ነው፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ክብርና የዓለም መዳን ይገለጣል፡፡ በአጠቃላይ የቤተክርስቲያን ታሪክ በምድር ላይ ያለው የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ ነው፡፡ ይህም መንግሥት እንዴት እንደተመሠረተና እንዴት እንደዳበረ የመንግሥቱም ዜጎች እንዴት እንደኖሩ በሰፊው ያትታል፡፡ የመንግሥቱም ዜጎች የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን አማኞችን ያጠቃልላል፡፡”
1.2. ታሪኩ መቼ፣ የት፣ ለምን፣ እንዴት?
ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ መንገዶችና ምክንያቶች በዓለም ዙሪያ ተሰብካለች፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክ ጥናት በክርስቶስ የተመሠረተችው ይህች ቅድስት ቤተክርስቲያን በማንና እንዴት እንደተስፋፋች፣ በየትኛው ጊዜና በየትኛው ቦታ ምን እንዳጋጠማት እናጠናለን፡፡ “በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርታችን (ቀደም ሲል እንደተገለፀው) የክርስትና እምነት የአምላክ መገለጥነው፡፡ ይሁን እንጂ በዘመን በቦታ የተደረገ ስለሆነ መቼ? ወዴትና ለምን? እንደሆነ የምናውቅበት ክፍል ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በጊዜው ሁሉ የገጠመውን ችግርና ምቾት የምንማርበት ነው፡፡”
1.3. የቤተ-ክርስቲያን ታሪክ ምንጮች
የታሪክ ጥናት (Historical Research) ምንጮች ቀዳማዊ ምንጮች (Primary Sources) እና ደኃራዊ ምንጮች (secondary Sources) ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የቤተክርስቲያን ታሪክ ምንጮችም ከእነዚሁ ክፍሎች የወጡ አይደሉም፡፡ የተለያዩ መጻሕፍት[የቤተክርስቲያን ታሪክ ቁጥር ፩ ፤ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ እና መ/ር ቸሬ አበበ ፤በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤ/ማ/መ ማኅበረ ቅዱሳን ፤ ሰኔ ፳፻ ዓ.ም.፤ገጽ 12 ፡፡የቤተክርስቲያን ታሪክ ፤ ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የታተመ ፤ ከሉሌ መላኩ አዲስ አበባ ፤ 1986 ዓ.ም. ፤ ገጽ 8-9] የዘረዘሯቸው የቤተክርስቲያን ታሪክ ምንጮች እንደሚከተለው ተዳሰዋል፡፡
1.የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት፤
2.የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት፣
3.በየጊዜው የተደረጉት የቤተክርቲያን ጉባኤዎችና ውሳኔዎቻቸው፤
4.የቤተክርስቲያን አባቶች የጻፏቸው የታሪክ መጻሕፍት፣ ታሪኩ በተፈፀመበት ቦታና ጊዜ ተገኝተው የቤተክርስቲያንንና የዘመኑን ታሪክ የጻፉ ጸሐፊዎች (ሩፊኖስ፣ ሶቅራጥስ፣ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን፣ አውሳብዮስ… የጻፏቸው መጻሕፍት፤
5.በየጊዘው የሚገኙት የቤተክርስቲያን መቃብራት፣ መቅደሶች፣ ሥዕሎች፣ ገንዘቦች፣ የድንጋይ ላይና የብራና ጽሑፎች፣ የአርኬዎሎጂ (የጥንታዊ ነገሮች ምርመራ) ጥናት ግኝቶች…ወዘተ ለአስረጅነት ይጠቀሳሉ፡፡
6.መንፈሳዊም ሆኑ ዓለማውያን ነገሥታት በቤተክርስቲያን ላይ የደነገጓቸው ልዩ ልዩ ሕግጋት…ወዘተ የታሪኳ ምንጮች ናቸው፡፡
1.4. የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ዓላማና ጥቅም
