Advertisement Image

የቤተክርስቲያን ታሪክ

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች

ምዕራፍ ሁለት : የቤተክርስቲያን ስያሜ ምሳሌዎችና ባሕሪያት

2.1. የቤተክርስቲያን ስያሜ
‘ቤተ ክርስቲያን’ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ክርስቶስ የህያው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በመመስከሩ ጌታ ሲያከብረውና ቤተክርስቲያንን በሐዋርያው ምስክርነት ላይ እንደሚያንፅ ሲገልጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ቃሉን ተጠቀመው፡፡[ማቴ. 16፡18]ከዛ በፊት ‘ቤተ ክርስቲያን’ የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ አናገኘውም፡፡ ጌታ ከተናገረው በኋላ ግን በብዛት በታላቁ መጽሐፍ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ሦስት ጊዜ፣ በሐዋርያት ሥራ ሀያ ሦስት ጊዜ፣ በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት 62 ጊዜ፣ በሌሎች መልእክታት 6 ጊዜ፣ በዮሐንስ ራእይ 20 ጊዜ፣ በድምሩ በመጽሐፍ ቅዱስ 114 ጊዜ ተጠቅሷል፡፡[የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ፤ አባ ጎርጎሪዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ ፤1978ዓ.ም. ፤ አዲስ አበባ ፤ ገጽ 13] ‘ቤተ ክርስቲያን’ ‘ቤተ’ እና ‘ክርስቲያን’ ከሚሉት ቃላት የተመሠረተ ጥምር ቃል ሲሆን ቤት (ይበይት፣ ይቢት፣ በያቲ፣ በያቲት….) የሚለውን መጽሐፍ ቅዱስ አደረገ፣ መኖር፣ መተዳደር፣ ትውልድ፣ ዘር፣ ወገን፣ የሚሉትን ትርጉሞች እንዲሰጥ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡[የቤተክርስቲያን ታሪክ ቁጥር ፩ ፤ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ እና መ/ር ቸሬ አበበ ፤በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤ/ማ/መ ማኅበረ ቅዱሳን ፤ ሰኔ ፳፻ ዓ.ም.፤ገጽ 1]

-ቤቱ ክልኤሆሙ በይእቲ ሌሊት፡፡(በዚያች ሌሊት ሁለቱም አብረው አደሩ፡፡)ጦቢት 8፡9፡፡

-በፀጋው ተፈጥረ ኩሉ ወበኂሩቱ ይበይት፡፡ (ሁሉ በፀጋው ተፈጠረ በቸርነቱም ይተዳደራል፡፡) ኢዮ. 39.2-7፡፡

-ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ፡፡ (የአባትሽን ቤትና ወገንሽን እርሽ፡፡) መዝ 44.10፡፡

‘ክርስቲያን’ የሚለው ቃል ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠሩበት የክርስቶስ ደቀመዛሙርት በአንፆኪያ (Antioch) ከተማ ነው፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ፤ ክርስቶሳውያን እንደማለት፡፡

ዘይቤያዊ ፍች፡-ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል (በዘይቤያዊ አፈታቱ) ሦስት ፍች አለው፡፡ አንደኛው በክርስቶስ አምነው የተጠመቁ የምእመናን አንድነት ወይም ማኅበረ ምእመናን ነው፡፡[ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 1 ፤ ማቴ.18 ፡ 17 ፤ ሐዋ. 20 ፡ 28] በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሕዝበ እግዚአብሔር ቤተ እሥራኤል ተብለው ይጠሩ እንደነበሩ በሐዲስ ኪዳን ያሉ ሕዝበ እግዚአብሔርም ቤተክርስቲያን ተብለዋል፡፡[የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት አምልኮትና የውጭ ግንኙነት ፤ ትንሳኤ ማተሚያ ድርጅት ፤ ገጽ 59]ሁለተኛው ፍች አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈፀምበት፣ ሥጋ ወደሙ የምንቀበልበት፣ ምእመናን የሚሰበሰቡበት፣ ታቦተ ሕጉ ያለበት ሕንፃ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ሦስተኛው የእያንዳንዱ ሰውን ቤተ መቅደስነትን በማንሳት እያንዳንዱ ሰው ቤተክርስቲያን መባሉ ነው፡፡ (1ቆሮ 3.16፣ ኤፌ. 2.20-22)በአጠቃላይ ቤተክርስቲያን ማለት ምስካየ ኅዙናን (የነዳያን መጠጊያ)፣ ማኅደረ እግዚአብሔር፣ የትምህርት፣የጸሎትና የአምልኮት ቤት (ማቴ. 12፡ 13፣ ዮሐ. 2፡ 7፣ መዝ.68፡9)፣ የኃጢአት ማስተሠሪያ፤ መስገጃና መማፀኛ፣ ወንጌል የሚሰበክባት፣ በጥምቀት ልጅነት የሚሰጥበት፣ ቅዱስ ቁርባን የሚቀርብባት፣ የክርስቲያኖች ዐፅም የሚያርፍባት፣ በሰዎች መካከል ካለ ልዩነት አገልግሎት የሚሰጥባት፣ የሚፈጸምባት ልዩ የክርስቲያኖች ቤት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት ራሷ ክርስቶስ የሆነአንዲት ዓለም አቀፋዊትና መንፈሳዊት አካል፣ የዘለዓለማዊቷ የእግዚአብሔር መንግሥት ምሳሌ የሆነች መንፈሳዊት አንድነት ናት፡፡[የቤተክርስቲያን ታሪክ ቁጥር ፩ ፤ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ እና መ/ር ቸሬ አበበ ፤በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤ/ማ/መ ማኅበረ ቅዱሳን ፤ ሰኔ ፳፻ ዓ.ም.፤ገጽ 2] ቤተክርስቲያን የምድራውያንና የሰማያውያን፣ በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉ ፍጥረታት አንድነት ናት፡፡ አንድነታቸውም በስብሃተ እግዚአብሔር ይገለፃል፡፡ (ሉቃ. 2.14፣ ማቴ. 17.1-8) ቤተክርስቲያን በሰማይም በምድርም ያለች ናት፡፡ (ራዕ 5.9-12፣ ሄኖ. 12.33-36) ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ተዋጅታ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋ ለዚህ ዘመን የደረሰች ወደፊትም የምትኖር መሠረቷ አለት የሆነ (ማቴ. 16.18) የማትናወፅ ዘለዓለማዊት ቤት ናት፡፡

