Advertisement Image

የቤተክርስቲያን ታሪክ

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች

ምዕራፍ ስድስት : ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት

6.1 የኒቅያ ጉባኤና አርዮስ (325 ዓ.ም)
የጉባኤው መንስኤ የአርዮስ ትምህርት ነበር፡፡ በአንደኛውና በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ‹‹ሥላሴን›› የተመለከተ አስተምሮ እንደ ችግር ሆኖ አልተዘከረም፡፡

ለዚህም በየአገሩ ያሉ ጳጳሳት ወደኒቂያ (የዛሬዋ ኢዚኒክ ቱርክ ውስጥ) እንዲመጡ በትህትና የተጻፈ መልእክት ላከላቸው፡፡ ለዚህም ጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በመንግስት ወጭ እንዲሟላላቸው አደረገ፡፡ በዚያም ፫፻፲ ጳጳሳት ብዙ ቁጥር ካላቸው ካህናት እና ዲያቆናት ጋር ከየቦታው ተሰበሰቡ፡፡ የእስክንድርያው እለእስክንድሮስ በዚሁ በኒቅያ ጉባኤ ላይ ጸሐፊውን ዲያቆኑን አትናቲዎስን ይዞት ነበር፡፡ በወቅቱ አትናቲዎስ በእድሜው ከ22-24 ደርሳል፡፡ የእምነት ዐቃቢ በመሆን አርዮስን ለመከላከል በቂ ዝግጅት አድርጓል፡፡

ሆኖም ይህ የተቀጠረው ቀን ከመድረሱ በፊት ጳጳሳቱ አርዮስን በመጥራት ክርክሮች ይካሄዱ ነበር፡፡በዚያ የተሰበሰቡት አባቶችም በአርዮስ አስተሳሰብ ከቤተ-ክርስትያን እምነት የወጣ ፈጠራና አስደንጋጭ መሆን ተበሳጩ፡፡ በዚያ ከነበሩት እና አርዮስን ተከራክረው ብላሽነቱን ካጋለጡትና እርቃኑን ካስቀሩት ብዙዎች በንጉሱና በጉባኤው አባላት ዘንድ ጎልተው ታዩ፡፡ ከእነዚህም መካከል በጣም ጎልቶ የወጣውና የአርዮስ ክህደት ውስጠ ምንነት ከስሩ ስለገባው የስህተቱን መሰረታዊ ፀረ ክርስቲያናዊነት ለጉባኤው በማጋለጥና በማስረዳት፤ አርዮስንም ተከራክሮ በመርታት ከፍተኛው ድርሻ የነበረው በዚያን ጊዜ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ከነበረው ከቅዱስ እለ እስክንድሮስ ጋር የሄደውና በወቅቱ ዲያቆን የነበረው ቅዱስ አትናቴዎስ ነበር፡፡

በጉባኤው አርዮስ አቋሙን እንዲያብራራ ተጠይቆ ሲናገር፡፡ ‹‹ወልድ ባልነበረበት ጊዜ አብ ነበር፡፡ ወልድን ከምንም ፈጠረና የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን አደረገው፡፡ ይህም ማለት አብ ወልድን እንደማንኛውም ፍጡር ፈጥሮታል ማለት ነው፡፡ አብም ወልድን ከፈጠረ በኋላ ስልጣን ሰጥቶት ሁሉን ነገር እንዲፈጥር አደረገው . . .›› በማለት አብራራ፡፡ በዚህ ወቅት እለእስክንድሮስ ‹አምልኮትና ስግደት የሚገባው ለፈጣሪያችን ነው ወይስ ላልፈጠረን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ አርዮስም ለ‹‹ፈጠረን›› ሲል መለሰ፡፡ እለ እስክንድሮስ ‹‹ፍጡር ነው ያልከው ወልድ የፈጠረን ከሆነ ለአብ አምልኮትና ስግደት እንዳቀረብን ለወልድስ ማቅረባችን ምን ያስጠይቃል?›› ሲለው አርዮስ ምላሽ አልነበረውም፡፡ አትናትዮስም፡‹‹ኢየሱስ የደህንነቴ ዋስትና ነው፡፡ለማዳን የበቃው አምላክ ስለሆነ ነው፡›› ማለቱ ይታወሳል፡፡