የቤተክርስቲያን ታሪክ ጥናት ጠቀሜታን ማኅበረ ቅዱሳን ያሳተመው መጽሐፍ[ዝኒ ከማሁ] እንደሚከተለው አትቶታል፡፡ “የሰው ልጅ በተፈጥሮ ጠያቂ አእምሮ ስለተሰጠው ከየት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሔድ ይጠይቃል፤ ያስባል፣ ይመራመራል፡፡ በክርስትና እምነት የሚኖር አንድ ክርስቲንም የቤተክርስቲያንን አካሔድና የትምህርት ይዘት ለመረዳት ጅምሩ ከየትና ከወዴት እንደሆነ በየዘመኑም የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ለማወቅና የራሱንም ማንነት በዚያው ለማገናዘብ መፈለጉ የግድ ነው፡፡ የቤተክርስቲን ታሪክ ማለት ወይም ሁለተኛ የመወለድ ምሥጢር የሚገለጥባት ሲሆን ይህም በምክንያት፣ በዘመንና በተወሰነ ቦታ የተፈፀመ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ የምንማርበትና የምንረዳበት ትምህርት ነው፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍት በየዘመኑና ታሪኩ በተፈጸመበት አካባቢ ላይ ተመርኩዘው የተጻፉ በመሆናቸው ይህን ለመረዳት ተያያዥነት ያለውን የቤተክርስቲያን ታሪክ መማር ያስፈልጋል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደምንማረው በየዘመኑ የነበሩ ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሲዋዥቅ፣ ሲወድቁ ሲነሱ፣ ሲቀጡ ከስህተታቸው ሲማሩ፣ አንዳንዶችም የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምተው አካሄዳቸውን ሲያስተካክሉ እንመለከታለን፡፡ ይህም ቀጥሎ ለመጣው እና ለሚመጣው ትውልድ የትምህርት መሠረት ነው፡፡ በየዘመኑ ያለፈውን ታሪክ የሚመስል ነገር መልኩን ቀይሮ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ስላለፈው ዘመን ማወቅ ከሚመጣው ፈተና ለመጠበቅ ይጠቅማል፡፡ የክርስትና እምነት የታሪክ ሃይማኖት ነው፡፡ እያንዳንዱን ያለፈውን ክንዋኔ ሁሉ ለሚመጣው ትውልድ ለትምህርት ይሆን ዘንድ የተጻፈ የመማሪያና የማስገንዘቢያ እንዲሁም የማስጠንቀቂያ ምልክት ነው፡፡ በዘመነ ኦሪት እግዚአብሔር አምላክ ለእስራኤል ዘሥጋ ያለፈውን የአባቶቻቸውንና የእናቶቻቸውን ታሪክ እንዲያስታውሱ በጸሎታቸው ሰዓት እንዲያነሡት “በእግዚአብሔር በአምላክህ ፊት እንዲህ ብለህ ተናገር፡- አባቴ የተቅበዘበዘ ሶርያዊ ነበር በቁጥር ጥቂት ሳለ ወደ ግብፅ ወረደ በዚያም ተቀመጠ ታላቅ የሆነ የበረታም ቁጥሩም የበዛ ሕዝብ ሆነ፡፡ ግብጻውያንም ክፉ ነገር አደረጉብን፡፡ እግዚአብሔር በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ድንጋጤ፣ በተአምራትም በድንቅም ከግብፅ አወጣን፣ ወደዚህም ሥፍራ አገባን፤ ወተትና ማር የምታፈስሰውንም ይህችን ምድር ሰጠን፡፡” በማለት አዝዞአቸዋል፡፡ ዘዳ 26.5-9)፡፡ ይህም እሥራኤላውያን የቀደሙ አባቶቻቸውን ታሪክ የራሳቸው ታሪክ አድርገው እንዲያወሱትና እንዲያስታውሱት የሚያደርግ ትዕዛዝ ነው፡፡
በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመስቀል ሞት ተላልፎ በተሰጠባት ምሽት የፋሲካ እራት ከደቀመዛሙርቱ ጋር ሲበሉ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት…ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና፡፡” እንዳለው ሉቃ. 21፤9 ፤ 1ኛ ቆሮ. 11.25-26፡፡ ዘወትር በቅዳሴ ሰዓት “ንዜኑ ሞተከ ስለሞትህ እንናገራለን” እያልን እናስበዋል፡፡ ይህም ማለት የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ ያለፈ ያበቃለት ሳይሆን በየዕለቱ በፊታችን እንደነበረ ሆኖ የሚታየን ነው፡፡ የጌታ ሥጋና ደምም አሁንም በቅድስት ቤተክርስቲያን ይፈተታል፡፡ ታዲያ ለእኛ ሲል ራሱን ለመስቀል አሳልፎ የሰጠልን የኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ሥራው እንደምን ተፈጸመ ብለን ይህንን በሚገባ ማስታወስ የምንችለው የቤተክርስቲያንን ታሪክ ያወቅን እንደሆነ ነው፡፡
የቤተክርስቲያን ታሪክ ከዓለማችን ታሪክ አንዱና ዋነኛው አካል ነው፡፡ አንድ ሰው የዓለምን ታሪካዊ ሁኔታ ለማጥናት ቢፈልግ የቤተክርስቲያንን ታሪክ ሊረዳና ሊያውቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም አልፎ የዓለምን የታሪክ መዛግብት በባለቤትነት ይዛ በየዘመኑ የነበረውንም አሰናድታ ያቆየች ቤተክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን የትኞቹ መዛግብት ለምንና የት እንደሚገኙ ለመረዳ የቤተክርስቲያንን ታሪክ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡”
1.5. የቤተ-ክርስቲያን ታሪክ አከፋፈል
የጥንት ሊቃውንት ስለቤተክርስቲያን ሲናገሩ “ቤተክርስቲያን ማለት እግዚአብሔር ግዕዛን ካላቸው ፍጥረታት ጋር ያለው ግንኙነት ነው ይላሉ፡፡ (ግዕዛን ያላቸው ፍጥረታት ሰውና መላእክት ናቸው) ከዚህም የተነሳ የቤተክርስቲያንን ዕድሜ በሦስት ይከፍሉታል፡፡ አንደኛ የመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ሰው ከመፈጠሩ በፊት የዓለም መላእክት የነበረችው የመላእክት አንድነት ናት፤ በሊቃውንት አመሥጥሮ ኹለተኛው የቤተክርስቲያን ዕድሜ ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ የነበሩ ደጋግ ሰዎች አንድነት ነው፡፡ ሦስተኛይቱ እና የመጨረሻይቱ ግን በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት ናት፡፡ እሷም የጸጋና የጽድቅ ምንጭ ናት (ኤፌ 3.1) ከላይ የተወሰኑት ሁለቱ ግን ምሳሌነት(symbol) ብቻ ነበራቸው፡፡[የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ፤ አባ ጎርጎሪዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ ፤1978ዓ.ም. ፤ አዲስ አበባ ፤ ገጽ 12] በግልጽ ለማስቀመጥ ያህል የቤተክርስቲያን ታሪክን በሚከተሉት ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለን እናጠናለን፡፡
1.በዓለመ መላእክት (እስከ አዳም መፈጠር) የነበረችው የመላእክት አንድነት፤
ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ (ማለትም እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዮሐንስ አባት እስከ ዘካሪያስ) ድረስ ያለው የደጋግ ሰዎች አንድነት፤
ይህን ክፍል ዘመነ አበው፤ ዘመነ መሣፍንት፤ ዘመነ ነገሥት እና ዘመነ ነቢያት ( ካህናት) ብለው የታሪክ ባለሙያዎች በአራት ይከፍሉታል፡፡ ዘመነ አበው እና ዘመነ ኦሪት ብለው ለሁለት የሚከፍሉትም አሉ፡፡
3.በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት፡፡
ይህንን ክፍል ደግሞ የቤተክርስቲያናችን የታሪክ ሊቅ ረዳት ፕሮፌሰር ሉሌ መላኩ[ዝኒ ከማሁ ፤ ገጽ 9] በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች እንደሚከፈል ይጠቁማሉ፡፡
