Advertisement Image

የቤተክርስቲያን ታሪክ

መሰረታዊ የክርስትና ትምህርቶች እና ትንታኔዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች

ምዕራፍ አምስት : ዘመነ መናፍቃን

መናፈቀ፡-ማለት ተጠራጠረ ማለት ሲሆን መናፍቅ ማለት ተጠራጣሪ ማለት ነው፡፡[ጠቅላላየቤተክርስቲያንታሪክ]ይህም በአንድ ሃይማኖት ውስጥ የተለየ አሳብ የሚከተል የሆነውን ለማመን የሚያመነታና የሚጠራጠር ወገን ነው፡፡ መናፍቅነት የስጋ ስራ ነውና መለያየትን ያመጣል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከነገስታት (ከውጭ) የሚመጣውን ስቃይና ፈተና በመጋደል ላይሰለች ከውስጧ አማኝ መስለው አደገኛ ጠላቶች በየጊዜው ተነስተውባታል፡፡ እነሱም ከሐዋርያት ጊዜ ጀምረው እስካሁን ድረስ የተነሱትና ያሉት መናፍቃን ናቸው፡፡ ለብዙዎቹ መናፍቃን መነሻ የሆኑት ደግሞ በየዘመናቱ የሚነሱት ፍልስፍናዎች ናችው በተለይም በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት ትልቅ እጩ ሆኖ ያገለግል የነበረው መናፍቃንን ለመፈልፈል የግሪክ ፍልስፍና ነው፡፡

5.1 የጥንት ግሪኮች የፍልስፍና አስተምሮ
በቀደመው ዘመን የግሪኮች ፍልስፍና ትምህርትና አስተሳሰብ በአብዛኛው በምዕራቡ አለም እንደ እምነት ይታይ ነበር፡፡ በየዘመኑ የተለያዩ ፈላስፎች ስለሥነ-ፍጥረት ፣ ስለ ዓለም አኗኗር ፣ ሁሉን ስላስገኘው ኃይል የተለያዩ መላምቶች በማቅረብ ለተከታዮቻቸው አቅርበዋል፡፡ የፕላቶናውያን የፍልስፍና አስተሳሰብ ሁሉን ፈጥሮ የሚገዛው አንድ ኃይል ከዓለም የተለየ ፣ፍፁም ፣ልዑል ፣ ከፍጥረቱ ጋር ግንኙነት የሌለው ፣ የማይታወቅ፣ከእውቀት ሁሉ በላይ የሆነ፣የማይናገር፣ስለእሱም ሊናገሩለት የማይቻል ነው ይሉ ነበር፡፡የሐዋ 17÷23 ከዚህ በተጨማሪም አለምን የሚያስተዳድሩ ሁለት አማልክት እንዳሉ ያምኑ ነበር፡፡ አንደኛው ፀሐይንና መልካም ነገር ያስገኘ ደጉ አምላክ ሲሆን ሁለተኛው ጨለማንና በዓለም የሚገኙ ክፉ ነገሮችን ሁሉ የፈጠረ ክፉ አምላክ ነው፡፡ይህም ትምህርት ምንታዌ ወይም ሁለትነት (dualism)ይባላል፡፡

ከዚህ በመነሳት በዚሁ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተነሱትና ፍልስፍናን ከክርስትና ትምህርት ጋር ለመቀላቀል የሞከሩት አዋቂዎች ነን ባዮች ደግሞ ግኖስቲኮች ይባላሉ፡፡(የቤተከርስቲያን ታሪክ)

5.2 ግኖስቲኮች (gnostics)
ግኖስቲክስ የሚለው ቃል “ግኖሲስ” (እውቀት) ከሚለው ግሪክኛ ቃል የወጣ ሲሆን ፍቺውም “ዐዋቂዎች“ ጥበበኞች” ማለት ነው፡፡ “ግንሲስ” ዕውቀት ዛሬ እኛ በሚገባን መንገድ ሳይሆን በግኖስቲክስ አስተሳሰብ ጥልቅ የሆነ ፍልስፍናዊ እውቀት ወይም ረቂቅ የሆነ ከሰብአዊ ባህሪይ በላይ የሆነ ዕውቀት ማለት ነው፡፡መዳን በዕውቀት ብቻ እንጂ በዕምነት አይደለም የሚሉ ናቸው፡፡ግኖስቲኮች ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ ዐወቅን ብለው በዘመናቸው የነበረውን ፍልስፍና ከክርስትና ሐይማኖት ጋር ይቀላቅሉ ነበር፡፡ከክርስትና እምነት ይልቅ በፍልስፍና ላይ ለመመስረት ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ይህ የሐሰት ትምህርትና የቅልቅል ሕይወት የተጀመረው በመጀመሪያ ክርስቲያኖች በብዛት በሚገኙባቸው ከተማዎች በሶርያ(በአንጾኪያ) ፣ በግብጽ(በእስክንድርያ) ፣ በታናሽ እስያ ነበር፡፡

5.2.1 ስለ አምላክ የግኖስቲኮች አስተምህሮ
ፈጣሪ ከፍጥረቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው በመግቦቱም ዓለምን እንደማይመግብ ይገልፃሉ፡፡ ይህንንም አምላክ ክፉ አምላክና ደግ አምላክ የተባሉ ሁለት አማልክትም እንዳሉ ያስተምራሉ፡፡

ደጉ አምላክ የፈጠረው
-ብርሃንን የፈጠረ
-የማይታየውንና ረቂቁን የፈጠረ
-የሐዲስ ኪዳን መስራች
ክፉ አምላክ የፈጠረው
- ጨለማን የፈጠረ
- የሚታየውንና ግዙፉን የፈጠረ
- ብሉይ ኪዳንን የሰራ