2.2.የቤተክርስቲያን ምሳሌዎች
ቤተክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ ምሳሌዎች ነበሯት፡፡ በክርስቶስ ተመሥርታ አማናዊት ሆና እስክትገለጥ ድረስ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንዲሁም ክርስቶስ ለሰው ሲል በተቀበለው ሞቱ እስክትመሠረት ድረስ በሐዲስ ኪዳን ዘመን በተለያዩ ጥላዎች (ምሳሌዎች) ተመስላ ተገልጻለች፡፡ ከዚህ ቀጥሎ እነዚህን ምሳሌዎች እንመለከታለን፡፡

2.2.1. በብሉይ ኪዳን
በብሉይ ኪዳን ማለትም በዘመነ ኦሪት ሥርዓተ አምልኮ ይፈጸምባቸው ከነበሩ የቤተክርስቲያን ምሳሌዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ. ሐመረ ኖህ (የኖኅ መርከብ)፡- የሰው ልጆች በምድር ላይ እየበዙ በሔዱ ጊዜ እግዚአብሔርን በድለው ነበር፡፡ በዚሁ ጊዜ በሕገ እግዚአብሔር የሚመራ ጻድቅ ኖኅ ብቻ ነበር፡ ሰዎች በበደላቸው ምክንያት በማየ አይኅ በንፍር ውኃ ሲመሰሉ ስምንት ቤተሰቡና ወደመርከቡ ያስገባቸው እንስሳት አራዊትና አዕዋፍ (በእየወገናቸው) ከጥፋት ድነዋል፡፡

የኖኅ መርከብ በውስጧ የነበሩትን ነፍሳት ሁሉ ከጥፋት ውኃ እንዳዳነች ቤተክርስቲያንም በክርስቶስ አምነው ወደ እርሷ የገቡትን ከሞተ ነፍስ ከኃጢአት ታድናቸዋለች፡፡ (ዘፍ. 7÷1-24፣ ዮሐ. 6÷37፣ ማቴ. 11÷28) ይህች አማናዊት በክርስቶስ የተመሠረተች ቤተክርስቲያን ምሳሌዋ ከምትሆን ከኖኅ መርከብ ትበልጣለች፡፡ ምክንያቱም የኖኅ መርከብ ያዳነችው ከሞተ ሥጋ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን የምታድነው ከሞተ ነፍስም ነውና፡፡ በኖኅ መርከብ ውስጥ የነበሩት አውሬዎች ሲወጡ ባሕርያቸው አልተለወጠም ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገቡ ግን ቀማኛው መጽዋች ዘማዊው ድንግል ይሆናሉ፡፡

በመርከብ ውስጥ የነበሩት ሲድኑ ከውጭ የነበሩት ግን በጥፋት ውኃ ተደምስሰዋል፡፡ በክርስቶስ አምነው ወደ ቤተክርስቲያን የገቡ ከዘላለማዊው መቅሰፍት ይድናሉ፡፡ በክርስቶስ አምነው ወደ ቤተክርስቲያን ያልገቡት ግን የመዳን ተስፋ የላቸውም፡፡

በኖኅ የተሠራች መርከብ ሦስት ክፍል ነበራት በክርስቶስ የተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያንም ሦስት ክፍሎች (መቅደስ፣ ቅድስት፣ ቅኔ ማኅሌት) አሏት፡፡ (ዘፍ. 6÷13-22፡፡)