1ኛ. የመጀመሪያው የጥንት ቤተክርስቲያን ታሪክ ክፍል፡፡ ጌታ ቤተክርስቲያንን በሐዋርያት ላይ ከመሠረተበት ዘመን ጀምሮ እስከ ትልቁ ቆስጠንጢኖስ ድረስ ነው (እስከ 313 ዓ.ም) አንዳንድ የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች የጥንት ቤተክርስቲያን ታሪክ የሮማ መንግሥት እስከወደቀበት እስከ 476 ዓ.ም ድረስ ነውም ይላሉ፡፡
2ኛ. ሁለተኛው የመካከለኛው የቤተክርስቲያን ታሪክ ክፍል፡፡ ከትልቁ ቆስጠንጢኖስ ጀምሮ ቁስጥንጥንያ በቱርኮች እጅ እከወደቀችበት ጊዜ ድረስ ነው (313-1453)
3ኛ. ሦስተኛው አዲሱ የቤተክርስቲያን ታሪክ ክፍል፡፡ ቁስጥንጥንያ በቱርኮች እጅ ከወደቀችበት ጊዜ ጀምሮ እስከአለንበት ዘመን ድረስ ነው፡፡ (1453-አሁን)
ይህንን በዝርዝር ወደፊት እናየዋለን፡፡ ለአሁን ግን በዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያዎቹሁለቱን ማለትም በዓለመ መላእክት የመላእክት አንድነትንና ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካሪያስ ያለውን የደጋግ ሰዎች አንድነትን እንመለከታለን፡፡
ሀ. ቤተ ክርስቲያን በዓለመ መላእክት
በማኅበረ ቅዱሳን የታተመው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ[ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 15-16] ይህንን እንደሚከተለው አብራርቶታል፡፡ በሀልዎተ እግዚአብሔር የሚያምኑ፣ በፍቅርና በአንድነት ስብሐተ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ግዕዛን ያላቸው ፍጥረታት አንድነት ቤተክርስቲያን ተብሎ ይጠራል፡፡ ስለዚህም ከሰማይ መላእክት መፈጠር እስከ ፍጥረተ አዳም ድረስ እንደዚሁም ከዚያ በኋላ የነበረውን የሰውና የመላእክት አንድነት የተገለፀበት ታሪክ ከቤተክርስቲያን የታሪክ ትምህርት ውስጥ ማካተት አስፈላጊ ነው፡፡
በሥነ ፍጥረት ትምህርት እንደምንማረው መላእክት እግዚአብሔር ሰማይን በፈጠረበት ዕለት፣ በዕለተ እሑድ የተፈጠሩና በሰማያት እግዚአብሔርን ዘወትር ያለማቋረጥ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ በአንድነት የሚያመሰግኑ ረቂቃን መንፈሳውያን ፍጥረታት ናቸው፡፡ የተፈጥሮ ክብራቸው እኩል ቢሆንም በነገድ በነገዳቸው አለቆች አሏቸው፡፡ አገልግሎታቸውም በየነገዳቸው የተከፋፈለ ነው፡፡ በአጠቃላይም የእግዚአብሔርን የምሕረት፣ የቁጣ ወይም የማስጠንቀቂያ መልእክት ወደ ሰው፣ የሰውንም ልመና ወደ እግዚአብሔር በማድረስ ያገለግላሉ፡፡ በአምልኮት፣ በስብሐተ እግዚአብሔርና ይህን በመሳሰለው ሁሉ አንድ በመሆናቸው ይህ አንድነታቸው ወይም ኅብረታቸው ቤተክርስቲያን ይባላል፡፡
ከመላእክት አለቆች ወገን የነበረው ሳጥናኤል ከአምልኮተ እግዚአብሔር በተናወጸበት፣ ጥርጥርና ክህደትን ባመነጨበት ጊዜ ከመላእክት አንድነት (ከቤተክርስቲያን) ተለየ፤ በክህደት የተባበሩት መላእክትም እንዲሁ ንጽሕት ከሆነችው ከመላእክት ማኅበር አብረውት ተለዩ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላም ርኩሳን መናፍስት (ሰይጣናት) ተብለው በመጠራት ከክብራቸው ተዋርደው ወደ ምድረ ፋይድ ወረዱ፡፡ እስከ ዓለም ፍጻሜም ድረስ የክፋት ምንጭ በመሆንና ሰውን አሳስተው ከእግዚአብሔር መንግሥት እንዲለይ ለማድረግ በመውጣትና በመውረድ ይኖራሉ፡፡ አዳምም ከተፈጠረ በኋላ በአምልኮትና እግዚአብሔርን