5.2.2 ስለ ሥነ ፍጥረት የግኖስቲኮች አስተምህሮ
ይህ ዓለም በክፉ አምላክ የተፈጠረ ስለሆነ የኃጢአት ምንጭ ነው፡፡ ስለዓለም አፈጣጠር ሲናገሩ ከባሕርየ መለኮት እንደምጣድ ብልጭታ እንደ የእሳት ነበልባል ክፋይ ከሚወጡ ነገሮች(Aeons) ሲሆን እነዚህ ነገሮች ከእግዚአብሔር እየራቁ በሔዱ መጠን ፍጹምነታቸው እየቀነሰ ይሔዳል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ፍጹምነታቸው መቀነስ በተጨማሪ ከእነዚህ ነገሮች (Aeons) አንዱ ተሳሳተ ከመስመር ወጣ፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ዓለም ተጣሉ ይህ የተሳሳተውና የተጣለው (Aeons) በመጨረሻ ሰውንና ቁሳዊውን ዓለም ፈጠረ ይላሉ፡፡

ሰው በመባል የሚታወቀው ሰብአዊ ክብርም ያለው ነፍስ እንጂ ስጋ አይደለም፡፡ ይህች የሰው ነፍስም እንደ እሳት ነበልባል ክፋይ ከመለኮት ባሕርይ እየተከፈለች የምትመጣ ናት፡፡ ሥጋ ግን ምድራዊ ስለሆነ የኃጥያትና የርኩሰት መሣሪያ ነው፡፡ የመዳን ተስፋ ያላት ነፍስ ብቻ ናት፣ ሥጋ በባሕርዩ ለጥፋት የተፈጠረ ስለሆነ ፈርሶ በስብሶ ይቀራል የሰው ነፍስ የመለኮት አካል ስትሆን በመዋቲ ሥጋ ውስጥ በዕድል ሠንሰለት ተጠፍራ ወይም ታስራ ትኖራለች፡፡ ይህን እሥራት ሊፈታ የሚችል ደግሞ ዕውቀት ብቻ ነው፡፡ የዕውቀት ምሥጢር ቁልፍ በእጃችን ነው ይላሉ፡

ግኖስቲኮች ሰውን በሦስት ደረጃዎች ይከፍሉታል እነዚህም:-
1.መንፈሳዊ ፡- የሚሉት ራሳቸውን ነው፡፡ በዕውቀት አስቀድመን ድነናል ባዮች ናቸው፡፡
2.ነፍሳዊ ፡- የሚሉት ክርስቲያኖችን ነው፡፡ በመዳንና በመጥፋት መካከል ያሉ ናቸው ቢያውቁ ይድናሉ፡፡
3.ሥጋዊ ፡- የሚሉት አሕዛብና አይሁድን ነው፡፡ ለጥፋት የተፈጠሩ ናቸው፡፡ የመዳን ተስፋ የላቸውም ይላሉ፡፡

ክርስቶስ ፍጹም ልዑልና የማይታወቅ የሆነውን አምላክ ለሰዎች ገለጸላቸው፡፡ ይህ ምድራዊ ግዙፍ (ቁስ አካላዊ) ዓለም ስጋም ጭምር ክፉ (evil) ስለሆነ ክርስቶስን በማስመሰል (በምትሐት) እንጂ በእውነትነት ስጋን አለበሰም፡፡ ስለዚህ ግኖስቲኮች የክርስቶስን ሰው መሆን ሞቱንና መነሳቱን አያምኑም፡፡ ኢየሱስ በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና መወለዱን አያምኑም፡፡ እንዲያውም አልፈው ተርፈው ኢየሱስ የዮሴፍ ልጅ ነው የሚሉት፡፡ በግኖስቲኮች እምነት ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ሰማያዊ ክርስቶስ በኢየሱስ ላይ አደረበት በስቅለት ጊዜ ግን ትቶት በመሄዱ ኢየሱስ ብቻውን መከራን ተቀበለ ይላሉ፡፡

በግኖስቲኮች እምነት ጋብቻ የሰይጣን ተግባር ነው፡፡ መውለድና መራባትም የሰይጣን ሥራ ስለሆነ በኅርምት፣ በጾምና በጸሎት መኖርን ይመክራሉ፡፡

ግኖስቲኮች በብዙ ክፍሎች ስለሚከፈሉ አንድ አይነት መመሪያ አንድ አይነት የሃይማኖት ትምህርትና ሥርአት የላቸውም፡፡ ሁሉንም በአንዴ ዘርዝረን ስለማንጨርሳቸው በዋናነት የተገለጡትን ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

ሲሞን መሠርይ
ሲሞን መሠርይ በፍልስጤም ምድር በሰማርያ ይኖር ነበር፡፡ የሚተዳደረውም በጥንቆላ ስራ ሲሆን ህዝቡን እያስደነቀ ነበር፡፡ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ የነበረው ፊሊጶስ እያስተማረና እያጠመቀ ወደዚያች ወደሰማርያ ከተማ በመጣ ጊዜ ሲሞን የፊሊጶስን ትምህርት ሰምቶና በእጁ ይደረጉ የነበሩትን ተአምራት አይቶ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቆ ነበር፡፡ የተጠመቀውም ከልቡ አምኖ ሳይሆን ወንጌላዊው ፊሊጶስ ያደርግ የነበረውን ተአምራት አይቶ ከእሱ የሚበልጥ ስለሆነበት እኔም አምኜ ብጠመቅ እንደርሱ ተአምራት አድርጋለሁ ብሎ አስቦ ነው፡፡በኋላ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ በሰማሪያ ለተጠመቁት ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን እያደሉ ሲመጡ እርሱም እንደነርሱ መንፈስ ቅዱስን ለህዝቡ ማደል እንደሚፈልግ ገልጾ በገንዘብ ሊደራደር በሞከረ ጊዜ ጴጥሮስ በጥብቅ ገስፆጻታል፡፡ ሐዋ 8÷5-24/p>