በዚህ ወቅት ለአርዮስም ለቆስጠንጢኖስም ወገናዊነት የነበረው የሲብየስ ድንጋጌን አዘጋጅቶ ለውሳኔ ቀረበ፡፡ ዝርዝሩ ግን የሚታረም ስለነበረው በተከታዩ ቀን ተስተካክሎ ለውሳኔ ፀድቆ ወጣ፡፡ውሳኔውም እንዲህ ይል ነበር ‹‹. . .ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ በተወለደ የአብ አንድያ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፤ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚስተካከል ሁሉ በእርሱ የሆነ በሰማይም ካለው በምድርም ካለው ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የለም ስለኛ ስለሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ የወረደ በመንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው የሆነ ሰው ሆኖም በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን የተሰቀለ ፡ የታመመ፡የሞተ፡የተቀበረም፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሳ፡በቅዱሳን መጻሕፍትም እንደተፃፈ በክብርም ወደ ሰማይ ያዐረገ፡በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ. . .››

የቤተ-ክርስቲያን ውሳኔ
1. "ወልድ ከአብ ጋር አንድ ባህርይ ነው“ የመለኮትን አንድነትና የአካላት ሦስትነት፤ የወልድን የባህርይ አምላክነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ አንቀፅ አፅድቀዋል
2. የአብ የሆነ ሁሉ የወልድ ገንዘብ በመሆኑ፤ ወልድ ከአብ ቅድመ ዓለም የተወለደ ፤ከአብጋር በባህርይ በመለኮት አንድ እንደሆነ እና ለዘላለም አለምን አሳልፎ እንደ ሚኖርመልስ ተሰጥቶታል፤

የቅዱስ አትናቴዎስ አስተምህሮ፡-
1.የሰው ልጅ መሆን አለበት፡-
በኃጢአት የወደቀው የተፈረደበትም ሰው በመሆኑ አዳኙ የሰው ልጆችን ወክሎ ቅጣቱን ለመቀበል ሰው መሆን አለበት
2. መሞት አለበት:-የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው ለአዳምና ሔዋን የተላለፈው የእግዚአብሔር ፍርድ ሞት ነው
3. አዳኛችን ኃጢአት የሌለበት ንፁሕ መሆን አለበት:-እርሱ እራሱ ኃጢአት ካለበት መድኃኒት የሚያስፈልገው ነው እኛን ከኃጢአት ሊፈውስ እንዴት ይችላል፡፡ ይህን ጉድለት ሊሞላ የሚችል ኃጢአት የማይስማማው ንጽሀ ባህርይ እግዚአብሔርብቻ ነው፡፡
4. ፈጣሪ መሆን አለበት:- ምህረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን በኃጢአት የረከስሰውን የሰው ልጅ ጠባይ እንደገና በመንፈስ ቅዱስ አዲስ ፍጥረት ማደረግ ነው፡፡ማዳን የሚችለው እግዚአብሔርብቻ ነው፡፡ፍጡር ፍጡርን ሊያድን አይችልም
5. ድህነታችን እውን የሚያደርጉት መስፈርቶች ሟሟላት የሚቻለው መለኮት ሥጋን ሲዋህድ ብቻ ነው፡፡
6. ስለዚህ እንደ አርዩስ አሰተምህሮ አልዳንም ማለት ነው፡፡ መዳናችንን ካመንን ያዳነንን አምላክን ማመንና ማወቅ ተገቢ ነው፡፡

ከዚህ ሽንፈትም ከብዙ ዓመት በኋላ አርዮስ በመጸዳጃ ቤት ሳለ ሆድቃው ተዘርግፎ ሰውነቱ በመሬት ላይ ተዘርሮ ሞቶ ተገኘ፡፡ ይህንንም ሞት ብዙዎች ‹‹ዳግማዊ ይሁዳ›› የሚል ስም ለአርዮስ አሰጣቸው፡፡ ይህም የተባለው ተመሳሳይ ሞት ሞቷል በማለት ነው፡፡