በማመስገን ከቅዱሳን መላእክት ጋር በኅብረት ይኖር ነበር፡፡ ሆኖም ግን አዳም ሕገ እግዚአብሔርን ከጣሰ በኋላ ያ በመጀመሪያ የነበረው ኅብረት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ጌታ በተወለደበት፣ የማዳን ሥራው በተጀመረባት ሌሊት ደግሞ ተቋርጦ የነበረው ኅብረት እንደገና ተመሥርቶ ሰውና መላእክት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ” በማለት በአንድነት ዘምረዋል፡፡ (ሉቃ. 5.14)፡፡ ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ውስጥም የጌታን መወለድ የምሥራች በመናገር፣ በተለያየ ጊዜም የሰውን ልጅ በመገሠጽ እና በማስተማር ተሳትፈዋል፡፡ ሉቃ. 2.9-14፣ ሐዋ. 8.4-6
ለ. ቤተ-ክርስቲያን ከአዳም መፈጠር ጀምሮ
እግዚአብሔር አምላክ ከሌሎቹ ፍጥረታት ሁሉ በተለየ ሁኔታ የሰውን ልጅ በራሱ አርአያና ምሳሌ አድርጎ በመፍጠር ከባረከው በኋላ ለቀሩትም ፍጥረታት የበላይ ገዢ እንዲሆን ሾመው ሰው በተፈጥሮ ነጻ ፈቃድ፣ ክፉና ደጉን የሚለይበት ሙሉ አእምሮ ያለው ሲሆን ፈጣሪውን የሚያስታውስባት አንዲት ትእዛዝ ተሰጥታው ነበር፡፡ ይኸውም “ከዕፀ በለስ አንዳትበላ” የሚል ነው፡፡ አንዳንድ የቤተክርስቲያን መምህራን ይህን ትእዛዝ የፍቅር ሕግ በማለት ይጠሩታል፡፡ምክንያቱም ከዕፀ በለስ ቀጥፎ ከበላ ይሞታልና እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጅ እንዳይሞትበት ፈልጎ ይህንን ትዕዛዝ ሰጠው፡፡ ነገር ግን አዳም ከሚወደው ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚያሳስተውን የእባብ ምክር ሰምቶ ዕፀ በለስን በመብላት ሞትን መረጠ፡፡ ይህንንም ትእዛዝ በማፍረሱ ሞት የማይስማማው የነበረው ሞትን በራሱ ላይ አመጣ፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የልጅነት ጸጋ በማጣቱም ከክብሩ ተዋርዶ፣ ከገነት ወጥቶ በነፍሱ በሲዖል እንዲቀጣ፣ እስከዚያውም ድረስ ወደ ምድረ ፋይድ በመውረድ ጥሮ ግሮ በወዙ ይበላ ዘንድ ተፈረደበት፡፡ ይህንንም ቅጣት ከርሱ የተወለዱ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ሁሉ በውርስ ተካፈሉት የሰው ልጆችም የኃጢአት ዝንባሌ እየጨመረ በመሔዱ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የነበረው ልዩነት እየሰፋ ሔደ፡፡ ብዙዎቹም የፈጠራቸውን እግዚአብሔርን ዘንግተው በተፈጥሮ ከነርሱ በታች የሆኑ በሰማይና በምድር ያሉትን ግዑዛን ፍጥረታት ከዚያም በባሰ የፍጥረታትን ቅርጽ (ምስል) ማምለክ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ አዳም ንስሐ በገባ ጊዜ የሰጠውን የተስፋ ቃል (ዘፍ. 3.15-22) በማሰብ የሰው ዘር ፈጽሞ እንዳይጠፋ በየወቅቱ ለበረከት የሚሆኑ አንዳንድ ሰዎችን አተረፈ፡፡ ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ ድረስ ያሉትና በዘፍጥረት ምዕራፍ አምስት ላይ የተዘረዘሩት አባቶች አሥሩ አበው በመባል ይጠራሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በትውልድ ሰባተኛ የሆነው ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉ ሲዖልን እንዳያይ ሳይሞት ተሰወረ፡፡ ልጁ ማቱሳላም ከሰው ልጆች ይልቅ ረጅም ዕድሜ 969 ዓመታት ኖረ፡፡