ሲሞን መሠርይም ፍላጎቱ ሳይሳካለት ስለቀረ በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ጥላቻና ስም መጥፋት ዘመቻ ጀመረ፡፡ ይባስ ብሎ ራሱን ከሰማይ የወረደው እውነተኛው ክርስቶስ እንደሆነ መናገር ጀመረ፡፡ ሲሞን የብሉይ ኪዳንን ትምህርት በአጠቃለይ ይጠላና ይቃወም ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሄደበት ሁሉ እየተከተለ ተቃውሞታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በቂሳሪያና በአንጾቂያ ህዝብ በተሰበሰበበት ተከራክሮ ረትቶታል፡፡ በመጨረሻም በምትሃቱ ወደ ሰማይ አርጋለው ሲል ጴጥሮስ በትዕምርተ መስቀል ቢያማትብበት ከአየር ላይ ወድቆ ሞቷል፡፡ ሆኖም የእርሱ ተከታዮች የእርሱን ኑፋቄ እያስተማሩ እስከ 3ኛው ክፍለ ዘመን ቆይተዋል፡፡[የእግዚአብሔር መንግስት በምድር ላይ ገጽ 228-229]

መርቅያን {marcion}
በትንሷ እስያ ከንበሩት ግኖስቲኮች መካከል ቀንደኛው መርቅያን ነበር፡፡ መርቅያን በጣም ጠንካራ ብርቱ አደገኛ ሰው በመሆኑ የግኖስቲክ አስተሳሰብ በምስራቅና በምዕራብ ማስፋፋት ችሏል፡፡ መርቅያን በትንሷ እሲያ ሲኖፕ (sinope)በምትባል ቦታ ከክርስቲያን ቤተሰብ ነው የተወለደው፡፡ አባቱ የፓንቱስ (pontus) ኤጲስቆጶስ ነበር፡፡ መርቅያን በጣም ሀብታምና የመርከብ ባለቤት ነበር፡፡ ጠንካራ ክርሰቲያንም በመሆኑ ያለውንም ንብረት ለቤተክርሲቲያንም ሠጥቶ ቤተክርስቲያንንም በማገልገል ተቀመጠ፡፡ ሆኖም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሰራጭ ለነበረው የኑፋቄና የክህደት ትምህርቱ አባቱ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ለየው፡፡ ከ140-155 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሮም ሄዶ ብዙ ተከታዮችን አፈራ በኋላ ግን ሮም ከነበሩት ከግኖስቲኮች ጋር በመቀላቀል ግኖስቲዝምን በስፋት ማሰራጨት ቻለ፡፡

መርቅያን እንደሌሎቹ ግኖስቲኮች ሁለት አማልክት (ደግና ክፉ)አማልክት መኖራቸውን አስተምሯል፡፡ የብሉይ ኪዳን አምላክ ክፉ አምላክ ነው ብሎ በማመኑ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት በሙሉ አይቀበልም ነበር፡፡ የክርስቶስን ሰው መሆን ስጋ መልበስ በምትሀት እንጂ በእውነት እንዳልሆነ አስተምሯል፡፡ ምክንያቱም ስጋ ርኩስና ክፍ መሆኑን ስለሚያምን ነው፡፡ ከሐዲስ ኪዳን መጽሐፍትም ጥቂቶቹን ብቻ ነው የሚቀበለው፡፡ እርሱም የሉቃስ ወንጌልንና አስሩን የጳውሎስ መልዕክታት ብቻ ነው የሚቀበለው፡፡ ጋብቻ የብሉይ ኪዳን አምላክ የሰራው ስለሆነ ርኩስ ነው በማለት አይቀበለውም ነበር፡፡ ለመጠመቅ የሚመጡትን ይቀበል የነበረው በቀጥታ ያላገቡትን ነበር ያገቡትን ግን ያለ ግንኙነት ንጽህናቸውን ጠብቀው የሚኖሩ መሆናቸውን ቃል አስገብቶ ነበር የሚያጠምቃቸው፡፡ ስለ ሚስጢረ ቁርባንም ከቤተ ክርስቲያን ስርአት የተለየ ስርአት ነበረው፡፡ ወይን ጠጅ መጠጣት በእርሱ ዘንድ ኃጢአት ስለሆነ ምሥጢረ ቁርባንን ይሰራ የነበረው በህብስትና በውሀ ነው፡፡

መርቅያን በምንፍቅና ትምህርቱ በጥንቱ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በጣም የተጠላ በመሆኑ እርሱና ተከታዮቹ የተጠሉ ነበሩ፡፡ የሮም ቤተ ክርስቲያን በ144 ዓ.ም ላይ መርቅያንን በይፋ አውግዛለች፡፡[የእግዚአብሔር መንግስት በምድር ላይ ገጽ 229-230]

