ምዕራፍ አራት : ዘመነ ሠማዕታት
4.1 ቤተ ክርስቲያን በኔሮን ቄሳር ዘመነ መንግስት
ኔሮን ከ54-68 ዓም ድረስ በሮም ከተማ ላይ የነገሰ ንጉስ ነው፡ ፡ይህ አዕምሮው የተቃወሰ ንጉስ ቤተሰቡን የገደለ ቢሆንም በመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት በክርስቲያኖች ላይ ምንም ችግር አልፈጠረም፡፡ በኋላ ላይ በ64 ዓ.ም ቤተ መንግስቱን አስፋፍቶና አስውቦ እንደገና ለመስራት ፈልጎ ሰፊ ቦታ ለማግኘት አስቦ በከተማዋ ላይ ከባድ እሳት አስነስቶ ለሰባት ቀናት ሲያጋይ ቆይቶ ከከተማዉ አጋማሽ የሚበልጠውን አወደመው፡፡ የጣዖት አምልኮ ቦታዎች፣ ታላላቅ ሐውልቶች ፣ የሕዝብና የቤተ መንግስት ሕንጻዎች በሙሉ ወደሙ፡፡ ወራቱ በጋና ሙቀት የበዛበት ስለነበረ እሳቱን ለማጥፋት በቀላሉ አልተቻለም፡፡ በዚህ ከፍተኛ ጥፋትና ውድመት በሮም ከተማ ሕዝብ ላይ ከባድ ሐዘን ደረሰ ሕዝቡም እጅግ ተቆጣ፡ በዚህ ጊዜ እሳቱን ንጉሡ ኔሮን እንዳስነሳው ጭምጭምታ በሮም ከተማ ውስጥ ይሰራጭ ጀመር፡፡ ኔሮን የሕዝቡ ቁጣና በከተማዋ የተሰራጨው ጭምጭምታ ሰለአስፈራው የእሳቱ መነሻ ሰበብ በሌሎች ላይ ለማድረግ ሰይጣናዊ መንፈስ አደረበት፡፡ ስለዚህም በሎሌዎቹ አማካኝነት “እሳቱን ያስነሱት ክርስቲያኖች ናቸው፡፡” የሚል የሐሰት ወሬ በመላዋ ከተማ እንዲሰራጭ አደረገ፡፡በመላዋ የሮም ከተማ የሚገኙ ክርስቲያኖችና መሪዎቻቸው እየታደኑ ተይዘው እንዲታሰሩና እንዲገደሉ ትዕዛዝ ከቄሳር ወጣ፡፡ ስለዚህ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች እየተያዙ በሚያሰቅቅ ሥቃይ ተገደሉ፡፡
ግማሾቹም በከብት ቆዳ እየጠቀለሉ ለውሾች ጣሏቸው፡፡ ሌሎችን ደግሞ በእንጨት እየሰቀሉ አቃጠሏቸው፡፡ በመጋዝ ሰነጠቋቸው፡፡ በዚህ አኳኋን በሮም ከተማ የነበሩ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች የሰማዕትነት ጽዋ በኔሮን ዘመነ መንግስት ተቀበሉ፡፡
4.2 ቤተ ክርስቲያን በድምጥያኖስ ዘመነ መንግሥት /፹፩-፺፮ ዓ.ም/
ከኔሮን ቄሳር በኋላ በክርስቲያኞች ላይ ብዙ ስቃይ በማድረስ የታወቀዉ ድምጥያኖስ ነዉ፡፡ ድምጥያኖስ ገና በሕይወት ዘመኑ እያለ የራሱን ምስል አሰርቶ እንዲሰገድለት በማዘዝ የታናሽ እስያ ክፍል ወደ ምትሆን ወደ ኤፌሶን ላከዉ፡፡ ያን ጊዜ ዮሐንስ ወንጌላዊ በኤፊሶን በሐዋርያዊ ተግባሩ ላይ እንደነበረ ይህን ምስል ተመልክቶ በጣም ተቃወመ፡፡የኤፊሶን ክርስቲያኖች ከዮሐንስ ጋር ሆነዉ የድምጥያኖስን የግዑዝነት ሥራ ተቃወሙ፡፡በዚህ ጊዜ ዮሐንስ ተይዞ ወደ ሮም እንዲወስድና የተቃወመበትን ፍርድ እንዲቀበል የሮም ምክር ቤት ወሰነ፡፡ ዮሐንስ ያን ጊዜ በእድሜ በጣም የሸመገለ ቢሆንም ሐዋርያዊ ግዴታ ስለሆነ ፍርዱን ለመቀበል ወደ ሮም ሔደ፡፡ ሮም በደረሰ ጊዜ የሮም ዳኞች በደሴተ ፍጥሞ እንዲጓዝ ወሰኑበት ዮሐንስም በሮም ቄሳሮች ላይ ያመፁ ሁሉ በእስራት ወደ ሚቀጡበት ወደ ደሴተ ፍጥሞ ተወሰደ፡፡ ዮሐንስም እዚያዉ እያለ ‹‹ራዕይ ዮሐንስን›› እግዚአብሔር ገልፆለት ሊፅፍ ችሏል፡፡ ራዕ ፩፥፱