ዓለም በንፍር ውኃ ከጠፋችበት ከኖኅ ዘመን በኋላ እንዲሁ በሴም በኩል 10 ትውልድ ቆጥረን አብርሃምን እናገኛለን፡፡ አብርሃም በትውልዱ ሶርያዊ ሲሆን እርሱ ብቻ በፍጹም ልቡናው እግዚአብሔርን (የሰማይንና የምድርን አምላክ) በማምለኩ ከዘመዶቹ (ከካራን ምድር) እንዲለይና ወደማያውቀው ሀገር እንዲሄድ በእግዚአብሔር ተጠራ፡፡ አብርሃምም ሳያቅማማ በእምነት የታዘዘውን በመፈጸሙ እግዚአብሔር ማርና ወተት የምታፈልቀውን ምድረ ከነዓንን ከርሱም በኋላ የልጅ ልጆቹ ሁሉ ይወርሷት ዘንድ ሰጠው፡፡ ስለዚህም ይህ ቦታ ምድረ ርስት፤ የቃል ኪዳን ሀገር ይባላል፡፡
ይስሐቅና ያዕቆብም የአባታቸውን የአብርሃምን ፈለግ በመከተላቸው እግዚአብሔር ባረካቸው፡፡ ነገር ግን በያዕቆብ ዘመን በከነዓን ረሃብ ስለነበር እርሱና 12 ወንዶች ልጆቹ በ1ሺህ7መቶዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ገደማ ወደ ግብጽ ምድር ገቡ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ግን በግብፅ ሀገር ዮሴፍን (የያዕቆብን 11ኛ ልጅ) የማያውቅ ንጉሥ በመንገሡ የእስራኤል(የያዕቆብ) ልጆች በግብፅ ምድር በባርነትና በስቃይ መኖር ጀመሩ፡፡ ከ400 ዓመታት በኋላም (በ1ሺ3መቶ) ዓመት ከጌታ ልደት በፊት) እግዚአብሔር የሕዝቡን ጩኸት ሰምቶ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የገባውን ቃል ኪዳን አስቦ ሕዝበ እሥራኤልን በግብፅ ሀገር በጸናች እጅ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ በሙሴ መሪነት አወጣቸው፡፡ በጉዞአቸውም ወቅት ሕጉን እንዳይዘነጉ ከአባቶቻቸው መንገድ ወጥተው እንዳያሳዝኑት እግዚአብሔር አምላክ ሕገ ኦሪትን ሰጣቸው፡፡ ይህንንም ሕግ እንዳይረሱትና የልጅ ልጆቻቸው በሥርዓት ይጓዙበት ዘንድ በመጽሐፍ እንዲያስቀምጠው ሙሴን አዘዘው፡፡ ይህም ማለት ሕገ ኦሪት ተሠራ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ያለው ዘመን ዘመነ ኦሪት ሲባል ከዚህ ቀደም የነበረው ደግሞ የሕገ ልቡና ዘመን በመባል ይታወቃል፡፡ የተጻፈ ሕግ ያልነበረበት ሰው ሁሉ በተፈጥሮ የተሰጠውን ክፉና ደጉን የመለየት ስጦታ (በሕሊና ሕግ) ብቻ ይመራ ነበርና፡፡
ሕዝበ እሥራኤልን እየመራ ይጓዝ የነበረው ሙሴ በናባው ተራራ ሲሞት መሪነቱን ኢያሱ ተረክቦት ሕዝቡን ዮርዳኖስን አሻግሮ በከነዓን ርስት አከፋፈላቸው፡፤ ከኢያሱ በኋላ ሳኦል ንጉሥ እስከሆነበት ድረስ ባሉት 450 ዓመታት ውስጥ ከ13 በላይ የሚሆኑ መሳፍንት እንደካህንም እንደመስፍንም እየሆኑ ሕዝቡን አስተዳድረዋል፡፡ ከሳኦል ቀጥሎ የነገሠው ዳዊት በኬብሮን 7 ዓመታት በንግሥና ከተቀመጠ በኋላ ኢየሩሳሌምን በመመሥረት ለ33 ዓመታት በዚያ ነግሦአል፤፤ የእሥራኤል ሦስተኛው ንጉሥ ሰሎሞን የመጀመሪያውን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም አሠርቷል፡፡
በሰሎሞን ልጅ በሮብአም ዘመን በ922 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት እሥራኤላውያን በአገዛዝ ተጣልተው ለሁለት ተከፈሉ፡፤ የይሁዳና የብንያም ነገዶች መናገሻ ከተማቸው ኢየሩሳሌም እንደሆነች በደቡብ በኩል ሲቀሩ አሥሩ ነገድ ተለይተው መናገሻቸውን ሴኬም፣ ከተማቸውን ሰማርያ ንጉሣቸውን ኢዮርብአም አድርገው በሰሜኑ ክፍል ለብቻቸው መኖር ጀመሩ፡፡ ነገር ግን በ792 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት በሰሜን በኩል የሚኖሩትን እነዚህን አሥሩን ነገረ አሦራውያን በስልምናሦር መሪነት ወርረው ከተማቸውን ደመሰሱባቸው በቅኝ ግዛትም ያዟቸው፡፡ በዚህ የቅኝ ግዛት ዘመንም ባሕላቸውም ሆነ ዘራቸው ከአሕዛብ ጋር በመደባለቁ ሳምራውያን ተብለው መጠራት ጀመሩ፡፡ በደቡብ በኩል የቀሩት ሁለቱ ነገዶች ደግሞ አይሁድ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህ ክፉ ነገር እንዳይደርስ ሀብታም ከደሃ ሳይለይ ሕዝቡ ተዛዝኖ በፍቅር እንዲኖር እግዚአብሔር በኤልያስና በኤልሳዕ እንዲሁም በተለያዩ ነቢያት አማካኝነት አስቀድሞ አስጠንቅቆ ነበር፡፡ ሰሚ ልቡና አላገኘም እንጂ፡፡