6.2 ጉባኤ ቁስጥንጥንያ
ከዓለም አቀፍ የቤተ-ክርስቲያን ጉባኤያት መካከል በሁለተኛ ጊዜ የተደረገው የቁስጥንጥንያ ጉባኤ ነው፡፡ ይህ ጉባኤ በ381 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በጥንታዊ አጠራሯ ታና እስያ በአሁኑ አጠራሯ ቱርክ ክፍል በምትሆን ቁስጥንጥንያ ከተማ 150 ኤጲስቆጶሳት በታላቁ ቴዎዶስዮስ የንግስና ዘመን መንግስት ተሰብስበዋል፡፡ የጉባኤው ዋና ዋና ምክንያቶች፡-

1.ጉባኤው በሎዶቅያ የተወለደውን የአቡሊናርዮስን የክህደት ትምህርትም አውግዟል፡፡ ትምህርቱም የኘላቶንን የሥጋዊ ፍልስፍና ወስዶ፤ ሰውን ለማወቅ የምትችለው ነባቢት ለባዊትና ሕያዊት ነፍስ ከመለኮት ተከፍላ የመጣች ነች፣ ቃልም ሥጋ ሲሆን የተዋሐደው ሥጋን እንጂ ነፍስን አይደለም፣ መለኮትም ለሥጋ ነፍስ ሆናት፤ ይል ነበር፡፡
2.መቅዶንዮስ «መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው = ከአብና ከወልድ መንፈስ ቅዱስ ያንሳል» ብሎ አስተምሮ ነበርና እርሱንና ትምህርቱን አውግዞ ለመለየት ነው።ይህ ሰው የቁስጥንጥንያ ኤጲስቆጶስ ነበር።

መቅዶንዮስ (Mecedonianism)
የመቅደኒያኒዝም የክህደት ትምህርት መሥራች ከ341-360 ዓ.ም የቆስጥንጥንያ ፓትርያርክ የነበረው መቅዶንዮስ ነው፡፡ ወልድ በባሕር የመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ ስለሆነ መንበር አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን በመለኮቱ ስለሚያንስ መንበር የለውም በማለት ያስተምር ነበር፡፡ ዘመኑ አርዮሳውያን የነገሡበት ስለነበረ ይህ ትምህርት ታላቁ ቴዎዶስዮስ እስከ ነገሠበት ድረስ እየተሠራጨ ኖሯል፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአርዮስ ትምህርት ጐን ለጐን ሌሎችም የምንፍቅና ትምህርት ብቅብቅ ብለው ስለነበር የመቅዶንዮስ የክህደት ትምህርትና እነዚህ ትምህርቶች መወገዝ ስላለባቸው በታላቁ ቴዎዶስዮስ ትእዛዝ በቁስጥንጥንያ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ (Ecumenical Council) በ381 ዓ.ም ተደረገ፡፡ የቁስጥንጥንያው ፓትርያርክ መላጥዮስ የጉባኤው ሊቀ መንበር ሆነ፡፡ በጉባኤው መካከል በድንገት ስለሞተ ከእርሱ ቀብር በኋላ ጎርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ተተካ፡፡ በመንገድ መዘገየት የተነሳ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ጢሞቴዎስ ጉባኤው ከተጀመረ በኋላ በመድረሱ በጎርጐርዮስ ሊቀ መንበርነት አልተስማማም ነበር፡፡ የተሰሎንቄው ሊቀ ጳጳስ አርኬላዎስም ዘግይቶ በመድረሱና ምልዓተ ጉባኤ ሳያሟላ የተደረገ ምርጫ ነው በማለት ከጢሞቴዎስ ጋር አንድ ሆኑ፡፡ ጎርጐርዮስን ከሥልጣኑ አወረዱት በምትኩም ኒክታሪያስን የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሲሾሙ የጉባኤው ሊቀ መንበር ደግሞ ጢሞቴዎስ ዘእስክንድርያ ተሾመ፡፡ መቅዶንዮስ መንፈስ ቅዱስ መንበር የለውም ሕጹጽ ነው ላለው ምላሽ ሲሰጡም “በዓመተ ሞተ ዖዝያን ንጉሥ ርኢክዎ ለእግዚአብሔር እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ልዑል ወነዊል ወሱራፌል ይጸርሑ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ምሉዕ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ፡፡” በማለት ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው አንዱ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ “ዲበ መንበር ነዋኃ” ብሏልና መንፈስ ቅዱስ መንፈስ እንዳለ ያሳያል በማለት የመቅዶንዮስንና የተከታዮቹን ትምህርት ውድቅ በማድረግ አውግዘዋል መቅዶንዮስ የተወገዘ ከሞተ በኋላ ነው፡፡የሞተው በ360 ነውና (ኢሳ. 6÷1-4)፡፡