4.3 ቤተ ክርስቲያን በትራጃን ዘመነ መንግሥት / ፺፰ -፻፲፯ዓ.ም/
በኃይል ብቻ ሳይሆን በዘዴና በማስፈራራትም ጭምር ክርስትያኞችን ወደ ቤተ- ጣዖት ለመመለስ ይሞከር ነበር፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ የሰማዕትነት ተጋድሎዉን የፈፀመዉ በዚህ ዘመን ነዉ፡፡ በቤተ ክርስትያን ታሪክ እንደ ሚነገረዉ ቅዱስ አግናጢዮስ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታን ‹‹በመንግስተ ሰማያት ካሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?››ባሉት ጊዜ በአጠገቡ የነበረዉ ንህፃን ልጅ በእጁ እያመለከተ ‹‹እንደዚህ ህፃን ካልሆናችሁ መንግስተ ሰማያትን አትወርሱም›› ያላቸዉ ህፃን እንደሆነ ይነገራል፡፡ ማቴ ፲፰፥ ፩-፱፡፡ አግናጢዮስ የወንጌላዊዉ ዮሐንስ ተማሪ ሲሆን በአንጾኪያም ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ቤተ-ክርስቲያን አገልግሏል፡፡ አግናጢዮስ በአንጾኪያ የክርስቶስን ወንጌለ መንግስት ሲያስተምርና ሲሰብክ በትራጃን ወታደሮች ተይዞ ወደ ሮም ተወሰደ፡፡ በህይወት እንዲቆይላቸዉ ጉጉት የነበራቸዉ የአንጾኪያ ክርስቲያኖች ልብን በሚሰብር ቃል እንዲያመልጥ መላልሰዉ ቢለምኑትም እርሱ ግን በክርስቶስ ስም መሞትን ስለመረጠ ለምእመኖቹ እንዲህ አላቸዉ፡፡ ‹‹ልጆቼ ተዉኝ ልቤን አትስበሩት፡፡ እኔ እንደ ንጹህ መገበሪያ (ስንዴ) ለፈጣሪዬ መስዕዋት ለሚሆን ነዉ የምሔደዉ›› እዚያ ሲደርሱ የሮም ነገስታት በክርስቲያኖች ላይ እንደሚያደርጉት ሁሉ በትያትር ማሳያ ቦታ /ኮሎሲየም/ ለነበሩት አናብስት ተጣለ፡፡ አግናጥዮስ ምጥዉ ላንበሳ ያሰኘዉ ይሀዉ ነዉ፡፡ በዚህ ሰማዕትነቱን ፈፀመ፡፡
ቤተ ክርስቲያን በማርቆስ ኦሬሊየስ (አዉሬሊየሰ) ዘመነ-መንግሥት /፻፩-፻፹ዓ.ም/ በማርቆስ ኦሬሊየስ ፈላስፋ የነበረ ንጉስ ሲሆን ክርስቲያኖች ሞገደኞች፤ ወፈፌዎች ይላቸዉ ነበር፡፡ እንዲህም እያለ ቤተ ክርስቲያንን ያሳድድና ክርስትያኖችን ያንቋሽሽ ነበር፡፡ ከ፻፹-፻፺፪ ዓ.ም የነገሰዉ ቄሳር ከሞዶስ ባይሳካለትም ቀስ በቀስ በስጋዊ ጥበብ ወይም በዘዴ ቤተ-ክርስትያንን ለማጥፋት ዕቅድ ነበረዉ፡፡ ሌሎችም እስክንድሮ ሳዊሮስ ከ፪፻፪ -፪፻፭ዓ.ም እነ ፊሊጶስ ዓረባዊ ከ፪፻፵፬-፪፻፵፱ ዓ.ም ያሉት ነገስታት ክርስቲያኖችን ንቀዉና ተጸይፈዉ ያሳድዷቸዉ ነበር፡፡
4.4 ቤተ ክርስቲያን በዳክዮስዘመነ መንግሥት /፪፻፵፱ -፪፻፶፩ዓ.ም/