ለ. ክህነተ መልከ ጼዴቅ፡- መልከ ጼዴቅ የሳሌም ንጉሥ የእግዚአብሔር ካህን በመባል የሚታወቅ ታላቅ አባት ነው፡፡ ይህ ሰው አብራምን (አብርሃምን) ባገኘ ጊዜ ኅብስትና ወይን አቅርቦ አብራምን ባርኮታል፡፡ አብራምም ለዚሁ ታላቅ ካህን ካለው ሁሉ አሥራት አበርክቶለታል፡፡ (ዘፍ. 14÷18-20፡፡)

ካህኑ መልከ ጼዴቅ የሰያሜ ካህናት የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ያቀረበው ኅብስትና ወይንም ዛሬ ካህናት በቤተክርስቲያን ለሚያቀርቡት መሥዋዕተ ሐዲስ /የክርስቶ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም/ ምሳሌ ነበር፡፡ መዝ. 109÷1-4፡፡ አበ ብዙኃን አብርሃም የምእመናን (የክርስቲያኖች) ምሳሌ ነው፡፡

ሐ. ቤተል /ቤትኤል/፡- ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ምሥጢረ እግዚአብሔርን ያየባትና በዚህ ቦታ ላይ መላእክተ እግዚአብሔር ሲወጡባት ሲወርዱባት ያያት የብርሃን መሰላል የእመቤታችንና የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ዛሬም መላእክተ እግዚአብሔር የምእመናን ጸሎትና ትሩፋት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ይወጣሉ ይወርዳሉና፡፡ ዛሬም ምእመናንን በረድኤት ከመጠበቅ ከመውጣት አላቋረጡም፡፡

መ. ደብረ ሲና/ የሲና ተራራ/፡- የሲና ተራራ ከግብፅ ሀገር በስተምሥራቅና ከእስራኤል በስተደቡብ በሚገኘው የሲና በረሃ ውስጥ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ደግሞም ኮሬብ ይባላል፡፡ ዘጸ. 3÷1፣ ዘዳ. 4÷9-10፡፡

በዚህ ተራራ ሙሴ ለአገልግሎት ተጠርቶበታል፡፡ የነበልባልና የሐመልማልን (ቅጠል) ምሥጢራዊ ውሕደት (ተዋሕዶ) ተመልክቶበታል፡፡ የእግዚብሔርን ድምጽ ሰምቶበታል፡፡ እስራኤል በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ይተዳደሩበት ዘንድ በአምላክ ጣት የተጻፉ 10ቱ ሕግጋት በሁለት የድንጋይ ጽላት ሠሌዳ ላይ በኋላም ከግራር እንጨት የተሠራ ሠሌዳ የተጻፉትን ተቀብሎበታል፡፡ ዘዳ 9÷9-12፣ ዘጸ.19÷1 ፣20÷3-21፡፡ በዚህ በምድረ በዳ ተረራ /የሲና ተራራ/ ሙሴ የእግሩን ጫማ እንዲያወልቅ ታዝዞ ነበርና፡፡ ዘጻ.3÷1፡፡ ዛሬም የሲና ተራራ ምሳሌ በሆነችው ቤተክርስቲያን ውስጥ ጫማ በማውለቅ ሥርዓት መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ የሐዋ. 7÷33፡፡

ሙሴ በዚህ ተራራ ምሥጢራዊ ውሕደት ተመልክቶባታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም የመለኮትና የትስብእት /ሰው የመሆን/ ምሥጢረ ተዋሕዶን /ምሥጠረ ሥጋዌን/ ታስተምራለች፡፡ ሙሴ በዚህ ተራራ ለባለሟልነት ተጠርቶበታል፡፡ እኛም ልጅነትን ድኅነትን ለማግኘት ተጠርተናል፡፡ በዚህ ተራራ እግዚአብሔር ክብሩን ገልጦበታል፡፡ ዛሬም በቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ክብር ተገልጧል፡፡ ይገለጣልም፡፡ በዚህ ተራራ ሕግ ተሠርቷል፡፡ ቤተክርስቲያንም የሕግ መገኛ ናት፡፡ በሲና ተራራ ሙሴ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሞባታል፡፡ ጸልዮባታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይጾምባታል፣ ይጸለይበታል፡፡

የሲና ተራራ ሦስት ክፍል ነበራት ሙሴ የወጣባት ጫፍ ክፍል፣ አሮን የወጣበት ግማሹ ክፍልና ካህናቱና ሕዝቡ የቆሙበት የግርጌው ክፍል ሦስት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያንም ሦስት ክፍል ማለትም የጌታ ሥጋና ደም የሚፈተትበት ካህናት ብቻ የሚገቡበት ቅድስተ ቅዱሳን /መቅደስ/፣ በንስሐ ራሳቸውን አዘጋጅተው ሥጋወደሙን የሚቀበሉት ሁሉ የሚቆሙበት ቅድስትና ሌሎች ምእመናን ሁሉ የሚገቡበት ቅኔ ማኅሌት አላት፡፡