በተመሣሣይ መልኩ በደቡብ በኩል ለነበሩት ለሁለቱ ነገዶችም ከወንድሞቻቸው ሁኔታ ባለመማራቸው እንዲያውም የነዚያ መጥፋት የነርሱን ትክክለኛነት ያሳየ መስሏቸው ተደስተው ስለነበር እነ ኢሳይያስንና ኤርምያስን ሌሎችንም ነቢያት እየላከ ከጥፋታቸው እንዲመለሱና እርሱን በማምለክ ሕጉን እንዲጠብቁ አስተማራቸው፡፡ ያም ባለመሆኑ የወገኖቻቸው ዕጣ ፈንታ ለነርሱም ደረሳቸው፡፡ በ586 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት በናቡከደነፆር መሪነት በባቢሎናውያን ዘምተው ኢየሩሳሌምን በማጥፋት በሰሎሞን ዘመን የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈረሱት፣ የቤተ መቅደሱን ንዋያት ሳይቀር ዘረፉ፤ ሕዝቡንም በምርኮ ወሰዱ፡፡
አይሁድ ለ70 ዓመታት በስደትና በምርኮ ከኖሩ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው መንግሥት መሥርተው መኖር ጀመሩ፡፡ ከዚያም በኋላ እንደገና በፋርሶች በኋላም በ330 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት በግሪኮች በቅኝ ግዛት ተገዝተዋል፡፡ በመጨረሻም በ63 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ሮማውያን የቅኝ ገዢነቱን ተረክበዋቸዋል፡፡ በዚህ የቅኝ ግዛት ቅብብሎሽ ውስጥ አይሁድ ባሕላቸው፣ ሃይማኖታቸውና አኗኗራቸው ሁሉ ችግር ላይ+ወድቆ ነበር፡፡ የቅኝ አገዛዙም ስለመረራቸው ነጻ ወጥተው የዳዊት መንግሥት እንደገና ተመሥርታ ለማየት እጅግ ይናፍቁ ነበር፡፡
የጌታችን በሥጋ መገለጫ ጊዜ በተቃረበበት ዘመን ደግሞ ራሳቸው አይሁድ አንኳን ሳይቀሩ በእምነትም በአመለካከትም ተለያይተው የተለያዩ ቡድኖችን መሥርተው ነበርና እንደሚከተለው እናያቸዋለን፡፡
ሀ. ፈሪሳውያን
ፈሪሳውያን ከአይሁድ የሃይማኖት ወገኖች አንዱ ክፍል ሲሆኑ የስማቸውንም ምንጭ ፈሪሳዊ በዕብራይስጥ ፓራሽ ከሚለው ቃል የተገኘ፣ ትርጉሙም የተለየ ማለት ነው፡፡ እነዚህም የሙሴን ሕግ በብዙ ጥንቃቄ እንጠብቃለን፣ እንተረጉማለን የሚሉና ሰውም ሕጉን እንዳይተላለፍ በማለት የራሳቸው ትእዛዝና ሥርዓት (ሥርዓተ ረበናት) ያወጡ ናቸው፡፡ አጠቃላይ ትምህርታቸውም የሰው ጽድቅ ሕግን በመፈጸም ላይ ነው የሚል ነው የሐዋ. 11፤47-27፡፡
ፈሪሳውያን የመሲህን መምጣት የሚጠባበቁና በትንሳኤ ሙታን የሚያምኑ ቢሆኑም ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ በዚህ ዓለም እንዳለው ዓይነት ሕይወት አለ ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ይጠብቁት (ተስፋ ያደርጉት) የነበረው መሲህ በጦር ኃይል ከሮማውያን ቅኝ ገዢዎች ነጻ የሚያወጣና ከዚያም ኢየሩሳሌምን መናገሻ ከተማው እነርሱን ደግሞ የቅርብ ባለሟሎቹ አድርጎ የዳዊትን መንግሥት የሚመልስ ምድራዊ ንጉሥ ነበር፡፡ ክርስቶስን ለማመንና ለመቀበል ዕንቅፋት የሆናቸውም አንዱ ይህ አስተሳሰባቸው ነበር፡፡
ለ.ሰዱቃውያን