በዚህ ጉባኤ የተሰበሰቡ ጳጳሳት ቁጥር 150 እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፡፡ በዚህ ጉባኤ ሌላው የተወገዘው የሎዶቅያ ኤጲስ የነበረው አቡሊናርዮስ ነው አቡሊናርዮስ በ360 ዓ.ም እ.ኤ.አ ገደማ ወልድ ሥጋን ነሳ እንጂ ነፍስን አልተዋሐደም፡፡ መለኮቱ እንደነፍስ ሆነው፡፡ ወንጌልም “ቃል ሥጋ ሆነ” ነው የሚለው በማለት የክህደት ትምህርቱን አሰራጨ፡፡ ነገር ግን ወንጌል ቃል ሥጋ ሆነ ማለቱ አካላዊ ቃል በተለየ አካሉሥጋና ነፍስን ነስቶ ፍጹም ሰው ሆነ ለማለት ነበር፡፡ሰውን (ሥጋና ነፍስ) ሥጋ ብሎ መጥራት ልማደ መጽሐፍ ነው፡፡ለምሳሌ “እፌኑ መንፈስየ ዲበ ኩሉ ዘሥጋ” በሥጋ ሁሉ ላይ መንፈሴን እልካለሁ ይላል፡፡ በሰው ሁሉ ላይ በማለት እንደ ሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡ (ኢዮ. 2÷28) ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ሰው ለማለት ብዙ ጊዜ የሚጠቀመው ሥጋ እንደሆነ ከመጻሕፍቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡ (ዮሐ. 17÷1-2፣ 1ዮሐ. 4÷2)፡፡ በዚህ ጉባኤ መቅዶንዮስ፣ አቡሊናርዮስ፣ ተረፈአርዮስ፣ በአጠቃላይ አርዮሳውያን፣ የመቅዶንዮስ ተከታዮች ተወግዘዋል፡፡ ወደ 36 የሚጠጉ መናፍቃውያን ጳጳሳትም እንደተወገዙ የቤተክርስቲያን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ከተወገዙ በኋላ “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ የሚለው እስከ ወንሴፎ” ትንሣኤሙታን እስከሚለው ድረስ ያለውን አንቀጸ ሃይማኖት አርቅቀው በኒቂያ ጉባኤ በረቀቀው ላይ ጨምረው የተሟላ አንቀጸ ሃይማኖት አድርገዋል፡፡ በዚህም የተነሣ አንቀጸ ሃይማኖታችን የኒቂያና ቁስጥንጥንያ ትብብር ጉባኤ አንቀጸ ሃይማኖት (The Neceo -Constantinople Creed) በመባል ይጠራል፡፡ ጥንታዊቷና ታሪካዊዋ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሃይማኖታቸው በቀና ሊቃውንቶቿ አውግዛ የለየቻቸውን መናፍቃን ትምህርት ትክክል ነው ብለው ዛሬ የቤተክርስቲያንን ተልእኮ በማወክ ላይ የሚገኙ ብዙ አሳቾች ተነስተዋል፡፡ እነዚህ አሳቾች እውነተኛውን የክርስቲያን ዶግማ ስለማይቀበሉ የአምልኮት ፀባይ ያላቸው እምነት መሳይ (Cult) ይባላሉ እንጂ ክርስቲያኖች አይደሉም፡፡

6.3 የኤፌሶን ጉባዔ
ይህ ጉባኤ ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ በመባል ይታወቃል፡፡ ለጉባኤው መሰብሰብ ምክንያት የሆነው የንስጥሮስ የክህደት ትምህርት ነው፡፡ በአንጾኪያ ትምህርት ቤት የጠርሴስ ሊቀ ጳጳስ ከሆነው ከዲያድርስ የክህደት ትምህርትን የተማረው ንስጥሮስ ይኖር የነበረው በግሪክ በሚገኝ ገዳም ነው፡፡