ማኒ
የፋርስ ተወላጅ የነበረው ማኒ (215-277) ዓም ፈላስፋ የስነፈለክ (የከዋክብት) ተመራማሪና ሰአሊ ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ያመልክ የነበረው የዞራስተርን እምነት ምንታዌ አማኝ ነበር፡፡ በወጣትነቱ ክርስትና ወደ ፋርስ ሲገባ ክርስትናን አምኖ ተጠመቀ፡፡ በዚህን ጊዜ ግኖስቲኮች በፋርስ ተሰራጭተው ስለነበር በእነርሱ ፍልስፍና የኑፋቄ ትምህርት ተጠመደ፡፡ እንዲያውም በ238 ዓም አዲስ ሃይማኖት ተገለጠልኝ ብሎ የብዙ ሃይማኖቶችን ቅልቅል ትምህርት ማስተማር ጀመረ፡፡በዚህም ምክንያት ከሀገሩ ወጠቶ ወደ ህንድና ቻይና ሄደ፡፡ ከቡድሃ ሃይማኖትም ብዙ ነገሮች ቀስሞ ወደ ራስ እምነት አስገባ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እልክላችኋለሁ ያለው ጰራቅሊጦስ እኔ ነኝ እያለ ማስተማር ጀመረ፡፡ የማኒ የኑፋቄ ትምህርት መሰረት ሁለቱ አማልክት የየራሳቸው የሚላላኳዋቸው መላዕክት አሏቸው፡፡ ስለ ሰው ተፈጥሮ ሲናገር ደግሞ ሰው ሁለት ነፍሳት አሉት አንዷስጋዊት ግዙፍ ስትሆን እርሷ የክፋት ምንጭ ናት፡፡ ሌላዋ ደግሞ ደግና ብርሃናዊት ናት፡፡ በማኒ አስተሳሰብ ይህቺን ብርሃናዊት ነፍስ ከክፉዋ ከግዙፏ ነፍስ ለመታደግ ኢየሱስ ሰው መስሎ (በምትሃት) ወደዚህ አለም መጣ፡፡ የሰዎች ነፍሳትም ከዚህ ግዙፍ አለም ተላቀው ወደ ደጉና መልካሙ አምላክ የሚጓዙበትን አስተማራቸው፡፡ ሆኖም ኢየሱስ ስራዉን ሳይፈጽም በመሄዱ ጅምሩን ለመፈጸም ለሐዋርያት በመጠኑ መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው፡፡ ሆኖም ሐዋርያት ክርሰትናን ያስተማሩት ከይሁዲነት ጋር ቀላቅለው ስለሆነ ሐሰት የተሞላ ነው ይላል፡፡ ለእርሱግን መንፈስ ቅዱስን የላከው በሙላት ስለሆነ እርሱ የሚያስተምረው ትምህርት ምጥቀትና ጥልቀት እንዳለው አስተምሯል፡፡ በመጨረሻም በ270ዓ.ም ወደሃገሩ ፋርስ ቢመለስም የሃገሩ ሰዎች ስላልተቀበሉት በ277 ዓ.ም ሰቅለው ገድለውታል፡፡[የእግዚአብሔር መንግስት በምድር ላይ ገጽ 231-232]

5.3 ሁለቱ የትርጓሜትምህርትቤቶች
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የምናገኛቸው ሁለቱ ትርጓሜ ቤቶች በቤተክርስቲያን ደረጃ ለተደረጉት ጉባዔያት መሠረቶች ናቸው፡፡ለምንቀበላቸውም ለማንቀበላቸውም ጉባዔያት መሰረቶች ናቸው፡፡እነዚህም የእስክንድርያው ትርጓሜ ቤት እና የአንፆኪያው ትርጓሜ ቤቶች ናቸው፡፡የሁለቱም ትምህርት ቤቶች መከፈት በቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ የራሱን የሆነ መልካምና መጥፎ የሚባሉ ጎኖችን አስከትሏል፡፡

5.3.1 የእስክንድርያው ትርጓሜ ቤት
የእስክንድርያው ትርጓሜ ቤትን በ 60 ዓ.ም የመሰረተው ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ነው፡፡ከጌታ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቅድስ ማርቆስ ያስተማረባት በመሆኑ ለብዙ ዘመናት የክርስትና መዲና ሆና ቆይታለች፡፡ በክርስትና መዲናነቷም ከሮምና ከአንጾኪያ ጋር በእጅጉ ትወዳደራለች፡፡ በዚህች በእስክንድርያ ከተማ የአይሁድ ብሉይ ኪዳን ወደ ግሪክ ቋንቋ በመተርጎሙ የግሪክ ፈላስፎች የዕብራውያኑን እምነትና የሕግ መጻህፍት በቀላሉ እንዲያውቁ ረድቷቸዋል፡፡

የእስክንድርያ የወጣንያን ክርስቲያኖች ትምህርት ቤት (catechetical school) የተመሰረተው በ185 ዓም አካባቢ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱም በእስክንድሪያ ቤተ ክርስቲያን ሲቋቋም የመጀመሪያው ኃላፊ ፓንዴኖስ ይባል ነበር፡፡ ፓንዴኖስ የረዋቅያን (stoics) ፍልስፍና ተከታይ ነበር፡፡ በኋላ ግን ወደክርስትና ተመልሶ ቀናኢ ሰባኪ ሆኖ ነበር፡፡ ለ17 አመታት በእስክንድሪያ መንፈሳዊ ት/ቤት ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ወደ ህንድ ሀገር በመሄድ ሰባኬ ወንጌል ሆኖ አገልግሏል፡፡

5.3.2 የአንጾኪያ የትርጓሜ ትምህርት ቤት
አንጾኪያ የተመሰረተችው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ300 ዓመት ላይ የትልቁ እስክንድር ወራሾች በሆኑ በአንድ በሴሌውቆስ ኒካቶር (Seleucus Nicayor) በተባለው መሪ ነበር፡፡ አንጾኪያ በ64 ዓ.ዓ በሮም ንጉሰ ነገስት መንግስት ተይዛ ለብዙ ጊዜ የመንግስቱ 3ኛ መናገሻ ከተማ ሆና ነበር፡፡ አንጾኪያ ከእስክንድርያ ከተማ ቀጥሎ የግሪክ ስነ-ጽሁፍና ስነ-ጥበብ ማዕከል ሆና ኖራለች፡፡

በዚህች ከተማ ሐዋርያት ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን የተባሉባት ከተማ ነች፡፡ አንፆኪያ ቅዱስ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ነዳያን ክርስቲያኖች ምጽዋት የሚሰበስቡባት ዋና መመላለሻቸው ነበረች፡፡ ስለዚህም በ3ኛው አጋማሽ ላይ የትርጓሜ ትምህርትቤቱ ተከፈተ፡፡ የዚህ ትምህርትቤት መስራች ደግሞ ሉቂያኖስ ነበር፡፡

በትርጓሜ ትምህርት አሰጣጣቸው ሁለቱም ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ነበሩ፡፡ የእስክንድርያ ትምህርት ቤት “ንባብ ይቀትል ወትርጓሜ የሐዩ፡- ንባብ ይገድላል ትርጓሜ ግን ያድናል”፡፡ በሚለው ቃለ እግዚአብሔር መሰረት ቅዱሳት መጻሕፍትን በአንድምታ ትርጓሜ በመተርጎም ምስጢራቸውን እንጅ ንባባቸውን አይከተልም ነበር፡፡ ይህም (allegorical interprtation) በመባል ይታወቃል፡፡