ሰዱቃውያን የፈሪሳውያን ተቃራኒ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ካህናት ነበሩ፡፡ ሊቀ ካህናትም ብዙ ጊዜ ከእነርሱ ይመረጥ ነበር፡፡ በአይሁድ ሸንጎም የሚበዙት ሰዱቃውያን ነበሩ፡፡ ፈሪሳውያንን በመቃወም የሙሴ የሕግ መጻሕፍትን ብቻ እንጂ የነቢያትን መጻሕፍት ፈሪሳውያን የጨመሯቸው የወግ ሥርዓቶች ናቸው በማለት አይቀበሉም ነበር፡፡
በትንሣኤ ሙታን ፈጽመው የማያምኑ ስለሆኑ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ሰው እንደሥራው ዋጋውን የሚቀበል መሆኑን አያምኑም፡፡ ዘዳግ. 25÷5-8፡፡ ክርስቶስ ስለሰዱቃውያን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ማቴ. 16÷6-17፡፡ እነርሱም ክርስቶስን አሳልፈው የሰጡ በኋላም ሐዋርያትን ያሳደዱ ናቸው፡፡ የሐዋ.ሥ 4÷1-22፡፡
ሐ. ኤሲያውያን
እነዚህ ደግሞ ከፈሪሳውያን ጋር በአስተሳሰብ ተጣልተው ከፈሪሳውያን ማኅበር የተለዩና የተገነጠሉ አንዱ ማኅበር ናቸው፡፡ ኩምራን በምትባል ቦታ ሙት ባሕር አካባቢ ገዳም ገድመው የመሲህን መምጣት በጾምና በጸሎት ይጠባበቁ ነበር፡፡ እንደ እነሱ አስተሳሰብ /እምነት/ መሲህ ሲመጣ በተአምራት ከጠላቶቻቸው /ከሮማውያን/ እጅ ነጻ ያወጣናል በማለት ያምኑ ነበር፡፡
መ. ሌሎች አነስተኛ ቡድኖች
ዚሎታውያን፡- ዚሎታውያን ማለት ታጋዮች ወይም ቀናተኞች ማለት ነው፡፡ እነዚህ የአይሁድ ወገኖች ሲሆኑ ዓላማቸውም አገራቸው ፍልስጥኤምን ከሮማውያን ነጻ ለማውጣት በኃይልና ጭካኔ በተሞላበት አመፅ ይታገሉ ነበር፡፡ በሃይማኖታቸው የፈሪሳውያንን እምነት የሚከተሉ ሲሆኑ ፈሪሳውያን ከፖለቲካ የተገለሉ በመሆናቸው ይንቋቸውና ይጠሏቸው ነበር፡፡ ዚሎተውያን በ6 ዓ.ም ከናዝሬት በስተሰሜን በ4 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የሴፕፎሪስ ከተማ መሽገው በፈጸሙት ጠጣር አመጽ በሮማውያን ብርቱ ጥቃት ተደመሰሱ፡፡ በዚህ ጊዜም ብዙ አይሁዶችም በስቅላት ተቀጡ፡፡
ሳዶቃውያን፡- ይህ ቡድን የሰዱቃውያንን እምነት የሚከተልና በጣም አጥባቂ (አክራሪ) ከመሆኑ የተነሳ የካህናትን መዝናናትና ቸልተኝነት በመቃወም እንደ ኤሰናውያን ተለይተው በአንድ መንደር ይኖሩ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ከተጻፈው ሕግ ጋር አፍአዊውን የአባቶች ወግ ማለት ትውፊት የሚሰጡት ትርጉም በጣም የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ ለምሳሌ በሰንበት ቀን አንድ እንስሳ ከጉድጓድ ላይ ቢወድቅ አያነሱትም ነበር፡፡
ሔሮዳውያን፡- እነዚህ ወገኖች የታላቁ ሔሮድስ ፓርቲ ደጋፊዎችና ወገኖች ሲሆኑ ታላቁን ሄሮድስ ከንጉሥ ዳዊት ጋር እያመሳሰሉ በዳዊት ቦታ የተተካ ዳግማዊ ዳዊት ነው፤ መሲህ ከሄሮድስ ዘር ይወለዳል እያሉ የሄሮድስን መንግሥት ሲያሞግሱና ሲያሞካሹ የነበሩ ናቸው፡፡ ሔሮዳውያንና የፈሪሳውያን ጠላቶች ነበሩ፡፡ ታላቁ ሔሮድስ በኃይለኛ ካንሰር (ነቀርሳ) ተሰቃይቶ ከሞተ በኋላ ልጁ አርኬላኦስ በቦታው ተተክቶ ይሁዳን ሲገዛ በአስተዳደሩ ደካማ ሆኖ በመገኘቱ እሱም በአውግስጦስ ቄሳር ከሹመቱ ተሸሮ በቦታው ሮማዊው ጲላጦስ (ፒለት) በመተካቱ ሄሮዳውያን ብርሃነ ዓለማቸው ስለጠፋባቸው በዚሁ አኩርፈው በሮማውያን ላይ ጥላቻን የፈጠሩና ዝንባሌያቸውም ወደ ቤተመቅደስ የሆነ የፖለቲካ ነገር ሕይወታቸውን በይበልጥ የገዛውና ያጠቃው ከአርኬላዎስ መሻር በኋላ በሮማውያን ላይ ሁለት ምላስ በመናገር ሲያጉረመርሙ የነበሩ ናቸው፡፡ በመጨረሻም ሄሮዳውያን ጌታ ኢየሱስን ለሞት አሳልፎ ለመስጠት ከፈሪሳውያን ጋር ተባብረዋል፡፡