ንስጥሮስ የዲያድርስን እምነትና የክህደት ትምህርት ማለትም፤ በምስጢረ ሥጋዌ ክርስቶስን በሁለት ከፍሎ አንዱን ወልደ ዳዊት ሁለተኛውን ወልደ እግዚአብሔር ነው ብሎ ያምንና ያስተምር ነበር፡፡ በእርሱ አባባል ከማርያም የተወለደው የዳዊት ልጅ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ወልደ እግዚአብሔር ነው ብሏል፡፡ ስለዚህም እመቤታችን የወለደችው ሰው እንጂ አምላክ አይደለም በማለት በአደባባይ የክህደት ትምህርቱን ያስተምር ነበር፡፡

በህዳር ወር 428 ዓ.ም አናስጣቴዎስ የተባለ ካህን የቁስጥንጥንያ ፖትርያርክ ንሰጥሮስ ከአንጾኪያ አስከትሎት የመጣ አገልጋይ በቅድስት ሶፍያ ቤተ ክርስትያን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ /ቲወቶኮስ/ አትባልም በማለት አስተማረ፡፡ ስለዚህ ማንም ወላዲተ አምላክ ብሎ እንዳይጠራት አለ፣ ማርያም ሰው ናት እግዚአብሔር ከሰው ይወለድ ዘንድ የሚሆን ነገር አይደለም አለ፡፡ ታሪክ ጸሐፊው ሶቅራጥስ እንደሚለው ከፍተኛ የሆነ ቁጣንና ተቃውሞን ቀሰቀሰ የአጸፋ መልሱ የዘገየ አልነበረም፡፡ በታህሳስ 26 ቀን የድንግልን በዓል ለማክበር በተሰበሰበው ብዙ ሕዝብ መካከል ኘሮቅለስ የተባለ ካህን ንሰጥሮስ ባለበት ቦታ ስለድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክነት አስደናቂ የሆነ ስብከትን ሰበከ፡፡ ማርያም አለ ኘሮቅለስ የሴትነት ጾታ ክብር ናት፡፡ በእርሷ ምክንያት ሴቶች ሁሉ ክብርን አግኝተዋል እናትና ድንግል በመሆኗ በውድቀት ምክንያት ያጣነውን ጸጋ እንዲመለስልን ምክንያት ሆናለች አለ፡፡ የሁለተኛው አዳም መንፈሳዊ የአትክልት ሥፍራናት፡፡ መለኮት ከትስብእት የተዋሐደባት ሠርቶ ማሳያናት፡፡ ወልድ ሥጋ የነሳባት የሙሽራው ዙፋን ናት፡፡ ማርያም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለች ልዩ የሆነች ድልድይናት፡፡ መለኮትና ትስብዕት በአንድነት የተገመዱባት ዝሀ ናት፡፡ ግብሩም የመፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በእርሷ ሰው የሆነ እግዚአብር አንድነቱን አገኘ ወደዓለሙም ገባ፡፡ በህፃን አምሳል ሲወለድም ማህተመ ድንግልናዋን አልለወጠውም፡፡ አማኑኤል ሰው እንደመሆኑ ተወለደ አምላክ እንደመሆኑ ተዋኸደ፡፡

የኤፌሶን ጉባኤ የተካሄደው በ431 ዓ.ም በትንሹ ቴዎድሮስ ዘመን ሲሆን የተሰባሰቡት አበው ብዛት 200 ነው፡፡ የስብሰባው ዋና ዓላማም ንስጥሮስን ከክህደት ለመመለስ ሲሆን የጉባኤው አፈጉባኤ ቅዱስ ቄርሎስ ነበር፡፡ በዚህ ጉባኤም ንስጥሮስ ከተወገዘ በኋላ ስምንት ቀኖናዎች ተወስነዋል፡፡

ንስጥሮስ ለክህደት ትምህርቱ የተጠቀመበት (ዮሐ.1.04) ‹‹ቃል ሥጋ ሆነ›› የሚለውን መለወጥን ያስከትላል፣ (ፌል.2.5-6) ‹‹ነሥዓ አርአያ ገበረ›› ያለውን፤ ቃል በሥጋ አደረ፤ ብሎ እንዲመቸው አድርጐ በመተርጐም መሪ ጥቁሱን ነበር፡፡