ተራራ ለመውጣት ብዙ ድካም አለበት በኋላ ግን ፍጹም ሰላም ንፁህ አየር ያለባት የራቀውን አቅርቦ /ሩቅ ድረስ/ የሚያሳይ ሁሉን አስተካክለው አጥርተው ሲያዩም ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ ወደ ቤተክርስቲንም ለመግባት ብዙ ፈተና አለ፡፡ ከፍትወታት እኩያት፣ ከኃጣውእ፣ ከአጋንንት ጋር ውጊያ አለ፡፡ ነገር ግን ሁሉን ድል አድርገው ሲገቡ ፍጹም ደስታ ዘላቂ ሰላም ይገኛል፡፡ የረቀቀው ምሥጢር ጎልቶ ይታወቃል፡፡ የራቀው በእምነት መነጽር ቀርቦ ይታያል፡፡ በአጠቃላይ ቤተክርስቲያን ጽድቅና ኃጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለች፡፡

ሠ. ደብተራ ኦሪት፡- ደብተራ ማለት ድንኳን ማለት ነው፡፡ ደብተራ ኦሪትም ታቦተ ሕጉ የኖረባት ሌዋውያን ሕግን የተማሩባትና ሥርዓትን የፈጸሙባት ድንኳን ናት፡፡ በዚህ ድንኳን ሰውና እግዚአብሔር ይገናኙባት ስለ ነበር መገናኛ ተብላለች፡፡ /ዘጸ. 33÷7-8)፡፡ እስራኤላውያን ከግብፅ ሀገር ቢወጡ በ2ኛው ዓመት የእግዚአብሔር ማደሪያ ደብተራ ኦሪት በደብረ ሲና ሥር ተሠርቶ ነበር፡፡ ከዚያም ለ35 ዓመታት በቃዴስ ተቀመጠ፡፡ በመቀጠልም በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ሲኖር በመጨረሻም ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፡፡ /2ሳሙ.6÷1)፡፡ ይህም ድንኳን የሚተከልና የሚነቀል ወይም የሚነሣ ነበር፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሰገድበትና እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥበት ነው፡፡ ስሙም የመገናኛ ድንኳን በ/ዘጸ. 27÷9፣ 29÷42/ የእግዚአብሔር ድንኳን /ራእ.21÷3፣ ዕብ. 8÷2-5/ ይባላል፡፡ ማደሪያው የተሠራው እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር እንዲገናኝበት ሕዝቡም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር መሆኑን እንዳይረሱ ነው፡፡ /ዘጸ. 25÷8-22፣ 20÷9-42/፡፡ በመገናኛው ድንኳን ከውስጠኛው ክፍል በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ አሠርቱ ቃላት (ትዕዛዛት) የተጻፉባቸው ሁለት ጽላቶች፣ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የአሮንም በትር ይዟል፡፡/ዘኁ.17÷1-11፣ ዘጸ 16-32/፡፡ ዛሬም አማናዊቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቃል ኪዳኑ ጽላትና የመገልገያ ንዋያተ ቅድሳት ይገኛሉ፡፡ ይኸውም መና የሥጋው:የወርቅ መሶብ (የእመቤታችን):የአሮን በትር የእመቤታችን፣ የቤተ መቅደሱ ንዋያተ ቅዱሳት የቤተክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ምሳሌ ናቸው፡፡

ረ. የሰለሞን ቤተመቅደስ፡- ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር በፈቀደለት በዳዊት ልጅ በሰሎሞን እጅግ ባማረና በተዋበ አሠራር ከተሠራ በኋላ ሰሎሞንና ካህናተ ኦሪት ለብዙ ዘመናት በድንኳን ትኖር የነበረችውን ታቦተ ሕግ ከጽዮን ከተማ አምጥተው ወደ ቤተ መቅደስ አስገቧት፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠቱን ቀጠለ፡፡ 1ነገ.6÷37፣ 8÷1-10፣ 2ዜና መዋ.3÷5፡፡ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ቤቱን እግዚአብሔር በደመና ተመስሎ ይሞላው እንደነበረ ሁሉ ዛሬም የእግዚአብሔር ረድኤት ከቤተ ክርስቲያን አልተለየም፡፡ 1ነገ.10÷58፡፡ ቤተመቅደሱ ውስጥ ካህናት አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ዛሬም አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ ቤተመቅደሱ መሥዋዕት ይሠዋበት እንደነበር ዛሬም በቤተክርስቲን መሥዋዕት ይሠዋል፡፡ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ምሳሌ እንደመሆኑ መጠን ከቤተክርስቲያን ያንሳል፡፡ ምክንያቱም ቤተመቅደስ የተመሠረተው /የተጀመረው/ በሰሎሞን ነው፡፡ ቤተክርስቲን ግን መሥራቿና ሠሪዋ ራሱ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቤተ መቅደሱ ምሳሌያዊ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ግን አማናዊት ናት በቤተክርስቲያን የሚቀርበው መሥዋዕት የወልድ እግዚአብሔር የክርስቶስ አማናዊ (እውነተኛ) ሥጋና ደም ነው፡፡ በቤተመቅደስ የሚሰጠው ግን ከሥጋዊ መቅሰፍት ብቻ የሚያድን ነበር በቤተክርስቲያን የሚፈጸመው አገልግሎት ግን ከሥጋና ከነፍስ ደዌ የሚያድን ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በምድር ያለች የታላቁ ንጉሥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከተማ ናትና ከሰሎሞን ቤተመቅደስ ትበልጣለች፡፡ ማቴ. 5÷35፡፡