በቤተ ክርስቲያን የመጨረሻዉን ድል ለማግኘት ብዙ ቄሳሮች ያላቸዉን ኃይልና ዘዴ በሙሉ ተጠቅመዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ከበድ ያለዉ ዘዴ ግን በዳክዮስ ዘመነ-መንግስት የወጣዉ አዋጅ ነዉ፡፡ ዳክዮስ ወዲያዉ እንደነገሰ የክርስቲያኖችን መመሪያ አጥንቶ ከርስቲያኖችን በጣም የሚጎዳቸዉን ነገሮች ከጠበብቱ ጋር ተመካክሮ የሚከተለዉን አዋጅ አወጀ፡፡ አዋጁም በሮም ግዛት በሮማዊ ዜግነት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሉ በሮማ ባህል መሰረት የሮማ መንግስት ህጋዊ ነዉ ብሎ የተቀበለዉንና ነገሰታቱንም ሲያመልኳቸዉ የኖሩትን ጣኦታት በግዴታ እንዲያመልኩና መብአ እንዲያቀርቡ የሚል ነበር፡፡ ይህንን ሳይፈጽም የተገኘ ማንኛዉም ዜጋ በሞት ይቀጣ ነበር፡፡ ይህን መንግስታዊ አዋጅ ሮም ለብዙ ዘመን ስትከተለዉ የነበረዉን የሃይማኖት ነፃነት ህግ የሚያፈርስ ስለሆነ በቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሮማ ግዛቶች በሚኖሩ አይሁዳዉያንና አረማዉያን ሁሉ ሁከት ተፈጠረ፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖች ሌላ አማራጭ መንገድ ስለሌላቸዉ አዋጁን አላከበሩም ስለዚህም ወንድ ፣ ሴት፣ ህፃንና ሽማግሌ ሳይለይ በሮማ ግዛት በሚኖሩ ክርስቲያኖች ላይ አሰቃቂ የሆነ የሞት ቅጣት ታዘዘ፡፡ ህፃናት ሁሉ ከእናታቸዉ እቅፍ ታረዱ፡፡ እናቶችም የልጆቻቸዉ መታረድ ከአዩ በኋላ አንድ እግራቸዉ በግንድ ላይ እየታሰረ ሌላ አካላቸዉ ደግሞ ወደ ታች ቁልቁል እየተንጠለጠለ በአሰቃቂ አሟሟት የሰማዕትነት ጽዋቸዉን ተረከቡ፡፡ ለዚህ ነው ከዚህ ዘመን ጀምሮ ክርስቲያኖች ስቃዩ ስለጸናባቸዉ በህይወት ለመኖርም ሆነ ሃይማኖታዊ ተልእኮአቸዉን ለመፈፀም እንዲችሉ በተለይም በሮማና አካባቢዋ ዋሻ በማዘጋጀት የአለት ፍርክታ ለመፈለግ ወደ ግበ ምድር የገቡት፡፡
4.5 ቤተ ክርስቲያን በዲዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግሥት /፪፻፹፬ -፫፻፭ዓ.ም/
ከላይ ከተገለፁት ቄሳሮች በኋላ በአይነቱ ሆነ በብዛቱ ተመሳሳይና ተወዳዳሪ የሌለዉ የክርስቲያኖች እልቂት የተፈፀመዉ በዲዮቅልጢያኖስ ዘመነ መንግስት ነዉ፡፡ ዲዮቅልጢያኖስ በ፪፻፸ ዓ.ም የሮማ መንግስት ንጉሰ ነገስት ሆኖ ከተሾመበት ጊዜ አንስቶ እስከ ፪፻፺፭ዓ.ም ድረስ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት አልሞከረም ነበር፡፡ጋለሪዮስ የተባለ የልጁ ባል ከበታቹ ሆኖ የምስራቋን ክፍል ይገዛ የነበረዉ ክርስትናን በጣም ይጠላ ስለነበር በእርሱ ምክር በመመረዝ መጀመሪያ በጦር ሰራዊቱ የነበሩትን ክርስቲያኖች ለጣኦት እንዲሰግዱ ሲያዛቸዉ እንቢ ስላሉ ማዕረግ ያላቸዉን ማዕረጋቸዉን እየገፈፈ ተራ ሰዎችንም ጭምር አባረራቸዉ፡፡ ከ፪፻፺፭ -፪፻፺፯ዓ.ም ድረስ ለሁለት አመተታት ያህል እያከታተለ በክርስቲያኖች ላይ ልዩ ልዩ የሆነ ጥብቅ አዋጆችን አወጀ፡፡ አዋጁም የሚከተለው ነበር፡፡
1.አብያተ ክርሰቲያናት እንዲ ደመሰሱ፡፡
2.ክርስቲያኖች እርስ በእርሳቸዉ እንዳይገናኙ፡፡
3.ስለክርስትና ሐይመኖት የሚናገሩ መጻሕፍት ሁሉ እንዲቃጠሉ፡፡
4.የቤተ-ክርስቲያን ንብረት የሆነ ሁሉ እንዲወረስ፡፡