ለንስጥሮስና ለክህደት ትምህርቱ በሚገባ ምላሽ የሰጠው በ375 ዓ.ም በእስክንድርያ የተወለደው የእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስ ነው፡፡ መዓርገ ዲቁናና ቅስናን ከቴዎፍሎስ ተቀብሎ፤ ቴዎፍሎስ በ412 ዓ.ም ሲያርፍ፤ የእስክንድርያ ሃያ አራተኛ ፓትርያርክ ሆኖ የተሾመውና የእስክንድሪያን ቤተ ክርስቲያን ለ"2 ዓመታት የመራው ታላቁ አባት ቅዱስ ቄርሎስ፤ የቃልና የሥጋን ተዋሕዶ በሚገባ በማስረዳት ስለውላጤና ኅድረት ተንትኖ በማብራራት ድል አድርጎአል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ተዋሕዶ የሚለውን ቃል አጉልቶ ተጠቅሞበታል፡

ማኅተመ አበው ቅዱስ ቄርሎስ ምስጢረ ተዋሕዶን ባስተማረበት ትምህርቱ አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ስንል በተዋሕዶ እንደሆነ በምሳሌ ገልጦ አስተምሯል፡፡ ተዋሕዶውም ነቢዩ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በጎቹን ሲጠብቅ ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥል ሐመልማሉም በነበልባሉ ሳይጠፋ እንዳልተጠፋፉት መለኮት ሥጋን ሳያቀልጠው መለኮትም በሥጋ ሳይጠፋ በተዋሕዶ አንድ ሆነ እንላለን፡፡ በእሳት ውስጥ የገባ ብረትም የባሕርዩ ያልነበረውን ብሩህነት በእሳቱ ያገኛል፤ ቀድሞ አይፋጅ የነበረው ብረት ይፋጃል፡፡ አካል ያልነበረው እሳትም በብረቱ ሆኖ ቅርጽ ይኖረዋል፡፡ አይጨበጥ የነበረው እሳት ይጨበጣል፤ አይዳሰስ የነበረው እሳት ይዳሰሳል፡፡ አንጥረኛው በጉጠት ብረቱን ይዞ ፍህም የሆነውን ብረት ይቀጠቅጠዋል፡፡ ብረቱ ሲደበደብ የተመታው እሳቱ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ብረቱ ነው አይባልም፡፡ እሳትና ብረት በተዋሕዶ አንድ ስለሆኑ ብረቱ ሲመታ እሳቱ አለ፤ እሳቱ ሲመታም ብረቱ አለ፡፡ እሳቱ ቢፋጅም /ቢያቃጥልም/ ብረቱ አለ፡፡የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶም በዚህ መልክ ስለሆነ መለኮት ሥጋን በመዋሐዱ መከራን ተቀብሎ ሞቶ አዳነን ብለን እናምናለን፡፡

በዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ዐይነ ስውሩን ሰው አምላካችን ሊያድነው በፈቀደ ጊዜ ምራቁን ወደመሬት እንትፍ ብሎ በጭቃ ዐይኑን ቀብቶ አድኖታል /ዮሐ.9፥1/ ምራቅ ብቻውን ዐይንን በማብራት ተአምር መሥራት የማይችል የሥጋ ገንዘብ ነበረ፡፡ መለኮት ብቻውንም ምራቅ ማውጣት አፈር ማራስ አይስማማውም ሥጋ ከመለኮት ጋር ተዋሕዷልና በምራቁ ዕውርን አበርቷል፡፡ ገቢረ ተአምራቱም የተከናወነው በሥጋ ብቻ ነው ወይም በመለኮት ብቻ ነው አይባልም፡፡

6.4 ጉባኤ ኬልቄዶን (ጉባኤ ከለባት)
በ443 ዓ.ም (451 እ.ኤ.አ.) በሮማው ንጉሥ መርቅያን ዘመነ መንግሥት ፮፻፶ ኤጲስቆጶሳት በተገኙበት የተሰበሰበው የኬልቄዶን ጉባኤ ከሮማው ሊቀጳጳሳት ቀዳማዊ ልዮን "ክርስቶስ ሁለት የተለያዩ ባሕርያት አሉት" የሚል ጽሑፍ አቅርቦላቸው ነበር። ዳሩ ግን የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ "ጌታ ሁለት ባሕርያት አሉት" የሚለው ትምሕርት ስሕተት ነው ብሎ ልዮንን አወገዘው። ከዚያን ጊዜጀምሮ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በእምነት ተለያዩ።