2.2.2. በሐዲስ ኪዳን
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ በኢየሩሳሌም ምድር /በእስራኤል/ በእግሩ ተመላልሶ ወደ መንግሥተ ሰማያት መርታ የምታስገባ ሕገ ወንጌልን በአምላካዊ ቃሉ አስተምሯል፡፡ ጌታችን ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ ስለ ቤተክርስቲያን በምሳሌነት የሚጠቀሱት ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.የዓሣ ማጥመጃ መረብ /ማቴ.13÷47/
2.ታላቅ የስንዴ አዝመራ /ማቴ. 13÷24/
3.የሰናፍጭ ቅንጣት /ማቴ. 13÷31፣ ሉቃ. 13÷18/
4.የከበረ ዕንቁ /ማቴ. 13÷45/
5.የሠርግ ቤት /ማቴ. 22÷1-8-፣ ዮሐ 2÷1/ሙሽራ /ኤፌ. 5÷21-33፣ ራእ. 21÷9-14/ ወዘተ ናቸው፡፡

2.3. የቤተክርስቲያን ባሕሪያት
በትምህርተ ሃይማኖት ውስጥ ወሳኝ የሆኑ ልዩ ልዩ ቃላትን እናገኛለን፡፡ ከነዚህ ቃላት መካከል ‘ባሕርይ’ የሚለው ቃል አንዱና ዋናው ነው፡፡…ባሕርይ ማለት የአካል መገኛ ሥር፣ አካል ሥራን የሚሠራበት መሣሪያ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አካል ያለ ባሕርይ ብቻውን አይቆምም፡፡ ባሕርይም ያለ አካል አይቆምም፡፡ አካልና ባሕርይ እንደ ሥጋና እንደ ዐጽቅ እንደ ቅንጣትና እንዳገዳ የተያያዙ የማይለያዩ ናቸው፡፡[ነገረ ሃይማኖት (ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ) ፤ ሳሙኤል ፍቃዱ ፤ ገጽ 126-127] ባሕርይ እንደ ፀባይ ያይደለ፣ የማይለወጥ፣ የማይሻሻል፣ የማይሻር፣ የአካል መገለጫ ነው፡፡ በመሆኑም ባሕርያተ ቤተክርስቲያን ስንል የማይለወጠው፣ የማይሻረው፣ የማይሻሻለው፣ እንዲሁ የምንቀበለው፣ እንዳለ የምናወርሰው፣ ከእግዚአብሔር የተሰጣት የቤተክርስቲያን መገለጫ ማለት ነው፡፡

የቤተክርስቲያን ባሕርያት በዋናነት አራት ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያን አንዲት፣ ቅድስት፤ ኩላዊት፣ ሐዋርያዊት ናት፡፡ (ይሁዳ 1÷3) ‘ወነአምነ በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት’ እንዲል ጸሎተ ሃይማኖት፡፡

1.አንዲት ናት፡- ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉ አባት አለ፡፡ አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት አንድ አካልና አንድ መንፈስ (ኤፌ 4÷4-6) ፡፡ ሐዋርያው በግልፅ እንዳስቀመጠው ያለው አንድ አምላክ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ ጌታ የለም፡፡ ይህ አምላክ የሚመለክበት ያለው አንድ ሃይማኖት ብቻ ነው፡፡ ከዛ ሌላ ሃይማኖት የለም፡፡ የአምላክ የፀጋ ልጅነት የሚገኝበት ያለችው አንዲት የማትደገም ጥምቀት ብቻ ነች፡፡ ሥርዓተ አምልኮው የሚፈፀምባት ቤተክርስቲያንም አንዲት ናት፡፡ በገጠርም ሆነች በከተማ፣ በግንብም ተሠራች በሣር፣ ሰፊም ሆነች ጠባብ፣ ብዙ ሕዝብም ኖራት ጥቂት የሚመለክባት አንድ አምላክ ነውና አንዲት ነች፡፡ ለቅድስናቸው መታሰቢያ ሰማያዊ በመላዕክትም ሆነ በሐዋርያት፣ በፃድቃንም ሆነ በሰማዕታት፣ በድንግል ማርያምም ሆነ በሌሎች ቅዱሳን፣ በሥላሴም ሆነ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚመለክባት እግዚአብሔር አምላክ አንድ ጌታ ነውና አንዲት ናት፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉ እንደጻፈውና አንድ ጌታ የሚሆን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው አንድ እውነተኛ የወይን ግንድ ነው ያለው፡፡ እርሱም ክርስቶስ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ (ዮሐ 15÷1-7) በአንዲት ቤተክርስቲያንም አንዱ አምላክ እየተመሰገነ ቅዱሳን ለኃጥአን እያማለዱ በአንዱ የወይን ግንድ አምላክነት ሕይወትን ያገኛሉ፡፡ አባ ህርያቆስም በቅዳሴ ማርያም አብ ጉንደወይን ነው፣ ወልድ ጉንደ ወይን ነው፣ መንፈስ ቅዱስም ጉንደ ወይን ነው ብሏል፡፡ ከዚህ ከአንዱ የወይን ግንድ ሌላ ስለሌላት ቤተክርስቲን አንዲት ናት፡፡

አንድነት በቤተክርስቲያን በስንት ወገን ነው?