የአንጾኪያ ትምህርትቤት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን በነጠላ ትርጓሜ (Literal interpretation) ብቻ ያስተምር ነበር ከዚህ አተረጓጎም መሠረታዊ ልዩነት የተነሣ ሁለቱ ትምህርት ቤቶች እርስ በርእሳቸው ይነቃቀፉ ነበር፡፡

5.3.3 ከሁለቱ ትምህርት ቤቶች የሚወጡ መናፍቃን
የብዙዎቹ መናፍቃን ችግራቸው የፍልስፍናውን አስተሳሰብ ከክርስትናው ጋር ለመቀላቀል በመሞከራቸው ነው፡፡ የቀደመ ፍልስፍናቸውም በሃይማኖት አይን ሲታይ ስህተት ነበር ብሎ መቀበልን ስለማይፈልጉ የክርስትናውን ትምህርት በፍልስፍናው ለመተርጎም እየሞከሩ ለውድቀት ተዳርገዋል፡፡ ከእነዚሁ መናፍቃን መካከል የተወሰኑትን ለመነሻነት ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

፩. ቀሌምንጦስ ዘእስክንድሪያ (Clement of Alexanderia)
የመጀመሪያ ስሙ ቲቶ ፍላቢያኖስ ነው ቀሌምንቶስ በእስክንድሪያ ከአረማውያን ቤተሰቦች በ150 ዓም ተወለደ፡፡ በተፈጥሮው የመማር የማጥናት የመመራመር ስጦታ ነበረው፡፡ የሮማውያንና የግሪኮችን ፍልስፍና በሚገባ አጥንቷል ክርስቲያን ከሆነ በኃላ በእስክንድሪያ የትርጓሜ ት/ቤት የቅዱሳት መጻህፍትን ትርጓሜ የሐዋርያውያን አባቶችን ድርሳናትና ምዕዳናት አጥንቷል፡፡ በ189 ዓ.ም የእስክንድሪያ ቤተ ክርስቲያን ለቀሌምንጦስ የቅስና ማዕረግ ሰጥታ ሾመዋለች፡፡

በ190 ዓም ግድም የፓንዴኖስ ተማሪ የነበረው የእስክንድሪያው ቀሌምንጦስ በፓንዴኖስ ፈንታ ተተክቶ ለ12 አመታት ያህል ሲያገለግል ቆይቶ ትምህርት ቤቱንም እጅግ ዝነኛ አድርጎታል፡፡ ሴፕቶሚዮስ ሳዊሮስ በተባለው የሮም ነጉሠ ነገሥት ዘመን በ202 ዓ.ም በግብፅ ክርስቲያኖች ላይ በተነሳው ስደት ቀሌምንጦስ ሸሽቶ በታናሽቱ እስያና ወደ ፍልስጤም ምድር ሄደ በዚያም እየተዘዋወረ ለ10 አመታት ከቆየ በኋላ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡ ቀሌምንጦስ በህይወቱ ጥቂት መጻሕፍትን የጻፈ ሲሆን በጣም የታወቁትና ከጥፋት የተረፉት ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም
1.“ለግሪኮች ምክር” (Exhortation to the Greeks) የክርስትና ሃይማኖትንበመደገፍ ከግሪክ ፍልስፍና ብልጫ እንዳለው ያመላክታል፡፡
2.“አስተማሪ”(Instructor) ክርስቲያናዊ ስነ ምግባርን በስፋት የሚያሳይ ነው፡፡
3.“የተለያዩ ትምህርቶች(Stromata)ስለ ልዩ ልዩ ጉዳዮች የተጻፉ ናቸው፡፡

ቀሌሜንጦስ ስለ አዳም ኃጢአትና ስለ ክርስቶስ የማዳን ስራ በሚናገርበት ጊዜ ሰው ኃጢአትን የሚሰራው ባለማወቅ ነው፡፡ ባለማወቅም ሆነ በግዴታ የሚሰራው ኃጢአት ለቅጣት አያበቃውም ይል ነበር፡፡ በቀሌምንጦስ አስተሳሰብ መዳን የሚገኘው በፍፁም ዕውቀት ነው፡፡ ቃልም ሰው የሆነውና ሥጋ የለበሰው ለአለም የምንድንበትን ዕውቀት ለመግለጥ ነው፡፡ በዚህም ከጥንት የግሪክ ፈላስፎች አንዱ ከሆነው ከሶቅራጥስ ጋር አንድሲሆን በእርሱ ዘንድ አለማወቅ የክፋት ምንጭ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ አለማወቅ ወደ ኃጢአት ጉድጓድ የሚጥል የጨለማ መንገድ ነው፡፡ ዕውቀት ግን ከዚህ የሚያድን ብርሀን ነው፡፡ በማለት ይናገራል፡፡

፪. አርጌንስ (Origen)
አርጌንስ የተወለደው በእስክንድርያ 185 ዓ.ም ከክርስቲያን ቤተሰብ ነው፡፡ አርጌንስ የመጀመሪያ ትምህርቱን የተማረው በእስክንድሪያ ትምህርት ቤት ሲሆን በትምህርት ኮትኩቶ ያሳደገው ቀሌምንጦስ ዘእስክንድሪያ ነው፡፡ በ202 ዓ.ም ክርስቲያኖች በእስክንድሪያ በግፍ ባለቁ ጊዜ መምህሩም ቀሌምንጦስ ወደ ፍልስጤም በመሰደዱ ያን ጊዜ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ድሜጥሮስ የአስራ ሰባት አመቱን አርጌንስን በመምህሩ እግር ስር ተተክቶ እንዲያስተምር ሾመው፡፡ አርጌንስ ለ30 ዓመታት ሲያገለግል ቆይቶ ወጣት ሳለ የተሰጠውን ስራ እየሰራ በእስክንድሪያ ከተማ ከነበረው ፍልስፍና ትምህርት ቤት ገብቶ የፕላቶን ፍልስፍና ከአሞንዮስ ተምሮአል፡፡