5.ማንኛዉም የሮማ ዜጋ ክርስቲያን ከሆነ ከመንግስት ስራ እንዲወገድ፡፡
6.ባሮች ክርስትናን ከተቀበሉ ነፃ የመዉጣት እድል የላቸዉም፡፡
7.ክርስቲያኖች ምንም ህጋዊ ምክንያት ቢኖራቸዉ በማንም ላይ ክስ መመስረት እና ስለ መብታቸዉ መከራከር አይችሉም የሚል ነበር፡፡
ከዚህ በኃላ ለጣኦትመሰዋትነት አናቀርብም ያሉ ክርስቲያኖች ደማቸዉ እንደ ጎርፍ ፈሰሰ፡፡ ከአራዊት በማታገል፣ በመጋዝ በማሰንጠቅ፣ በእሳት በማቃጠል፣ ለተራቡ አዉሬዎች በመጣል ክርስቲያኖችን ፈጇቸዉ፡፡ ይህ ሁሉ መከራና ስቃይ በክርስቲያኖች ላይ ከደረሰ በኋላ የዲዮ ቅልጢያኖስ ዙፋን እያዘመመና እየወደቀ ሲሄድ በ፫፻፭ዓ.ም ስልጣኑን ለአማቹ ለጋሌሪየስ ለቆ ወደ ግል የስጋዊ ኑሮ ተመለሰ፡፡ እንደዚህ ያሉ ስቃዮችም ክርስቲያኖችን በማጥፋት ፈንታ እያደፋፈሯቸዉና እያበረታቷቸዉ ይሄዱ ነበር፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ቄሳሮች ሌላ ልዩ ልዩ ስደቶችን በክርስቲያኖች ላይ ያወጁ ቄሳሮችም ነበሩ፡፡ ከ፫፻ የመከራና የስደት ዓመታት በኋላ ቤተ-ክርስቲያን ጥቂት እረፍት ያገኘችዉ በታላቁ በቆስጠንጢኖስ ዘመነ መንግስት ነዉ፡፡ በዚያ ክፉ ዲዮቅልጢያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ካረፉት ቅዱሳን መካከል እነዚህን ለምሳሌ ይመልከቱ፡፡
ቅድስት ካቴሪኒ ዘእስክንድርያ[የቤተክርስቲያን ታሪክ በሉሌ መልአኩገጽ 75]፡-ቅድስት ካቴሪኒ የዲዮቅልጢያኖስ የአንድ ክፍል እረዳት ገዢ በነበረው በማክሴንዴዮስ (በመክሰሚያኖስ) ዘመነ መንግስት ለጣዖት ይቀርብ የነበረውን አምልኮ በመቃወሟና የክርስትና እምነቷን አልክድም በማለት ስለጸናች አንገቷን በሰይፍ በመቁረጥ በሰማዕትነት ዐርፋለች፡፡ አስከሬኗ በመላእክት ተወስዶ በሲና ተራራ ተቀበረ፡፡
ግብጻዊው ቅዱስ ሚናስ[ዝኒ ከማሁ ገጽ 75]፡- የመርዌ ገዥ የነበረው ቅዱስ ሚናስ በዲዮቅልጢያኖስ በታወጀው የስደት ወቅት ለጣዖት አልሰግድም የክርስትና እምነቴን አልክድም በማለቱ በመሰየፍ በ303 ዓም በሰማዕትነት አረፈ፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያንም ከታላላቆቹ ሰማዕታት እንደ አንዱ በመቁጠር በስሙ ቤተ ክርስቲያን አሳንጻለታለች፡፡
የልዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ[ዝኒ ከማሁ ገጽ76]፡-በክርስቲያኑ ዓለም ታዋቂና ተወዳጅ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዲዮቅልጢያኖስ በክርስቲያኖች ላይ ያወጀውን ሕገወጥ ትዕዛዝ ባለመቀበሉና በክርስትና እምነቱ በመጽናቱ በሰባት ፅኑ ገድል የተጋደለ ከግብጽ ውጭ ፍልስጥኤም በምትገኘው ልዳ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
4.6 ቤተ ክርስቲያን በቁስጠንጢኖስ ዘመነ መንግስት