የክርስቲያኖች አንድነት በሦስት ወገን ነው፡፡ የመጀመሪያው እኛ እርስ በራሳችን ያለን አንድነት ነው፡፡ መቶ ሀያው የጌታ ቤተሰብ ጌታ ከዐረገ በኋላ በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ (ሐዋ 1÷14) እኛ ክርስቲያኖችም በቅዳሴ፣ በሠርክ ጉባኤ፣ በመዝሙር፣ በማኅበር ጸሎት፣ በጾም፣ በስግደት….ወዘተ ወደ አምላክ በአንድ ልብ ሆነን ሳንለያይ ያለንን ለአምላክ እንሰዋለን፡፡ ቋንቋችን አንድ ነው-ፍቅር፡፡ ብሔራችን አንድ ነው -ክርስትና፡፡ ሀገራችን አንድ ነው - መንግሥተ ሰማያት፡፡ ፍቅር ከሌለ ክርስትና የለም፡፡ ክርስትና ከሌለ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ የለም፡፡ ሀሳብ ከተለያየ ፣ ቋንቋ ከተደበላለቀ፣ ፍቅር ከጠፋ፣ ግለኝነት ከበዛ፣ ክርክር ካለ፣ ፀብ ካለ አንድነት የለም፡፡ እንደ ሰብአ ባቢሎን መበጥበጥ ብቻ እንጂ፡፡ አንድነት ከሌለ ቤተክርስቲያን የለም፡፡ ሰብአ ባቢሎን አንድነት በነበራቸው ጊዜ ግንቡን ጥሩ መገንባት ችለው ነበር፡፡ ቋንቋቸው ሲለያይ አንድነታቸው ሲበተን ግን መግባባት አልቻሉ፡፡ (ዘፍ 11÷1-9) ቤተክርስቲያን አንድ አምላክ በአንድ ልብ የሚመለክባት ናትና ያንን ማጠናር ያስፈልጋል፡፡

ሁለተኛው ወገን አንድነት በህይወት በምድር ያለነው እኛ ከሕይወተ ሥጋ ከአረፉት ቅዱሳን፣ ከሚመጣው ትውልድ፣ ከመላእክት ጋር ያለን አንድነት ነው፡፡ ሙታን ይስእሉ በእንተ ህያዋን፣ ህያዋን ይስእሉ በእንተ ሙታን እንዲል መጽሐፍ›› (ሄኖ 12÷33-36) ቤተክርስቲያን በሰማይም በምድርም ያለች ናት፡፡ ቅዱሳን አብረውን እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩ ለመግለጥ ቅዱሳን ስዕላት በቤተ ጸሎታችን ሁሉና በቤተ መቅደስ አሉ፡፡ በደብረ ታቦር ከሞቱት ሙሴ ካረጉት ኤሊያስ በህይወተ ሥጋ ካሉት አዕማደ ሐዋርያት በአንድነት አንዱን አምላክ ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን አመስግነዋል፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን የቅዱስ ተራራ የደብረ ታቦር ምሳሌ ናት፡፡ ቅዳሴዋ ከታቦሩ ምስጋና ጋር አንድ ነው፡፡ የቅዳሴ ልዑካኑ የአምስቱ ቅዱሳን ምሳሌ ናቸው፡፡ ታቦቱ የጌታችን ምሳሌ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ዛሬም ወደፊትም ቅዱሳን በአንድነት ያመሰግናሉ፡፡ መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ (ኢሳ. 6÷3፤ ራዕ. 4÷8) እንዲያመሰግኑት እኛም ከመላእክት ጋር በቅዳሴያችን አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ እንላለን፡፡ በዚህ አንድነት ውስጥ ያለ ማንም ሰው በአንድነቱ ለማቆየት በሥርዓተ አምልኮው መሣተፍ ግዴታው ነው፡፡ ይህ ካልሆነ የቤተክርስቲያን አካል አይደለም ማለት ነው፡፡ አባ ህርያቆስ በእርሱና በሐዋርያት መካከል ከ3 መቶ ዓመት በላይ ልዩነት እያለ በቅዳሴው ከሐዋርያት ጋር ሥጋውን በላን ደሙን ጠጣን ማለቱ ሌላ ምስክር ነው፡፡