አርጌንስ የማስተማርና የመናገር ስጦታ የነበረው በትምህርት ቤቱ ክርስቲያኖችና አህዛብ ወንዶችና ሴቶች ይማሩ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ አርጌንስ ከሐሜት ለመራቅ ራሱን ሕፅው (ጃንደረባ) አደረገ፡፡ ጌታ በማቴዎስ 19÷12 የተናገረውን ምስጢራዊ አነጋገር ቃል በቃል በመገንዘብ ያደረገው እንጂ ይህ ተግባር በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሰረት ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ ራሱም ቢሆን ቆይቶ ትክክል አለመሆኑን ተረድቶታል፡፡ ታዲያ በዚህ ምክንያት የእስክንድርያው መንበር ፓትርያርክ ድሜጥሮስ ስልጣነ ክህንት አልሰጠውም፡፡

በ230-231 ዓ.ም ለመልእክት ወደ ግሪክና ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተላከ፡፡ በዚያም ቀድሞ በእስክነድርያ የአርጌንስ ትምህርት ቤት ጓደኞቹንና ተማሪዎቹን አግኝቶ እየተዘዋወረ ማስተማርና መስበኩን ጀመረ፡፡ አርጌንስ እየዞረ እንደልቡ ማስተማር እንዲችል ጓደኞቹ የነበሩት የኢየሩሳሌሙ ኤጲስቆጶስ እለእስክንድሮስና የቂሳሪያ ኤጲስቆጶስ ቴዎክቲቶስ ማዕረገ ቅስና ሰጡት፡፡ በዚህ ምክንያት ድሜጥሮስ በ232 ዓ.ም ጉባኤ ጠርቶ ለሌላ ሃገረ ስብከት ሰው ስልጣነ ክህነት መስጠት የሀገረ ስብከትን ክልል በማለፍ የተፈጸመ ሕገ ወጥ ተግባር በመሆኑ ሹመቱን አልተቀበለውም፡፡ እንዲያውም በዚህና በሌሎች ምንፍቅና ጉዳዮች አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ለየው፡፡ በሮሙ ቄሳር በዳኪዮስ ዘመን በተነሳው የክርስቲያኖች ስደት እርሱም ታስሮ በብዙ ስቃይና መከራ ከተቀበለ በኃላ ተለቀቀ፡፡ ብዙም ሳይቆይ በ254 ዓ.ም በጢሮስ ከተማ እንደሞተ ይነገራል፡፡

የአርጌንስ የኑፋቄ አስተምሮ
1.ስለ እግዚአብሔር ያለው አስተምሮ
እግዚአብሔር ወልድ በባህሪይ ከአብ ጋር የተካከለ ነው ይላል ይህ በእርግጥ ኦርቶዶክሳዊ ነው፡፡ ነገር ግን በሌላ ቦታ ወልድን ከአብ ያሳንሳል ፤ በሌላ ቦታ ደግሞ በባህሪ ይመሳሰላሉ እንጂ አንድ ናቸው አይልም
2.ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ ሲናገር ደግሞ ሁለት ባሕሪይ እንዳለው የሚያመላክት ስሜት ያሳያል
3.ስለ ስነ ፍጥረት ያስተማረው ትምህርት ደግሞ ይህ ዓለም በእግዚአብሔር የተፈጠረ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቢፈጠርም ልክ እንደ እግዚአብሔር ዘመን አቆጠርለትም ዘላለማዊ ነው፡፡
4.ስለ መዳን ሲናገር እግዚአብሔር ቸር መሐሪ ነው ርኅሩኁ ስለሆነ ዓለሙን ሁሉ ያድናል ኃጢአተኞችን በክርስትና እምነት እርሱን ያልተከተሉትንም ቢሆን በመጨረሻ በሚያነጻ እሳት አንጽቶ ያነሳቸዋል፡፡ በአለም መጨረሻ ሰይጣንና አጋንንትም ቢሆን አድኖአቸው ወደ ቀደመ ክብራቸው ይመልሳቸዋል፡፡ ብሎ ያስባል
5.ስለ ነፍስ አስቀድሞ መኖር (pre-existence of soul)

በፕላቶን ፍልስፍና መሰረት ነፍስ ከሁሉ አስቀድማ በሌላ አለም የነበረች ናት፡፡ ነፍስ ከአካል በፊት የነበረች፡፡ እያንዳንዷ ነፍስ በበደል ምክንያት ወደዚህ ዓለም መጥታ በሰው ስጋ ውስጥ እንደ እስር ቤት ትገባለች፡፡ ይህን የፕላቶንን ቲዎሪ አርጌንስ በእጅጉ አስፋፍቶ አስተምሯል፡፡

፫. ሰባልዮስ
የሊቢያ ተወላጅ ነው፡፡ ሰባልዮስ ወደ ሮም ሄደ በዚያም እግዚአብሔር አንድ ገጽ አንድ አካል ነው የሚለውን አፍላጦናዊ የፍልስፍና ትምህርት ተማረ፡፡ እነዚህ መናፍቃን ፍልስፍናን ከክርስትና ጋር ቀላቅለው ከሚያስተምሩ “አብ መከራን ተቀበለ” ከሚሉ መናፍቃን (patri passian) ነው፡፡ እነዚህ መናፍቃን በሮም ያስተምሩት የነበረው “ሞዳለስቲክ ሞናርኪያኒዝም” (modelistic monarchianism) ይባላል፡፡ አንድ ገጽ በተለያዩ ዘመናት ቅርጹን ለዋውጦ ታየ ማለት ነው፡፡ ሰባልዮስም ይህን ሁሉ አግበስብሶ ወደ ሃገሩ ተመለሰ፡፡ ይህንኑ የክህደት ትምህርትም ማስተማር ጀመረ፡፡