ክርስትና ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በሦስቱ ዘመናት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ ስደቶች ቢደርሱባትም ሕዝቦችን በማጽናናትና በማስተማር ተግታ ሠርታለች፡፡ ይህንን የተቀደሰ እርምጃ በምታደርግበት ጊዜ የብዙ ክርስቲያኖች ንጹሕ ደም በግፍ ፈሰሰ፡፡ የክርስቲያኖችን ጸሎት በመስማትና በግፍ የፈሰሰውን ደማቸውን በመመልከት እግዚአብሔር በትልቁ ቁስጠንጢኖስ አድሮ በ312 ዓም ለክርስቲያኖች ሙሉ ነጻነት ሰጣቸው[የቤተክርስቲያን ታሪክ በሉሌ መልአኩ ገጽ 43-44]፡፡ ቁስጠንጢኖስ ሰርቪያ ኒሳ (ዩጎዝላቪያ) በምትባል ቦታ ከቁንስጣና ከእናቱ ከእሌኒ በ272 ዓም ተወለደ፡፡ ከአባቱ ሞት በኋላ ሕዝቡና የጦር ሰራዊቱ ንጉሰ ነገስት አድርጎ ሾመው፡፡ እርሱም በጦር ሰራዊቱና በውጭ የነበሩትን ክርስቲያኖች በመልካም ዐይን ይመለከታቸው ነበር፡፡
አንድ ጊዜ ቁስጠንጢኖስ ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ሊዋጋ ሲል እንዴት አድርጎ ጠላቱን እንደሚያሸንፍ በማሰላሰል በሐሳብ ባሕር ሲዋኝ በ312 ዓም በለሊት በራዕይ “በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ታሸንፋለህ” የሚል ጽሑፍ ያለበት የሚያበራ መስቀል ከሰማይ አየ፡፡ እሱም ይህ በራዕይ ያየው መስቀል እግዚአብሔር በቸርነቱ የሰጠው መሆኑን ተገንዝቦ በማመን በሰንደቅ አላማው ላይ የወርቅ መስቀል አስቀርጾ ከሰራዊቱ ፊት አስይዞ ዘመተ፡፡ ወዲያው ሙሉቢያ በተባለው በቴቢር ወንዝ ድልድይ ላይ ጠላቱን ድል ነስቶ በጠቅላላው የሮም መንግስት ግዛቶች ሁሉ ገዢ ሆነ፡፡
ክርስትናን ስለወደደ በ313 ዓም ሚላን በተባለች ከተማ ውስጥ ለክርስትና ሃይማኖት የነጻነት አዋጅ አወጀ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን አሳነጸ፡፡ በነዲዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግስት የተወረሰው የክርስቲያኖች ንብረትና ሀብት የአብያተ ክርስቲያናትንም ንዋያተ ቅዱሳት ሁሉ እንዲመለሱ አዘዘ፡፡ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በክርስቲያኖች ላይ ይፈጸም የነበረው ስደት ቆመ፡፡ ክርስትና የመንግስት ስለሆነች በሚገዛቸው ሀገሮች ሁሉ እሑድ የዕረፍት ቀን እንድትሆን ወሰነ፡፡ ይህም የዕረፍት ቀን ስለተገኘ ማንኛውም ሰው ባሮችም ጭምር ሳይቀሩ የነፍሳቸውን ድኅነት ለማግኘት ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት መልካም እድል አጋጠማቸው፡፡ ቀደም ሲል የሮማ ዜጋ ያልሆነ ወንጀለኛ በስቅላት መቅጫ የነበረው መስቀል ጌታ ተሰቅሎ በደሙ ዓለምን ስላዳነበትና ቁስጠንጢኖስም ጠላቱን ድል ስለነሳበት በክርስቲያኖች ዘንድ የተከበረና የሰራዊቱ ምልክት ሆነ፡፡
ከእናቱ ሞት በኋላ በጸና ስለታመመ በኒቆምዲያ ኤጲስ ቆጶስ በአውሳቢዮስ እጅ ሊቆምዲያ በምትባል ቦታ ተጠምቆ በ337 ዓም በተወለደ በ65 ዓመቱ አረፈ፡፡