ሦስተኛው ወገን አንድነት በህይወተ ሥጋ ያለነውም፣ በህይወተ ሥጋ የሌሉ ቅዱሳንም መላእክትም ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን አንድነት ነው፡፡ በ40 እና በ80 ቀን ተጠምቆ የሥላሴን ልጅነት ያገኘ በሥጋ ወደሙ የከበረ ሁሉ ከሥላሴ ጋር በፀጋ አንድነት አለው፡፡ እግዚአብሔር በእርሱ አለ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ (ዮሐ 6÷56) እንዲል ወንጌል፡፡ ከሦስቱም ወገን አንድነቶች ይሄኛው ዋናው ነው፡፡ ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ስንል የአንድነቷ ጉልላት ሥጋወደሙ ነው፡፡ የአንድነቷ መሠረቱና ማሠሪያው ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡ በሉቃ 15÷11-32 ላይ ጌታ የተናገረው አንድ ምሳሌ አለ፡፡ በአባቱ ቤት ሁሉ ተሟልቶለት ሳለ አንድ ልጁ ድርሻዬን ስጠኝ ብሎ ተነጥሎ ከአባቱ ቤት አንድነት ወጥቶ ሄደ፡፡ በሄደበትም ገንዘቡ አልቆ በጣም ተቸገሮ አባቱን ይቅርታ ጠየቀና ወደ ቤቱ ገባ፡፡ በዚህም ተደስቶ አባቱ ፍሪዳ ቢያርድለት ሌላኛው ልጁ ቀና፡፡ እኔ ሁሌ በዚህ እያለሁ ይህ አልተደረገልኝም ብሎም አሰበ፡፡ አባታቸው ግን እንዲህ አለው፡፡ “ልጄ ሆይ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፣ ለእኔም የሆኑ ሁሉ የአንተ ነው፡፡ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበር ሕያው ስለሆነ ጠፍቶም ነበር ስለተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል” (ሉቃ 15÷31-32) አለው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስንሆን የእርሱ የሆነች የኛ የሚሆኑበት ልዩ ረቂቅ አንድነት ይኖረናል፡፡ በዚሁ የወንጌል ምዕራፍ ቁጥር 7 እና 10 ላይ በአንድ ኃጥእ ወደ እግዚአብሔር አንድነት መመለስ በሰማይ የሚኖረውን ደስታ ይገልጻል፡፡

2. ቅድስት ናት፡- እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ (1 ጴጥ 1÷15-16፣ ዘሌ 19÷2) ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእግዚአብሔር የባሕርይ ቅድስና የእግዚአብሔር አካላት ሁሉ የማያልቅ ቅድስናን በፀጋ ከእርሱ ዘወትር ያገኛሉ፡፡ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ናትና ሁሌም ቅድስት ናት፡፡ (ሐዋ. 20÷28) ቤተክርስቲያን የሥጋ ያልሆነ የነፍስ፣ የምድር ያልሆነ ሰማያዊ፣ የርኩሰት ያልሆነ የቅድስና ሥራ ብቻ የሚሠራባት ስለሆነች ቅድስት ናት፡፡ (ሉቃ 19÷45-46) ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽማ የተሰጠች ናትና ቅድስት ናት፡፡ (ይሁዳ 1÷3)

ማንም በቤተመቅደስ የርኩሰት ሥራ (ኃጢአት) ቢሠራ እራሱ ይረክሳል፣ ይቀሰፋል እንጂ የቤተክርስቲንን ቅድስና አያጎድልም፡፡ በኖኅ መርከብ ውስጥ የሚበሉም የማይበሉም (በሌዋውያን ልማድ ርኩሳን) እንስሳት ነበሩባት፤ርኩሳኑ መኖራቸው ግን መርከቢቱን አላሰጠመም፣ አላረከሰም፡፡ በቅድስት ሐገር ኢየሩሳሌም ትልቁ የባሃኡላህ የአምልኮ ሥፍራ አለ፡፡ ኢየሩሳሌም ግን ዛሬም ቅድስት ነች፡፡ ታላቁ የሀጊያ ሶፊያ ቤተክርስቲያን ሙዚየምም፣ የእስልምና መስጊድም በግዴታ ሆኗል፡፡ የቤተክርስቲያን ቅድስና ግን ዘላዓለማዊ ነው፡፡

አፍኒንና ፊንሐስ የርኩሰት ሥራን በቤተመቅደስ ይሠሩ ነበር፡፡ ታቦተ ጽዮንንም ከሥርዓት ውጭ ተዳፍረዋል፡፡ (1ሳሙ. 2-4) በዚህም እነርሱ ተቀሰፉ፣ ለአባታቸውም ተረፉ እንጂ ታቦተ ጽዮንማ በተማረከችበትም በቅድስና ርኩሳንን ድል አድርጋለች፡፡ ፀሐይ ቆሻሻ ላይ በርሃኗን ብታወጣ ፀሐይ አትቆሽሽም፡፡ ቆሻሻው ግን ይከረፋል ይሸታል፡፡ በቤተክርስቲያንም ርኩሰትን የሚሠራ ቅድስት ቤተክርስቲያንን አያረክስም፤ እርሱ ግን ይኮነናል፡፡