በሰባልዮስ አስተሳሰብ ትምህርት በተለያየ መልክ ያለ አንድ አምላክ አንዱ አካል ራሱ ማለት ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት ቅርጹን እየለዋወጠ ታየ ማለት ነው፡፡ አንዱ አካል አብ ብሉይ ኪዳንን ስለሰራ አብ ተባለ በዘመነ ስጋዌ ሰው ሆኖ ስጋ ለብሶ ስለታየና አዲስ ኪዳንንም ስለሰጠን ወልድ ተባለ ኋላም በበዓለ ጰንጠቆስጤ በአምሳለ እሳት ወርዶ በሐዋርያት ምስጢርን በመግለጹ ቋንቋን በማናገሩ መንፈስ ቅዱስ ተባለ እንጂ አንድ አካል አንድ ገጽ ነው ብሏል፡፡

በዚያን ዘመን ከ249-269ዓ.ም የነበረው የእስክንድሪያ ፓትርያሪክ ዲዮናስዮስ ትምህርቱን አውግዞ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ አብራርቶ ጻፈ፡፡

፬. ጳውሎስ ሳምሳጢ
የተወለደው ሶርያ ነው፡፡ ሳምሳጢ የተባለበትም ኤጲስቆጶስ በተሾመበት ሀገረ ስብከቱ በነበረችው በሳሞስታ ነው፡፡ ከ260-268 ዓ.ም የአንጾኪያ ውስጥ የሳምሳታ ኤጲስቆጶስ ነበር፡፡ ትምህርቱ በጠባይ ይለያይ እንጂ ወደ አንድ ገጽ ያደላ ነው ዳይናሚክ ሞናርኪያኒዝም (Dianomic Monarchianism) ይባላል፡፡ ቃል አካል ሳይኖረው በአብ አካል ውስጥ የኖረ ሆኖ አምላክ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሃይል ነው፡፡ ከሥጋዌ በፊት ቃል አካል አልነበረውም በአብ ህልውና ውስጥ የኖረ ዝርው (ብትን) ኃይል ነው እንጂ፡፡ ስለ መንፈስ ቅዱስም ቢሆን እንደ ቃል በአብ አካል ህልውና ሆኖ የሚያገለግል ዝርው (ብትን) ኃይል እንጂ አካላዊ አይደለም ብሏል፡፡ በ 268 ዓ.ም በአንጾኪያ ጉባኤ ተወግዟል፡፡

በጳውሎስ ሳምሳጢ የክህደት ትምህርት አምነው የተጠመቁ ቢኖሩ እንደገና እንዲጠመቁ ሠልስቱ ምዕት በቀኖናቸው “ለዘተወልደ እምጳውሎስ ሳምሳጢ ካዕበ ያጥምቅዎ” በማለት በቀኖና ኒቅያ አንቀጽ 19 ወስነዋል፡፡

፭. ሉቂያኖስ
የአንጾኪያ ትምህርት ቤትን የመሠረተ እና በትምህርት ቤቱም ለረዢም ዓመታት በማስተማር ያገለገለ ሰው ነው፡፡ ሉቂያኖስ የጳውሎስ ሳምሳጢ ደጋፊ ነው፡፡ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት እለእስክንድሮስ የጳውሎስ ሳምሳጢ አልጋ ወራሽ ይለዋል፡፡የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ኤጲፋንዮስ ሉቅያኖስን ሲገልፀው ከአርዮስ በፊት የነበረ አርዮስ ይለዋል፡፡

ሉቂያኖስ ግኖስቲክ ነው፡፡መዳን በዕውቀት ብቻ እንጂ በእምነት አይደለም የሚል ግኖስቲክ ነበር፡፡ሉቂያኖስ በቅድምና የነበረው ቃል (ወልድ) አብ ጋር የተካካለ፣ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት አንድ ሆነ….. በሥልጣንም የተካካለ መሆኑን አይቀበልም ነበር.... ስለዚሕ እርሱ በመሰረተው የአንፆኪያ ትርጓሜ ወይም በዘመናችንን አነጋገር ስነ መለኮት ትምሕርት ቤት /Theology College/ ገብተው ተምረው የሚወጡ ግለሰቦች በሙሉ…… በሉቂያኖስ መርዝ የተለከፉ እና ትክክለኛውን የቤተክርስቲያን አስተምሕሮ ለመበረዝ ሆነ ተብለው ተፈልፍለው የሚወጡ በሀሰት ላይ የተመሰረቱ ነበሩ፡፡

፮. አርዮስ
አርዮስ በ257 ዓ.ም ገደማ በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ የተወለደ ሲሆን በአንፆክያ ትርጓሜ ትምህርት ቤት የተማረ እና የሉቂያኖስ ደቀ መዝሙር ነበር፡፡ በትውልድ ሀገሩ መሠረታዊ ትምህርቱን ከአጠናቀቀ በኋላ እስክንድርያ በሚገኘው ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብቶ ከፍተኛ ትምህርት ተምሯል፡፡ አርዮስ የእስክንድርያ ከፍተኛ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሄዶ በአንጾኪያ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብቶ የነገረ መለኮት ትምህርት ተምሯል፡፡ በዚህም በአንጾኪያ ትምህርት ቤት መምህሩ የነበረው ሉቅያኖስ ነበር፡፡ አርዮስ አብዛኛው የኑፋቄ ትምህርቱን ያገኘው ከሉቅያኖስና ከአንጾክያ ትምህርት ቤት ነው፡፡

አርዮስ እጅግ ብልህና አዋቂ በመሆኑ ብዙ ሰዎች ያደንቁት ነበር፡፡ አንደበተ ርቱዕም ስለነበር ተናግሮ ህዝቡን በቀላሉ ማሳመን እንደሚችል ይነገርለታል፡፡ በዚያ በነበረው ታላቅ እውቀትና ታላቅ የንግግር ችሎታ የእስክንድርያ ፓትርያርክ የነበረው ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ዲቁና ሾመው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ዲቁናውን ከሰጠው በኋላ ከአርዮስ ልቦና የተደበቀውን ተንኮልና ክፋት የወደፊት ሁኔታ በሱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን እንደምትቸገር ለተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተገለጸለት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይናገራል፡፡