ሰዎች ከቤተክርስቲያን ውጭ ቅድስናን አያገኙም፡፡ የቤተክርስቲያን ሳይሆን የተቀደሰ የለም፡፡ የቅዱሳን ሁሉ ማረፊያ፣ መጠጊያ ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ቅድስት ኢየሩሳሌም ሰማያዊትን (መንግሥተ ሰማያትን) በምድር የምትመስል ታላቅ ሥፍራ ቅድስት ቤተክርስቲያን ነች፡፡ በቤተክርስቲያን ሳያልፍ፣ ምሥጢራቷን ሳይካፈል መንግሥተ ሰማያትን የሚወርስ የለም፡፡

3. ኩላዊት /የሁሉ፤ ከሁሉ የበላይ/ ናት፡- ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛላት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተክርስቲያን ሰጠው፡፡ እርሷም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት፡፡ (ኤፌ. 1÷23) ቤተክርስቲያን የአንድ ሀገር፣ የአንድ ብሔር፣ የአንድ ዘር፣ የአንድ ፆታ ወይም የአንድ አካባቢ ሳትሆን ዓለምአቀፋዊት (Universal, catholic) ናት፡፡ የመምህሩ ብቻ ፣የጳጳሱ ብቻ፣ የካህኑ ብቻ፣ የዘማሪው ብቻ ወይም የሰንበት ተማሪው ብቻ ሳትሆን የሁሉ ነች፡፡ መምህሩም፣ ጳጳሱም ፣ ካህኑም፣ ዘማሪውም ፣ የሰንበት ተማሪውም፣ ምዕመናኑም የቤተክርስቲያን ናቸው እንጂ የአንዱ ብቻ አይደለችም፡፡ በሌላ አነጋገር የምስራችም ሆነ ፈተና ለቤተክርስቲያን ቢያጋጥም የሚመለከተው ሁሉንም ነው፡፡ ሁሉም እንደፀጋው እኩል ይጠየቅበታል፡፡ የእገሌ ተብሎ የሚተው ነገር የለባትም፡፡ ቤተክርስቲያን የህፃኑም ፣የወጣቱም፣ የሽማግሌውም፤ የነጩም፣ የጥቁሩም፤ የሴቱም የወንዱም፤ የህመምተኛውም፣ የጤነኛውም፤ የህጋዊውም፣ የድንግሉም፤ የካህኑም፣ የምዕመናኑም፤ የአጭሩም፣ የረዥሙም፤ የሊቁም፣ የደቂቁም፤ የባህላዊውም፣ የዘመናዊውም የሁሉም ነች፡፡ የሁሉ እንደሆነች እንዲሁ ደግሞ ከሁሉ የበላይ ነች፡፡

4.ሐዋርያዊት ናት፡- “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፣ በእርሱም ሕንፃ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተመቅደስ እንዲሆን ያድጋል፡፡ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን አብራችሁ ትሠራላችሁ፡፡ “(ኤፌ 2÷20-22) ከጌታ እግር ሥር በመሄድ ተአምራቱን በመመልከት ትምህርቱን በመስማት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሐዋርያት ናቸው፡፡ የመጀመሪያውን የቤተክርስቲያን ጉባኤ ያደረጉት፣ ምስጢራተ ቤተክርስቲያንን መጀመሪያ የፈጸሙት፣ መጀመሪያ የቆረቡት፣ጌታን ከጥምቀቱ እስከ ዕርገቱ ያዩት፣ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት ሐዋርያት ናቸው፡፡

ቤተክርስቲያን ከሐዋሪያት የተለየ ትምህርት፣ ሥርዓት፣ ሃይማኖት የላትም፡፡ እንደ ሐዋርያት ምስጢራትን ትፈጽማለች፡፡ እንደ ሐዋርያት በቅዱስ ትውፊት ትመራለች፡፡ እንደ ሐዋርያት ቅዱስ ሲኖዶስ አላት፡፡ እንደ ሐዋርያት ክህነት ትሰጣለች፡፡ እንደ ሐዋርያት ታጠምቃለች፡፡ እንደ ሐዋርያት ታወግዛለች፡፡ እንደ ሐዋርያት ትፈውሳለች፣ ተአምራት ታደርጋለች፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ ከሐዋርያት ሥርዓትና ትምህርት የተለየ ሆኖ የቤተክርስቲያን አባል መሆን አይቻልም፡፡

በአጠቃላይ ቤተክርስቲያን አንዲት፣ ቅድስት፣ ኩላዊትና ሐዋርያዊት ናት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ዘለዓለማዊት ናት፡፡ ይህ ትምህርተ ሃይማኖት ነው፡፡ የማይለወጥ የማይሻርና የማይሻሻል ነው፡፡ አምላካችን ሁላችንንም በቅድስት ቤተክርስቲን ጥላ ውስጥ ለዘለዓለም በአንድነት አኑሮን ሐዋርያዊ መሠረትን ይዘን እንቀደስ ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፡፡