አርዮስ አጥብቆ ተመራመረ ወልድ ፍጡር ነው ብሎ ወደቀ፤ ይህንንም በድብቅ ለሰው ማስተማር ጀመረ፤ በዚህ ጊዜ ጌታችን ለተፍጻሚተ ሰማዕት ጴጥሮስ የተቀደደ ልብስ ለብሶ ተገለጸለት አንተ ማን ነህ ይለዋል የናዝሪቱ ኢየሱስ ነኝ ታዲያ ልብስህ ለምን ተቀደደ ይለዋል “አርዮስ ሰጠጣ ለልብስየ” ይለዋል አርዮስ ልብሴን ቀደደው ማለት ነው፤ ከባህሪ አባቴ ከአብ ከባህሪ ህይወቴ ከመንፈስ ቅዱስ ለይቶ ፍጡር ነው አለኝ ይለዋል፤ይህን ራዕይ አይቶ ብዙም ሳይቆይ አርዮስ መጣ ቁጭ አድርጎ መከረው “በልብህ ያለውን ኑፋቄ ካሰብክ እንዳትናገር ከተናገርክ እንዳትደግመው ብሎም ያስጠነቅቀዋል፤ ሊሰማው ግን አልቻለም፤ አውግዞ ይለየዋል፤ ጓደኞች አኪላስና እለእስክንድሮስ ሊማልዱለት ይመጣሉ፤ አባታችን አርዮስ ተመልሻለው እያለ ነው ከግዝቱ ፍታው ይሉታል፤ እርሱም እንደማይመለስ ጌታ በራዕይ ነግሮኛል አሁን እኔ የምሞትበት ጊዜ ደርሷል ከኔ በኋላ አኪላዎስ ሊቀጳጳስ ትሆናለህ ጓደኝነት በልጦብህ አርዮስን ከግዝቱ ትፈታዋለህ ነገር ግን ብዙ አትቆይም ትሞታለህ ብሎ ትንቢት ይነግራቸዋል፤ የእረፍቱ ቀን እንደደረሰም አውቆ “ጌታሆይ የኔን ሞት የሰማእታት መጨረሻ አድርግልኝ ከኔ በኋላ የአንድስ እንኳን ሰማዕት ደም አይፍሰስ” ብሎ ጸለየ፤ ህዳር 29 ቀን የዲዮ ቅልጥያኖስ ጭፍሮች አንገቱን ቆርጠው ገድለውታል፤ ለዚህም ነው ቤተክርሰቲያን “ተፍጻሚተ ሰማዕት ጴጥሮስ” ብላ የምትጠራው በዚህ ጸሎቱ ነው የሰማእታት መጨረሻ ማለት ነው፡፡

የክህደት ትምህርቱን ይዞ ብቅ ያለው በ311 ዓ.ም ሲሆን ብዙ የቤተክርስቲያን አባቶች አርዮስን “ርዕሰ መናፍቃን” እያሉ ይጠሩታል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች የቆጵሮሱ ኤጲስቆጶስ የሆነው ኤጲፋንዮስ ስለ አርዮስ ሲናገር “አርዮስ ቁመቱ በጣም ረጅም ፣ ጠባዩም ብስጩና ተንኮለኛ ፣ ትምክህትና ውዳሴ ከንቱ ያጠቃው የነበር፣ ንጽሕናውን ጠብቆ ከሴት ርቆ የሚኖር በሙያውም በኩል የአንጾኪያን ትምህርት ቤት ነጠላ ትርጓሜና የምንታዌ /ዱዋሊዝም/ ትምህርት ያውቅ ነበር ከዚህ በተጨማሪም ድርሰት መድረስ ሥጦታው እንደ ነበር ጽፏል፡፡

1.እግዚአብሔር ፈጣሪነት እንጂ ወላዲነት የለውም ቀዳሚ ጥንት የሌለው ያልተፈጠረ አብ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ግን ፍጡር ነው፡፡ተወለደ የሚለውን በተመሳሳይ መንገድ ተፈጠረ በሚለው ለውጦ ሀሳቡን ይገልፃልጥበብ ፣ ወልድ ፣ ቃል የተባለው ፍጡር ስለሆነ ያልነበረበት ጊዜ ነበር ይህም ከመፈጠሩ በፊት አልነበረም በማለት የአብን አካለዊ ባህሪ ማየትም ለማወቅም አይችልም ይላል፡፡
2.አብ ሌሎችን ፍጥረት ሊፈጥርበት ራሱን የቻለ ጥገኛ ያልሆነ በመጀመሪያ የተፈጠረ እና ሌላው ፍጥረትን ሁሉ በእርሱ የተፈጠረ ነው ብሎ ያምናል፡፡ፍጡር በመሆኑም ወሱን ነው ፣ በገድል በትሩፋት የአምላክነት ባህሪ አገኘ ብሎ ያምናል፡፡
3.ስለወልድ ይህን ካለ መንፈስ ቅዱስንም እንደ ወልድ ፍጡር ስለ ሆነ ውሱን ነው የመንፈስ ቅዱስም ክብር ከወልድ ያነሰ ነው ይላል፡፡

ምሳ 8፤22 “እግዚአብሔር ለስራው የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ" አርዮስ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ አካል፣ መለኮታዊ ባህሪ እና የማዳን ስራ ባለው መናፍቃዊ አመለካከት በ321 ዓ.ም ተወግዞ ነበር፡፡

በ325 ዓ.ም በጉባዔ ኒቂያ ቱርክ ውስጥ /የዛሬዋ ኢዚንክ/ 318 ሊቃውንት በተገኙበት በክህደት ትምህርቱ ተረትቶ የተወገዘ ሰው ነው፡፡